የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 4/15 ገጽ 3-5
  • ልጆችን መቅጣት ቀረ እንዴ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልጆችን መቅጣት ቀረ እንዴ?
  • ንቁ!—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የወላጆች ሥልጣን እየተዳከመ ነው
  • በየጊዜው የሚለዋወጡ አመለካከቶች
  • እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ጠቃሚ የሆነ ተግሣጽ
    ንቁ!—2015
  • ራስ ወዳድ በሆነ ዓለም ውስጥ ጨዋ ልጆች ማሳደግ
    ንቁ!—2013
  • ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ እርዷቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2015
g 4/15 ገጽ 3-5
1. አንድ የአራት ዓመት ልጅ መጫወቻ ይዞ፣ 2. አንዲት የአምስት ዓመት ልጅ እጆቿን አጣምራ፣ 3. አንድ የ12 ዓመት ልጅ እጁን ወገቡ ላይ አድርጎ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ልጆችን መቅጣት ቀረ እንዴ?

ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በምዕራባውያን አገሮች የቤተሰብ ሕይወት በአስገራሚ ሁኔታ ተለውጧል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በቤት ውስጥ አመራር የሚሰጡት ወላጆች ሲሆኑ ልጆች ደግሞ ወላጆቻቸው የሚሏቸውን ይሰሙ ነበር። አሁን ግን በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ሁኔታው የተገላቢጦሽ የሆነ ይመስላል። እስቲ ከዚህ በታች የቀረቡትን ምሳሌዎች ተመልከት፤ እነዚህ ምሳሌዎች ብዙ ጊዜ በሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው።

  • አንድ የአራት ዓመት ልጅ ከእናቱ ጋር ሱቅ ሄዶ አንድ መጫወቻ አነሳ። እናቱ፣ መጫወቻውን የማትገዛበትን ምክንያት ልታስረዳው ሞከረች። “አንተ እኮ በቂ መጫወቻዎች አሉህ፤ አይደል?” አለችው። ይህን ጥያቄ ማንሳት እንዳልነበረባት የተገነዘበችው ግን ከተናገረች በኋላ ነው። “ይሄንንም እፈልገዋለኋ!” በማለት ልጁ ተነጫነጨ። በዚህ ጊዜ እናቲቱ፣ ልጁ እንደለመደው እንዳይጮኽ በመፍራት መጫወቻውን እንዲወስድ ፈቀደችለት።

  • አንዲት የአምስት ዓመት ልጅ፣ አባቷ ከአንድ ትልቅ ሰው ጋር እያወራ ሳለ አቋርጣው “እዚህ መሆን ሰልችቶኛል። ቤት መሄድ እፈልጋለሁ!” አለችው። አባቷም የጀመረውን ዓረፍተ ነገር እንኳ ሳይጨርስ ወደ ልጅቱ ጎንበስ ብሎ “ትንሽ ብቻ ታገሺኝ፤ እሺ የኔ ቆንጆ” በማለት አባበላት።

  • የ12 ዓመቱ ጄምስ አሁንም መምህሩ ላይ በመጮኹ ተከስሷል። የጄምስ አባት በልጁ ሳይሆን በመምህሯ ተናደደ። ጄምስን እንዲህ አለው፦ “እሷ ደግሞ አንተ ብቻ ነህ እንዴ የምትታያት? ቆይ፣ ለትምህርት ቤቱ ኃላፊ እከስሳታለሁ!”

ከላይ የቀረቡት ምሳሌዎች እውነተኛ ታሪክ ባይሆኑም እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ማየት በጣም የተለመደ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ሥርዓት የጎደለው ነገር ሲያደርጉ በቸልታ የሚመለከቱ፣ ልጆቻቸው የሚጠይቋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያደርጉላቸው እንዲሁም ጥፋታቸው የሚያስከትልባቸውን መዘዝ እንዳይቀምሱ የሚከላከሉላቸው ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆች ሥልጣናቸውን ለትናንሽ ልጆቻቸው ሲለቁላቸው ማየት እየተለመደ መጥቷል። . . . ከጥቂት ዓመታት በፊት ልጆች የቤቱ ኃላፊ ማን እንደሆነ ይኸውም እነሱ እንዳልሆኑ ያውቁ ነበር።”

እርግጥ ነው፣ አሁንም ቢሆን ብዙ ወላጆች ጥሩ ምሳሌ በመሆን እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጥብቅ የሆነ ሆኖም ፍቅር የሚንጸባረቅበት እርማት በመስጠት ለልጆቻቸው ተገቢ የሥነ ምግባር እሴቶችን ለማስተማር ይጥራሉ። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የተጠቀሰው መጽሐፍ እንደገለጸው እንዲህ ማድረግ ያለውን ጥቅም የሚገነዘቡ ወላጆች በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካገኘው አካሄድ ተቃራኒ የሆነ ነገር ማድረግ ጠይቆባቸዋል።

ይሁንና ሁኔታው እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው እንዴት ነው? ለልጆች ተግሣጽ መስጠት የቀረው ለምንድን ነው?

የወላጆች ሥልጣን እየተዳከመ ነው

የወላጆች ሥልጣን መዳከም የጀመረው ጠበብት የተባሉ ሰዎች ወላጆች በልጆች አያያዛቸው ለቀቅ ያሉ እንዲሆኑ መምከር ከጀመሩበት ጊዜ ማለትም ከ1960ዎቹ ወዲህ እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ። እነዚህ ባለሙያዎች ለወላጆች እንደሚከተሉት ያሉ ምክሮችን ይሰጡ ነበር፦ ‘ለልጆቻችሁ ጓደኛ ሁኗቸው እንጂ ባለሥልጣን አትሁኑባቸው።’ ‘ልጆችን ማመስገን ለእነሱ እርማት ከመስጠት የተሻለ ነው።’ ‘ስህተታቸውን ከማረም ይልቅ የሚያደርጉትን መልካም ነገር ፈልጋችሁ አመስግኗቸው።’ እንዲህ ዓይነቱ ምክር፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በማመስገንና ለእነሱ እርማት በመስጠት ረገድ ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ አያበረታታም፤ ከዚህ ይልቅ ልጆችን መገሠጽ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ስሜታቸው እንዲጎዳና ካደጉ በኋላ ወላጆቻቸውን እንዲጠሉ ሊያደርግ ይችላል የሚል መልእክት ያስተላልፋል።

ብዙም ሳይቆይ ባለሙያዎቹ፣ ልጆች ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ማድረግ ጥሩ ነገር እንደሆነ መለፈፍ ጀመሩ። ጥሩ የልጅ አስተዳደግ ሚስጥር በድንገት የተገለጠላቸው ይመስል ነበር፤ ይህም በአጭሩ ‘ልጆቻችሁ ስለ ራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው አድርጉ’ የሚል ነበር። እርግጥ ነው፣ ልጆች በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ መርዳት አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር የሚለው አመለካከት ወደ ሌላኛው ጽንፍ ሄዶ ነበር። ባለሙያዎቹ ለወላጆች እንደሚከተሉት ያሉ ምክሮችን ይሰጡ ነበር፦ ‘አይሆንም እና መጥፎ ነው እንደሚሉት ያሉ አሉታዊ ቃላትን አትጠቀሙ።’ ‘ልጆቻችሁ፣ ልዩ እንደሆኑና መሆን የሚፈልጉትን ሁሉ መሆን እንደሚችሉ ደጋግማችሁ ንገሯቸው።’ እንደ ባለሙያዎቹ አባባል ከሆነ ጥሩ ከመሆን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ልጆቹ ስለ ራሳቸው ጥሩ የሚሰማቸው መሆኑ ነው።

አንድ ልጅ ዙፋን ላይ ተቀምጦ፤ ወላጆቹ ከልክ ባለፈ መንገድ ሲያሞጋግሱት

ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር የሚለው አመለካከት ልጆች የሁሉ ባለሥልጣን እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓል

በውጤቱ እንደታየው ከሆነ ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር የሚለው አመለካከት ልጆቹ ዓለም ሁሉ እነሱን የማገልገል ግዴታ ያለበት ይመስል የሁሉ ባለሥልጣን እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓል። በተጨማሪም ጀነሬሽን ሚ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ይህ ዓይነቱ አመለካከት ብዙ ትናንሽ ልጆች “በእውኑ ዓለም ትችት ቢደርስባቸው እንዲሁም አልፎ አልፎ ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሳኩላቸው ቢቀሩ ሁኔታውን መያዝ ስለሚችሉበት መንገድ በቂ ሥልጠና እንዳይኖራቸው” አድርጓል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “በሥራው ዓለም ለራስህ ጥሩ ግምት ይኑርህ የሚባል ነገር የለም። . . . በመሥሪያ ቤትህ ጥሩ ዝግጅት ያልተደረገበት ሪፖርት ጽፈህ ብታቀርብ አለቃህ ‘የጻፍክበትን ወረቀት ቀለሙን ወድጄዋለሁ’ አይልህም። በመሆኑም ልጆችን በዚህ መንገድ ማሳደግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።”

በየጊዜው የሚለዋወጡ አመለካከቶች

ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የነበሩት የልጅ አስተዳደግ ልማዶች በየጊዜው የሚለዋወጠውን የሰዎች አመለካከት የሚያንጸባርቁ ነበሩ። ሮናልድ ሞሪሽ የተባሉ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ተግሣጽ አሰጣጥ በየጊዜው ይለዋወጣል። ይህም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ለውጦች የሚያንጸባርቅ ነው።”a ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስ ‘በማዕበል የሚነዱ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣ የሚንገዋለሉና ወዲያና ወዲህ የሚሉ’ በማለት እንደሚገልጻቸው ዓይነት ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።—ኤፌሶን 4:14

በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ወላጆች ተግሣጽ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ልል መሆናቸው አሉታዊ ውጤቶች አምጥቷል። ይህ መሆኑ የወላጆች ሥልጣን እንዲዳከም አድርጓል፤ በተጨማሪም ልጆች ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንዲሁም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራስ በመተማመን ስሜት ለመጋፈጥ የሚያስችላቸውን ሥልጠና እንዳያገኙ አድርጓል።

ታዲያ ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖር ይሆን?

a በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ሴክሬትስ ኦቭ ዲሲፕሊን፦ 12 ኪስ ፎር ሬይዚንግ ሪስፖንሲብል ችልድረን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

የተሳሳተ ትምህርት እያስተማራችሁ ይሆን?

ራሳችሁን ቀጥሎ በተገለጹት ሁኔታዎች ውስጥ ለማስቀመጥ ሞክሩ።

  • ልጆችሽን ወደተለያዩ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ቦታዎች በመውሰድ ብዙ ጊዜ ታጠፊያለሽ። ከትምህርት በኋላ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ልጆችሽ እንዳይደብራቸው ስትዪ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ወደሚደረጉባቸው ቦታዎች ወይም ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤቶች በመኪና ትወስጃቸዋለሽ። በጣም ይደክምሻል፤ ሆኖም ‘ልጆቼ የምኖረው ለእነሱ እንደሆነና ማንኛውንም ነገር እንደማደርግላቸው ያውቃሉ። ጥሩ እናት ለመሆን የሚያስፈልገውስ ይህ አይደል?’ ብለሽ ታስቢያለሽ።

    እስቲ የሚከተለውን አስቢ፦ ልጆችሽ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንዲጠመዱ ስትዪ ብቻ ሰውነትሽ እስኪዝል ድረስ የምትደክሚ ከሆነ ለልጆችሽ ምን እያስተማርሻቸው ነው? ከጊዜ በኋላ ልጆችሽ፣ ትላልቅ ሰዎች በተለይም ወላጆች የሚኖሩት የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ እንደሆነ ያስቡ ይሆን?

    ከሁሉ የተሻለው መንገድ፦ ልጆችሽ፣ አንቺም የራስሽ ፍላጎት እንዳለሽ እንዲያውቁ አድርጊ። ይህም አንቺን ጨምሮ ለሌሎች ሰዎች አሳቢ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

  • አባትህ ጥብቅ እንዲሁም ምስጋና የሚባል ነገር የማያውቅ ሰው ነበር፤ በመሆኑም ልጆችህን አንተ ባደግክበት መንገድ ላለማሳደግ ቆርጠሃል። ስለዚህ ሁለት ወንዶች ልጆችህን ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ሌላው ቀርቶ የሚያስመሰግን ነገር ሳያደርጉም እንኳ ታሞግሳቸዋለህ። ‘ስለ ራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው። ልዩ እንደሆኑ ከተሰማቸው በራስ የመተማመን ስሜት ስለሚኖራቸው በሕይወታቸው ስኬታማ ይሆናሉ’ ብለህ ታስባለህ።

    እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ስትል ብቻ ልጆችህን ብታሞግሳቸው ምን እያስተማርካቸው ነው? ልጆችህ ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከመጠን ያለፈ ትኩረት መስጠትህ አሁንም ሆነ ወደፊት ይጎዳቸው ይሆን?

    ከሁሉ የተሻለው መንገድ፦ ሚዛናዊ ሁን። ከመጠን በላይ ነቃፊ አትሁን፤ በሌላ በኩል ግን ልታመሰግናቸው የሚገባው እንዲመሰገኑ የሚያደርግ ነገር ሲያደርጉ መሆን እንዳለበት አትዘንጋ።

  • የስድስትና የአምስት ዓመት ሴቶች ልጆች አሉሽ። ትልቋ ልጅሽ ቶሎ ትቆጣለች። ትናንት፣ በጣም ተናድዳ ታናሽ እህቷን ክንዷ ላይ መታታለች። ሁኔታውን የያዝሽበትን መንገድ ቆም ብለሽ ስታስቢ ለራስሽ እንዲህ አልሽ፦ ‘እሷን ከመቅጣት ይልቅ ምክንያት እያቀረብኩ ለማሳመን መሞከሬ ትክክል ነበር። ደግሞስ እህቷን መምታቷ መጥፎ ነገር እንደሆነ ብነግራት ስሜቷ አይጎዳም ነበር?’

    እስቲ የሚከተለውን አስቢ፦ ከስድስት ዓመት ልጅ ጋር ምክንያት እያቀረቡ መነጋገር ብቻውን በቂ ነው? እህቷን መምታቷ ተገቢ እንዳልሆነ ለመግለጽ “መጥፎ” የሚለውን ቃል መጠቀም በእርግጥ ስሜቷን ይጎዳዋል?

    ከሁሉ የተሻለው መንገድ፦ ልጆችሽ ሥርዓት የጎደለው ነገር ሲያደርጉ በተገቢው መንገድ ቅጪያቸው። ተግሣጹ የተሰጠው በፍቅር ከሆነ ልጆቹ ባሕርያቸውን እንዲያስተካክሉ ይረዳቸዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ