ለዘመናት ሰዎችን ሲያሠቃይ የኖረው የጥርስ ሕመም
በመካከለኛው ዘመን በአንዲት ከተማ ውስጥ በሚገኝ የገበያ ቦታ ትኩረት የሚስብ ልብስ የለበሰ አስመሳይ ሰው ምንም ሳያሳምም ጥርስ መንቀል እንደሚችል በጉራ ይናገራል። ከአጫፋሪዎቹ መካከል አንዱ መጀመሪያ ላይ እንደማመንታት ብሎ ለመነቀል ፈቃደኛ ሲሆን ጥርስ ነቃዩም የነቀለ በማስመሰል ደም የነካካው መንጋጋ ለሕዝቡ ከፍ አድርጎ ያሳያል። በዚህ ጊዜ በጥርስ ሕመም ሲሠቃዩ የነበሩ ሰዎች ገንዘብ ከፍለው ጥርሳቸውን ለማስነቀል ተበረታቱ። እነዚህ ሰዎች የሚያሰሙትን ጩኸት በመስማት ሌሎቹ ከመነቀል ወደኋላ እንዳይሉ ለማድረግ ከበሮ ይደለቃል እንዲሁም ጥሩንባ ይነፋል። የተነቀሉት ሰዎች ከጥቂት ቀናት በኋላ ከባድ ኢንፌክሽን ያጋጥማቸው ይሆናል። አስመሳዩ ሰው ግን አካባቢውን ለቅቆ ተሰውሯል።
በዛሬው ጊዜም አንዳንድ የጥርስ ሕመምተኞች እንዲህ ወዳሉ አታላይ ሰዎች መሄድ ግድ ሆኖባቸዋል። ዘመናዊ የጥርስ ሐኪሞች የጥርስ ሕመምን ማከም የሚችሉ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ ጥርስን ከመነቀል ሊያድኑ ይችላሉ። ይሁንና ብዙ ሰዎች የጥርስ ሐኪም ዘንድ መሄድ ያስፈራቸዋል። የጥርስ ሐኪሞች የታካሚዎቻቸውን ሥቃይ ማስታገስ የሚችሉበትን ዘዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት እንዴት እንደሆነ ማወቃችን ዛሬ ላሉት የጥርስ ሐኪሞች ያለንን አድናቆት ከፍ ያደርግልናል።
የጥርስ ሕመም ከጉንፋን ቀጥሎ ብዙዎችን የሚያጠቃ በሽታ እንደሆነ ይነገር ነበር። ይህ ሕመም ዛሬ የጀመረ ነገር አይደለም። ንጉሥ ሰሎሞን የተናገረው ምሳሌ በጥንቷ እስራኤል በዕድሜ የገፉ ሰዎች ጥርሳቸው እያለቀ ሲሄድ መቸገራቸው የሚጠበቅ መሆኑን ያሳያል።—መክብብ 12:3
ንጉሣውያን ቤተሰቦችም ከሥቃይ አላመለጡም
ቀዳማዊት ኤልዛቤት የእንግሊዝ ንግሥት ብትሆንም እንኳ በጥርስ ሕመም ከመሠቃየት አላመለጠችም ነበር። አንድ ጀርመናዊ ጎብኚ የንግሥቲቱ ጥርስ በጣም መበለዙን አይቶ “እንግሊዛውያን ስኳር ስለሚያበዙ የመጣ ችግር” እንደሆነ ተናግሯል። በታኅሣሥ 1578 ንግሥቲቱን የጥርስ ሕመም ቀን ከሌት ያሠቃያት ጀመር። ሐኪሞቿ የበሰበሰው ጥርስ መነቀል እንዳለበት ሐሳብ ያቀረቡላት ቢሆንም እሷ ግን ሥቃዩን ስለፈራች ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። የለንደኑ ጳጳስ ጆን አልመር እሷን ለማበረታታት ሲሉ የበሰበሰ ጥርሳቸውን ሳይሆን አይቀርም በእሷ ፊት ለመነቀል ተስማሙ። በእርግጥ እኚህ ሰው የቀሯቸው ጥርሶች ጥቂት ስለነበሩ እንዲህ ማድረጋቸው ትልቅ መሥዋዕትነት ነበር!
በዚያ ዘመን ተራው ሰው ጥርሱን ማስነቀል ቢፈልግ ወደ ጸጉር አስተካካይ አሊያም ወደ አንጥረኛ ይሄድ ነበር። ስኳር የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ሲመጣ የጥርስ ሕመምም እየተስፋፋ መጣ። በዚህ ጊዜ ጥርስ የሚነቅሉ ባለሙያዎችን ማግኘት አስፈላጊ ሆነ። በመሆኑም አንዳንድ ሐኪሞችና የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በጥርስ ሕመም የሚሠቃዩ ሰዎችን የማከም ፍላጎት አደረባቸው። ይሁን እንጂ በዚህ ሙያ የተወሰነ ችሎታ የነበራቸው ሰዎች ምቀኝነት ስላደረባቸው እውቀታቸውን ለማጋራት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ፤ በዚህም ምክንያት የሕክምና ባለሙያዎቹ በራሳቸው ጥረት መማር ግድ ሆነባቸው። ከጥርስ ሕክምና ጋር በተያያዘ የወጡት መጻሕፍትም ቢሆኑ ጥቂት ነበሩ።
ቀዳማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ከሞተች ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ ሉዊ አሥራ አራተኛ የፈረንሳይ ንጉሥ ሆነ። እሱም አብዛኛውን ዕድሜውን በጥርስ ሕመም ተሠቃይቷል፤ በዚህም ምክንያት በ1685 ከላይ በስተ ግራ በኩል ያሉትን ጥርሶች በሙሉ አስነቅሎ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ንጉሡ በዚያ ዓመት ፈረንሳይ ውስጥ የሃይማኖት ነፃነት እንዲኖር ያስቻለውን ሕግ የሚሽር አደገኛ ውሳኔ ያደረገው በጥርስ ሕመሙ ሳቢያ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ውሳኔ በአነስተኛ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ላይ ከፍተኛ የስደት ማዕበል ቀስቅሷል።
የዘመናዊው የጥርስ ሕክምና አጀማመር
የሉዊ አሥራ አራተኛ የቅንጦት አኗኗር በፓሪስ ሕዝብ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ለዘመናዊ የጥርስ ሕክምና እድገት መንገድ ከፍቷል። አንድ ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦ መርታቱ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ ከበሬታ ማግኘቱ የተመካው በአለባበሱና በቁመናው ማማር ላይ ሆኖ ነበር። ምግብ ለማኘክ ሳይሆን ለውበት ሲባል ጥርስ ማስተከል ሀብታሞችንና ታዋቂ ሰዎችን ብቻ የሚያክሙ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ብቅ እንዲሉ ምክንያት ሆኗል። በፓሪስ፣ ታዋቂ የነበረው የጥርስ ሐኪም ፕየር ፎሼር ሲሆን ይህን ሙያ የተማረው በፈረንሳይ ባሕር ኃይል ውስጥ ነበር። ራሱን የመጀመሪያው የጥርስ ሐኪም ብሎ የሚጠራው ይህ ሰው ጥርስ የመንቀሉን ሥራ ለጸጉር አስተካካዮችና ባለሙያ ነን ለሚሉ ሰዎች የተዉትን የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ይተች ነበር።
ፎሼር በ1728 ሙያውን በምስጢር የመያዙን ልማድ ችላ በማለት ከሕክምናው ጋር በተያያዘ የሚያውቃቸውን ነገሮች በሙሉ በመጽሐፍ አወጣ። በዚህም ምክንያት “የጥርስ ሕክምና አባት” ተብሎ ተጠራ። ታካሚዎችን መሬት ላይ አስቀምጦ ከማከም ይልቅ ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ያደረገ የመጀመሪያው ሰው እሱ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፎሼር ጥርስ ለመንቀል የሚያገለግሉ አምስት መሣሪያዎችን ፈልስፏል። ሆኖም ይህ ሰው ጥርስ ነቃይ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የመሰርሰሪያ መሣሪያ ሠርቶ የተቦረቦረን ጥርስ ይሞላም ነበር። በጥርስ ውስጥ ያለውን ነርቭ ገድሎ የተቦረቦረውን ቦታ መሙላት እንዲሁም ጥርስ መትከል የሚቻልበትን ዘዴም አዳብሮ ነበር። ከዝሆን ጥርስ የሚሠራቸው ሰው ሠራሽ ጥርሶች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ ነገር ተገጥሞላቸዋል። ፎሼር የጥርስ ሕክምና ራሱን የቻለ ሙያ እንዲሆን አድርጓል። ይህ ሰው ያደረጋቸው ነገሮች ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ባሻገር በምትገኘው በአሜሪካም ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሥቃይ
ሉዊ አሥራ አራተኛ ከሞተ ከመቶ ዓመት ገደማ በኋላ አሜሪካዊው ጆርጅ ዋሽንግተን በጥርስ ሕመም ይሠቃይ ጀመር። ከ22 ዓመቱ ጀምሮ በየዓመቱ ማለት ይቻላል አንድ አንድ ጥርስ ያስነቅል ነበር። አሜሪካ ከእንግሊዝ ጋር ባደረገችው ውጊያ የሰራዊቱ አዛዥ ሆኖ ባገለገለባቸው ዓመታት ምን ያህል ተሠቃይቶ እንደነበር መገመት አያዳግትም! በ1789 የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ ሥልጣን በያዘበት ወቅት ምንም ጥርስ አልነበረውም ለማለት ይቻላል።
ጆርጅ ዋሽንግተን ጥርሶቹን በማጣቱ ምክንያት የፊቱ ገጽታ መበላሸቱ እንዲሁም ሰው ሠራሽ ጥርሱ በሚገባ አለመግጠሙ የስሜት ቀውስ ፈጥሮበት ነበር። በሕዝቡ ፊት ጥሩ ስብዕና ይዞ በመቅረብ አዲስ የተመሠረተችው አገር ፕሬዚዳንት ለመሆን ጥረት ያደርግ ስለነበር የመልኩና የቁመናው ጉዳይ በጣም ያስጨንቀው ነበር። በዚያ ዘመን ሰው ሠራሽ ጥርስ የሚዘጋጀው እንደ አሁኑ በረቀቀ መንገድ ሳይሆን የዝሆንን ጥርስ በመቅረጽ ስለነበር በትክክለኛው ቦታ ላይ መግጠም አስቸጋሪ ነበር። እንግሊዛውያን ወንዶችም የጆርጅ ዋሽንግተንን የመሰለ ችግር ነበረባቸው። እነዚህ ሰዎች ከልባቸው የማይስቁት ሰው ሠራሽ ጥርሳቸው እንዳይታይባቸው እንደሆነ ይነገራል።
የጆርጅ ዋሽንግተን ሰው ሠራሽ ጥርስ ከእንጨት የተሠራ ነው ተብሎ የሚወራው ወሬ ሐሰት ነው። ሰው ሠራሽ ጥርሳቸው የተሠራው ከሰው ጥርስ፣ ከዝሆን ጥርስ እንዲሁም ከሊድ እንጂ ከእንጨት አልነበረም። የጥርስ ሐኪሞቹ ጥርሱን ያገኙት መቃብር ቆፍረው ከሚሰርቁ ሰዎች ሊሆን ይችላል። የጥርስ ነጋዴዎች የጦር ሠራዊቶችን ተከትለው በመሄድ በውጊያ ወቅት የሞቱ ወታደሮችን ጥርስ ነቅለው ይወስዱ ነበር። በመሆኑም ሰው ሠራሽ ጥርስ የሚያስተክሉት ሀብታሞች ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ በ1850ዎቹ ዓመታት ጎማን በማጣራት የሰው ሠራሽ ጥርስ ማቀፊያ መሥራት በመቻሉ ተራውም ሕዝብ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆነ። የጆርጅ ዋሽንግተን የጥርስ ሐኪሞች በሙያው ተራቀው የነበረ ቢሆንም የጥርስ ሕመምን መንስዔ ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር።
የጥርስ ሕመም እውነተኛ ገጽታ
እስከ 1700ዎቹ ዓመታት ድረስ ሰዎች የጥርስ ሕመም መንስዔው ትሎች እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር። ይሁንና በ1890 ጀርመን በሚገኘው በርሊን ዩኒቨርሲቲ የሚሠራው ዊለቢ ሚለር የተባለ አሜሪካዊ የጥርስ ሐኪም ለጥርስ ሕመም ዋነኛ መንስዔ የሆነው የጥርስ መበስበስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ደረሰበት። አንድ የባክቴሪያ ዓይነት የሚያመነጨው አሲድ ጥርስን የሚጎዳ ሲሆን ለዚህ ባክቴሪያ መራባት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ስኳር ነው። ይሁንና የጥርስ መበስበስን መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ የተገኘው በአጋጣሚ ነበር።
ለበርካታ ዓመታት በኮሎራዶ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚገኙ የጥርስ ሐኪሞች በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ጥርሳቸው የበለዘው ለምን እንደሆነ አይገባቸውም ነበር። ከጊዜ በኋላ ለዚህ መንስዔው በውኃ ውስጥ የሚገኘው ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ። ይሁንና ተመራማሪዎች የአካባቢያቸውን ችግር ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ የጥርስ ሕመምን መከላከል የሚቻልበትን ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ ያለው አንድ ሐቅ ተገነዘቡ፤ ይኸውም አነስተኛ የፍሎራይድ መጠን ያለው ውኃ ባለበት አካባቢ ያደጉ ሰዎች ከሌሎች በበለጠ የጥርስ መበስበስ ያጋጥማቸዋል። በብዙ አካባቢዎች የሚገኘው ውኃ በተፈጥሮው ፍሎራይድ አለው። ይህ ማዕድን ደግሞ በጥርስ ውስጥም ይገኛል። አነስተኛ ፍሎራይድ ያለው ውኃ ለሚጠጡ ሰዎች ተመጣጣኝ የፍሎራይድ መጠን ያለው ውኃ ሲሰጣቸው ጥርሳቸው የመበስበሱ አጋጣሚ 65 በመቶ ቀነሰ።
በዚህ መንገድ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ ታወቀ። ለአብዛኛው የጥርስ ሕመም መንስዔው የጥርስ መበስበስ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ስኳር ትልቁን ሚና ይጫወታል። ፍሎራይድ ግን የጥርስ መበስበስን ይከላከላል። ይህ ሲባል ግን ፍሎራይድ ጥርስ መቦረሽንና በሚገባ ማጽዳትን ይተካል ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ያለ ሥቃይ ማከም የሚቻልበትን ዘዴ ለማግኘት የተደረገው ጥረት
ማደንዘዣ መድኃኒት ከመፈልሰፉ በፊት ሰዎች ጥርሳቸውን ሲታከሙ ለከፍተኛ ሥቃይ ይዳረጉ ነበር። የጥርስ ሐኪሞቹ የበሰበሰውን የጥርስ ክፍል በስለታም መሣሪያ ቦርቡረው ካወጡት በኋላ ቦታውን በጋለ ብረት ይሞሉታል። በወቅቱ ሌላ ዓይነት መድኃኒት ስላልነበራቸው ሐኪሞቹ ነርቭ ያለበትን የጥርስ ማዕከላዊ ክፍል በጣም በጋለ ብረት ይተኩሱት ነበር። ልዩ የሆኑ የማከሚያ መሣሪያዎችና ማደንዘዣዎች ከመፈልሰፋቸው በፊት ጥርስ መነቀልም ቢሆን በጣም የሚያሠቃይ ነበር። ሰዎች ጥርሳቸውን ለመነቀል ፈቃደኞች የሚሆኑት የታመመው ጥርስ የሚያስከትለው ሥቃይ ከዚህ የከፋ ስለነበር ነው። እንደ ኦፒየም፣ የሕንድ ካናቢስና ማንድሪክ የመሳሰሉት ከዕጽዋት የሚዘጋጁ ነገሮች ለዘመናት ሲወሰዱ የነበረ ቢሆንም ሕመምን ከማስታገስ የበለጠ ጥቅም አልነበራቸውም። ታዲያ የጥርስ ሐኪሞች ሕመምተኞቹ ሥቃይ ሳይደርስባቸው ማከም ይችሉ ይሆን?
እንግሊዛዊው ኬሚስት ጆሴፍ ፕሪስትሊ በ1772 ናይትረስ ኦክሳይድ ወይም ላፊንግ ጋስ ካገኘ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህ ጋዝ የማደንዘዝ ባሕርይ እንዳለው ታወቀ። ነገር ግን እስከ 1844 ድረስ ማንም ሰው ለማደንዘዣነት ተጠቅሞበት አያውቅም ነበር። በዚያው ዓመት ታኅሣሥ 10 በሃርትፎርድ፣ ኮኔክቲከት፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖረው ሆረስ ዌልስ የተባለ የጥርስ ሐኪም ሰዎች ናይትረስ ኦክሳይድ በመጠቀም ትርዒት በሚያሳዩበት የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ተገኝቶ ነበር። ዌልስ ይህንን ጋዝ የወሰደ ሰው በእግሩ አግዳሚ ወንበሩን በኃይል ቢመታም እንኳ ምንም ዓይነት የሕመም ስሜት እንዳልታየበት አስተዋለ። ይህ ሰው አዛኝ ስለነበር ታካሚዎቹ በሕክምና ወቅት በሚያጋጥማቸው ሥቃይ በጣም ይረበሽ ነበር። ትርዒቱን ከተመለከተ በኋላ ግን ናይትረስ ኦክሳይድን ለማደንዘዣነት የመጠቀም ሐሳብ መጣለት። ይሁን እንጂ ለሌሎች መስጠት ከመጀመሩ በፊት በራሱ ላይ ለመሞከር አሰበ። በማግሥቱም በታካሚዎቹ ወንበር ላይ ተቀምጦ ራሱን እስኪስት ድረስ ጋዙን ሳበ። ከዚያም የሥራ ባልደረባው የታመመውን የመንጋጋ ጥርሱን እንዲነቅልለት አደረገ። ይህ ታሪካዊ ክንውን ነበር። በመጨረሻም ጥርሳቸውን የታመሙ ሰዎችን ያለ ሥቃይ ማከም የሚቻልበት ዘዴ ተገኘ!a
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የጥርስ ሕክምና በቴክኖሎጂ እየታገዘ ከፍተኛ መሻሻል አድርጓል። በመሆኑም በዛሬ ጊዜ ጥርስ መታከም እንደ ድሮው ለሥቃይ የሚዳርግ አይደለም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዛሬው ጊዜ ከናይትረስ ኦክሳይድ ይልቅ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉት ሌሎች የማደንዘዣ ዓይነቶች ናቸው።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የጆርጅ ዋሽንግተን ከዝሆን ጥርስ የተሠራ ሰው ሠራሽ ጥርስ
[ምንጭ]
Courtesy of The National Museum of Dentistry, Baltimore, MD
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1844 ናይትረስ ኦክሳይድን በመጠቀም የተደረገውን የመጀመሪያውን የጥርስ ሕክምና የሚያሳይ የአንድ ሰዓሊ ሥዕል
[ምንጭ]
Courtesy of the National Library of Medicine
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of the National Library of Medicine