መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ በዛሬው ጊዜ የሚደረጉ ጦርነቶችን ይደግፋል?
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ስላካሄዳቸው ጦርነቶች ሲናገር “እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናቸዋል፤ ክንዴም የናስ ቀስት መገተር ይችላል” ብሏል።—መዝሙር 18:34
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምንም እንኳ በሥጋ የምንኖር ቢሆንም የምንዋጋው በሥጋዊ መንገድ አይደለም። ምክንያቱም የምንዋጋባቸው የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉም።”—2 ቆሮንቶስ 10:3, 4
እነዚህ ጥቅሶች እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ? ወይስ አምላክ የጥንቶቹ እስራኤላውያን እንዲዋጉ የፈቀደበት፣ ክርስቲያኖች ግን ይህን እንዳያደርጉ የከለከለበት በቂ ምክንያት አለው? አምላክ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት ተለውጧል? በእስራኤልና በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ መካከል ያሉትን ሦስት ዋና ዋና ልዩነቶች ስንመለከት የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ግልጽ ይሆንልናል።
ሦስት ጉልህ ልዩነቶች
1. የጥንት እስራኤላውያን አምላክ የሰጣቸው የራሳቸው የሆነ የተከለለ ምድር የነበራቸው ሲሆን ብዙውን ጊዜም በዙሪያቸው ከሚኖሩት ብሔራት ጋር ሰላም አልነበራቸውም። በመሆኑም አምላክ ሕዝቡን ምድራቸውን ከጠላት እንዲጠብቁ ያዘዛቸው ከመሆኑም በላይ ጠላቶቻቸውን በእጃቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። (መሳፍንት 11:32, 33) በሌላ በኩል ግን የክርስቲያን ጉባኤ የራሱ የሆነ የተከለለ ምድር የሌለው ሲሆን አባላቱም በሁሉም አገሮች ውስጥ ይገኛሉ። ስለዚህ በአንድ አገር ያሉ የክርስቶስ ተከታዮች ከሌላ አገር ጋር በሚደረግ ጦርነት ውስጥ የሚካፈሉ ከሆነ የእምነት አጋሮቻቸውን ማለትም መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መውጋታቸው አይቀርም፤ ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የእምነት አጋሮቻቸውን እንዲወዱ፣ ሌላው ቀርቶ ሕይወታቸውን ለእነሱ ሲሉ አሳልፈው እንዲሰጡ ታዘዋል።—ማቴዎስ 5:44፤ ዮሐንስ 15:12, 13
2. የጥንት እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ የነበራቸው ሲሆን የንጉሡም ዙፋን በኢየሩሳሌም ነበር። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚመሩት በሰማይ በሚገኘው ዙፋኑ ተቀምጦ በመግዛት ላይ ባለው ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዳንኤል 7:13, 14) ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው ብሏል፦ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።” (ዮሐንስ 18:36) በመሆኑም በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ፖለቲካዊ መንግሥት ወይም አገዛዝ የክርስቶስ ነኝ ሊል አይችልም። ታዲያ ይህ ለኢየሱስ ‘አገልጋዮች’ ወይም ተከታዮች ምን ትርጉም አለው? ሦስተኛው ነጥብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።
3. የጥንት እስራኤላውያን ሌሎቹ ብሔራት ያደረጉት እንደነበረው ሁሉ ብዙውን ጊዜ መልእክተኞችን ማለትም እንደ ዘመናችን አጠራር አምባሳደሮችን ወይም ተወካዮችን ወደ ሌሎች አገሮች ይልኩ ነበር። (2 ነገሥት 18:13-15፤ ሉቃስ 19:12-14) ክርስቶስም እንዲሁ አድርጓል፤ ይሁንና እሱ የላካቸው አምባሳደሮች በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ከሌሎቹ ይለያሉ። አንደኛ፣ ተከታዮቹ በሙሉ አምባሳደሮች ወይም ተወካዮች ሆነው ያገለግላሉ። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት አጋሮቹን ወክሎ “እኛ ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ አምባሳደሮች ነን” በማለት ሊጽፍ ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 5:20) ሰላማውያን የሆኑ አምባሳደሮች እንደመሆናቸው መጠን የጦር መሣሪያ አያነሱም። ሁለተኛ፣ የኢየሱስ ተከታዮች ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ መልእክታቸውን ይናገራሉ። ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) በተጨማሪም “ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 28:19, 20
የሚያሳዝነው፣ የክርስቶስ አገልጋዮች ሁልጊዜ ጥሩ አቀባበል አይደረግላቸውም። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ ክርስቲያን ወንጌላዊ ለሆነው ለጢሞቴዎስ “የክርስቶስ ኢየሱስ መልካም ወታደር እንደመሆንህ መጠን አንተም በበኩልህ መከራ ተቀበል” በማለት ጽፎለታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:3) እርግጥ ነው፣ ጢሞቴዎስ የነበሩት የውጊያ መሣሪያዎች መንፈሳዊ የጦር ትጥቆች ናቸው፤ ከእነሱም መካከል “የመንፈስ ሰይፍ” ተብሎ የተጠራው በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ይገኝበታል።—ኤፌሶን 6:11-17
አምላክ እስራኤላውያንን ትቶ የክርስቲያን ጉባኤን ያቋቋመው ለምን ነበር?
የእስራኤል ብሔር 1,500 ለሚያህሉ ዓመታት ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን ወይም በሕጋዊ ውል ላይ የተመሠረተ ልዩ ዝምድና ነበረው። (ዘፀአት 19:5) ሙሴ መካከለኛ የሆነለት ያ ቃል ኪዳን አሥርቱን ትእዛዛትና ሌሎች ሕጎችን የያዘ ነበር፤ እነዚህ ሕጎች እውነተኛው አምልኮ እንዲስፋፋና ሕዝቡ ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ጠብቆ እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጉ ነበር። (ዘፀአት 19:3, 7, 9፤ 20:1-17) የሚያሳዝነው ግን፣ በጥቅሉ ሲታይ እስራኤላውያን ለአምላክ ታማኝ ሳይሆኑ ከመቅረታቸውም በላይ ነቢያቱን እስከ መግደል ደርሰው ነበር።—2 ዜና መዋዕል 36:15, 16፤ ሉቃስ 11:47, 48
በመጨረሻም ይሖዋ አይሁዳዊ ሆኖ የተወለደውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ላከ። ይሁን እንጂ በቡድን ደረጃ ሲታይ የአይሁድ ብሔር ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ከዚህም የተነሳ አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ለረጅም ጊዜ የቆየ ቃል ኪዳን በመተው አይሁዳውያንን ከሌሎች ብሔራት የሚለየው ምሳሌያዊ ግድግዳ እንዲፈርስ አደረገ።a (ኤፌሶን 2:13-18፤ ቆላስይስ 2:14) በዚያው ወቅት አምላክ የክርስቲያን ጉባኤን በማቋቋም ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርጎ ሾመው። ከዚህም በተጨማሪ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ከማለቁ በፊት ጉባኤው ከተለያየ ብሔር የመጡ ሰዎችን ያቀፈ ሆኖ ነበር። አይሁዳዊ የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ “ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” በማለት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 10:35
የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ ይከተላሉ። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ሥራቸውና በፖለቲካዊ ጉዳዮችም ሆነ በሰብዓዊ ጦርነቶች ላይ የማይካፈሉ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ። (ማቴዎስ 26:52፤ የሐዋርያት ሥራ 5:42) አዎ፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከማወጅ ምንም ነገር ትኩረታቸውን እንዲሰርቅባቸው አይፈቅዱም፤ ክፋትን በሙሉ አስወግዶ በምድር ላይ ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍነው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን ‘ከአምላክ ጋር ታረቁ’ ብለን እንለምናለን” በማለት ሲጽፍ ይህን ውድ ተስፋ በአእምሮው ይዞ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 5:20) በዛሬው ጊዜ እነዚህ ቃላት ያያዙትን መልእክት መስማት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጣዳፊ ነው፤ ምክንያቱም የምንኖረው ይህ ክፉ ዓለም ሊጠፋ በተቃረበበት “የመጨረሻዎቹ ቀኖች” መደምደሚያ ላይ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “አይሁዳዊ” የሚለው ስያሜ በመጀመሪያ ያመለክት የነበረው ከእስራኤል ነገዶች መካከል የይሁዳ ነገድ አባል የሆነን ሰው ነበር። በኋላ ግን ይህ ስያሜ ሁሉንም ዕብራውያን ያመለክት ጀመር።—ዕዝራ 4:12
ይህን አስተውለኸዋል?
● ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው የትኛውን እጅግ አስፈላጊ ባሕርይ ማሳየት አለባቸው?—ዮሐንስ 13:34, 35
● የአንድ እውነተኛ ክርስቲያን ዋነኛ “መሣሪያ” ምንድን ነው?—ኤፌሶን 6:17
● የክርስቶስ ወኪሎች የትኛውን አስፈላጊ መልእክት ለሰዎች ያውጃሉ?—ማቴዎስ 24:14፤ 2 ቆሮንቶስ 5:20
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን ያቀፈ የወንድማማች ማኅበር ያላቸው ሲሆን በብሔራት መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች ላይ ፈጽሞ አይካፈሉም