ሰማያዊ በቢጫ ማካው። ርዝመቱ 85 ሴንቲ ሜትር ነው
ቀልብ የሚስበው ማካው
ጥቅጥቅ ካለው ጫካ ላይ ብዛት ያላቸው ወፎች አንድ ላይ መብረር ሲጀምሩ አካባቢው ድንገት በቀለማት አሸበረቀ! ይህ ቀልብ የሚስብ እይታ ከ15ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አንስቶ ወደ መካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ የመጡትን አውሮፓውያን አሳሾች አስደመማቸው። እነዚህ ሰዎች ያዩት ማካው የተባሉትን፣ በአሜሪካ የሐሩር ክልል የሚገኙ ባለ ረጅም ጅራት በቀቀኖች ነበር። ብዙም ሳይቆይ የዚህ ዕጹብ ድንቅ ፍጥረት ምስል በቅርቡ የተገኘውን ይህን ውብ ክልል ለማመልከት በካርታዎች ላይ ይሰፍር ጀመር።
ከአብዛኞቹ የወፍ ዝርያዎች በተለየ ወንዱም ሆነ ሴቷ ማካው ደማቅ ቀለም አላቸው። ማካዎች በኅብረት የሚኖሩ የማስተዋል ችሎታ ያላቸው ወፎች ናቸው፤ ድምፃቸው ግን የሚያስጠላ ከመሆኑም ሌላ ጆሮ ይበሳል። ሠላሳ የሚያህሉ ወፎች አንድ ላይ በመሆን ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬ ወይም ሌሎች ምግቦችን ለመለቃቀም ጎጇቸውን ለቀው በማለዳ ይሰማራሉ። እንደ ሌሎች በቀቀኖች ሁሉ እነሱም አብዛኛውን ጊዜ ምግብ የሚይዙት በጥፍራቸው ሲሆን ቆልመም ባለው ትልቅ መንቆራቸው እየቦጨቁ ይበላሉ። ጠንካራ ቅርፊት ያላቸውን ፍሬዎች እንኳ በመንቆራቸው ሰብረው መክፈት ይችላሉ! ከተመገቡ በኋላ ወደ ገደል አፋፍ ወይም ወደ ወንዝ ዳርቻ ሄደው የሸክላ አፈር የመቃም ልማድ አላቸው፤ እንዲህ የሚያደርጉት በበሉት ምግብ ውስጥ ያሉ መርዛማ ነገሮችን ለማርከስ ወይም የሚያስፈልጓቸውን ንጥረ ነገሮች ለማግኘት ሊሆን ይችላል።
“አምላክ ሁሉንም ነገር በወቅቱ ውብ አድርጎ ሠርቶታል።”—መክብብ 3:11
ማካዎች የሚቆራኙት ለዕድሜ ልክ ነው፤ ጫጩቶቻቸውንም ተጋግዘው ያሳድጋሉ። አብዛኞቹ ዝርያዎች ጎጇቸውን የሚሠሩት በተቦረቦረ ዛፍ ውስጥ፣ በወንዝ ዳርቻዎችና በምስጦች ኩይሳ ላይ በሚገኙ ጉድጓዶች ውስጥ ወይም በዓለት ክፍተቶችና ስንጥቆች መካከል ነው፤ በዚያም ጥንዶቹ አንዳቸው ሌላውን ሲያጸዱ ይታያሉ። ጫጩቶቹ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እድገታቸውን የሚያጠናቅቁ ቢሆንም ለሦስት ዓመታት ያህል ከወላጆቻቸው ሳይለዩ ይቆያሉ። ማካዎች ዱር ውስጥ ከ30 እስከ 40 ዓመት ይኖራሉ፤ በእንስሳ ማቆያዎች ውስጥ ከሆነ ደግሞ ከ60 ዓመት በላይ ሊኖሩ ይችላሉ። በግምት 18 የማካው ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል።
ባለ አረንጓዴ ክንፍ ማካው። ቀይ በአረንጓዴ ማካው ተብሎም ይጠራል። ርዝመቱ እስከ 95 ሴንቲ ሜትር ይደርሳል
ሐምራዊ ማካው። ርዝመቱ 85 ሴንቲ ሜትር ነው
ያክንት ማካው። ርዝመቱ እስከ 1 ሜትር ይደርሳል። ይህ ከሁሉ የሚበልጠው በቀቀን ሲሆን እስከ 1.3 ኪሎ ግራም ሊመዝን ይችላል