የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 7/15 ገጽ 10-11
  • መጠናናት ስታቆሙ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጠናናት ስታቆሙ
  • ንቁ!—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተፈታታኙ ነገር
  • መለያየት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • መለያየታችን የፈጠረብኝን ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
  • ከወንድ ጓደኛዬ ጋር መለያየቴ ያስከተለብኝን ሐዘን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2009
  • ይህ ሰው ይሆነኛል?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2015
g 7/15 ገጽ 10-11
አንድ ወጣት ከእሱ ጋር ትጠናና ስለነበረች ወጣት ሲያስብ

ለቤተሰብ | ወጣቶች

መጠናናት ስታቆሙ

ተፈታታኙ ነገር

“የሚሆነኝን ሰው እንዳገኘሁ ተሰምቶኝ ነበር። ‘አብረን ለዘላለም እንኖራለን’ የሚል ሐሳብ ነበረኝ። ይሁን እንጂ ከሁለት ወራት በኋላ መጠናናታችንን ለማቆም ወሰንኩ። ደስ በሚል መንገድ የጀመርነው የፍቅር ግንኙነት እንዲህ በፍጥነት ይቆማል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ማመን ነው ያቃተኝ!”—አናa

“ብዙ የምንመሳሰልባቸው ነገሮች ስለነበሩ በሁሉ ነገር እንግባባ ነበር ማለት ይቻላል። እንዲያውም የተጋባን ያህል ነበር የሚሰማኝ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን በጣም የተለያየን ሰዎች እንደሆንን ማስተዋል ጀመርኩ። ምን ያህል እንደተሳሳትኩ ስገነዘብ ከእሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋረጥኩ።”—ኢሌን

እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ሁኔታውን መወጣት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁምሃል።

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ግንኙነቱን ለማቆም የወሰነው ሰው እንኳ የስሜት ሥቃይ ሊያጋጥመው ይችላል። ለስድስት ወራት ስትጠናና ቆይታ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የተለያየች ሣራ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በጣም አዝኜ ነበር፤ ከተወሰነ ጊዜ በፊት የሕይወቴ ክፍል የነበረና ወደፊት አብሮኝ ይኖራል ብዬ ያሰብኩት ሰው አጠገቤ ነበር፤ አሁን ግን የለም። የምንወዳቸውን አንዳንድ ዘፈኖች ስሰማ አብረን ያሳለፍናቸውን አስደሳች ጊዜያት አስታውሳለሁ። ከዚህ ቀደም እንሄድባቸው ወደነበሩ ቦታዎች ስሄድ የእሱ አብሮኝ አለመኖር የሚፈጥርብኝ ስሜት ያሠቃየኛል። ይህ ሁሉ የሚሰማኝ እንድንለያይ የፈለግኩት እኔ ራሴ ሆኜ ነው!”

ግንኙነቱን ማቆም የስሜት ሥቃይ ቢያስከትልም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ኢሌን እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ በኩል ጓደኛችሁን መጉዳት አትፈልጉም። በሌላ በኩል ደግሞ እንደማይሆን እያወቃችሁ ግንኙነቱን መቀጠሉ የኋላ ኋላ ሁለታችሁንም እንደሚጎዳ ታውቃላችሁ።” ሣራም በዚህ አባባል ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከአንድ ሰው ጋር በምትጠናኑበት ወቅት ደስተኛ ካልሆናችሁ ከተጋባችሁ በኋላም ደስተኛ ልትሆኑ እንደማትችሉ ግልጽ ነው። ስለዚህ ከአሁኑ ግንኙነታችሁን ማቆሙ የተሻለ ነው።”

መለያየታችሁ የሆነ ችግር እንዳለባችሁ የሚያሳይ አይደለም። ሁለት ሰዎች የሚጠናኑበት ዓላማ ግቡን መትቷል የሚባለው ሰዎቹ ሲጋቡ ብቻ ሳይሆን ለመለያየት ሲወስኑም ጭምር ነው። ከሁለት አንዳችሁ ግንኙነታችሁ እንደማይዘልቅ እንዲሰማችሁ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት ካለ ትክክለኛው ውሳኔ መጠናናቱን ማቆም ሊሆን ይችላል። ግንኙነቱን ለማቆም መወሰናችሁ የሆነ ችግር እንዳለባችሁ የሚያሳይ አይደለም። ሁኔታውን መርሳትና የቀድሞው ዓይነት ሕይወት መምራት ትችላላችሁ። እንዴት?

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

መለያየት ሥቃይ እንደሚያስከትል አምናችሁ ተቀበሉ። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ኢሌን “ያጣሁት እንዲሁ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን በጣም የምቀርበው ጓደኛዬን ነው” በማለት የሚሰማትን ተናግራለች። በጣም ትወዱትና ትቀርቡት ከነበረ ሰው ጋር መጠናናታችሁን ስታቆሙ የሐዘን ስሜት ቢሰማችሁ የሚያስገርም አይደለም። አዳም የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “መጠናናታችሁን ማቆሙ የተሻለ እንደሆነ ብታውቁም እንኳ ይህን ማድረግ ምንጊዜም የስሜት ሥቃይ ያስከትላል።” እናንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው እንደ ንጉሥ ዳዊት ዓይነት ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል። መከራ ባጋጠመው ወቅት “ሌሊቱን ሙሉ መኝታዬን በእንባ አርሳለሁ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 6:6) አንዳንድ ጊዜ ከሥቃይ ለመገላገል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ማምለጫ ቀዳዳ መፈለግ ሳይሆን በዚያ ውስጥ ማለፍ ነው። መጠናናት ማቆም የስሜት ሥቃይ እንደሚያስከትል አምናችሁ መቀበላችሁ ራሱ ለማገገም የሚረዳ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 3:1, 4

ከሚያስቡላችሁ ሰዎች ጋር ተቀራረቡ። ይህ ከባድ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው አና እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “መጀመሪያ ላይ ሰው ማየት እንኳ ያስጠላኝ ነበር፤ ከደረሰብኝ የስሜት ሥቃይ ለማገገምና ያለሁበትን ሁኔታ በትክክል ለመረዳት ጊዜ ወስዶብኝ ነበር።” ከጊዜ በኋላ ግን አና ሊያበረታቷት ከሚችሉ የቅርብ ጓደኞቿ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያለውን ጠቀሜታ ተገነዘበች። “አሁን ትክክለኛ አመለካከት አለኝ፤ መጠናናታችን መቆሙ የፈጠረብኝ የስሜት ሥቃይ አሁን ቀለል ብሎልኛል” ብላለች።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 17:17

ከደረሰባችሁ ነገር ተማሩ። ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ያጋጠመኝ ሁኔታ በምን በኩል ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብኝ ጠቁሞኛል? ወደፊት መጠናናት ብጀምር ላደርግ የምችለው የተለየ ነገር አለ?’ ማርስያ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ጊዜ እያለፈ ሲመጣ ስላጋጠመኝ ነገር የተሻለ ግንዛቤ አግኝቻለሁ፤ ይሁንና በስሜት ከመነዳት ይልቅ ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማየት ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶብኛል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው አዳምም እንደዚህ ተሰምቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “መለያየታችን ያስከተለብኝን ቀውስ ለመርሳት አንድ ዓመት ፈጅቶብኛል። በዚያ ውስጥ ማለፌ ምን ጥቅም እንዳስገኘልኝ ለመገንዘብ ደግሞ ከዚያ የበለጠ ጊዜ ወስዶብኛል። ያጋጠመኝ ነገር ስለ ራሴ፣ ስለ ተቃራኒ ፆታና ስለመጠናናት ብዙ ነገር አስተምሮኛል። መለያየታችን ያስከተለብኝ ሥቃይ አሁን ያን ያህል አይሰማኝም።”

ስለሚያስጨንቃችሁ ነገር ጸልዩ። አምላክ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤ ቁስላቸውን ይፈውሳል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝሙር 147:3) አምላክ ትዳር ፈላጊዎችን የሚያገናኝም ሆነ የሚያለያይ ባይሆንም የእናንተ ደህንነት ያሳስበዋል። በጸሎት አማካኝነት የሚሰማችሁን ነገር ግልጥልጥ አድርጋችሁ ንገሩት።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ጴጥሮስ 5:7

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ቁልፍ ጥቅሶች

  • “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለዋይታ ጊዜ አለው።” —መክብብ 3:1, 4

  • “እውነተኛ ወዳጅ . . . ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።” —ምሳሌ 17:17

  • “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7

“ልብ ሊፈወስ ይችላል”

“ከወንድ ጓደኛዬ ጋር ስንለያይ የጥፋተኝነትና ግራ የመጋባት እንዲሁም የብቸኝነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፤ አልፎ ተርፎም ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ለመቋቋም እጅግ ከባድ ከሆኑት ነገሮች አንዱ የልብ መሰበር ነው። ከምንወደው ሰው መለየት ሥቃይ እንደሚፈጥር ባይካድም ይሖዋ የፈጠረን ከዚህ ስሜት ማገገም እንድንችል አድርጎም ነው። ከአንድ ሰው ጋር ለመዋደድ ጊዜ እንደሚወስድ ሁሉ ከዚያ ሰው ጋር መለያየት ከሚያስከትልባችሁ ሥቃይ ለመላቀቅም ጊዜ ይወስዳል። ያም ቢሆን የማይቻል ነገር አይደለም። ልብ ሊፈወስ ይችላል።”—ማርስያ

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተሰኘውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 31 ተመልከት። የሕትመት ውጤቶች > መጻሕፍትና ብሮሹሮች በሚለው ሥር ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ