ከፍቺ ጋር በተያያዘ ልታውቋቸው የሚገቡ አራት ነገሮች
የቤቱ ባለቤቶች ቤቱ ምን ያህል እንደተጎዳ ካመዛዘኑ በኋላ ሁለት ምርጫ ይኖራቸዋል፦ ቤቱን ማፍረስ ወይም ማደስ።
የእናንተስ ትዳር የሚገኝበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል? የትዳር ጓደኛችሁ ታማኝነቱን አጉድሎ ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ ትዳራችሁ በማያባራ ጭቅጭቅ የተሞላ በመሆኑ ደስታችሁን አጥታችሁ ሊሆን ይችላል። ያላችሁበት ሁኔታ እንደዚህ ከሆነ ‘በቃ ፍቅራችን አልቋል’ ወይም ‘ቀድሞውንም ቢሆን የማንኳኳን ሰዎች ነበርን’ አሊያም ‘ሳናስብ የገባንበት ትዳር ነው’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ከዚያም አልፋችሁ ‘መፋታት ሳይኖርብን አይቀርም’ ልትሉ ትችላላችሁ።
ሆኖም ቸኩላችሁ ትዳራችሁን ለማፍረስ ከመወሰናችሁ በፊት ቆም ብላችሁ አስቡ። ፍቺ በሕይወት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሁልጊዜ መፍትሔ አይሆንም። ከዚህ በተቃራኒ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ዓይነት ችግር በሌላ ይተካል። ዶክተር ብራድ ሳክስ ዘ ጉድ ኢነፍ ቲን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ለመለያየት የሚያስቡ ባልና ሚስቶች ፍቺ ስለሚያስገኝላቸው ፍጹም ሕይወት ይኸውም በንትርክና በጦፈ ጭቅጭቅ ከተሞላው ሕይወታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገላግለው በምትኩ ሰላምና እርጋታ የሰፈነበት ምቹ ሕይወት ስለሚመሩበት ጊዜ ይቃዣሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ሕልም፣ ፍጹም የሆነ ትዳር ለማግኘት ከመመኘት ባልተለየ መልኩ ጨርሶ ሊሆን የማይችል ነገር ነው።” ስለዚህ ስለ ፍቺ የሚያስቡ ሰዎች ግራና ቀኙን በእርጋታ ተመልክተውና እውነታውን አገናዝበው መወሰናቸው በጣም አስፈላጊ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስና ፍቺ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍቺ እንደ ቀላል ጉዳይ አይታይም። ምናልባትም ሌላ ለማግባት ሲባል የትዳር ጓደኛን በማይረባ ምክንያት መፍታትን ይሖዋ አምላክ አጥብቆ እንደሚጠላና እንደ አታላይነት እንደሚቆጥረው ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ። (ሚልክያስ 2:13-16) ጋብቻ ዘላቂ ትስስር ነው። (ማቴዎስ 19:6) በአልባሌ ምክንያቶች የፈረሱ ብዙ ትዳሮች ባልና ሚስቶቹ ይበልጥ ይቅር ባዮች ቢሆኑ ኖሩ ከመፍረስ በዳኑ ነበር።—ማቴዎስ 18:21, 22
ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ተፋትቶ ሌላ ማግባት የሚቻልበት አንድ ምክንያት እንዳለ ይገልጻል፤ ይህም ከትዳር ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ነው። (ማቴዎስ 19:9) በመሆኑም የትዳር ጓደኛችሁ ታማኝነቱን ካጎደለ ጋብቻውን የማፍረስ መብት አላችሁ። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን መወሰን እንዳለባችሁ ሌሎች እንዲነግሯችሁ መፍቀድ የለባችሁም፤ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም እንዲህ ወይም እንደዚያ አድርጉ ለማለት አይደለም። ውሳኔያችሁ ከሚያስከትልባችሁ ውጤት ጋር የምትኖሩት እናንተው ስለሆናችሁ ውሳኔ ማድረግ ያለባችሁ ራሳችሁ ናችሁ።—ገላትያ 6:5
መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ስለዚህ ለፍቺ የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ቢኖራችሁም ይህ እርምጃ የሚያስከትለውን ውጤት በጥሞና ማሰብ ይኖርባችኋል። (1 ቆሮንቶስ 6:12) በብሪታንያ የሚኖረው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ቶሎ ውሳኔ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሚያስቡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ፍቺ ምን ማለት እንደሆነ ስለማውቀው ነገሮችን አውጥቶና አውርዶ ለማሰብ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ከራሴ ተሞክሮ መናገር እችላለሁ።”a
ልታስቡባቸው የሚገቡ አራት አስፈላጊ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ከጠቀስናቸው የተፋቱ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ውሳኔያቸው ስህተት እንደነበረ እንዳልተናገሩ ልብ በሉ። ይሁን እንጂ የሰጡት አስተያየት ፍቺው ከተፈጸመ በኋላ ባሉት ወራት ሌላው ቀርቶ ከዓመታት በኋላ እንኳ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በግልጽ ያሳያል።
1 የገንዘብ ችግር
በጣሊያን የምትኖረውና በትዳር ዓለም 12 ዓመታት ያሳለፈችው ዳንዬላ ባለቤቷ የሥራ ባልደረባው ከሆነች ሴት ጋር እንደሚባልግ አወቀች። ዳንዬላ “ነገሩን ባወቅኩበት ጊዜ ሴትየዋ የስድስት ወር እርጉዝ ነበረች” ብላለች።
ለተወሰነ ጊዜ ተለያይተው ከኖሩ በኋላ ዳንዬላ ለመፋታት ወሰነች። ዳንዬላ “ትዳሬን ከመፍረስ ለማዳን ጥረት ባደርግም ባለቤቴ በእኔ ላይ መወስለቱን አላቆመም” በማለት ትናገራለች። ዳንዬላ ውሳኔዋ ትክክል እንደሆነ ይሰማታል። ያም ቢሆን እንዲህ ብላለች፦ “እንደተለያየን ከባድ የገንዘብ ችግር አጋጠመኝ። እራት እንኳ የማልበላበት ጊዜ ነበር። ወተት ብቻ ጠጥቼ አድር ነበር።”
በስፔን የምትኖረው ማሪያም ተመሳሳይ ችግር ደርሶባታል። እንዲህ ብላለች፦ “የቀድሞ ባለቤቴ ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ አያደርግልንም፤ ይህ እንዳይበቃ ደግሞ እሱ የገባውን ዕዳ ለመክፈል ብዙ መሥራት ነበረብኝ። በተጨማሪም ምቹ ከሆነ ቤት ወጥቼ አደገኛ በሆነ አካባቢ ጠባብ አፓርታማ ውስጥ ለመኖር ተገደድኩ።”
እነዚህ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት አብዛኛውን ጊዜ የትዳር መፍረስ በሴቶች ላይ ከባድ የሆነ የገንዘብ ችግር ያስከትላል። እንዲያውም በአውሮፓ ውስጥ ለሰባት ዓመት የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከፍቺ በኋላ የወንዶች ገቢ በ11 በመቶ ሲጨምር የሴቶች ገቢ ግን በ17 በመቶ ቀንሷል። ጥናቱን የመሩት ሚኬ ያንሰን “አንዳንድ ሴቶች ፍቺ ያስከተለባቸውን ስሜታዊ ቁስል ከመቋቋም በተጨማሪ ለልጆቻቸው እንክብካቤ ማድረግና ሥራ ማግኘት ስለሚኖርባቸው ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል” ብለዋል። የለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ እንደገለጸው ከሆነ እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች “ሰዎች ከመፋታታቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ እያስገደዷቸው” መሆኑን አንዳንድ ጠበቆች ይናገራሉ።
ምን ሊከተል ይችላል? ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ከተፋታችሁ ገቢያችሁ ሊቀንስ ይችላል። በተጨማሪም የምትኖሩበትን ቤት ለቅቃችሁ መውጣት ይኖርባችሁ ይሆናል። የአሳዳጊነት መብት ካገኛችሁ ራሳችሁን ማስተዳደርም ሆነ ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሚገባ ማሟላት አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 5:8
2 ልጆችን ከማሳደግ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች
ጄን የምትባል በብሪታንያ የምትኖር ሴት “ባለቤቴ ለእኔ ታማኝ እንዳልሆነ ማወቄ በጣም አስደንግጦኝ ነበር” ብላለች። “ይባስ ብሎ ደግሞ ትቶን ለመሄድ እንደመረጠ ሳስብ ስሜቴ ተደቆሰ።” ጄን ከባሏ ጋር ተፋታች። አሁንም ያደረገችው ውሳኔ ትክክል እንደነበር ይሰማታል፤ ያም ሆኖ “ካጋጠሙኝ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንዱ ለልጆቼ እናትም አባትም መሆን ነው። ሁሉንም ውሳኔዎች ማድረግ ያለብኝ እኔው ነበርኩ” ብላለች።
ግራስዬላ የተባለችው በስፔን የምትኖር እናትም ከባሏ ጋር ስትፋታ ያጋጠማት ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “የ16 ዓመት ወንድ ልጄን የማሳደግ ሙሉ መብት ተሰጠኝ። ይሁን እንጂ ጉርምስና አስቸጋሪ ጊዜ ከመሆኑም ባሻገር እኔም ልጄን ብቻዬን ለማሳደግ ዝግጁ አልነበርኩም። ቀንና ሌሊት አለቅስ ነበር። ጥሩ እናት እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር።”
የአሳዳጊነት መብት ለአባትና ለእናት በጋራ በሚሰጥበት ጊዜ ደግሞ ተጨማሪ ችግር ይፈጠራል፤ ልጁን መጠየቅን፣ ለልጁ የገንዘብ ድጋፍ መስጠትን፣ ተግሣጽንና የመሳሰሉትን ጥንቃቄ የሚጠይቁ ጉዳዮች አንስቶ ከፈቱት ሰው ጋር መነጋገር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ክርስቲን የተባለች ከባልዋ ጋር የተፋታች እናት “ከቀድሞ የትዳር ጓደኛ ጋር መግባባት ቀላል አይደለም። ስሜታችን ዝብርቅርቅ ስለሚል ካልተጠነቀቅን በልጃችን ተጠቅመን የምንፈልገውን ለማግኘት የመሞከር አዝማሚያ ሊኖረን ይችላል” ብላለች።
ምን ሊከተል ይችላል? የልጁን አሳዳጊ በተመለከተ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ብያኔ እናንተ የምትመርጡት ዓይነት ላይሆን ይችላል። የጋራ የአሳዳጊነት መብት የሚሰጣችሁ ከሆነ ልጁን መጠየቅንና የገንዘብ ድጋፍ መስጠትን የመሳሰሉ ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ የቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ የምትፈልጉትን ያህል ምክንያታዊ እንዳልሆነ ይሰማችሁ ይሆናል።
3 ፍቺ በእናንተ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ
በብሪታንያ የሚኖረው የማርክ ባለቤት ከአንድ ጊዜ በላይ ታማኝነቷን አጉድላለች። ማርክ እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለተኛ ጊዜ ከሌላ ሰው ጋር ስትባልግ፣ ከአሁን በኋላም ተመሳሳይ ነገር ልታደርግ ትችላለች የሚለው ስሜት በጣም ረበሸኝ።” አሁን ከሚስቱ ጋር ቢፋታም ለእሷ ያለው ፍቅር እንዳልጠፋ ይሰማዋል። እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ስለ እሷ መጥፎ ነገር ሲናገሩ እኔን ያገዙ ይመስላቸዋል፤ ግን እየረዱኝ አይደለም። ፍቅር ለረጅም ጊዜ ይቆያል።”
ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ዴቪድም ሚስቱ ከሌላ ወንድ ጋር እንደምትወሰልት ባወቀ ጊዜ ስሜቱ በጣም ተጎዳ። እንዲህ ይላል፦ “ነገሩን ጨርሶ ማመን አልቻልኩም። ሕይወቴን በሙሉ ከእሷና ከልጆቼ መለየት አልፈልግም ነበር።” ዴቪድ ለመፋታት ቢመርጥም ፍቺው ስለ ወደፊት ሕይወቱ ጥርጣሬ እንዲያድርበት አድርጎታል። እንዲህ ብሏል፦ “‘ከልቧ ልትወደኝ የምትችል ሴት ትኖር ይሆን?’ ወይም ‘ሌላ ባገባ ተመሳሳይ ነገር ይደርስብኝ ይሆን?’ ብዬ አስባለሁ። የነበረኝ በራስ የመተማመን ስሜት ተናጋ።”
እናንተም ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተፋትታችሁ ከሆነ የተዘበራረቀ ስሜት እንደሚኖራችሁ የሚጠበቅ ነገር ነው። በአንድ በኩል፣ እንደ አንድ ሥጋ ሆናችሁ አብራችሁት ለኖራችሁት ግለሰብ የነበራችሁ ፍቅር ላይጠፋ ይችላል። (ዘፍጥረት 2:24) በሌላ በኩል ደግሞ የተፈጸመው ነገር በጣም ያበሳጫችሁ ይሆናል። ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ግራስዬላ እንዲህ ብላለች፦ “በርካታ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንኳ ግራ ልትጋቡ እንዲሁም እንደተዋረዳችሁና ረዳት እንደሌላችሁ ሆኖ ሊሰማችሁ ይችላል። በትዳር ዘመናችሁ ያሳለፋችኋቸው አስደሳች ጊዜያት ወደ አእምሯችሁ ይመጣሉ፤ እንዲሁም ‘ያለ እኔ መኖር እንደማይችል ይነግረኝ ነበር። ያን ሁሉ ጊዜ እየዋሸኝ ነበር ማለት ነው? ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?’ ብላችሁ ታስባላችሁ።”
ምን ሊከተል ይችላል? የትዳር ጓደኛችሁ በፈጸመባችሁ በደል የተሰማችሁ ብስጭትና ምሬት ለረጅም ጊዜ ከሆዳችሁ አልወጣ ይላችሁ ይሆናል። በብቸኝነት ስሜት የምትዋጡበት ጊዜ ሊኖር ይችላል።—ምሳሌ 14:29፤ 18:1
4 ፍቺ በልጆች ላይ የሚያሳድረው ጫና
በስፔን የሚኖረው ሆሴ የተባለ ከሚስቱ ጋር የተፋታ አባት “ሁኔታው ቅስም የሚሰብር ነበር” ብሏል። “ነገሩ በጣም የከበደኝ ደግሞ ሚስቴ የባለገችው ከእህቴ ባል ጋር መሆኑን ሳውቅ ነበር። በወቅቱ ብሞት እመርጥ ነበር።” ሆሴ፣ ሁለትና አራት ዓመት የሆናቸው ወንዶች ልጆቹም እናታቸው በወሰደችው እርምጃ እንደተጎዱ አስተውሏል። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሁኔታውን ሊረዱትም ሆነ ሊቀበሉት አልቻሉም። እናታቸው ከአክስታቸው ባል ጋር የምትኖረውና እኔም እነሱን ይዤ ከእህቴና ከእናቴ ጋር መኖር የጀመርኩት ለምን እንደሆነ በጭራሽ ሊገባቸው አልቻለም። ወደ አንድ ቦታ መሄድ ካለብኝ ‘አባዬ መቼ ነው የምትመለሰው?’ ብለው ይጠይቁኛል፤ ወይም ‘አባዬ፣ ጥለኸን አትሂድ!’ ይሉኛል።”
ወላጆች ለመፋታት በሚያደርጉት ትግል አብዛኛውን ጊዜ ችላ የሚባሉት ተጠቂዎች ልጆች ናቸው። ታዲያ ወላጆች ተስማምተው መኖር ካቃታቸው ምን ይደረጋል? እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ “ለልጆቹ የሚሻለው” ወላጆቻቸው ቢፋቱ ነው? ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በተለይ በትዳሩ ውስጥ ያለው ችግር በጣም የከፋ ካልሆነ ተቀባይነት እያጣ መጥቷል። ዚ አንኤክስፔክትድ ሌጋሲ ኦቭ ዲቮርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ፈጽሞ ደስታ በራቀው ትዳር ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ልጆቻቸው በአንጻራዊ ሁኔታ ደስተኞች እንደሆኑ ሲያውቁ ይገረማሉ። ልጆቹ፣ ቤተሰቡ አብሮ እስከኖረ ድረስ አባባና እማማ አልጋ ለይተው ቢተኙ ግድ የላቸውም።”
አብዛኛውን ጊዜ ልጆች በወላጆቻቸው መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ማስተዋል አያቅታቸውም፤ እንዲሁም በትዳር ውስጥ የሚፈጠር ውጥረት በለጋ አእምሮአቸውና በልባቸው ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል የሚካድ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ መፋታት የተሻለ ይሆንላቸዋል ብሎ ማሰብ ስህተት ሊሆን ይችላል። ሊንዳ ዌትና ማጊ ጋላገር ዘ ኬዝ ፎር ሜሬጅ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ወላጆች ትዳራቸው ደስታ የራቀው ቢሆንም እንኳ የጋብቻ ዝግጅት ለልጆቻቸው ወጥ የሆነና ሚዛኑን የጠበቀ ተግሣጽ እንዲሰጡ ያስችላል፤ ልጆችም እንዲህ ዓይነቱን ተግሣጽ መቀበል አይከብዳቸውም።”
ምን ሊከተል ይችላል? በተለይ ልጆቻችሁን ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ካላበረታታችኋቸው ፍቺ በልጆቻችሁ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።—“አጣብቂኝ ውስጥ መግባት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ለመፋታት እያሰባችሁ ከሆነ ልታገናዝቧቸው የሚገቡ አራት ነጥቦች በዚህ ርዕስ ውስጥ ተብራርተዋል። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የትዳር ጓደኛችሁ ታማኝነቱን ካጎደለ ስለ ጉዳዩ ውሳኔ ማድረግ ያለባችሁ እናንተ ራሳችሁ ናችሁ። የትኛውንም መንገድ ብትመርጡ ሊያስከትልባችሁ የሚችለውን ውጤት ማገናዘብ ይኖርባችኋል። ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟችሁ እወቁ፤ እንዲሁም ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ዝግጅት አድርጉ።
ጉዳዩን ካገናዘባችሁ በኋላ የሚሻለው ትዳራችሁን ማስተካከል እንደሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ሆኖም ይህን ማድረግ ይቻላል?
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።