የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 10/12 ገጽ 12-14
  • የቆላ ጎሪላዎችን መጎብኘት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የቆላ ጎሪላዎችን መጎብኘት
  • ንቁ!—2012
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተራራ ጎሪላዎችን መጎብኘት
    ንቁ!—1999
  • ለዱር እንስሳት ምቹ መኖሪያ የሆነችው ጋቦን
    ንቁ!—2008
  • የሕፃኗ ጎሪላ ለቅሶ
    ንቁ!—2008
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2012
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2012
g 10/12 ገጽ 12-14

የቆላ ጎሪላዎችን መጎብኘት

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ በሚገኙ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ውስጥ ብዙ ሰዎች ያላዩት የተፈጥሮ ሀብት ይገኛል። አስቸጋሪ በሆነ መንገድ ለ12 ሰዓት ያህል በመኪና ከተጓዝን በኋላ በአገሪቱ ደቡባዊ ምዕራብ ጫፍ ማለትም በካሜሩንና በኮንጎ ሪፑብሊክ መካከል ወደሚገኘው የዛንጋ እንዶኪ ብሔራዊ ፓርክ ደረስን። ዓላማችን በምዕራብ ቆላማ አካባቢ የሚገኘውን ማኩምባ የተባለውን ጎሪላና ቤተሰቡን ማየት ነበር።

አስጎብኚያችን፣ በእግራችን የምንሄድበት አቅጣጫ ዝሆኖች ምግብ ፍለጋ በየቀኑ የሚመላለሱበት መንገድ ስለሆነ ሳንነጣጠል እንድንጓዝና ከዝሆኖች እንድንጠነቀቅ ነገረችን። ይሁን እንጂ ልንጠነቀቅ የሚገባው እንስሳ ዝሆን ብቻ አልነበረም። አስጎብኚያችን እንዲህ በማለት አስጠነቀቀችን፦ “አንድ ጎሪላ ሊያጠቃችሁ ከሞከረ ቀጥ ብላችሁ ቁሙና መሬት መሬት እዩ። ዝም ብሎ ይጮሃል እንጂ ጉዳት አያደርስባችሁም። ፊት ለፊት አትዩት። እንዲያውም በዚህ ወቅት ዓይን መጨፈን እንደሚጠቅም ተገንዝቤያለሁ።”

ከአስጎብኚያችን ጋር ሆኖ ይመራን የነበረው ሰው በቁመናቸውና አጫጭር በመሆናቸው ምክንያት ከፒግሚዎች መካከል ከሚመደቡት የባአካ ሕዝቦች አንዱ ነው። የአካባቢው ተወላጅ የሆነው መንገድ መሪያችን ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሲሆን ብዙም የማይስተዋሉ ነገሮችን በማየትና በማሽተት እንዲሁም አነስተኛ ድምፆችን በመስማት፣ ደብዛቸውን የሚያጠፉ እንስሳት እንኳ የት እንዳሉ መለየት ይችላል። በጉዟችን ወቅት ንቦች እየወረሩን እረፍት አሳጡን። በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ በቀላሉ እየተሹለከለከ ከሚሄደው መንገድ መሪያችን ጋር እኩል መራመድ አስቸጋሪ ሆኖብን ነበር።

ብዙም ሳይቆይ መንገድ መሪያችን፣ ምዕራባውያን ደርሰውበት ወደማያውቁት ድንግል ጫካ ውስጥ አስገባን። ከዚያም ድንገት ቆም አለና መንገዳችን አጠገብ ያለውን ሰፊ ቦታ በእጁ አሳየን። ዞር ስንል ግልገል ጎሪላዎች ሲጫወቱ ያበላሹትን ቁጥቋጦና የረጋገጡትን ሣር ተመለከትን፤ እንዲሁም ከጠዋቱ መክሰሳቸው የተራረፉ የእንጨት ስብርባሪዎችን አየን። ጉዟችንን በቀጠልን መጠን ጎሪላዎቹን የማየት ጉጉታችን እየጨመረ ሄደ።

ሦስት ኪሎ ሜትር የሚያህል ርቀት ከተጓዝን በኋላ መንገድ መሪያችን ፍጥነቱን ቀነስ አደረገ። ጎሪላዎቹ እንዳይደነግጡ አስቀድሞ በምላሱ ድምፅ አሰማ። ወፍራም የእንስሳ ድምፅ እንዲሁም እንጨት ሲሰበር የሚሰማ ድምፅ ከቅርበት ሰማን። አስጎብኚያችን በቀስታ ወደ ፊት እንድንራመድ ጠቆመችን። ከዚያም እጇን አፏ ላይ በማድረግ ምንም ዓይነት ድምፅ እንዳናሰማ በምልክት አስጠነቀቀችን። ቁጢጥ እንድንል ከነገረችን በኋላ በዛፎቹ መሃል ወዳለ ቦታ አመለከተችን። ስምንት ሜትር በሚያህል ርቀት ላይ ማኩምባን አየነው!

ብዙ ውካታ የነበረው ጫካ በአንድ ጊዜ ረጭ ከማለቱ የተነሳ የልባችን ምት ይሰማን ነበር። በዚህ ጊዜ በሁላችንም አእምሮ ውስጥ የነበረው ጥያቄ ‘ማኩምባ ይመጣብን ይሆን?’ የሚለው ነው። ማኩምባ ፊቱን ወደኛ አዙሮ ቃኘት ካደረገን በኋላ በረጅሙ በማዛጋት አቀባበል አደረገልን። በዚህ ወቅት ሁላችንም ‘እፎይ’ አልን!

በአካ ቋንቋ ማኩምባ ማለት “ፈጣን” ማለት ቢሆንም ማኩምባ አብረነው ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ ቁርሱን ዘና ብሎ ከመብላት በስተቀር የተለየ እንቅስቃሴ አላደረገም። ከአጠገቡ ሁለት ግልገሎች ሲላፉና ሲጫወቱ ይታያል። ትላልቅ ዓይኖች ያሉት ሶፖ የተባለው ግልገል ጎሪላ ከእናቱ ከሞፓምቢ ጋር ይጫወታል፤ የአሥር ወር ዕድሜ ያለው ሶፖ አካባቢውን ለማወቅ ባለው ጉጉት የተነሳ ከእናቱ ጉያ ለመውጣት ሲሞክር እናቱ ቀስ አድርጋ ትመልሰው ነበር። ከቀሩት የቤተሰቡ አባላት መካከል ግማሾቹ ከቅርንጫፎች ላይ ቅጠል ሲቀነጣጥሱና ቅርፊቱን ሲልጡ ሌሎቹ ደግሞ አንድ ላይ ሆነው ይጫወቱ ነበር። በመሃል እኛን ማየት ይጀምሩና ቶሎ ስለሚሰለቻቸው ወዲያው ወደ ጨዋታቸው ይመለሳሉ።

ከአንድ ሰዓት በኋላ የጉብኝት ጊዜያችን አለቀ። ማኩምባም እንደኛው ሳይሰማው አልቀረም፤ ጎርነን ያለ ድምፅ እያሰማ በወፍራም ክንዱ ተደግፎ ከተነሳ በኋላ ወደ ጫካው ገባ። በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ መላው ቤተሰብ ከዓይናችን ተሰወረ። ከእነዚህ አስደናቂ እንስሳት ጋር ያሳለፍነው ጊዜ አጭር ቢሆንም ይህ ጉብኝት የፈጠረብን ስሜት ለብዙ ዓመታት አብሮን ይኖራል።

የጎሪላዎች ሕይወት

አስጎብኚያችን እንደነገረችን ከሆነ ጎሪላዎች በጣም ግዙፍ ሰውነት ሊኖራቸው የቻለው ጥቂት ቀንበጦችን፣ ቅጠሎችንና የዛፍ ቅርንጫፎችን በመመገብ ብቻ ነው። በተጨማሪም ነፍሳትንና ወቅት ጠብቀው የሚያፈሩ ፍራፍሬዎችን የሚመገቡ ሲሆን ምግብ ፍለጋ በቀን እስከ 4 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊጓዙ ይችላሉ። አንድ የጎሪላ ቤተሰብ መሬት ላይ ሊያድር ይችላል፤ አሊያም ዛፍ ላይ በሠራው ጎጆ ውስጥ ይተኛል። አውራው ጎሪላ የጀርባው ፀጉር የሸበተ ስለሚመስል ባለ ብርማ ጀርባ ይባላል። ባለ ብርማ ጀርባ ጎሪላ ቤተሰቡን ለመጠበቅ ሲል አብዛኛውን ጊዜ መሬት ላይ ይተኛል።

ጎሪላዎቹ ከሰው ጋር እንዲላመዱ ለማድረግ ሲባል መንገድ መሪዎቹ ቢያንስ ለአምስት ዓመት ያህል በየቀኑ እንዲጎበኟቸው ይደረጋል። በዚህ መንገድ ለማዳ እንዲሆኑ የተደረጉትን ጎሪላዎች ቱሪስቶች ይጎበኟቸዋል፤ ቱሪስቶቹ ወደ ፓርኩ ለመግባት የሚከፍሉት ክፍያ እነዚህን ለመጥፋት የተቃረቡ እንስሳት ለመታደግ ለሚደረገው ምርምርና ጥበቃ ይውላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ