የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g19 ቁጥር 1 ገጽ 10-11
  • “ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም”
  • ንቁ!—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “መንግሥትህ ይምጣ”
  • ሰላማዊው የአምላክ መንግሥት
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • የተሻለ መንግሥት ለማግኘት የሚደረግ ጥረት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ምድራችንን ማስተዳደር የሚችል የተረጋጋ መንግሥት አለ?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2019
g19 ቁጥር 1 ገጽ 10-11
የዓለም ካርታ

መፍትሔ የሚያስገኝ መንግሥት

“ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም”

የተባበሩት መንግሥታት ሰዎች ሁሉ እንዲተባበሩ፣ ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እንዲሁም ምድርን እንዲንከባከቡ እያበረታታ ነው። የተባበሩት መንግሥታት እንዲህ ዓይነት ማበረታቻ እንዲሰጥ ያነሳሳው ምንድን ነው? ማኼር ናስር፣ ዩ ኤን ክሮኒክል በተሰኘው መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተደራጁ ወንጀለኞች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ልዩነት፣ መፍትሔ ያላገኙ ግጭቶች፣ የሰዎች መፈናቀል፣ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት፣ ተላላፊ በሽታዎች እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ድንበር አይገድባቸውም።”

ሌሎች ደግሞ አንድ ዓለም አቀፍ መንግሥት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ከእነዚህ መካከል ጣሊያናዊው ፈላስፋ፣ ገጣሚ እና የፖለቲካ ሰው ዳንቴ (1265-1321) እንዲሁም የፊዚክስ ሊቅ የነበረው አልበርት አንስታይን (1879-1955) ይገኙበታል። ዳንቴ፣ በፖለቲካ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ዘላቂ ሰላም ሊኖር እንደማይችል ያምን ነበር። ዳንቴ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን በመጥቀስ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት . . . ይጠፋል” ይል ነበር።—ሉቃስ 11:17

ሁለት አቶሚክ ቦምቦች ጥቅም ላይ የዋሉበት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ አልበርት አንስታይን ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ደብዳቤ ጽፎ የነበረ ሲሆን ደብዳቤውም በመጽሔቶችና በጋዜጦች ላይ ወጥቶ ነበር። አንስታይን በደብዳቤው ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የተባበሩት መንግሥታት አንድ ዓለም አቀፍ መስተዳድር እንዲቋቋም መሠረቱን በመጣል፣ በመላው ዓለም መረጋጋት እንዲሰፍን አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት።”

ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱን ኃያል መንግሥት የሚያቋቁሙት ፖለቲከኞች ከጭቆናና ከሙስና የጸዱ እንዲሁም የብቃት ማነስ ችግር የማይታይባቸው ይሆናሉ? ወይስ እነሱም የሌሎቹን መሪዎች መጥፎ ምሳሌ ይከተላሉ? እነዚህ ጥያቄዎች ብሪታኒያዊው ታሪክ ጸሐፊ ሎርድ አክተን “ሥልጣን ያባልጋል፤ ገደብ የሌለው ሥልጣን ደግሞ የባሰ ያባልጋል” በማለት የተናገሯቸውን ቃላት ያስታውሱናል።

የሰው ዘር እውነተኛ ሰላምና ስምምነት እንዲኖረው ከተፈለገ አንድነት ሊኖረው ይገባል። ይሁን እንጂ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ለመሆኑ ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ‘አዎ’ የሚል መልስ ይሰጣል። ይህ ሊሆን የሚችል ነገር ነው፤ ደግሞም ወደፊት መሆኑ አይቀርም። ግን እንዴት? ይህ የሚሆነው ሰብዓዊ መሪዎች በሚያቋቁሙት ዓለም አቀፍ መንግሥት አማካኝነት አይደለም፤ ሰብዓዊ ገዢዎች ምግባረ ብልሹ የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው። እውነተኛ ሰላምና ስምምነት የሚሰፍነው አምላክ ራሱ ባቋቋመው መስተዳድር አማካኝነት ነው። አምላክ በዚህ መስተዳድር በመጠቀም በፍጥረታቱ ላይ የመግዛት መብት ያለው እሱ እንደሆነ ያሳያል። ይህ መስተዳድር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መስተዳድር ‘የአምላክ መንግሥት’ ሲል ይጠራዋል።—ሉቃስ 4:43

“መንግሥትህ ይምጣ”

ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም” ብለው እንዲጸልዩ ባስተማራቸው ወቅት እየተናገረ የነበረው ስለ አምላክ መንግሥት ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) አዎ፣ የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርገው የአምላክን ፈቃድ እንጂ የሥልጣን ጥመኛ ወይም ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎችን ፈቃድ አይደለም።

በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት “መንግሥተ ሰማያት” ተብሎም ተጠርቷል። (ማቴዎስ 5:3) እንዲህ ያለ ስያሜ የተሰጠው ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚገዛ ቢሆንም የሚገዛው ከሰማይ ሆኖ ነው። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው። ዓለምን የሚያስተዳድረው የአምላክ መንግሥት፣ ቁሳዊ ወይም የገንዘብ ድጋፍ አያስፈልገውም። ይህም ለሚያስተዳድራቸው ሰዎች ሁሉ ታላቅ እፎይታ ያስገኛል!

የአምላክ መንግሥት ንጉሣዊ መስተዳድር ነው። የዚህ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ሥልጣኑን የተቀበለውም ከአምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦

  • “መንግሥትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። . . . እየተጠናከረ የሚሄደው መንግሥቱም ሆነ ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7 ግርጌ

  • “ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣ ክብርና መንግሥት ተሰጠው። የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍ . . . ነው።”—ዳንኤል 7:14

  • “የዓለም መንግሥት የጌታችንና [የአምላካችንና] የእሱ መሲሕ መንግሥት ሆነ።”—ራእይ 11:15

ኢየሱስ ለተከታዮቹ ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ የተጠቀሰው ልመና ምላሽ የሚያገኘው፣ በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት በምድር ላይ የአምላክ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ሲያደርግ ነው። በዚህ መንግሥት አገዛዝ ሥር፣ የሰው ልጆች ሁሉ ምድራችን እንደገና ምቹ መኖሪያ መሆን እንድትችል እንዴት ተንከባክበው ሊይዟት እንደሚገባ ይማራሉ።

በዚያን ጊዜ የአምላክ መንግሥት ዜጎቹን ያስተምራል። ሁሉም አንድ ዓይነት የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ይማራሉ። በመካከላቸው ግጭት ወይም መከፋፈል አይኖርም። ኢሳይያስ 11:9 “ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ምክንያቱም ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች” ይላል።

የተባበሩት መንግሥታት በአሁኑ ጊዜ ሊያከናውን ያልቻለው ነገር በዚያን ጊዜ እውን ይሆናል፤ የሰው ልጆች ሁሉ በአንድነትና በሰላም አብረው ይኖራሉ። መዝሙር 37:11 “በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል” ይላል። እንደ “ወንጀል፣” “ብክለት፣” “ድህነት” እና “ጦርነት” ያሉትን ቃላት የማንጠቀምበት ጊዜ ይመጣል። ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር መግዛት የሚጀምረው መቼ ነው? የሚገዛውስ እንዴት ነው? አንተስ የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ይህን ቀጥለን እንመለከታለን።

ቁልፍ ነጥብ

የአምላክ መንግሥት፣ አምላክ ያቋቋመው ዓለም አቀፋዊ መስተዳድር ነው። የአምላክ መንግሥት ዜጎች በፖለቲካዊ ድንበሮች አይከፋፈሉም፤ ከዚህ ይልቅ በአንድነትና በሰላም ይኖራሉ

አንድ ዓለም አቀፋዊ መስተዳድር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል

  • ዳንቴ

    ዳንቴ፣ በፖለቲካ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ዘላቂ ሰላም ሊኖር እንደማይችል ያምን ነበር

  • አንስታይን

    አንስታይን፣ የተባበሩት መንግሥታት “አንድ ዓለም አቀፍ መስተዳድር እንዲቋቋም መሠረቱን በመጣል፣ በመላው ዓለም መረጋጋት እንዲሰፍን አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች” ጥሪ አቅርቧል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ