በአየር ንብረት ዙሪያ የሚደረጉ ስብሰባዎች ውጤት ያስገኙ ይሆን?
“ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለማስወገድ መላው ዓለም መረባረብ አለበት። አንድ እርምጃ ካልወሰድን አሁን ያለው ድርቅ፣ ረሃብና የሕዝቦች ከቀያቸው መፈናቀል እየተባባሰ እንደሚሄድና ይህም ለአሥርተ ዓመታት የሚዘልቁ ተጨማሪ ግጭቶች ሊያስነሳ እንደሚችል ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ይስማማሉ።”—የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት፣ ባራክ ኦባማ
አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ ፕላኔቷ ምድራችን ታምማለች። ትኩሳቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። እንደ እነሱ አባባል ከሆነ የምድር ሙቀት ገደቡን ወደማለፍ ደረጃ እየደረሰ ያለ ይመስላል፤ በሌላ አባባል በቋፍ ላይ ያለው የሙቀት መጠን በጥቂቱም እንኳን ከፍ ቢል “የምድር ሙቀት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር የሚያደርግ ለውጥ በከባቢ አየር ላይ ሊከሰት እንደሚችል” ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የብሪታኒያ ጋዜጣ ገልጿል።
ለመሆኑ እንዲህ ያለ ጣጣ ውስጥ ልንገባ የቻልነው እንዴት ነው? ሁኔታውን ማሻሻል የሚቻልበትስ መንገድ ይኖር ይሆን? በእርግጥ የሰው ልጆች፣ ከፊታቸው የተጋረጡባቸውን ሌሎች በርካታ ከባባድ ችግሮች ጨምሮ ከምድር ሙቀት መጨመር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አቅም አላቸው?
በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚያምኑት ከሆነ ለምድር ሙቀት መጨመር ዋነኛው መንስኤ የሰው ልጆች ናቸው፤ ለዚህ እንደ ምሳሌ ከሚጠቀሱት ነገሮች አንዱ የኢንዱስትሪው አብዮት እንደ ነዳጅ ዘይትና የድንጋይ ከሰል ያሉ ከቅሪተ አካል የሚገኙ ነዳጆች ፍጆታ እንዲጨምር ማድረጉ ነው። ሌላው ደግሞ በጣም እየተስፋፋ የመጣው የደን ጭፍጨፋ ነው። ደኖች ለከባቢ አየራችን እንደ ሳንባ ሆነው ያገለግላሉ። ዛፎች፣ ግሪንሃውስ የሚባሉትን ለምድር ሙቀት መጨመር ምክንያት የሚሆኑ አንዳንድ ጋዞችን ወደ ውስጣቸው ያስገባሉ። ደኖች በብዛት እየተጨፈጨፉ ሲመጡ ግን በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የእነዚህ ጋዞች መጠን እየጨመረ ይሄዳል። በመሆኑም ለእነዚህ ችግሮች እልባት ለመስጠት የዓለም መሪዎች በአየር ንብረት ዙሪያ የሚመክሩ የተለያዩ ስብሰባዎችን አካሂደዋል።
የኪዮቶው ስምምነት
በ1997ቱ የኪዮቶ ስምምነት ላይ የዓለም መሪዎች የካርቦን ዳይኦክሳይድን ልቀት ለመቀነስ ቃል ገብተው ነበር። የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችና በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሌሎች 37 አገሮች የካርቦን ዳይኦክሳይድን ልቀት በ1990 ከነበረው በአማካይ 5 በመቶ ለመቀነስና ይህንንም ከ2008 እስከ 2012 ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን በፊርማቸው አረጋግጠው ነበር።
ይሁንና የኪዮቶው ስምምነት አንዳንድ የጎሉ ድክመቶች ነበሩበት። ለምሳሌ ያህል፣ ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱን አልፈረመችም። በተጨማሪም እንደ ቻይናና ሕንድ የመሳሰሉ በማደግ ላይ ያሉ ትላልቅ አገሮች በጋዝ ልቀት መጠን ላይ የተጣለባቸውን ገደብ ሳይስማሙበት ቀርተዋል። የሚገርመው ግን ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና ብቻ የሚለቁት የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን በዓለም ዙሪያ ወደ ከባቢ አየር ከሚገባው ውስጥ 40 በመቶ ይሆናል።
የኮፐንሃገኑ ስብሳባ
ኮፕ 15 (COP 15) ተብሎ የተጠራው የኮፐንሃገኑ ስብሰባ ዓላማ የኪዮቶውን ስምምነት በመተካት በ2012ና ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ተግባራዊ የሚሆን አዲስ ስምምነት መፈራረም ነበር።a ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለማስወገድ 119 የአገር መሪዎችን ጨምሮ ከ192 አገሮች የመጡ ተወካዮች ታኅሣሥ 2009 በኮፐንሃገን፣ ዴንማርክ ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። ይሁንና ኮፕ 15 የሚከተሉት ሦስት ዋና ዋና ተፈታታኝ ችግሮች ተጋርጠውበት ነበር፦
1. ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው ስምምነት ላይ መድረስ። ያደጉ አገሮች በጋዝ ልቀት መጠን ላይ የተጣለባቸውን ገደብ ይቀበሉት ይሆን? በማደግ ላይ ያሉ ትላልቆቹ አገሮችስ እየጨመረ በሚሄደው የጋዝ ልቀት መጠናቸው ላይ ገደብ ለማበጀት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ? እነዚህ ጥያቄዎች መፍትሔ የሚያሻቸው ናቸው።
2. ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ። በማደግ ላይ ያሉ አገሮች፣ በምድር ሙቀት ሳቢያ በፍጥነት እየጨመሩ ያሉ ችግሮችን መቋቋምና አካባቢን የማይበክል ቴክኖሎጂን ማስፋፋት እንዲችሉ ለረጅም ዓመታት የሚቆይ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
3. የጋዝ ልቀትን መቆጣጠር የሚቻልበትን ዘዴ በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረስ። እንዲህ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ ቢቻል ኖሮ እያንዳንዱ አገር በጋዝ ልቀት መጠን ላይ የተጣለበትን ገደብ ከማለፍ ይቆጠብ ነበር። በተጨማሪም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በእርዳታ ያገኙትን ገንዘብ በአግባቡ እየተጠቀሙበት መሆኑን ለመቆጣጠር ያስችል ነበር።
ታዲያ እነዚህ ሦስት ተፈታታኝ ችግሮች መፍትሔ ተገኝቶላቸዋል? የተለያዩ ድርድሮች ቢደረጉም በቀላሉ ስምምነት ላይ ይደረስባቸዋል ተብለው በተገመቱ ጉዳዮች እንኳ መግባባት አልተቻለም ነበር። በስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይ ከ28 አገሮች የመጡ መሪዎች ከብዙ ፍትጊያ በኋላ የኮፐንሃገን ስምምነት ተብሎ የሚጠራውን ሰነድ አጽድቀዋል። ይህ ስምምነት ይፋ በሆነበት ወቅት “ይህ ጉባኤ . . . ለኮፐንሃገኑ ስምምነት ትኩረት ይሰጣል” በማለት የተናገሩ ሲሆን ይህ አባባላቸው ቁርጥ አቋም የማይንጸባረቅበት እንደሆነ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ገልጿል። በሌላ አነጋገር ስምምነቱን ተግባራዊ የማድረጉ ጉዳይ ለእያንዳንዱ አገር የተተወ ነው ማለት ነው።
ወደፊትስ ምን ታስቧል?
ከኮፐንሃገኑ ጉባኤ በኋላ የተደረጉም ሆነ ሊደረጉ በእቅድ የተያዙ ስብሰባዎች ቢኖሩም መፍትሔ የማምጣታቸው ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ነው። ኒው ዮርክ ታይምስ በተሰኘው ጋዜጣ ላይ የአንድ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ፖል ክሩግማን “ፕላኔቷ ምድራችን በሙቀት መቀቀሏን ትቀጥላለች” በማለት ተናግረዋል። ብዙውን ጊዜ፣ ወደፊት በአካባቢ ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ይልቅ አሁን የሚገኘው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የተሻለ መስሎ ስለሚታይ ነገሮች ባሉበት እንዲቀጥሉ ይደረጋል። “የዓለም መሪዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚወሰደውን እርምጃ መቀበል የከበዳቸው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ከፈለጋችሁ የገንዘብ ምንጫቸውን ማወቅ ነው” በማለት ክሩግማን ይናገራሉ። በተጨማሪም ክሩግማን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በአገራቸው ሊወሰዱ የታሰቡት እርምጃዎች ለመክሸፋቸው በዋነኝነት የሚጠቀሱት “ስግብግብነትና [የፖለቲከኞቹ] ወኔ ማጣት” እንደሆኑ ጽፈዋል።
የምድር ሙቀት መጨመር በብዙ መንገድ ከአደገኛ አውሎ ነፋስ ጋር ይመሳሰላል ማለት ይቻላል። የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ፍጹም ትክክል ይሆናሉ ባይባልም በአብዛኛው አውሎ ነፋሱ በሚያልፍበት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን ለማስጠንቀቅ ሲባል የነፋሱን ኃይል በመሣሪያ ሊለኩ እንዲሁም የሚጓዝበትን አቅጣጫ በካርታ ላይ ሊያሰፍሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በዓለም ያሉ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ፖለቲከኞች ወይም ታላላቅ ነጋዴዎች አውሎ ነፋሱን ማስቆም አይችሉም። የምድር ሙቀት መጨመርን በተመለከተም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም ለማለት ይቻላል። ይህ እውነታ በኤርምያስ 10:23 ላይ “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ያስታውሰናል።
አምላክ ከምድር ሙቀት መጨመር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ያስወግዳል
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ምድርን ያበጃትና የሠራት ባዶ እንድትሆን’ አለመሆኑን ይናገራል። (ኢሳይያስ 45:18) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” ይላል።—መክብብ 1:4
አዎን፣ ሰዎች ምድርን ለመኖሪያነት የማትመች እንድትሆን ሲያደርጓት አምላክ ዝም ብሎ አይመለከትም። ከዚህ ይልቅ ጣልቃ በመግባት ስኬታማ ያልሆነውን ሰብዓዊ አገዛዝና ለምድር ምንም ደንታ የሌላቸውን ሰዎች ያስወግዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም ያላቸውና በሙሉ ልባቸው እሱን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች በሕይወት እንዲተርፉ ያደርጋል። ምሳሌ 2:21, 22 እንዲህ ይላል፦ “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዘ ኮንፈረንስ ኦቭ ዘ ፓርቲስ (The Conference of the Parties) በምህጻረ ቃል ኮፕ (COP) የሚባለው መደበኛ ጉባኤ የሚዘጋጀው በዩናይትድ ኔሽንስ ፍሬምዎርክ ኮንቬንሽን ኦን ክላይሜት ቼንጅ አማካኝነት ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ግሪንሃውስ ጋዝ በከባቢ አየር ውስጥ ከሚገኙ ጋዞች አንዱ ሲሆን ከምድር ገጽ የሚነሳውን ሙቀት አፍኖ የማስቀረት ባሕርይ አለው። ከዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ከሚለቀቁት ጋዞች ውስጥ አብዛኞቹ ግሪንሃውስ ጋዞች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ክሎሮፍሎሮካርቦን፣ ሜቴንና ናይትረስ ኦክሳይድ ይገኙበታል። ካርቦን ዳይኦክሳይድን ብቻ እንኳ ብንወስድ በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ከ25 ቢሊዮን ቶን በላይ ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃል። ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የኢንዱስትሪው ዘመን ከጀመረ ወዲህ በከባቢ አየሩ ውስጥ ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን 40 በመቶ ጨምሯል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Earth: NASA/The Visible Earth (http://visibleearth.nasa.gov/); Barack Obama: ATTILA KISBENEDEK/AFP/Getty Images