ሰዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁ የተደረገበት መንገድ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው መዝሙራዊው ዳዊት “የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ስም በዝማሬ አወድሳለሁ” ሲል ዘምሯል። ዳዊት የአምላክን ስም ያውቅ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር በአንድ መዝሙሩ ላይ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ይባረክ። ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ” ብሏል። (መዝሙር 69:30፤ 72:18, 19) በአማርኛ የአምላክ ስም በሰፊው የሚታወቀው ይሖዋ በሚለው አጠራር ሲሆን ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ከሚገኘው יהוה ከሚል የዕብራይስጥ ቃል የተተረጎመ ነው።
ባለፉት ጥቂት መቶ ዓመታት የአምላክን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በርካታ ነገሮችም ላይ ማግኘት ይቻል ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ “ይሖዋ አምላክ ይወደስ” የሚል ትርጉም ያላቸው ቤኔዲክተስ ሲት የሖዋ ዲየስ (Benedictus Sit Iehova Deus) የሚሉት የላቲን ቃላት በስዊዘርላንድ ለበርካታ ዓመታት ይሠራባቸው በነበሩ የወርቅ ሳንቲሞች [1] ላይ ይገኙ ነበር። እንዲያውም ባለፉት በርካታ መቶ ዓመታት የአምላክ ስም ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ልዩ ልዩ ሳንቲሞች፣ ሜዳልያዎችና ለመገበያያነት የሚያገለግሉ ሌሎች ነገሮች ላይ በዕብራይስጥና በላቲን ቋንቋ ተጽፎ ይገኝ ነበር!
በዚህና በሚቀጥለው ገጽ ላይ ካሉት ሥዕሎች መመልከት እንደሚቻለው ሰዎች በመለኮታዊው ስም በሰፊው እንዲጠቀሙ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
ሰዎች በአምላክ ስም የተጠቀሙት ለምን ነበር?
ከ16ኛው መቶ ዘመን አንስቶ መላው ምዕራብ አውሮፓ በሮም ካቶሊኮችና በፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጆች መካከል ይካሄድ በነበረው ሃይማኖታዊ ጦርነት ይታመስ ነበር። በስፔን ይተዳደሩ የነበሩ አንዳንድ ክልሎች ከተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመወገን በወቅቱ ከፍተኛ ተቀባይነት ከነበራት የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተገነጠሉ። ይህ ደግሞ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆነ። ሁለቱም ወገኖች አምላክ ከእነሱ ጎን እንደሆነ የሚገልጽ መልእክት ለማስተላለፍ ሳንቲሞችንና ምስሎችን ይጠቀሙ ነበር።
ሰዎች መለኮታዊውን ስም የተጠቀሙበት እንዴት ነበር?
ሳንቲም የሚቀርጹ ሰዎች ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ለማመልከት ቴትራግራማተን ተብለው የሚጠሩትን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ተጠቅመዋል። እነዚህ ፊደላት በእንግሊዝኛ የሚጻፉት JHVH ወይም YHWH ተብለው ነው። በጥቅሉ ሲታይ ሳንቲም የሚቀርጹት ሰዎችም ሆኑ ሌላው ሕዝብ ዕብራይስጥ ማንበብ አይችሉም ነበር። በመሆኑም የአምላክን ስም የሚወክሉት አራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት በየጊዜው በተለያዩ ሰዎች ሲቀረጹ በተለያዩ መንገዶች ይጻፉ ጀመር።
ስዊድን በ1568 ገደማ የአምላክ ስም በተቀረጸበት ሳንቲም [2] መጠቀም የጀመረች ሲሆን ስኮትላንድም በ1591 ተመሳሳይ ሳንቲሞችን ማዘጋጀት ጀመረች። በ1600 ገደማ የስዊድኑ ንጉሥ ቻርልስ ዘጠነኛ Ihehova, Iehova እና Iehovah ተብሎ ይጻፍ የነበረው የአምላክ ስም በሳንቲሞች [3] ላይ እንዲቀረጽ አደረገ። ንጉሡ አንደኛው የሳንቲም ዓይነት ከወርቅ እንዲሠራ አዘዘ። ይህ አስደናቂ ሳንቲም ያለው ዋጋ አንድ የጉልበት ሠራተኛ ከአራት ወር በላይ ሠርቶ ከሚያገኘው ደሞዝ ጋር ይመጣጠናል!
ከ1588 እስከ 1648 ካስተዳደረው የዴንማርክና የኖርዌይ ንጉሥ ክርስቲያን አራተኛ የግዛት ዘመን ጀምሮ የይሖዋ ሳንቲሞች በመባል የሚጠሩ ከ60 የሚበልጡ የሳንቲም ዓይነቶች ጥቅም ላይ ውለው ነበር። በተጨማሪም በ17ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ እነዚህ “የይሖዋ ሳንቲሞች” በፖላንድና በስዊዘርላንድ ይሠሩ ጀመር። ጀርመንም ከጊዜ በኋላ እነዚህን ሳንቲሞች ማዘጋጀት ጀመረች።
በአውሮፓ በሃይማኖት ስም በተቀሰቀሰውና ከ1618 እስከ 1648 በተካሄደው የሠላሳ ዓመት ጦርነት ወቅት እንዲህ ዓይነቶቹ ሳንቲሞች በብዛት ተዘጋጅተው ነበር። የስዊድኑ ንጉሥ ዳግማዊ ጉስታቭ አዶልፍ በ1631 በብሪተንፌልት ውጊያ ድል ካደረገ በኋላ የአምላክን ስም የሚወክሉት አራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት የሚገኙባቸውን ሳንቲሞች [4] አስቀርጾ ነበር። እነዚህ ሳንቲሞች የተዘጋጁት ኤርፈርት፣ ፉርት፣ ማይንትስ እና ዎርትስበርግ በተባሉት ከተሞች ነበር። በተጨማሪም ከስዊድን ንጉሥ ጋር ኅብረት የፈጠሩ በመስፍን የሚተዳደሩ ሌሎች ግዛቶች የአምላክ ስም የሚገኝባቸውን ሳንቲሞች ማስቀረጽ ጀመሩ።
ለሠላሳ ዓመታት የተካሄደው አሰቃቂ ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበሩት 150 የሚያህሉ ዓመታት ውስጥም የአምላክን ስም በሳንቲሞች፣ በሜዳልያዎችና በሌሎች ነገሮች ላይ የመቅረጹ ሥራ ቀጥሎ ነበር። እንዲህ ዓይነት ሳንቲሞች የሚቀረጹት በኦስትሪያ፣ በፈረንሳይ፣ በሜክሲኮና በሩሲያ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ነበር። ይሁንና በ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የአምላክን ስም በሳንቲሞች ላይ መቅረጽ እየቀነሰ መጥቶ ከጊዜ በኋላ ሙሉ በሙሉ ቆመ።
የአምላክን ስም ማሳወቅ
ምንም እንኳ የአምላክ ስም በዛሬው ጊዜ ለመገበያያነት በምንጠቀምባቸው ገንዘቦች ላይ ላይገኝ ቢችልም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሰዎች ይህን ስም እንዲያውቁት እየተደረገ ነው። ከብዙ ዘመናት በፊት አምላክ እሱን የሚያገለግሉ ሰዎችን የመረጠ ሲሆን ‘እኔ አምላክ ነኝ፤ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ’ ብሏቸዋል። (ኢሳይያስ 43:12) እንዲህ ያለው ታላቅ መብት ለሳንቲም የሚሰጥ አይደለም። እንዲያውም በሳንቲሞቻቸው ላይ የአምላክን ስም ያስቀርጹ የነበሩ ሰዎች ባካሄዷቸው አሰቃቂ ጦርነቶች አምላክ ከጎናቸው እንደነበር በመግለጽ ስለ እሱ የሐሰት ምሥክርነት ሰጥተዋል። ይሁንና በዛሬው ጊዜ የአምላክ ስም እሱ በሚፈልገው መንገድ እንዲታወቅ በማድረግ ላይ ያሉ ሰዎች አሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋም ሆነ ስሙ ስላለው ትርጉም ይበልጥ እንድታውቅ ያበረታቱሃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ መዝሙራዊ “ስምህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የሆነው አንተ ብቻ፣ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ” በማለት ስለ ይሖዋ ጽፏል። (መዝሙር 83:18) የይሖዋ ውድ ልጅ “አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት በጸሎት እንደገለጸው ይሖዋን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 20,21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳንቲም ለመቅረጽ ያገለግሉ የነበሩ መሣሪያዎች
[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
ሳንቲም 1 እና መሣሪያዎቹ:- Hans-Peter-Marquardt.net;
ሳንቲም 2:- Mit freundlicher Genehmigung Sammlung Julius Hagander
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሳንቲም 3 እና 4:- Mit freundlicher Genehmigung Sammlung Julius Hagander