የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 11/14 ገጽ 10-11
  • ልጃችሁ ሲዋሽ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልጃችሁ ሲዋሽ
  • ንቁ!—2014
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተፈታታኙ ነገር
  • ልጆቻችሁን ከጥቃት መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
    ንቁ!—2007
  • “አይሆንም” ማለት የምትችሉት እንዴት ነው?
    ንቁ!—2014
  • መዋሸት በጣም ቀላል የሆነው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • የውሸት እውነተኛ ገጽታ
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2014
g 11/14 ገጽ 10-11
አንድ ትንሽ ልጅ የአበባ ማስቀመጫ እንዳልሰበረ በውሸት ሲናገር

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጃችሁ ሲዋሽ

ተፈታታኙ ነገር

የአምስት ዓመት ልጅሽ በሌላ ክፍል ውስጥ ሆኖ እየተጫወተ ነው።a በድንገት አንድ ነገር ወድቆ ሲሰበር ሰማሽ። ወደ ልጅሽ ሮጠሽ ስትሄጂ ልጁ በተሰበረው የአበባ ማስቀመጫ አጠገብ ቆሟል። በፊቱ ላይ የሚነበበውን የጥፋተኝነት ስሜት ስትመለከቺ ምን እንደተፈጠረ ተረዳሽ።

ልጅሽን በቁጣ “አበባ ማስቀመጫውን ሰበርከው?” ብለሽ ጠየቅሽው።

እሱ ግን “አይ፣ እማዬ፣ እኔ አይደለሁም የሰበርኩት!” ብሎ በፍጥነት መለሰ።

የአምስት ዓመት ልጅሽ ሽምጥጥ አድርጎ ሲዋሽሽ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ታዲያ ጉዳዩ ሊያስጨንቅሽ ይገባል?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ውሸት ሁሉ መጥፎ ነው። ይሖዋ አምላክ ‘ሐሰተኛ ምላስን’ እንደሚጠላ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 6:16, 17) ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ሰዎችን ማታለልን በጥብቅ ያወግዛል።—ዘሌዋውያን 19:11, 12

ይሁን እንጂ ሁሉም ውሸት እኩል ክብደት አለው ማለት አይደለም። አንድን ሰው ለመጉዳት ተብለው የሚነገሩ ውሸቶች በጣም ጎጂ ናቸው። ሁኔታዎች በፈጠሩባቸው ጫና የተነሳ ይኸውም ከኀፍረት ወይም ከቅጣት ለመዳን ብለው የሚዋሹ ሰዎች አሉ። (ዘፍጥረት 18:12-15) ውሸት ሁሉ ስህተት ቢሆንም አንዳንድ ውሸቶች ከሌሎቹ ይበልጥ ከበድ ተደርገው መታየት ይኖርባቸዋል። ስለዚህ ልጃችሁ ውሸት ከተናገረ ዕድሜውን እንዲሁም እውነቱን ለመደበቅ የተነሳሳበትን ምክንያት ከግምት አስገቡ።

ልጃችሁ ገና ሕፃን ሳለ ችግሩን መፍታት ይኖርባችኋል። ዶክተር ዴቪድ ዎልሽ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ልጆች፣ እውነቱን መናገር ከባድ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር ይህን ማድረጋቸው አስፈላጊ እንደሆነ መማር ይኖርባቸዋል። ከሰዎች ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት መተማመን አስፈላጊ ነው፤ ውሸት ግን ሰዎች እንዳይተማመኑ ያደርጋል።”b

ይሁንና ውሸት በመናገሩ አትደናገጡ። ልጃችሁ ውሸት ተናገረ ማለት በአንዴ መጥፎ ሰው ይሆናል ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” እንደሚል አስታውሱ። (ምሳሌ 22:15) አንዳንድ ልጆች፣ ምናልባትም ከቅጣት ለመዳን ብለው በመዋሸት የሞኝነት ድርጊት ይፈጽማሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ምላሽ የምትሰጡበት መንገድ ለውጥ ያመጣል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ልጃችሁ የዋሸበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ልጃችሁ የዋሸው ቅጣት ፈርቶ ነው? እናንተ እንዳታዝኑበት ፈልጎ ነው? ልጃችሁ ጓደኞቹን ለማስደመም ብሎ የፈጠራ ታሪኮችን የሚያወራ ከሆነ ይህን የሚያደርገው በእውነታው ዓለምና በተረት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት የሚችልበት ዕድሜ ላይ ስላልደረሰ ይሆን? ልጃችሁ የዋሸበትን ምክንያት ካወቃችሁ እሱን ለማረም ምን ማድረግ እንደምትችሉ ግልጽ ይሆንላችኋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ቆሮንቶስ 13:11

አንዳንድ ጊዜ ልጃችሁን ስታነጋግሩ በጥያቄ ፋንታ ዓረፍተ ነገር ተጠቀሙ። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው እናት መጀመሪያውኑም ቢሆን ልጇ የፈጸመውን ነገር አውቃለች፤ ይሁንና ልጇን በቁጣ ድምፅ “የአበባ ማስቀመጫውን ሰበርከው?” ብላ ጠይቃዋለች። ልጁ የዋሸው ምናልባትም የእናቱን ቁጣ ፈርቶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እናቱ ወቀሳ አዘል ጥያቄ በማቅረብ ፋንታ “የአበባ ማስቀመጫውን ስለሰበርከው አዝኛለሁ!” ብላ ተናገረች እንበል። እናትየዋ በጥያቄ ፋንታ ዓረፍተ ነገር ብትጠቀም ልጁ ለመዋሸት አይፈተንም፤ በተጨማሪም የሐቀኝነትን ባሕርይ እንዲያዳብር ትረዳዋለች።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ቆላስይስ 3:9

ስለ ሐቀኝነት በአድናቆት ተናገሩ። ልጆች በተፈጥሯቸው ወላጆቻቸውን የማስደሰት ምኞት አላቸው፤ ስለዚህ ይህን ዝንባሌ በሚገባ ተጠቀሙበት። እውነትን መናገር በቤተሰቡ ውስጥ ከፍ ተደርጎ እንደሚታይና እናንተም ሐቀኛ እንዲሆን እንደምትጠብቁበት ልጃችሁ እንዲያውቅ አድርጉ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ዕብራውያን 13:18

መዋሸት መተማመንን እንደሚያጠፋና መተማመን አንዴ ከጠፋ ደግሞ መልሶ ለማግኘት ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ለልጃችሁ ግልጽ አድርጉለት። ልጁ እውነት በሚናገርበት ጊዜ በማመስገን በዚያው እንዲገፋበት እርዱት። ለምሳሌ ያህል፣ “ሐቀኛ ልጅ ስለሆንህ ደስ ብሎኛል” ልትሉት ትችላላችሁ።

ምሳሌ ሁኑ። ለአብነት ያህል፣ ስልክ የደወለላችሁን ሰው ማነጋገር በማትፈልጉበት ጊዜ “እቤት የለም በለው” ወይም ከሥራ ለመቅረት ስትሉ ሳያምማችሁ “አሞኛል” ብላችሁ ስትናገሩ ልጃችሁ የሚሰማችሁ ከሆነ እሱ እውነተኛ እንዲሆን መጠበቅ እንደማትችሉ ግልጽ ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ያዕቆብ 3:17

መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቀሙ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መመሪያዎችና እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች ሐቀኝነትን ያበረታታሉ። ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በልጃችሁ ልብ ውስጥ ለመቅረጽ ሊረዳችሁ ይችላል። የዚህ መጽሐፍ 22ኛ ምዕራፍ “መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው?” የሚል ርዕስ አለው። (ከመጽሐፉ ተቀንጭቦ የተወሰደውን ክፍል “ልጃችሁን ለመርዳት የተዘጋጀ መጽሐፍ” በተሰኘው ሣጥን ውስጥ ተመልከቱ።)

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

b ኖ፦ ዋይ ኪድስ ኦቭ ኦል ኤጅስ ኒድ ቱ ሂር ኢት ኤንድ ዌይስ ፓረንትስ ካን ሴይ ኢት ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ።

ቁልፍ ጥቅሶች

  • “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ . . . እንደ ሕፃን አመዛዝን ነበር።”—1 ቆሮንቶስ 13:11

  • “አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ።”—ቆላስይስ 3:9

  • “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር [እንመኛለን]።”—ዕብራውያን 13:18

  • “ከላይ የሆነው ጥበብ . . . ግብዝነት የሌለበት ነው።”—ያዕቆብ 3:17

ልጃችሁን ለመርዳት የተዘጋጀ መጽሐፍ

“ሳታስበው አንድ ነገር ወድቆ ተሰብሮብህ ይሆናል። ማን እንደሰበረው ስትጠየቅ ወንድምህ ወይም እህትህ እንደሰበሩት አድርገህ ትናገራለህ? ወይም ደግሞ እንዴት እንደተሰበረ እንደማታውቅ ለማስመሰል ትሞክራለህ? . . . ምንም ነገር ብናደርግ፣ መዋሸት ምንጊዜም የባሰ ችግር ከማምጣት በቀር ምንም ስለማይጠቅመን ግማሹን እውነት ደብቀን ግማሽ እውነት ብቻ እንኳ መናገር የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነትን ተነጋገሩ’ ይላል። በተጨማሪም ‘አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ’ ይላል። ይሖዋ ምንጊዜም እውነትን ስለሚናገር እኛም እውነት እንድንናገር ይፈልጋል።—ኤፌሶን 4:25፤ ቆላስይስ 3:9”

ከታላቁ አስተማሪ ተማር ከተባለው መጽሐፍ ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ