ዓመፅ የተጠናወተው ዓለም
የምንኖርበት ዓለም ዓመፅ የተጠናወተው ሆኗል። ዓመፅ ምንጊዜም በመዝናኛ ውስጥ እንደ ቅመም የሚጨመር መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው። ይሁን እንጂ ሚዲያ አዌርነስ ኔትወርክ እንደገለጸው ከሆነ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርበው ዓመፅ ሌላ መልክ እየያዘ መጥቷል። በአንድ በኩል፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡት የዓመፅ ድርጊቶች በጣም በዝተዋል።” በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ የዓመፅ ድርጊቶች ይበልጥ “ሰቅጣጭ፣ የፆታ ብልግና የሞላባቸው እንዲሁም በሌሎች ሥቃይ መደሰትን የሚያንጸባርቁ” ሆነዋል። ቀጥሎ የቀረበውን መረጃ ተመልከት።
ሙዚቃ፦ የግጥም ይዘታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው እየሆነ የመጡ ዘፈኖች “በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እየተሰጣቸው መጥተዋል” በማለት ቀደም ሲል የተጠቀሰው ምንጭ ይናገራል። አንዳንድ ዘፈኖች መግደልንና አስገድዶ መድፈርን የሚያበረታቱ ጸያፍ ቃላትን ይጠቀማሉ፤ ሌላው ቀርቶ በሚስቶችና በእናቶች ላይ እንዲህ ያለውን ተግባር መፈጸም ጥሩ ነገር እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ።
የቪዲዮ ጨዋታዎች፦ “የቪዲዮ ጨዋታዎች ደም መፋሰስ የሞላባቸው መሆኑ የሚያሳዝን ነው” በማለት ለቪዲዮ ጨዋታ አፍቃሪዎች የሚዘጋጅ አንድ በብሪታንያ የሚታተም መጽሔት ተናግሯል። አክሎም “የቪዲዮ ጨዋታ የሚወድ ሰው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የዓመፅ ድርጊቶችን መውደዱ ግድ እየሆነበት መጥቷል” ብሏል። ለምሳሌ ያህል፣ ተወዳጅ በሆነ አንድ የቪዲዮ ጨዋታ ላይ ተጫዋቹ፣ ሴቶችን ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ በቤዝቦል ኳስ መምቻ መደብደብ ይችላል። የቪዲዮ ጨዋታዎች ተጠቃሚውን የሚያሳትፉ በመሆናቸው ከቴሌቪዥን ይበልጥ በልጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው አንዳንድ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
ፊልሞች፦ በፊልሞች ውስጥ የሚታዩት ወሲባዊና የዓመፅ ድርጊቶች እንዲሁም ጸያፍ ንግግሮች በጣም እንደጨመሩ ብሎም ለፊልሞቹ የሚወጣላቸው የደረጃ ምደባም ቢሆን እምነት የሚጣልበት እንዳልሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከዚህም በላይ የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙት “መጥፎ” ገጸ ባሕርይ የተሰጣቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። አንድ ጥናት እንደሚገልጸው ከሆነ በቴሌቪዥን፣ በፊልሞችና በሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ ከሚተላለፉት የዓመፅ ድርጊቶች ውስጥ ወደ ግማሽ ገደማ የሚሆነው የሚፈጸመው “ጥሩ” ገጸ ባሕርይ በተሰጣቸው ሰዎች ነው።
ዜና፦ ብዙ የቴሌቪዥን ዜና አዘጋጆች የሚመሩበት ደንብ “ደም ያለበት ነገር ብዙ ተመልካች አለው” የሚል ነው። ዜናዎች ትልቅ ትርፍ የሚገኝባቸው እየሆኑ መጥተዋል፤ ተመልካቾች የዓመፅ ድርጊት የሚታይባቸውን ዘገባዎች እንደሚወዱ የዜና ሰዎች ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ብዙ ተመልካቾች ያሉት መሆኑ ደግሞ የማስታወቂያ ድርጅቶችን ትኩረት ይስባል። ይህም በብዙ አገሮች ውስጥ ለቴሌቪዥን ድርጅቶች የገቢ ምንጭ ሆኖላቸዋል።
ድረ ገጾች፦ በኮምፒውተር የተቀነባበሩ ወይም በገሃዱ ዓለም የተፈጸሙ የዓመፅ ድርጊቶችን ይኸውም ማሠቃየትን፣ የሰዎችን አካል መቆራረጥን፣ በሌሎች አካል ላይ ጉዳት ማድረስንና ግድያን የሚያሳዩ ምስሎችን በኢንተርኔት ላይ ማግኘት ይቻላል። ብዙ ልጆች ደግሞ እነዚህን ድረ ገጾች ይመለከታሉ።
በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የዓመፅ ድርጊቶች ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ?
በቴሌቪዥን፣ በፊልሞች፣ በመጻሕፍት፣ በሙዚቃና በሌሎችም ዓይነት መዝናኛዎች የሚተላለፉት የዓመፅ ድርጊቶች በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ? እርግጥ ነው፣ በእነዚህ አማካኝነት ከፍተኛ ትርፍ የሚያጋብሱ ሰዎች ለሕዝብ የሚያቀርቡት ነገር ምንም ጉዳት እንደሌለው በመናገር ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የንግዱ ዓለም በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ለቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣል፤ ምናልባትም አንዱ ማስታወቂያ የሚወስደው ጊዜ ከ30 ሴኮንዶች የማይበልጥ ይሆናል። ታዲያ ዋና ተዋንያኑ የሥነ ምግባር ብልግናና ዓመፅ ሲፈጽሙ የሚታዩበት የ90 ደቂቃ ፊልም፣ በተለይ የሚያዩትን ነገር ሁሉ ትክክል አድርገው በሚቀበሉ ሕፃናት ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ማሰብ ምክንያታዊ ነው?
ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ስለ ሰዎች ባሕርይ ከእኛ እጅግ የላቀ እውቀት አለው። ታዲያ እኛን ለማዝናናት እንደተዘጋጁ ተደርገው በሚቆጠሩ ተወዳጅ በሆኑ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚቀርቡ ሰዎችን ጨምሮ የዓመፅ ድርጊት ከሚፈጽሙ ጋር ስለ መቀራረብ ምን ነግሮናል? ቀጥሎ የሰፈሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተመልከት፦
● “እግዚአብሔር ጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤ ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች።”—መዝሙር 11:5
● “ከግልፍተኛ ጋር ወዳጅ አትሁን፤ በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋር አትወዳጅ፤ አለበለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤ ራስህም ትጠመድበታለህ።”—ምሳሌ 22:24, 25
እርግጥ ነው፣ መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ራሳችንን መጠበቅ አንችልም። ይሁን እንጂ የምንዝናናበትን ነገርና አብረን ጊዜ የምናሳልፋቸውን ሰዎች መምረጥ እንችላለን። ስለዚህ ‘ምን ዓይነት ሰው መሆን ነው የምፈልገው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከዚያም እንዲህ ከመሰሉ ሰዎች ማለትም የአንተ ዓይነት ግቦችና የሥነ ምግባር ደንቦች ካላቸው ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ጥረት አድርግ።—ምሳሌ 13:20
ለዓመፅ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት አብረናቸው ጊዜ የምናሳልፋቸው ሰዎችና የመዝናኛ ምርጫችን ብቻ አይደለም፤ ተጽዕኖ ሊያደርጉብን የሚችሉ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ታዲያ እነዚህ ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመዝናኛ ምርጫችን ለዓመፅ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል