የጡት ካንሰር ፈውስ ይገኝለት ይሆን? እንዴትስ መቋቋም ይቻላል?
ኮንቺታ ለካንሰር ያጋልጣሉ ከሚባሉት የተለመዱ ነገሮች አንዱም እንኳ የሚያሰጋት ሴት አልነበረችም።a ጤነኛ የሆነች የ40 ዓመት ሴት ስትሆን ከቅርብ ዘመዶቿም መካከል የጡት ካንሰር ይዞት የሚያውቅ ማንም የለም። በየጊዜው በምታደርገው የማሞግራም ወይም የጡት ምርመራም ምንም የተገኘባት ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ገላዋን እየታጠበች ሳለ ጡቷን ስትዳብስ እብጠት ነገር እንዳለ ተሰማት። በኋላም ይህ እብጠት ካንሰር ሆኖ ተገኘ። ኮንቺታና ባለቤቷ ዶክተሩ ምን አማራጮች እንዳሏቸው ሲያስረዳቸው በድንጋጤ ተውጠው ያዳምጡት ነበር።
ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ዶክተር የጡት ካንሰር ለያዛት ሴት የሚሰጠው አማራጭ ሕክምና ጡትን፣ በብብትና በደረት አካባቢ የሚገኙ ዕጢዎችን እንዲሁም የደረት ጡንቻዎችን ቆርጦ ማውጣትን የሚጠይቅ ከባድ ቀዶ ሕክምና ብቻ ነበር። ኬሞቴራፒ የሚባለው ሕክምና ዓይነትም ሆነ የጨረር ሕክምና በአብዛኛው ሥቃዩን ከማራዘም በስተቀር ያን ያህል ፋይዳ አልነበረውም። በመሆኑም ብዙዎቹ ከበሽታው ይልቅ “ሕክምናውን” መፍራታቸው አያስገርምም።
ከጡት ካንሰር ጋር የሚደረገውን ውጊያ እልህ አስጨራሽ ያደረገው ከባድ የሕክምና ዘዴዎችን በመጠቀም ይህን ቀሳፊ በሽታ ለማከም የሚደረገው ሙከራ የታካሚውን መልክ የሚያበላሽ እንዲሁም ለከፍተኛ ሥቃይ የሚዳርጉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን የሚያስከትል መሆኑ ነው። እንደ ኮንቺታ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ በጡት ካንሰር የተያዙ ሰዎች በርካታ የሕክምና አማራጮች አሏቸው።b በየጊዜው የሚደረጉ የሕክምና ጥናቶችና የመገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ይህን ሕመም ድል መንሳት እንደሚቻል የሚጠቁሙ አዳዲስ የሕክምና ግኝቶችን፣ በሽታው ይከሰት እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ የሚደረጉ ቅድመ ምርመራዎችን እንዲሁም በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ የአመጋገብ ዓይነቶችን እያበሰሩን ነው።
በሕክምናው መስክ የተገኙ በርካታ መሻሻሎች ቢኖሩም የጡት ካንሰር ለሴቶች ሞት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ አልቀረም።c በጡት ካንሰር በሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ የሰሜን አሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ቢሆኑም በዚህ ረገድ ዝቅተኛ ቁጥር በነበራቸው የእስያና የአፍሪካ አገሮችም ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል። ከዚህም በላይ በእስያና በአፍሪካ ከሚገኙት በጡት ካንሰር ከተያዙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ይሞታሉ። ለምን? በአፍሪካ የሚገኙ አንዲት ዶክተር “የበሽታውን መኖር የሚጠቁሙ ምልክቶችን አስቀድሞ ለማወቅ ጥረት አይደረግም” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። “አብዛኞቹ ታካሚዎች ወደ እኛ የሚመጡት በሽታው በጣም ከጠናባቸው በኋላ ነው።”
ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ በበሽታው የመያዝ አጋጣሚም ሊጨምር ይችላል። በጡት ካንሰር ከሚያዙ ሴቶች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ናቸው። ደስ የሚለው ነገር ግን የጡት ካንሰር በሕክምና ሊድኑ ከሚችሉት የካንሰር ዓይነቶች አንዱ መሆኑ ነው። እንዲያውም የጡት ካንሰሩ ሥር ከመስደዱ በፊት ከታወቀላቸውና በሰውነታቸው ውስጥ ካልተስፋፋባቸው ሴቶች መካከል 97 በመቶ የሚሆኑት በሽታው ከታወቀላቸው ከአምስት ዓመት በኋላም በሕይወት መኖር ችለዋል። ኮንቺታም በቅርቡ አምስት ዓመት አልፏታል።
ስለ ጡት ካንሰር የሚታወቁ መሠረታዊ ነገሮች
ከኮንቺታ ሁኔታ ማየት እንደቻልነው የጡት ካንሰር መኖሩ የሚታወቀው አብዛኛውን ጊዜ በጡት ውስጥ አበጥ ያለ ባዕድ ነገር ሲገኝ ነው። ነገር ግን እንደነዚህ ካሉት እባጭ መሰል ነገሮች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ካንሰርነት የመለወጥ ባሕርይ የሌላቸው ሲሆኑ ብዙዎቹ ሲስት የሚባሉ እንዲሁ ውኃ የቋጠሩ እባጮች ናቸው።
የጡት ካንሰር የሚጀምረው አንድ ሴል ከተለመደው ውጭ በሆነ ሁኔታና ፍጥነት እየተባዛ ሄዶ ቀስ በቀስ ዕጢ ሲሆን ነው። የዚህ ዕጢ ሴሎች ሌሎች ሕብረ ሕዋሳትን መውረር ሲጀምሩ ዕጢው ወደ ካንሰርነት ይለወጣል። አንዳንድ ዕጢዎች እድገታቸው በጣም ፈጣን ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ መኖራቸው እንኳ ሳይታወቅ እስከ አሥር ዓመት ሊቆዩ ይችላሉ።
ኮንቺታ ካንሰር ይኖርባት እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ዶክተሯ በቀጭን መርፌ ከእባጩ ላይ ናሙና ወሰደ። እባጩ የካንሰር ሴሎች እንዳሉት ታወቀ። በዚህም ምክንያት ዕጢውንና በዕጢው ዙሪያ ያሉትን የጡት ሕብረ ሕዋሳት ለማስወገድ እንዲሁም ዕጢው የሚገኝበትን ደረጃ (መጠኑን፣ ዓይነቱንና ስርጭቱን) እና ሁኔታ (የእድገቱን ፍጥነት) ለማወቅ ቀዶ ሕክምና ተደረገላት።
ብዙዎቹ ታካሚዎች ከቀዶ ሕክምና በኋላ ካንሰሩ በሰውነታቸው ውስጥ እንዳይሰራጭና እንዳያገረሽባቸው ለመከላከል ተጨማሪ ሕክምናዎች ይሰጧቸዋል። የካንሰር ሴሎች ከዕጢው ወጥተው በደም ሥር ወይም በሊምፋቲክ ሲስተም ውስጥ በመሄድ እንደገና ማደግ ሊጀምሩ ይችላሉ። ካንሰሩ ተሰራጭቶ እንደ አንጎል፣ ጉበት፣ ቅልጥምና ሳንባ ወዳሉት ዋነኛ የአካል ክፍሎች ውስጥ ከገባ በሽታው ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
ኮንቺታ ዕጢው በነበረበት አካባቢ ያሉትንና በመላ አካላቷ የተሰራጩትን አምልጠው የወጡ ሴሎች ለመቆጣጠር የጨረርና የኬሞቴራፒ ሕክምና ተደረገላት። የያዛት የካንሰር ዓይነት ኢስትሮጅን የተባለውን ሆርሞን የሚያሟጥጥ በመሆኑ አዳዲስ ካንሰሮች እንዳያድጉ ለማድረግ ተጨማሪ ፀረ ሆርሞን ሕክምና ተደረገላት።
በጡት ካንሰር ሕክምና መስክ የተደረጉ እድገቶች እንደ በሽተኞቹ ዕድሜ፣ ጤና፣ የካንሰር ታሪክና የካንሰር ዓይነት ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የሕክምና አማራጮችን አስገኝተዋል። ለምሳሌ አርሌት የተባለች አንዲት ሴት ካንሰር እንዳለባት የታወቀው ካንሰሩ ከወተት መውረጃ ቱቦው ወጥቶ ከመሰራጨቱ በፊት ነበር። ስለሆነም ጡቷን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ሳያስፈልግ እባጩን ብቻ ቆርጦ ማውጣት ተችሏል። አሊስ ቀዶ ሕክምና ከመደረጉ በፊት እባጩ እንዲሟሽሽ የሚያደርግ የኬሞቴራፒ ሕክምና ተሰጥቷት ነበር። የጃኒስ ሐኪም ደግሞ ማስወገድ ያስፈለገው እባጩንና ሴንቲነል የሊምፍ ዕጢውን ማለትም ከእባጩ የሚወጣ ፈሳሽ መጀመሪያ የሚጠራቀምበትን ዕጢ ብቻ ነው። በዕጢው ውስጥ ምንም ዓይነት የካንሰር ሴል ስላልነበረ ሌሎቹን ዕጢዎች መንካት አላስፈለገም። በዚህም የተነሳ ጃኒስ ብዙ የሊምፍ ዕጢዎች በሚወገዱበት ጊዜ ሊያጋጥም የሚችለው የብብት ንፍፊት አልያዛትም።
የጡት ካንሰር ስለሚያድግበት ሁኔታ ብዙ የታወቀ ነገር ቢኖርም የጡት ካንሰር የሚጀምረው ለምንና እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም መልስ አላገኘም።
መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?
የጡት ካንሰር መንስኤዎች ዛሬም በውል አይታወቁም። ተቺዎች እንደሚሉት አብዛኛውን ጊዜ ምርምር የሚደረገው በመንስኤዎቹና በሽታውን መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሳይሆን ብዙ ትርፍ ሊያስገኝ በሚችለው ነገር ላይ ይኸውም በሽታውን መመርመርና ማከም በሚቻልበት መንገድ ላይ ነው። ያም ሆኖ ሳይንቲስቶች ጠቃሚ የሆኑ ፍንጮችን ማግኘት ችለዋል። አንዳንዶች የጡት ካንሰር ብዙ ደረጃዎች ያሉት ውስብስብ ሂደት ውጤት ሲሆን ይህ ሂደት የሚጀምረው ሴሎች ከተለመደው ሥርዓት ውጭ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ይኸውም በከፍተኛ ፍጥነት እንዲባዙ፣ ሌሎች ሕብረ ሕዋሳትን እንዲወርሩ፣ በሽታ ተከላካይ ከሆኑ ሴሎች እንዲያመልጡ እንዲሁም በዋና ዋና የአካል ክፍሎች ላይ አደገኛ ጥቃት እንዲሰነዝሩ በሚያደርግ እንከን ያለበት ጂን ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ።
እነዚህ እንከን ያለባቸው ጂኖች የሚመጡት ከየት ነው? ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ለጡት ካንሰር ከሚያጋልጡ ጂኖች ጋር ይወለዳሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን ጤነኛ የሆኑ ጂኖች ጉዳት የሚደርስባቸው ውጭያዊ በሆኑ ምክንያቶች ነው፤ ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት ከሚጠረጠሩት ነገሮች መካከል ጨረርና ኬሚካሎች ይገኙበታል። ወደፊት የሚደረጉ ምርምሮች ይህን በይበልጥ ያረጋግጡ ይሆናል።
ሌላው መንስኤ ደግሞ አንዳንድ የጡት ካንሰር ዓይነቶችን ሊቀሰቅስ ይችላል የሚባለው ኢስትሮጅን የተባለ ሆርሞን ነው። ስለሆነም አንዲት ሴት የወር አበባ ማየት የጀመረችው ቀደም ብላ ከሆነ ወይም ያረጠችው የተለመደው ዕድሜ ካለፈ በኋላ ከሆነ አሊያም ለመጀመሪያ ጊዜ ያረገዘችው ዘግይታ ከሆነ ወይም ጨርሶ አርግዛ የማታውቅ ከሆነ ወይም ደግሞ የሆርሞን ሕክምና ወስዳ ከነበረ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድሏ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። የስብ ሴሎች ኢስትሮጅን ስለሚያመነጩ ኦቫሪያቸው ሆርሞን ማመንጨት ያቆመ ያረጡ ሴቶችም በጣም ወፍራም ከሆኑ በጡት ካንሰር የመያዝ አጋጣሚያቸው ሊጨምር ይችላል። በመንስኤነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ሌሎቹ ደግሞ ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን መብዛትና በአብዛኛው የሌሊት ሽፍት ሠራተኞች በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰተው ሚላቶኒን የተባለው እንቅልፍ እንዲወስደን የሚያደርገው ሆርሞን ማነስ ናቸው።
ይበልጥ ውጤታማ የሆኑና ብዙ ሥቃይ የማያስከትሉ የጡት ካንሰር ሕክምናዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ የመገኘት ተስፋ ይኖራቸው ይሆን? ተመራማሪዎች የሰውነትን በሽታ የመከላከል ችሎታ እንዲሁም የካንሰሩን እድገት በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ለመግታት የሚያስችሉ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ የሕክምና ዘዴዎችን ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ነው። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የሰውነትን የውስጥ ክፍሎች ለማየት የሚያስችሉት ዘመናዊ መሣሪያዎች ሐኪሞች ጨረርን በሚፈለገው ቦታ ላይ ብቻ እንዲያነጣጥር በማድረግ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለሕክምና እንዲጠቀሙበት ይረዷቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
በተጨማሪም የሳይንስ ሊቃውንት የካንሰር ሴሎች የሚሰራጩበትን መንገድ ለይቶ ለማወቅ፣ ፀረ ካንሰር መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸውን የካንሰር ሴሎች ለማሸነፍ፣ የካንሰር ሴሎች እንዳያድጉ ለመግታትና እያንዳንዱን ዕጢ ነጥሎ ማከም የሚቻልበትን መንገድ ለማግኘት ከፍተኛ ትግል በማድረግ ላይ ናቸው።
ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም በዚህ በዛሬው ዓለም በሽታ ፈጽሞ ሊወገድ የማይችል ሲሆን የሰው ልጆችም መሞታቸው አይቀርም። (ሮም 5:12) ይህን አሳዛኝ እውነታ ሊለውጥ የሚችለው ፈጣሪያችን ብቻ ነው። ግን በእርግጥ ያደርገዋል? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ይህን እንደሚያደርግ ያረጋግጥልናል! “‘ታምሜአለሁ’ የሚል” ሰው የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል።d (ኢሳይያስ 33:24) ይህ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም።
c በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ የጡት ካንሰር በወንዶች ላይ ብዙ ጊዜ አይከሰትም።
d ይህ ተስፋ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀውና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዳው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በስፋት ተብራርቷል።
[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ምልክቶች
በሽታው ሥር ከመስደዱ በፊት መታወቁ ወሳኝ ነገር ነው፤ ይሁን እንጂ በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ የሚደረጉ ማሞግራሞችና ሌሎች የጡት ምርመራዎች ትክክለኛነታቸው አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ጥናቶች ያስጠነቅቃሉ፤ ይህም ሳያስፈልግ ሕክምናው እንዲሰጣቸው እንዲሁም እንዲጨነቁ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም አንዳንድ ባለሙያዎች፣ ሴቶች በጡቶቻቸውና በሊምፍ ዕጢዎቻቸው ወይም በንፍፊቶቻቸው ላይ የሚከሰቱ ለውጦችን ነቅተው እንዲከታተሉ አበክረው ይመክራሉ። ልብ ሊባሉ የሚገባቸው አንዳንድ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦
● በብብት ወይም በጡት አካባቢ የሚፈጠር እብጠት ወይም ዕጢ
● ከጡት ጫፍ የሚወጣ ከወተት የተለየ ማንኛውም ዓይነት ፈሳሽ
● በቆዳው ላይ የሚታይ ማንኛውም ዓይነት የቀለም መቀየር፣ መሻከር ወይም ሌላ ዓይነት ለውጥ
● ያልተለመደ የጡት ጫፍ መጎድጎድ ወይም ሕመም
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የጡት ካንሰር እንዳለብሽ ከታወቀ
● ለመታከምና ለማገገም አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድብሽ እንደሚችል አስቢ።
● የሚቻል ከሆነ ፍላጎትሽንና እምነትሽን የሚያከብሩልሽ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሐኪሞች ምረጪ።
● ስለ ሕመምሽ ለማንና መቼ እንደምትናገሪ ከቤተሰቦችሽ ጋር ሆነሽ ወስኚ። ይህም ወዳጆችሽ ፍቅራቸውን እንዲገልጹልሽና አብረውሽ እንዲጸልዩ እንዲሁም በግላቸው ለአንቺ እንዲጸልዩልሽ ያስችላቸዋል።—1 ዮሐንስ 3:18
● የሚደርስብሽን ስሜታዊ ውጥረት ለመቋቋም መጽሐፍ ቅዱስን አንብቢ፣ ጸልዪ እንዲሁም ገንቢ በሆኑ ነገሮች ላይ አሰላስዪ።—ሮም 15:4፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
● የጡት ካንሰር ይዟቸው ከሚያውቁና ሊያጽናኑሽ ከሚችሉ ሴቶች ጋር ተነጋገሪ።—2 ቆሮንቶስ 1:7
● ስለ ነገ ሳይሆን ዛሬ ስላለው ነገር ብቻ ለማሰብ ሞክሪ። ኢየሱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 6:34
● ጉልበትሽን በቁጠባ ተጠቀሚ። በቂ እረፍት አድርጊ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከሐኪምሽ ጋር መነጋገር
● ከጡት ካንሰር ጋር የተያያዙ መሠረታዊ የሕክምና ቃላትን እወቂ።
● ሐኪሙ ፊት ከመቅረብሽ በፊት ጥያቄዎችሽን በዝርዝር ጻፊ፤ እንዲሁም ባለቤትሽ ወይም ሌላ ሰው አብሮሽ ሆኖ ማስታወሻ በመያዝ እንዲረዳሽ ጠይቂ።
● ሐኪሙ የተናገረው ነገር ካልገባሽ እንዲያስረዳሽ ጠይቂው።
● ሐኪምሽ እንዳንቺ ያለ ሁኔታ ያጋጠማቸው ምን ያህል ሰዎች አክሞ እንደሚያውቅ ጠይቂው።
● ከተቻለ የሌላ ሐኪም ምክር ጠይቂ።
● ሐኪሞቹ የሚሰጡሽ ሐሳብ የማይጣጣም ከሆነ ያላቸውን የሥራ ልምድ አመዛዝኚ። ተገናኝተው እንዲወያዩ ጠይቂያቸው።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ተጓዳኝ ችግሮችን መቋቋም
አንዳንድ የካንሰር ሕክምናዎች እንደ ማቅለሽለሽ፣ የፀጉር መርገፍ፣ ሥር የሰደደ ድካም፣ ሕመም፣ መደንዘዝ፣ የእጅና የእግር መንዘር እንዲሁም የቆዳ መቆጣት የመሰሉ ተጓዳኝ ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። የሚከተሉትን ቀላል እርምጃዎች መውሰድ እነዚህን ችግሮች ሊቀንስ ይችላል፦
● በሽታ የመከላከል አቅምሽ እንዲዳብር በሚገባ ተመገቢ።
● የአቅምሽን ሁኔታና የተለያዩ ምግቦች የሚያስከትሉብሽን ውጤት ተከታትለሽ መዝግቢ።
● የማቅለሽለሽና የሕመም ስሜትሽን መድኃኒት፣ አኩፓንክቸር ወይም እሽት ይቀንስልሽ እንደሆነ እዪ።
● አቅም እንዲኖርሽ፣ ክብደትሽን መቆጣጠር እንድትችዪና በሽታ የመከላከል አቅምሽ የተሻለ እንዲሆን መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርጊ።e
● በቂ እረፍት አድርጊ፤ ይሁን እንጂ ብዙ መተኛት ድካም ሊያባብስ እንደሚችል አትርሺ።
● ቆዳሽ እንዳይደርቅ አድርጊ። ለቀቅ ያለ ልብስ ልበሺ። በሙቅ ውኃ ታጠቢ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
e የካንሰር ሕመምተኞች ማንኛውንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራም ከመጀመራቸው በፊት የሕክምና ባለሙያ ማማከር አለባቸው።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንድ የምትቀርቡት ሰው ካንሰር ቢይዘው
አንድ የምትቀርቡት ሰው ካንሰር ቢይዘው ድጋፍ ልትሰጡት የምትችሉት እንዴት ነው? “ደስ ከተሰኙ ሰዎች ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ሰዎች ጋር አልቅሱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ሥራ ላይ በማዋል ነው። (ሮም 12:15) ስልክ በመደወል፣ ደብዳቤ ወይም ኢሜይል በመጻፍ፣ ካርድ በመላክና ጎራ ብሎ በመጠየቅ ፍቅራችሁንና አሳቢነታችሁን ግለጹ። አብራችሁት ጸልዩ እንዲሁም የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንብቡለት። ቤርል የተባለች የአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ አገልጋይ ሚስት “በሕይወት ስላሉት እንጂ በካንሰር ስለሞቱት ሰዎች አታንሱ” በማለት ትመክራለች። በአንድ ወቅት የካንሰር ሕመምተኛ የነበረችው ጃኒስ “የታመመችውን ወዳጃችሁን ሄዳችሁ እቅፍ አድርጓት” በማለት ትመክራለች። “ስለ በሽታዋ ማውራት ከፈለገች ራሷ ታወራለች።” በተለይ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደሚወዷቸው ደጋግመው ማረጋገጥ ያስፈልጋቸዋል።
ጄፍ “ስለ ካንሰር የማናወራባቸው የተወሰኑ ቀናት ነበሩ” በማለት ያስታውሳል። “ባለቤቴ የሁላችንም ትኩረት በእሷ ጤና ላይ ብቻ እንዳይሆን ለማድረግ ትጥር ነበር። በመሆኑም በተወሰኑ ጊዜያት ስለ ካንሰር የማናወራበት ሙሉ ቀን እንዲኖር ወሰንን። ከዚህ ይልቅ በዚያ ቀን አዎንታዊ በሆኑት የሕይወታችን ዘርፎች ላይ እናተኩር ነበር። ይህም ከበሽታው እረፍት የመውሰድ ያህል ነበር።”
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ምን ተሰምቷቸው ነበር?
የምርመራውን ውጤት ሲሰሙ
ሻረን፦ ሕይወቴ በቅጽበት ተለወጠ። “በቃ አለቀልኝ” አልኩ።
እጅግ አስቸጋሪ በሆነው ወቅት
ሳንድራ፦ ከሕክምናው የሚብሰው የአእምሮ ሥቃዩ ነው።
ማርግሬት፦ ከሁለተኛው ሕክምና በኋላ “ሁለተኛ አላደርገውም” ትላለህ። ቢሆንም ማድረግህ አይቀርም።
ስለ ወዳጆቻቸው
አርሌት፦ እንዲጸልዩልን ስላሰብን ለወዳጆቻችን ነገርናቸው።
ጄኒ፦ ማንም ሰው የሚያሳየን ፈገግታ ወይም የሚሰጠን ሰላምታ ለእኛ ትልቅ ትርጉም ነበረው።
ጥሩ ድጋፍ ስለሚሰጡ ባሎቻቸው
ባርብራ፦ ፀጉሬ ረግፎ ከማለቁ በፊት ልላጨው ወሰንኩ። በዚህ ጊዜ ኮሊን “የጭንቅላትሽ ቅርጽ እኮ በጣም ያምራል” አለኝ። አነጋገሩ አሳቀኝ።
ሳንድራ፦ አብረን ሆነን ፊታችንን በመስተዋት ተመለከትን። በጆ ፊት ላይ ምንም ዓይነት የስሜት መለዋወጥ አልታየም።
ሳሻ፦ ካርል ለሌሎች ሲናገር “ካንሰር ይዞናል” ይል ነበር።
ጄኒ፦ ጄፍ ለእኔ ያለው ፍቅር ቀንሶ አያውቅም፤ መንፈሳዊነቱም ቢሆን የሚያረጋጋና የማይዋዥቅ ነበር።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የካንሰር ሴሎች ከተለመደው ውጭ በብዛት ይራባሉ እንዲሁም ሌሎች ሕብረ ሕዋሳትን ይወርራሉ
[ሰንጠረዥ]
ጤነኛ ሴሎች ያሉት የወተት መውረጃ ቱቦ
ያልተሰራጨ የቱቦ ውስጥ ካንሰር
የተሰራጨ የቱቦ ውስጥ ካንሰር
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወዳጆችና ዘመዶች ለበሽተኛው የሚሰጡት ፍቅራዊ ድጋፍ የካንሰር ሕክምና ዋነኛ ክፍል ነው