የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 12/12 ገጽ 19-21
  • የካውካሰስ ተራሮች—የቋንቋዎች መናኸሪያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የካውካሰስ ተራሮች—የቋንቋዎች መናኸሪያ
  • ንቁ!—2012
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጉራማይሌ ሕዝብ
  • በካውካሰስ የደረሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅ መቋቋም
    ንቁ!—2003
  • “ከየቋንቋው” የተውጣጡ ሰዎች ምሥራቹ ደረሳቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ቋንቋዎች ለሐሳብ ልውውጥ እንደ ድልድይ ወይም እንደ አጥር ሊሆኑ ይችላሉ
    ንቁ!—2000
  • በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ሌላ ቋንቋ ለሚናገር ሰው መመሥከር
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2015
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2012
g 12/12 ገጽ 19-21

የካውካሰስ ተራሮች​—የቋንቋዎች መናኸሪያ

ሰፊና ተራራማ በሆነ አንድ አካባቢ እንደምትገኝ አድርገህ አስብ። በዚህ አካባቢ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ብሔረሰቦች እንደሚኖሩ ስታውቅ ትገረም ይሆናል። በዚያ ላይ ደግሞ ቅርብ ለቅርብ ባሉ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች እንኳ በቋንቋ ምክንያት ላይግባቡ ይችላሉ! የመካከለኛው ዘመን የጂኦግራፊ ሊቃውንትም ይህ ሁኔታ ሳይገርማቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው አንዱ ይህን የካውካሰስ አካባቢ “የልሳናት ተራራ” ሲል ሰይሞታል።

በጥቁር ባሕርና በካስፒያን ባሕር መካከል የሚገኙት የካውካሰስ ተራሮች፣ የአህጉራት መሸጋገሪያና የታላላቅ ሥልጣኔዎች ማዕከል በመሆናቸው የረጅም ጊዜ ታሪክና የተለያዩ ባሕሎች ሊኖራቸው ችሏል። የአካባቢው ሕዝቦች ለአረጋውያን ባላቸው አክብሮት፣ ለጭፈራ ባላቸው ፍቅርና ሞቅ ባለ የእንግዳ ተቀባይነታቸው ይታወቃሉ። ብዙ ጎብኚዎች የሚደነቁት ግን በካውካሰስ ባለው የጎሳዎችና ቋንቋዎች ብዛት ነው፤ በአውሮፓ ተመሳሳይ ስፋት ካላቸው ሌሎች ቦታዎች የበለጠ በዚህ አካባቢ ብዛት ያላቸው ቋንቋዎች ይነገራሉ።

ጉራማይሌ ሕዝብ

በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ሄሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ የታሪክ ምሁር “የተለያየ ባሕል ያላቸው በርካታ ሕዝቦች በካውካሰስ ይኖራሉ” ሲል ጽፏል። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ገደማ ደግሞ ስትራቦ የተባለ ሌላ ግሪካዊ የታሪክ ምሁር በዚህ አካባቢ ስለሚኖሩ 70 የሚያክሉ ነገዶች ጽፏል። እያንዳንዱ ነገድ የራሱ ቋንቋ የነበረው ሲሆን ሁሉም ዳዮስኪዩሪየስ ትባል በነበረ ቦታ መጥተው ይገበያዩ ነበር፤ በጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ይህች ከተማ በአሁኑ ጊዜ ሱኩሚ ትባላለች። ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ሮማዊ ምሁር የሆነው ትልቁ ፕሊኒ፣ ሮማውያን በዳዮስኪዩሪየስ ለመነገድ 130 አስተርጓሚዎች እንደሚያስፈልጓቸው ጽፏል።

በዛሬው ጊዜ በካውካሰስ የሚኖሩ ከ50 የሚበልጡ ጎሳዎች አሉ። እያንዳንዱ ጎሳ በራሱ ባሕል፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በራሱ አለባበስ፣ ሥነ ጥበብና ሥነ ሕንፃ ይኮራል። በዚህ አካባቢ በትንሹ 37 የሚያክሉ ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ አንዳንዶቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ያሏቸው ሲሆን ሌሎቹ ቋንቋዎች ደግሞ በጥቂት መንደሮች ብቻ የሚነገሩ ናቸው። በቋንቋዎች ብዛት የበላይነቱን የያዘው በሩስያ የሚገኘው የዳግስታን ሪፑብሊክ ሲሆን 30 የሚያክሉ ጎሳዎች ይኖሩበታል። በእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ያለው መወራረስ እንዲሁም ከሌሎች የቋንቋ ቡድኖች ጋር ያላቸው ዝምድና እስካሁን ድረስ በውል አይታወቅም።

የይሖዋ ምሥክሮች በካውካሰስ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስተምሩ

በካውካሰስ አካባቢ የሚነገሩት የኮውኬዢያ ቋንቋዎች የትኞቹ እንደሆኑ ማወቅ ትፈልጋለህ? www.jw.org የተባለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ድረ ገጽ ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች መመልከት ይቻላል። ከእነዚህ መካከል የቋንቋዎች መናኸሪያ በሆነው በዚህ ተራራማ አካባቢ የሚነገሩ አንዳንድ ቋንቋዎች ይገኙበታል።

ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፊደላትና ድምፆች

የኮውኬዢያ ቋንቋዎች የተለያየ ዓይነት ፊደላትን ይጠቀማሉ። አርመንኛም ሆነ ጆርጂያኛ የራሳቸው የሆኑ ፊደላት አሏቸው። ሌሎቹ ደግሞ የሲሪሊክ ፊደላትን ወይም የተሻሻሉ የላቲን ፊደላትን ተጠቅመው ይጽፋሉ።

የሰሜናዊ ምዕራብ ኮውኬዢያ ቋንቋዎች በተነባቢዎች ብዛት በዓለም ካለ ከየትኛውም ቋንቋ የሚበልጡ ሲሆን አናባቢ ፊደሎቻቸው ግን በጣም ጥቂት ናቸው። አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው እነዚህ ቋንቋዎች “በአፍና በጉሮሮ ክፍሎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ድምፆችን በሙሉ” የሚወክሉ ተነባቢ ፊደላት አሏቸው። ከኮውኬዢያ ቋንቋዎች አንዱ የሆነውን ኧበክን የሚናገረው የመጨረሻው የአገሬው ተወላጅ የሞተው በ1992 ሲሆን ይህ ቋንቋ 80 ተነባቢዎች እንዳሉትና አናባቢዎቹ ግን ምናልባት ከሁለት እንደማይበልጡ ይነገርለታል።

አንድ የቱርክ ሱልጣን፣ ኧበክ የተባለውን ቋንቋ እንዲማር አንድን ምሁር ወደ ካውካሰስ ልኮት እንደነበር አፈ ታሪክ ይናገራል። ምሁሩ ሲመለስ፣ ቋንቋውን ሊማር ያልቻለበትን ምክንያት ለማስረዳት ጠጠር የተሞላበት ከረጢት ወስዶ ጠጠሮቹን ከእብነ በረድ በተሠራው ወለል ላይ ዘረገፋቸው። ምሁሩ “እነዚህን ድምፆች ያድምጡ” በማለት ለሱልጣኑ ነገረው። ከዚያም “የኧበክን ቋንቋ የውጭ አገር ሰዎች ከዚህ የተሻለ ሊረዱት አይችሉም” በማለት ተናግሯል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ