የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g19 ቁጥር 2 ገጽ 8-9
  • ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ
  • ንቁ!—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ምንድን ነው?
  • ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ማዳበር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
  • ልጆች ችግሮችን እንዲቋቋሙ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?
  • መንፈሰ ጠንካራ ነኝ?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ልጆች ሽንፈትን በጥሩ ሁኔታ እንዲወጡ መርዳት
    ለቤተሰብ
  • እርማት ሲሰጠኝ ምን ላድርግ?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ልጆችን ትሕትና ማስተማር
    ንቁ!—2017
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2019
g19 ቁጥር 2 ገጽ 8-9
አንዲት ልጅ የጋገረችው ኬክ ስለተበላሸባት ተበሳጭታ ሳለ እናቷ ስትረዳት

ትምህርት 3

ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ

ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ምንድን ነው?

ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ችሎታ ያለው ሰው እንቅፋት ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ሲያጋጥመው እጅ ከመስጠት ይልቅ በቆራጥነት ወደ ፊት ይገፋል። ይህ ችሎታ የሚገኘው በተሞክሮ ነው። አንድ ልጅ አልፎ አልፎ ሳይወድቅ፣ መራመድ ሊማር አይችልም። በተመሳሳይም በሕይወቱ ውስጥ ምንም እንቅፋት ሳይገጥመው፣ ስኬታማ መሆን የሚቻልበትን መንገድ ሊማር አይችልም።

ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ማዳበር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ልጆች አንድ ነገር ሳይሳካላቸው ሲቀር፣ ችግር ሲያጋጥማቸው ወይም ሌሎች ሲተቿቸው ቅስማቸው ይሰበራል። ሌሎች ደግሞ ከናካቴው ተስፋ ይቆርጣሉ። ይሁን እንጂ ልጆች የሚከተሉትን እውነታዎች መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል፦

  • በምናደርገው ነገር ሁሉ ስኬታማ መሆን የማይቻል ነገር ነው።—ያዕቆብ 3:2

  • ሁሉም ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሆነ ወቅት ላይ መከራ ያጋጥመዋል።—መክብብ 9:11

  • እርማት ካላገኘን ከስህተታችን መማር አንችልም።—ምሳሌ 9:9

ልጃችሁ ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ ካዳበረ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በልበ ሙሉነት መጋፈጥ ይችላል።

ልጆች ችግሮችን እንዲቋቋሙ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

አንድ ነገር ሳይሳካለት ሲቀር።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳል።”—ምሳሌ 24:16

ልጃችሁ ለነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው እርዱት። ለምሳሌ ያህል፣ በትምህርት ቤት ፈተና ቢወድቅ “ምንም ነገር ሊሳካልኝ አይችልም!” ብሎ ተስፋ ይቆርጥ ይሆናል።

ልጃችሁ ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ እንዲያዳብር ለመርዳት፣ በቀጣዩ ጊዜ ማሻሻያ ማድረግ የሚችልበትን ዘዴ እንዲቀይስ እርዱት። ይህም በችግሩ ከመሸነፍ ይልቅ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት እንዲያደርግ ይረዳዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጣልቃ ገብታችሁ ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ እሱ ራሱ ችግሩን መፍታት የሚችልበት መላ እንዲፈጥር እርዱት። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ፈተና ከወደቀ “ለወደፊቱ ይህን ትምህርት በተሻለ መንገድ ለመረዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ።

ችግር ሲያጋጥመው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን እንኳ አታውቁም።”—ያዕቆብ 4:14

ማናችንም ብንሆን ነገ ምን እንደሚያጋጥመን አናውቅም። ዛሬ ሀብታም የሆነ ሰው ነገ ድሃ ሊሆን ይችላል፤ ዛሬ ጤነኛ የሆነ ሰው ነገ ሊታመም ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ ኃያላን በውጊያ ሁልጊዜ ድል አይቀናቸውም። . . . ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።”—መክብብ 9:11

ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጃችሁን ከአደጋ ለመጠበቅ አንዳንድ እርምጃዎችን እንደምትወስዱ የታወቀ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ልጃችሁን በሕይወቱ ውስጥ ከሚያጋጥሙት ችግሮች ሁሉ ልትጠብቁት አትችሉም።

እርግጥ ነው፣ ልጃችሁ ከሥራ እንደመፈናቀል ወይም ሀብት ንብረትን እንደማጣት ያሉ ችግሮችን ለመጋፈጥ ዕድሜው ገና አልደረሰ ይሆናል። ያም ቢሆን ሌሎች ችግሮች ሲያጋጥሙት ለምሳሌ ከጓደኛው ጋር ሲጣላ ወይም የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ ሁኔታውን እንዴት መቋቋም እንደሚችል ልታሠለጥኑት ትችላላችሁ።a

ትችት ሲሰነዘርበት።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የኋላ ኋላ ጥበበኛ እንድትሆን ምክርን ስማ።”—ምሳሌ 19:20

ትችት በራሱ ጎጂ አይደለም፤ ተገቢ የሆነ ትችት አንድ ሰው ትክክል ያልሆነን ድርጊት ወይም ዝንባሌ እንዲያስተካክል ሊረዳው ይችላል።

ልጃችሁ እርማት እንዲቀበል የምታስተምሩት ከሆነ እሱንም ሆነ ራሳችሁን ከብዙ ሐዘን ትጠብቃላችሁ። የሦስት ልጆች አባት የሆነ ጆን የተባለ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች ስህተታቸውን እንዲያስተካክሉ ካልተደረጉ መቼም ቢሆን ሊማሩ አይችሉም። ከአንዱ ችግር ዘለው ሌላ ችግር ውስጥ የሚገቡ ሲሆን እናንተም ከኋላ ከኋላ እየተከተላችሁ እነሱ የለኮሱትን እሳት ስታጠፉ ትኖራላችሁ። ይህ ደግሞ የእናንተንም ሆነ የልጆቹን ሕይወት መራራ ያደርገዋል።”

ታዲያ ልጃችሁ፣ ገንቢ ከሆነ ትችት ጥቅም እንዲያገኝ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? ልጃችሁ በትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ ቦታ እንዲህ ያለ ትችት ሲሰነዘርበት፣ ትችቱ ተገቢ እንዳልሆነ ለመናገር ብትፈተኑም እንዲህ ከማለት ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ ልጃችሁን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልትጠይቁት ትችላላችሁ፦

  • “ይህ እርማት የተሰጠህ ለምን ይመስልሃል?”

  • “ለወደፊቱ ምን ማሻሻያ ማድረግ ትችላለህ?”

  • “ሌላ ጊዜ እንዲህ ያለ እርማት ቢሰጥህ ምን ታደርጋለህ?”

ገንቢ ትችት፣ ልጃችሁን አሁንም ሆነ አዋቂ ከሆነ በኋላ በእጅጉ እንደሚጠቅመው አስታውሱ።

a በሐምሌ 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

አንዲት ልጅ የጋገረችው ኬክ ስለተበላሸባት ተበሳጭታ ሳለ እናቷ ስትረዳት

ከወዲሁ አሠልጥኗቸው

ልጆች ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ወይም ስህተት ሲሠሩ እጅ ከመስጠት ይልቅ በቆራጥነት የሚጸኑ ከሆነ ወደፊት ሙያ ሲማሩ በቀላሉ ተስፋ አይቆርጡም፤ እንዲሁም በሙያቸው የተካኑ የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው

ምሳሌ በመሆን አስተምሩ

  • ጥፋቴን አምናለሁ ወይስ በሌሎች ላይ አላክካለሁ?

  • ስለሠራኋቸው ስህተቶችና ሳይሳኩልኝ ስለቀሩ ነገሮች እንዲሁም ከእነዚህ ስላገኘሁት ትምህርት እናገራለሁ?

  • ሌሎች በሠሩት ስህተት አሾፋለሁ?

አንዳንድ ወላጆች ያደረጉት ነገር

“ልጆቻችን ምንም ችግር እንዳያገኛቸው አንከላከልላቸውም ነበር፤ እንዲሁም የሆነ ነገር ሳይሳካላቸው ሲቀር ወይም ስህተት ሲሠሩ ጣልቃ ገብተን ችግሩን ልንፈታላቸው አንሞክርም። ልጅ ሳለሁ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ተቋቁሜ ማለፌ ዛሬ የተሻልኩ ሰው እንድሆን ረድቶኛል። ሁለቱም ልጆቻችን ሚዛናዊና በሳል አዋቂዎች መሆን የቻሉት ተሞላቀው ስላላደጉ እንደሆነ ይሰማኛል።”—ጄፍ

“እኔና ባለቤቴ ከልጆቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ስህተት ስንሠራ ምንጊዜም ይቅርታ እንጠይቃለን። ወላጆች እነሱ ራሳቸው የሠሯቸውን ስህተቶች፣ ለልጆቻቸው መንገር እንዳለባቸው አምናለሁ፤ እንዲህ ማድረጋቸው ልጆች ስህተት መሥራት በማንም ሰው ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥም ነገር እንደሆነ እንዲገነዘቡ ይረዳል።”—ጄምስ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ