የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 3/13 ገጽ 4-7
  • ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—2013
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥሩ አባት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ለቤተሰባችሁ መዳን ጠንክራችሁ ሥሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ትኩረት መስጠት
    ንቁ!—2005
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2013
g 3/13 ገጽ 4-7
[ሥዕል]

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ማይክልa “የተሳሳትኩት ነገር ምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ እረፍት ይነሳዋል። ጥሩ አባት ለመሆን ብዙ ቢያደርግም ዓመፀኛ ስለሆነው የ19 ዓመት ልጁ ባሰበ ቁጥር የተሻለ አባት መሆን ይችል እንደነበረ ይሰማዋል።

በተቃራኒው በስፔን የሚኖረው ቴሪ ደግሞ የአባትነት ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ የተሳካለት ይመስላል። ልጁ አንድሩ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ አባቴ ያለኝ የልጅነት ትዝታ ደስ የሚል ነው፤ ሲያነብልኝ፣ ሲያጫውተኝ እንዲሁም ለብቻችን ጊዜ ለማሳለፍ እንድንችል ወደተለያዩ ቦታዎች ሲወስደኝ ትዝ ይለኛል። በጨዋታ መልክ ያስተምረኝ ነበር።”

ጥሩ አባት መሆን ቀላል ነገር እንዳልሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊረዷችሁ የሚችሉ ምክሮችን ይዟል። ብዙ አባቶች እነሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር ሥራ ላይ ሲያውሉ እንደሚጠቀሙ አስተውለዋል። እስቲ አባቶችን ሊያግዙ የሚችሉ አንዳንድ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን እንመልከት።

1. ለቤተሰባችሁ ጊዜ ስጡ

አባት እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁ በእናንተ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? ለልጆቻችሁ ምግብና መጠለያ ለማቅረብ የምትከፍሉትን መሥዋዕትነት ጨምሮ በርካታ ነገሮች እንደምታደርጉላቸው የታወቀ ነው። ልጆቻችሁ በእናንተ ዘንድ ትልቅ ቦታ ባይኖራቸው ኖሮ እነዚህን ነገሮች አታደርጉም ነበር። ይሁን እንጂ ከልጆቻችሁ ጋር በቂ ጊዜ የማታሳልፉ ከሆነ ከእነሱ ይልቅ ለሥራችሁ፣ ለጓደኞቻችሁ፣ በትርፍ ጊዜ ለምትሠሯቸው ነገሮችና ለመሳሰሉት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጡ ሊያስቡ ይችላሉ።

አንድ አባት ከልጆቹ ጋር ጊዜ ማሳለፍ መጀመር የሚኖርበት መቼ ነው? እናት ከልጇ ጋር ትስስር መፍጠር የምትጀምረው ልጁ ገና ማህፀን ውስጥ እያለ ነው። አንድ ጽንስ በ16 ሳምንታት ውስጥ መስማት ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አባትም ቢሆን ካልተወለደው ልጁ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና መመሥረት ይችላል። በዚህ ወቅት አባትየው የልጁን የልብ ትርታ ሊያዳምጥ፣ ልጁ ሲንፈራገጥ ሊሰማው፣ ሊያወራለትና ሊዘምርለት ይችላል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አባቶች ልጆቻቸውን ያስተምሩ ነበር። በዘዳግም 6:6, 7 ላይ ከሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው አባቶች ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው ጊዜ እንዲያሳልፉ ይጠበቅባቸው ነበር፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።”

2. ጥሩ አባቶች ጥሩ አዳማጮች ናቸው

ልጃችሁ ላይ ሳትፈርዱ በእርጋታ አዳምጡ

ከልጆቻችሁ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ጥሩ አድማጭ መሆን ያስፈልጋችኋል። ሳትደናገጡ ወይም ሳትቆጡ ማዳመጥ መቻል ይኖርባችኋል።

በቁጣ ቶሎ የምትገነፍሉ ከሆነ አሊያም በልጆቻችሁ ላይ የመፍረድ አዝማሚያ ካላችሁ የውስጣቸውን አውጥተው ለእናንተ የመናገር ፍላጎት አይኖራቸውም። በእርጋታ የምታዳምጧቸው ከሆነ ግን ከልብ እንደምታስቡላቸው ማየት ይችላሉ። ይህ ደግሞ የውስጣቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ያነሳሳቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር በብዙ የሕይወት ዘርፎች ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት” ይላል። (ያዕቆብ 1:19) ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሥራ ላይ የሚያውሉ አባቶች ከልጆቻቸው ጋር በደንብ መግባባት ይችላሉ።

3. ፍቅራዊ ተግሣጽ ስጧቸው እንዲሁም አመስግኗቸው

በምታዝኑበት ወይም በምትቆጡበት ጊዜ እንኳ የምትሰጡት ተግሣጽ ለልጃችሁ ዘላቂ ጥቅም እንደምታስቡ የሚያሳይ መሆን አለበት። ተግሣጽ ሲባል ምክርን፣ እርማትንና ትምህርትን አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ቅጣትን ያካትታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ተግሣጽ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው አባት ልጆቹን አዘውትሮ የሚያመሰግን ከሆነ ነው። በጥንት ጊዜ የተነገረ አንድ ምሳሌ “ባግባቡ የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው” ይላል። (ምሳሌ 25:11) ምስጋና አንድ ልጅ ጥሩ ባሕርያትን እንዲያፈራ ያደርገዋል። ልጆች በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖራቸው እውቅና ሊሰጣቸው አልፎ ተርፎም አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ልጆቹን ለማመስገን አጋጣሚዎችን በንቃት የሚከታተል አባት ልጆቹ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብሩና ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንዳይሉ ይረዳቸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ “አባቶች ሆይ፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።”—ቆላስይስ 3:21

4. ለትዳር ጓደኛችሁ ፍቅርና አክብሮት ይኑራችሁ

አንድ አባት ሚስቱን የሚይዝበት መንገድ ልጆቹ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚያጠና አንድ የባለሙያዎች ቡድን እንዲህ ብሏል፦ “አንድ አባት ለልጆቹ ሊያደርግ ከሚችላቸው ጥሩ ነገሮች አንዱ እናታቸውን ማክበር ነው። . . . እርስ በርሳቸው የሚከባበሩና ለልጆቻቸው ይህን የሚያሳዩ ወላጆች ልጆቻቸው ደስተኛ እንዲሆኑ እንዲሁም እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ።”—ዚ ኢምፖርታንስ ኦቭ ፋዘርስ ኢን ዘ ሄልዚ ዴቨሎፕመንት ኦቭ ችልድረንb

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ “ባሎች ሆይ፣ . . . ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ፤ . . . ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ።”—ኤፌሶን 5:25, 33

5. የአምላክን ጥበብ ሥራ ላይ አውሉ

ለአምላክ ልባዊ ፍቅር ያላቸው አባቶች ለልጆቻቸው ውድ የሆነ ቅርስ ማውረስ ይችላሉ፤ ይኸውም ከሰማዩ አባታቸው ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዲመሠርቱ ሊረዷቸው ይችላሉ።

[ሥዕል]

ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ስድስት ልጆቹን ለማሳደግ ሲደክም የኖረውና ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ የሆነው አንቶንዮ ከሴት ልጁ የሚከተለው መልእክት ደርሶት ነበር፦ “ውድ አባቴ፣ ይሖዋ አምላክን፣ ጎረቤቶቼንና ራሴን እንድወድ በአጠቃላይ ሚዛናዊ ሰው እንድሆን ስለረዳኸኝ አመሰግንሃለሁ። ይሖዋን እንደምትወድና ለእኔም በግል እንደምታስብልኝ ማየት ችያለሁ። አባዬ፣ በሕይወትህ ይሖዋን ስላስቀደምክና ልጆችህን ከአምላክ እንደተገኙ ስጦታዎች አድርገህ ስለያዝከን አመሰግንሃለሁ!”

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፦ “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ። ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ።”—ዘዳግም 6:5, 6

አባትነት ከእነዚህ አምስት ነጥቦች በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ነገሮችን እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው፤ ጥሩ አባት ለመሆን የተቻላችሁን ያህል ጥረት ብታደርጉም ፍጹም አባት ልትሆኑ እንደማትችሉ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህን ነጥቦች ሚዛናዊና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ ለማዋል ከጣራችሁ ጥሩ አባት መሆን ትችላላችሁ።c

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b አባት ከልጆቹ እናት ጋር የተፋታ ቢሆንም እንኳ አክብሮት የሚያሳያት ከሆነ ልጆች ከእናታቸው ጋር ጥሩ ዝምድና ሊኖራቸው ይችላል።

c በቤተሰብ ሕይወት ረገድ ተጨማሪ መመሪያ ማግኘት ከፈለጋችሁ የቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከቱ፤ ይህን መጽሐፍ www.jw.org በተባለው ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል።

ጥሩ አባት ለልጆቹ ጊዜ አያጣም

የባርቤዶስ ተወላጅ የሆነው ሲልቫን የሚኖረው ከሚስቱና በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ ሦስት ልጆቹ ጋር ነው። ሲልቫን በኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ የከተማ አውቶቡስ ሾፌር ስለሆነ የሥራ ፕሮግራሙ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከሰዓት ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ጀምሮ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝና አሥር ሰዓት ድረስ ይሠራል። ሐሙስና ዓርብ እረፍት ቢኖረውም ቅዳሜና እሁድ ምሽት ላይ ይሠራል። ያም ቢሆን ሲልቫን ለልጆቹ የሚሆን ጊዜ አያጣም።

ሲልቫን እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ከባድ ቢሆንም የቻልኩትን አደርጋለሁ። ሁሉም ልጆቼ ከእኔ ጋር ብቻቸውን የሚያሳልፉት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ትልቁ ልጄ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ከእሱ ጋር ጊዜ አሳልፋለሁ። ዓርብ ከመካከለኛው ልጄ ጋር እሁድ ጠዋት ደግሞ ከትንሹ ልጄ ጋር እሆናለሁ።”

አድናቆት ያተረፉ አባቶች

“አብሮኝ ይጫወታል። ማታ ማታም ያነብልኛል።”—ሲየራ፣ 5 ዓመት

“በደንብ ካጫወተን በኋላ ‘በቃ፣ አሁን ደግሞ እናጽዳ’ ይለናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ስንሠራ ከቆየን በኋላ ሥራውን ያቆምና ‘አሁን የጨዋታ ጊዜ ነው’ ይለናል።”—ማይክል፣ 10 ዓመት

“አባቴ ሰብዓዊ ሥራውም ሆነ በትርፍ ጊዜው የሚያከናውናቸው ነገሮች እማዬን በቤት ውስጥ ሥራ ከመርዳት ወደኋላ እንዲል አድርገውት አያውቁም። እስካሁን ድረስ ከእማዬ እኩል ምግብ ያበስላል፣ ዕቃ ያጥባል፣ ቤቱን በማጽዳት ይረዳል፤ እንዲሁም እሷን በፍቅርና በደግነት ይይዛታል።”—አንድሩ፣ 32 ዓመት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ