የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 5/15 ገጽ 12-13
  • አል ክዋሪዝሚ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አል ክዋሪዝሚ
  • ንቁ!—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “የዓረብኛ ሒሳብ ሊቅ”
  • የዓረብኛ ሒሳብ ተስፋፋ
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2015
  • አረብኛ የምሁራን ቋንቋ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2012
  • ሥነ ፈለክና የመካከለኛው ዘመን ሊቃውንት
    ንቁ!—2012
  • አንድ ንጉሥ ጥበብን ለማግኘት ያደረገው ጥረት
    ንቁ!—2007
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2015
g 5/15 ገጽ 12-13
የአል ክዋሪዝሚ ሐውልት

የታሪክ መስኮት

አል ክዋሪዝሚ

ሰዎች ክብደታቸውን ለመለካት ወይም ከገበያ የገዙትን ሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ ለማስላት በአብዛኛው የሚጠቀሙት የሂንዱ ዓረብኛ ቁጥሮችን ነው። “ሂንዱ ዓረብኛ” የሚለውን ስያሜ መጠቀም ያስፈለገው ለምንድን ነው? በዘመናችን የምንጠቀምባቸው ከዜሮ እስከ ዘጠኝ ያሉት ቁጥሮች መጀመሪያ ሥራ ላይ የዋሉት በሕንድ ሲሆን ለምዕራቡ ዓለም የተዋወቁት ደግሞ በዓረብኛ ፊደላት ይጽፉ በነበሩ የመካከለኛው ዘመን ምሁራን አማካኝነት ነው። ከእነዚህ ምሁራን መካከል ሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል ክዋሪዝሚ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ይህ ሰው በ780 ዓ.ም. ገደማ በአሁኗ ኡዝቤክስታን እንደተወለደ የሚገመት ሲሆን “የዓረብኛ ሒሳብ ሊቅ” የሚል ስም አትርፏል። እንዲህ ያለውን እውቅና ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

“የዓረብኛ ሒሳብ ሊቅ”

አል ክዋሪዝሚ የአሥርዮሽ የቁጥር ሥርዓት ወይም ዴሲማል ስላለው ጠቀሜታ የጻፈ ሲሆን አንዳንድ የሒሳብ ስሌቶችን መሥራት ስለሚቻልበት መንገድ ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቷል። ይህን ዘዴ ዘ ቡክ ኦቭ ሪስቶሪንግ ኤንድ ባላንሲንግ በተባለው መጽሐፉ ላይ አብራርቷል። ኪታብ አል ጃብር ወል ሙካቤላ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው አልጀብራ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘው አል ጃብር ከሚለው የዓረብኛ ቃል ነው። የሳይንስ ጽሑፍ አዘጋጅ የሆኑት ኤሳን ማሰኡድ፣ አልጀብራ “እስከ ዛሬ ከተፈለሰፉት የስሌት ዘዴዎች ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትና ለሁሉም የሳይንስ ዘርፎች ጠቃሚ መሣሪያ እንደሆነ ይታሰባል” ብለዋል።a

የዓረብኛ ቁጥሮች ምን ያህል ቀላል እንደሆኑ በምሳሌ ለማስረዳት 188 በሮማውያን ቁጥር ሲጻፍ፦ CLXXXVIII

አንድ ጸሐፊ “በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች [አል ክዋሪዝሚ] እንዲህ ያለውን ነገር ለምን ፈጠረ ብለው ሲያማርሩ ኖረዋል” በማለት በቀልድ መልክ ተናግረዋል። አል ክዋሪዝሚ ግን ዓላማው ከንግድ፣ ከውርስ ክፍፍል፣ ከቅየሳና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር የተያያዙ ስሌቶችን በቀላሉ መሥራት እንዲቻል ማድረግ እንደሆነ ተናግሯል።

በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ጋሊልዮንና ፊቦናቺን ጨምሮ ምዕራባውያን የሒሳብ ሊቃውንት ስሌቶችን በሚመለከት ግልጽ የሆነ ማብራሪያ በመስጠቱ ለአል ክዋሪዝሚ ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። የአል ክዋሪዝሚ ማብራሪያዎች በአልጀብራ፣ በአሪትሜቲክና በትሪጎኖሜትሪ ለሚደረጉ ተጨማሪ ጥናቶች መንገድ ከፍተዋል። ትሪጎኖሜትሪ የመካከለኛው ምሥራቅ ምሁራን የባለ ሦስት ጎን ቅርጾችን ማዕዘኖችና የጎን ርዝመቶች ለማስላት እንዲችሉ እንዲሁም በሥነ ፈለክ መስክ ይበልጥ ጥናት እንዲያካሂዱ አድርጓል።b

አልጀብራ፦ “እስከ ዛሬ ከተፈለሰፉት የስሌት ዘዴዎች ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት”

የአል ክዋሪዝሚን ግኝቶች መሠረት ያደረጉ ሰዎች የአሥርዮሽ ክፍልፋዮች ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉባቸውን አዳዲስ መንገዶች ከማግኘታቸውም በላይ ስፋትንና ይዘትን ለማስላት የሚያስችሉ አዳዲስ ዘዴዎችን አዳብረዋል። የመካከለኛው ምሥራቅ መሐንዲሶችና ግንበኞች እንደነዚህ ባሉት ዘመናዊ ዘዴዎች መጠቀም የጀመሩት ከምዕራባውያን አቻዎቻቸው ቀድመው ነው። ምዕራባውያኑ ከዚህ ዘዴ ጋር የተዋወቁትና ይህን ዘዴ ወደ አገራቸው እንዲገባ ያደረጉት በመስቀል ጦርነት ወቅት በማረኳቸው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የተማሩ ምርኮኞችና ስደተኞች አማካኝነት ነው።

የዓረብኛ ሒሳብ ተስፋፋ

ከጊዜ በኋላ የአል ክዋሪዝሚ ሥራዎች ወደ ላቲን ተተረጎሙ። የፒዛው ሌኦናርዶ በሚል ስያሜም ይታወቅ የነበረው ጣሊያናዊው የሒሳብ ሊቅ ፊቦናቺ (1170-1250 ገደማ) የሂንዱ ዓረብኛ ቁጥሮችን ለምዕራቡ ዓለም እንዳስተዋወቀ ይነገርለታል። ፊቦናቺ ስለ እነዚህ ቁጥሮች ያወቀው በሜድትራንያን አካባቢዎች ጉዞ ባደረገበት ወቅት ነው፤ ከጊዜ በኋላ ቡክ ኦቭ ካልኩሌሽን (የስሌት መጽሐፍ) የተባለውን መጽሐፍ ጽፏል።

የአል ክዋሪዝሚ ሥራዎች በሚገባ ሳይታወቁ በርካታ ምዕተ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ግን እሱ ያስተዋወቃቸው ዘዴዎችና እነዚህን ዘዴዎች መነሻ ያደረጉት ስሌቶች ለንግድና ለኢንዱስትሪ እንዲሁም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ደም ሥር ሆነዋል።

a በዘመናዊ አልጀብራ፣ በአንድ ስሌት ውስጥ ዋጋቸው ምን ያህል እንደሆነ ያልታወቁ ቁጥሮች እንደ x ወይም y ባሉ ፊደላት ይወከላሉ። ለምሳሌ x + 4 = 6 የሚለውን ስሌት እንመልከት። ከውጤቱ ላይ 4 ብንቀንስ የx ዋጋ 2 ይሆናል።

b የግሪክ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች፣ የባለ ሦስት ጎን ቅርጾችን የጎን ርዝመትና ማዕዘን የማስላትን ዘዴ በግንባር ቀደምትነት አስፋፍተዋል። የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ምሁራን መካ የሚገኝበትን አቅጣጫ ለማወቅ በትሪጎኖሜትሪ ተጠቅመዋል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ፊታቸውን ወደ መካ አቅጣጫ አድርገው መጸለይ ይመርጣሉ። ሰው ሲሞት አስከሬኑን ወደ መካ አቅጣጫ አዙረው እንዲቀብሩ እንዲሁም ከብት አራጆች ከብቶችን በሚያርዱበት ጊዜ ፊታቸውን ወደ መካ እንዲያዞሩ የሚያዝ ወግ ነበራቸው።

አጭር መረጃ

  • በዘመናችን ከሚሠራባቸው አኃዞች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ቁጥሮች ከሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ጀምሮ በሕንድ ይሠራባቸው ነበር።

  • የሂንዱ ምሁራን የሒሳብ እውቀታቸውን ባግዳድ ይኖር ለነበረው ለካሊፍ አልማንሱር ቤተ መንግሥት አስተዋውቀዋል።

  • ካልኩሌሽን ዊዝ ኢንድያን ኑመራልስ (በሕንድ አኃዞች ማስላት) የተባለው የአል ክዋሪዝሚ መጽሐፍ የአሥርዮሽ የቁጥር ሥርዓትን ወይም ዴሲማልን አስተዋውቋል። አል ክዋሪዝሚ የግሪክ፣ የዕብራይስጥና የሂንዱ ጥናታዊ ጽሑፎችን ጨምሮ ጥንታዊ ከሆኑ ምንጮች ያገኛቸውን ጽንሰ ሐሳቦች አብራርቷል።

በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ቅርስ

“ከሒሳብና ከቁጥር ጋር በተያያዘ [የመካከለኛው ምሥራቅ ምሁራን የተዉት] ቅርስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ሊታበል የማይችል ነው።”—ሳይንስ ኤንድ ኢስላም፣ በኤሳን ማሰኡድ የተዘጋጀ

“ዘመናዊው የምዕራባውያን ቁጥር የብዙ ምንጮች ቅይጥ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እስካሁን በሚታወቀው መሠረት እነዚህን ቁጥሮች በብዛት በመጠቀም ረገድ የመጀመሪያ የሆነችው ሕንድ ነች።”—ብሪታኒካ ኦንላይን ኢንሳይክሎፒዲያ

በአውሮፓ የሂንዱ ዓረብኛ ቁጥሮች “በስፋት የታወቁት በ15ኛው መቶ ዘመን ነው።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሶሳይቲ ኤንድ ካልቸር ኢን ዘ ሚዲቫል ወርልድ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ