ንድፍ አውጪ አለው?
የባክቴሪያ ፍላጀለም
● ጥቃቅን ነገሮችን በሚያሳይ አጉሊ መነጽር ሲታይ እንኳ እጅግ በጣም ትንሽ ነው። በጀልባዎች ውጨኛ ክፍል ላይ ከሚገጠም ኃይለኛ ሞተር ጋር ተመሳስሏል። የባክቴሪያ ፍላጀለም ወይም ጅራት መሰል መንቀሳቀሻ አካል ምንድን ነው?
የፍላጀለም ዓይነቶች የተለያዩ ቢሆኑም ጠለቅ ያለ ጥናት የተካሄደው በባክቴሪያ ፍላጀለም (በላቲን “ጅራፍ” ማለት ነው) ላይ ሳይሆን አይቀርም። ከባክቴሪያው ሴል ሽፋን ጋር የተያያዘው ፍላጀለም በሚሽከረከርበት ጊዜ ረቂቅ ሕዋሱ ወደፊት እንዲጓዝ፣ እንዲቆም፣ በተቃራኒው አቅጣጫ እንዲሄድና አቅጣጫውን እንዲቀይር ያስችለዋል። እስከ አሁን ከታወቁት የባክቴሪያ ዓይነቶች ግማሽ የሚሆኑት በተለያየ መልኩም ቢሆን ፍላጀለም ወይም ጅራት እንዳላቸው ይገመታል።
በባክቴሪያ ወይም በረቂቅ ሕዋሳት ውስጥ ያለው ዲ ኤን ኤ የፍላጀለምንና የማስፈንጠሪያውን “ንድፍ” ይዟል። ሙሉው ፍላጀለም በአንድ ሞተር ውስጥ ከሚገኙት የተለያዩ ክፍሎች ጋር ሊመሳሰሉ በሚችሉ 40 ያህል ፕሮቲኖች የተገነባ ነው። የሚያስደንቀው ነገር ፍላጀለም ራሱን በራሱ ለመሥራት የሚፈጅበት ጊዜ 20 ደቂቃ ብቻ ነው!
ዚ ኢቮሉሽን ኮንትሮቨርሲ የተባለው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “በባክቴሪያ ፍላጀለም ውስጥ በደቂቃ ከ6,000 እስከ 17,000 ጊዜ በሚደርስ ፍጥነት የሚሾር ተሽከርካሪ ሞተር ይገኛል። ይበልጥ የሚያስደንቀው ደግሞ ይህ ሞተር በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ የሚዞርበትን አቅጣጫ በመቀየር በደቂቃ እስከ 17,000 ጊዜ በሚደርስ ፍጥነት በተቃራኒው አቅጣጫ መሽከርከር መቻሉ ነው።” ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ስለ ባክቴሪያ ፍላጀለም እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ውስብስብ ለሆነ ሞለኪውላዊ ሥርዓት ግሩም ምሳሌ ሲሆን ማንም ሰብዓዊ መሐንዲስ ሊሠራው የማይችል እጅግ በጣም ትንሽ የሆነ የተራቀቀ ማሽን ነው።”
በጣም አነስተኛ የሆነው የባክቴሪያ ፍላጀለም 40 ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህ ክፍሎች በሙሉ በትክክል እንዲገጣጠሙና በሚገባ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ በሚያስችል ቅደም ተከተል ራሱን በራሱ መሥራት መቻሉ ለሳይንቲስቶች እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የባክቴሪያ ፍላጀለም እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ማሽከርከሪያ
መደላድል
መጋጠሚያ
ማስፈንጠሪያ
ፍላጀላ
[ሥዕል]
ባክቴርየም ጎልቶ ሲታይ
[የሥዕሉ ምንጭ]
Bacterium inset: © Scientifica/Visuals Unlimited, Inc.; flagellum diagram: Art source courtesy of www.arn.org