የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g17 ቁጥር 1 ገጽ 3-7
  • የመንፈስ ጭንቀትና ወጣቶች—መንስኤውና መፍትሔው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመንፈስ ጭንቀትና ወጣቶች—መንስኤውና መፍትሔው
  • ንቁ!—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መንስኤው ምን ሊሆን ይችላል?
  • ለአካልህና ለአእምሮህ እንክብካቤ አድርግ
  • መንሥኤውን ማወቅ
    ንቁ!—2001
  • በጣም የምጨነቀው ለምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • ለመንፈስ ጭንቀት ምን ዓይነት ሕክምና ማግኘት ይቻላል?
    ንቁ!—2009
  • መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
    ንቁ!—2001
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2017
g17 ቁጥር 1 ገጽ 3-7
በመንፈስ ጭንቀት የተዋጠ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ወጣት አልጋው ላይ ቁጭ ብሎ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

የመንፈስ ጭንቀትና ወጣቶች​—መንስኤውና መፍትሔው

አናa እንዲህ ብላለች፦ “በመንፈስ ጭንቀት በምዋጥበት ወቅት ምንም ነገር የማድረግ ፍላጎት አይኖረኝም፤ ሌላ ጊዜ የሚያስደስቱኝን ነገሮች እንኳ ማድረግ ያስጠላኛል። መተኛት ብቻ ነው የሚያሰኘኝ። ማንም እንደማይወደኝ፣ ምንም ዋጋ እንደሌለኝና በሌሎች ላይ ሸክም እንደሆንኩ ይሰማኛል።”

ጁልያ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ራሴን ለመግደል አስቤ ነበር። ይህን እርምጃ ለመውሰድ ያሰብኩት መሞት ስለፈለግኩ ሳይሆን ከሚሰማኝ ስሜት መገላገል ስለፈለግኩ ነበር። በባሕርዬ ለሌሎች አሳቢ ነኝ፤ በመንፈስ ጭንቀት በምዋጥበት ጊዜ ግን ስለ ማንም ሆነ ስለ ምንም ግድ አይኖረኝም።”

አና እና ጁልያ የመንፈስ ጭንቀት የጀመራቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳሉ ነበር። ማንኛውም ወጣት አልፎ አልፎ በጭንቀት ይዋጥ ይሆናል፤ አና እና ጁልያ የተሰማቸው ጭንቀት ግን ለሳምንታት ብሎም ለወራት የዘለቀ ነበር። አና እንዲህ ብላለች፦ “ምንም መውጫ በሌለው ጨለማ ጉድጓድ ውስጥ የመሆን ያህል ነው። አእምሯችሁን እንደሳታችሁ ይሰማችኋል፤ እንዲሁም የቀድሞ ማንነታችሁን ያጣችሁ ይመስላችኋል።”

እንዲህ ያለ ችግር የሚያጋጥማቸው አና እና ጁልያ ብቻ አይደሉም። የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወጣቶች ቁጥር በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ ነው፤ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) እንደገለጸው የመንፈስ ጭንቀት፣ “ከ10 እስከ 19 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለሚያጋጥማቸው ሕመምና የአካል ጉዳት ዋነኛ መንስኤ” ነው።

የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች በጉርምስና ዕድሜ ሊታዩ ይችላሉ፤ ከእነዚህም መካከል የእንቅልፍ ወይም የአመጋገብ ልማድ መዛባት አሊያም የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ ይገኙበታል። በተጨማሪም የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወጣቶች ተስፋ ሊቆርጡ እንዲሁም የሐዘንና የዋጋ ቢስነት ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ራሳቸውን ሊያገልሉ፣ ትኩረት የመሰብሰብ ወይም የማስታወስ ችግር ሊያጋጥማቸው፣ ራሳቸውን ለማጥፋት ሊያስቡ ወይም ሙከራ ሊያደርጉ እንዲሁም በሕክምናው ዓለም በትክክል ያልታወቁ ሌሎች ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላል። የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች አንድ ሰው የመንፈስ ጭንቀት ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ የሚያውቁት የግለሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያውኩ ለሳምንታት የዘለቁ ምልክቶች መኖር አለመኖራቸውን በመመልከት ነው።

መንስኤው ምን ሊሆን ይችላል?

የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው “የመንፈስ ጭንቀት የማኅበራዊ፣ የሥነ ልቦናዊና የአካላዊ ችግሮች ድምር ውጤት ነው።” እስቲ እነዚህን ነገሮች በዝርዝር እንመልከት፦

አካላዊ ችግር። በጁልያ ቤተሰብ ላይ እንደታየው በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ በላይ ሰው የመንፈስ ጭንቀት ሊኖርበት ይችላል። ይህም የመንፈስ ጭንቀት በዘር ሊወረስ እንደሚችል ይጠቁማል፤ በአንጎል ውስጥ ባለው ኬሚካላዊ ሂደት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮች በዘር ሊተላለፉ ይችላሉ። በመንፈስ ጭንቀት የመያዝን አጋጣሚ ከፍ ከሚያደርጉ ሌሎች አካላዊ ችግሮች መካከል ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች፣ የሆርሞን መጠን መዛባት እንዲሁም ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ መጠቀም ይገኙበታል፤ አንድ ሰው ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን ለረጅም ጊዜ አላግባብ ከተጠቀመ የመንፈስ ጭንቀት ሊይዘው ወይም ሊባባስበት ይችላል።b

ውጥረት። በተወሰነ መጠን ውጥረት የሚሰማን መሆኑ ጤናማ ሊሆን ቢችልም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወይም ከመጠን ያለፈ ውጥረት ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊዳርግ ይችላል፤ በተጨማሪም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛ የሆርሞን ለውጥ ስለሚያጋጥማቸው በሚሰማቸው ውጥረት የተነሳ ለመንፈስ ጭንቀት ሊጋለጡ ይችላሉ። ሆኖም የመንፈስ ጭንቀት ትክክለኛ መንስኤ እስካሁን ድረስ በግልጽ አይታወቅም፤ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የመንፈስ ጭንቀት፣ የተለያዩ ችግሮች ድምር ውጤት ሊሆን ይችላል።

የመንፈስ ጭንቀት እንዲከሰት ከሚያደርጉ ከውጥረት ጋር የተያያዙ መንስኤዎች መካከል የወላጆች መፋታት ወይም መለያየት፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት፣ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት፣ ከባድ አደጋ እንዲሁም ሕመም ይገኙበታል፤ በተጨማሪም አንድ ልጅ ትምህርት የመቀበል ችግር ካለበትና በዚህም ምክንያት በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው የሚሰማው ከሆነ ለመንፈስ ጭንቀት ሊጋለጥ ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ውጤት እንዲያመጡ የሚጠብቁባቸው ከሆነም ልጆቹ ለውጥረት ሊዳረጉ ይችላሉ። በተጨማሪም ወጣቶች ከጉልበተኞች የሚደርስባቸው ማስፈራሪያ፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰማቸው ስጋት፣ ከወላጆቻቸው አንዱ ባለበት የመንፈስ ጭንቀት የተነሳ ከእነሱ በስሜት መራቁ እንዲሁም ወላጆቻቸው ተለዋዋጭ ባሕርይ ያላቸው መሆኑ ለጭንቀት ሊያጋልጣቸው ይችላል። ታዲያ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ወጣት በመንፈስ ጭንቀት ከተያዘ ምን ሊረዳው ይችላል?

ለአካልህና ለአእምሮህ እንክብካቤ አድርግ

መጠነኛም ሆነ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው አብዛኛውን ጊዜ መድኃኒት መውሰድ ወይም የአእምሮ ጤና ባለሙያ ማማከር ያስፈልገዋል።c ኢየሱስ ክርስቶስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” በማለት ተናግሯል። (ማርቆስ 2:17) ሕመም ደግሞ አንጎላችንን ጨምሮ የትኛውንም የአካል ክፍላችንን ሊያጠቃ እንደሚችል የታወቀ ነው! የአኗኗር ለውጥ ማድረጋችንም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም አካላችንና አእምሯችን በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው።

በመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ ከሆነ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትህን ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃዎችን ውሰድ። ለምሳሌ ያህል፣ ገንቢ ምግብ ተመገብ፤ በቂ እንቅልፍ ተኛ፤ እንዲሁም አዘውትረህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግህ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ፣ የተሻለ ጥንካሬ እንዲኖርህ እንዲሁም ጥሩ እንቅልፍ እንድትተኛ የሚያደርጉ ኬሚካሎች በሰውነትህ ውስጥ እንዲመነጩ ያደርጋል። የመንፈስ ጭንቀት እንዲነሳብህ የሚያደርጉ ነገሮችንና በመንፈስ ጭንቀት ልትዋጥ እንደሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶችን ለይተህ ለማወቅ ሞክር፤ ከዚያም ልትወስዳቸው የምትችላቸውን እርምጃዎች አስቀድመህ አስብ። የሚሰማህን ስሜት ለምታምነው ሰው ተናገር። ከጎንህ ሆነው ሊረዱህ የሚችሉ ቤተሰቦችና ጓደኞች ካሉህ የመንፈስ ጭንቀትን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ትችላለህ፤ የሚሰማህ ጭንቀትም ሊቀንስልህ ይችላል። ወደ አእምሮህ የሚመጡትን ሐሳቦችና የሚሰማህን ስሜት በጽሑፍ አስፍር፤ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጁልያም እንዲህ ማድረጓ ረድቷታል። ከምንም በላይ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎትህን ለማሟላት ጥረት አድርግ። እንዲህ ማድረግህ ለሕይወት ጥሩ አመለካከት እንዲኖርህ ሊያደርግ ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 5:3

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ወጣት ከወላጆቿ ጋር ስትመገብ፣ እንቅስቃሴ ስታደርግ እና ስትተኛ

በደንብ ተመገብ፤ አካላዊ እንቅስቃሴ አድርግ፤ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ ተኛ

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ወጣት መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ

መንፈሳዊ ፍላጎትህን በማርካት መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ

አና እና ጁልያ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን በራሳቸው ሕይወት ተመልከተዋል። አና እንዲህ ብላለች፦ “መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረጌ ባሉብኝ ችግሮች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በሌሎች ሰዎችም ላይ ትኩረት እንዳደርግ ይረዳኛል። ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም ይበልጥ ደስተኛ እንድሆን አስችሎኛል።” ጁልያም መጸለይዋና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቧ እንደሚያጽናናት ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ወደ አምላክ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረቤ የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በአምላክ ዓይን ውድ እንደሆንኩና አምላክ ለእኔ በጣም እንደሚያስብልኝ እንድገነዘብ ይረዳኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝም ረድቶኛል።”

ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን አስተዳደጋችን፣ በዘር የወረስነው ነገርና በሕይወታችን ያጋጠሙን ችግሮች በአመለካከታችንና በስሜታችን ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብን በሚገባ ይረዳል። በመሆኑም የሚያስፈልገንን ድጋፍና ማጽናኛ ሊሰጠን ይችላል፤ ይህንንም የሚያደርገው ሩኅሩኅና አሳቢ በሆኑ ሰዎች አማካኝነት ሊሆን ይችላል። ወደፊት ደግሞ አምላክ ያሉብንን አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ሕመሞች በሙሉ ያስወግዳል። ኢሳይያስ 33:24 “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም” በማለት ይናገራል።

አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “እንባን ሁሉ [ከዓይናችን] ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ራእይ 21:4) ይህ እንዴት የሚያጽናና ተስፋ ነው! አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ስላለው ዓላማ ይበልጥ ማወቅ ከፈለግክ እባክህ jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንን ተመልከት። ድረ ገጹ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ትችላለህ፤ እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀትን ጨምሮ ስለተለያዩ ጉዳዮች የሚናገሩ ርዕሶችን ታገኛለህ።

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

b በርካታ በሽታዎች፣ መድኃኒቶችና ዕፆች በስሜት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፤ ይህም አንድ ሰው ያለበትን የመንፈስ ጭንቀት መንስኤ ለማወቅ የሕክምና ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልገው ያሳያል።

c ንቁ! አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም።

ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?

  • የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ስሜታቸውን መግለጽ ሊከብዳቸው ወይም ያሉበትን ሁኔታ በትክክል ላይረዱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህ ልጆች የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች ምን እንደሆኑ እንኳ ላያውቁ ይችላሉ።

  • በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ልጆች ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ ከአዋቂዎች የተለየ ነው፤ ስለሆነም የልጃችሁ ባሕርይ፣ አመጋገብ፣ ስሜት፣ የእንቅልፍ ሰዓት ወይም ማኅበራዊ ግንኙነት እንደተለወጠ ካስተዋላችሁ ለጉዳዩ ትኩረት ስጡ፤ በተለይ ደግሞ ለውጡ ለሳምንታት የዘለቀ ከሆነ ይበልጥ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

  • ልጃችሁ ራስን ስለ ማጥፋት ሲናገር ከሰማችሁ ወይም ራሱን ለማጥፋት እንዳሰበ የሚያሳይ ፍንጭ ካያችሁ ጉዳዩን አቅልላችሁ አትመልከቱ።

  • ልጃችሁ የመንፈስ ጭንቀት (አልፎ አልፎ የሚታይና ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ የሐዘን ስሜትን አይጨምርም) እንዳለበት ከተጠራጠራችሁ የሕክምና ባለሙያ ጋር በመሄድ እንዲመረመር አድርጉ።

  • ልጃችሁ ሐኪም ያዘዘለትን መድኃኒት በአግባቡ እንዲወስድ አድርጉ፤ መድኃኒቱን እየወሰደም ምንም መሻሻል ካላሳየ ወይም መድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ካስከተለበት ሐኪሙን አማክሩ።

  • ቤተሰባችሁ የሚመገብበት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግበት እንዲሁም የሚተኛበት ቋሚ ፕሮግራም እንዲኖረው አድርጉ።

  • ከልጃችሁ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ አድርጉ፤ እንዲሁም የመንፈስ ጭንቀት ያለበት በመሆኑ እንዳይሸማቀቅ እርዱት።

  • የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ብቸኛ እንደሆነና እንደማይረባ እንዲሁም ዋጋ ቢስ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል፤ በመሆኑም ለልጃችሁ አዘውትራችሁ ፍቅራችሁን ግለጹለት።

“የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ሣጥን” አዘጋጅ

ደስ የሚሉና የሚያበረታቱ ሐሳቦችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን፣ መዝሙሮችን እና ከዚህ በፊት ያጋጠሙህን አስደሳች ነገሮች የያዘ ስሜትህን ለማከም የሚረዳ “የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ሣጥን”

በመንፈስ ጭንቀት የምትሠቃይ ከሆነ ስሜትህን ለማከም “የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ ሣጥን” አዘጋጅ፤ ይህም ሐሳብህንና ስሜትህን ለመቆጣጠር ይረዳሃል። በሣጥኑ ውስጥ በዚህ ገጽ ላይ የሚገኙትን ነገሮች ማካተት የምትችል ሲሆን ከፈለግክ ሌሎች ነገሮችንም መጨመር ትችላለህ።

  • በጭንቀት ስትዋጥ ልትደውልላቸው የምትችላቸው ሰዎች ስልክ ቁጥር

  • ጥሩ ስሜት እንዲሰማህና ዘና እንድትል የሚያደርጉህ ዘፈኖች ወይም መዝሙሮች

  • ደስ የሚሉ አባባሎችን እንዲሁም የሚያበረታታቱ ሐሳቦችን የያዙ ጽሑፎች

  • እንደ መዝሙር 34:18፤ 51:17፤ 94:19፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ያሉ የሚያጽናኑና የሚያበረታቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

  • የሚወዱህን ሰዎች እንድታስታውስ የሚያደርጉህ ነገሮች

  • አዎንታዊ ሐሳቦችንና ያጋጠሙህን አስደሳች ነገሮች የምትጽፍበት ማስታወሻ ደብተር

በወጣት ሴቶች ላይ የሚከሰት የመንፈስ ጭንቀት

በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ በመንፈስ ጭንቀት የተያዙ ሴት ልጆች ቁጥር ከወንዶቹ ይበልጣል። ምክንያቱም ስሜታዊ፣ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት አሊያም ፆታዊ ትንኮሳ በአብዛኛው የሚደርሰው በሴት ልጆች ላይ ነው፤ ይህ ደግሞ ውጥረት ይፈጥርባቸዋል። ሻረን ኸርሽ የተባሉ አንዲት አማካሪ እንደተናገሩት “በዙሪያቸው ያለው አስፈሪ ዓለም የሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ በውስጣቸው ከሚሰማቸው ውጥረት ጋር ሲዳመር ከባድ ጭንቀትና ግራ መጋባት ይፈጥርባቸዋል።” በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን “ቆንጆ” ብሎ የሚያቀርበው የሰውነት ቅርጽ፣ ሴት ልጆች ለራሳቸው ባላቸው አመለካከት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። አንዲት ልጅ ቆንጆ እንዳልሆነች የምታስብ ከሆነ ወይም በእኩዮቿ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ካላት በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ አጋጣሚዋ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።d

d በቁጥር 4 2016 ንቁ! ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? —አካላዊ ውበት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ