የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g19 ቁጥር 2 ገጽ 10-11
  • ኃላፊነት የሚሰማው መሆን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኃላፊነት የሚሰማው መሆን
  • ንቁ!—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኃላፊነት የሚሰማው መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
  • ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
  • ልጆች ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?
  • ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ ማድረግ ያለው ጥቅም
    ንቁ!—2017
  • 8 ምሳሌ መሆን
    ንቁ!—2018
  • መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችህን ለማሰልጠን ይረዳህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ልጆች ሽንፈትን በጥሩ ሁኔታ እንዲወጡ መርዳት
    ለቤተሰብ
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2019
g19 ቁጥር 2 ገጽ 10-11
አንድ አባት አትክልቶችን ውኃ እንዲያጠጣ ልጁን ሲያስተምረው

ትምህርት 4

ኃላፊነት የሚሰማው መሆን

ኃላፊነት የሚሰማው መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። የተሰጣቸውን ሥራ በጥሩ ሁኔታና በተመደበላቸው ጊዜ ውስጥ ሠርተው ያጠናቅቃሉ።

ሕፃናትም እንኳ አቅማቸው ውስን ቢሆንም ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ መሠልጠን ይችላሉ። ፓረንቲንግ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሕፃን አሥራ አምስት ወር ሲሞላው፣ አድርግ የተባለውን ነገር ማድረግ የሚጀምር ሲሆን አሥራ ስምንት ወር ሲሞላው ደግሞ ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር እያየ ማድረግ ይጀምራል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በብዙ ባሕሎች ወላጆች ልጆቻቸው በተለይ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት እንዲያግዟቸው ያደርጋሉ፤ በዚህ ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆችም እንኳ ብዙ የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብረው በመሥራት ወላጆቻቸውን ማገዝ ይችላሉ።”

ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ከቤት ከወጡ በኋላ ኑሮ ስለሚከብዳቸው ወደ እናታቸውና ወደ አባታቸው ይመለሳሉ። ይህ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ልጆቹ ስለ ገንዘብ አያያዝ፣ ስለ ቤት አያያዝ ወይም የዕለት ተዕለት ኃላፊነቶችን መወጣት ስለሚቻልበት መንገድ ምንም ሥልጠና ስላላገኙ ነው።

ስለዚህ ልጆቻችሁ አዋቂ ሲሆኑ ለሚጠብቃቸው ኃላፊነት ከወዲሁ ብታሠለጥኗቸው ጥሩ ነው። ሃው ቱ ሬይዝ አን አዳልት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ከቤት የሚወጡበት ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ በጫንቃችሁ ላይ ተሸክማችሁ ካቆያችኋቸው በኋላ ልክ አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላቸው ወደ ውጭው ዓለም አውጥታችሁ ልትጥሏቸው እንደማትፈልጉ የተረጋገጠ ነው።”

ልጆች ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

የቤት ውስጥ ሥራ ስጧቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።”—ምሳሌ 14:23

ትናንሽ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው መሥራት ያስደስታቸዋል። እንግዲያው ለልጆቻችሁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመስጠት ልጆች ያላቸውን ይህን ተፈጥሯዊ ፍላጎት በሚገባ ተጠቀሙበት።

አንዳንድ ወላጆች ግን እንዲህ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ልጆቹ በትምህርት ቤት በየቀኑ ብዙ የቤት ሥራ ስለሚሰጣቸው ሌላ ሸክም ሊጨምሩባቸው አይፈልጉም።

ይሁን እንጂ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ልጆች፣ የተሰጣቸውን ሥራ መቀበልንና ሠርቶ ማጠናቀቅን ስለሚማሩ በትምህርት ቤትም ስኬታማ የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው። ከዚህም በላይ ፓረንቲንግ ዊዝአውት ቦርደርስ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “ልጆቻችን ገና ትናንሾች እያሉ የሚኖራቸውን ሌሎችን የመርዳት ጉጉት ችላ የምንለው ከሆነ ልጆቹ ሌሎችን ማገዝ አስፈላጊ እንዳልሆነ ማሰብ ሊጀምሩ ይችላሉ። . . . በተጨማሪም ሁሌም ሌሎች እንዲያደርጉላቸው መጠበቅ ይጀምራሉ።”

መጽሐፉ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ እንደሚያመለክተው ልጆች የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራታቸው ተቀባይ ከመሆን ይልቅ ሰጪ፣ ተረጂ ከመሆን ይልቅ ሌሎችን የሚረዱ እንዲሆኑ ያሠለጥናቸዋል። የቤት ውስጥ ሥራዎች፣ ልጆች በቤተሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳላቸውና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ይረዳሉ።

ልጆቻችሁ ላጠፉት ጥፋት ኃላፊነት እንዲወስዱ አድርጉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የኋላ ኋላ ጥበበኛ እንድትሆን ምክርን ስማ፤ ተግሣጽንም ተቀበል።”—ምሳሌ 19:20

ልጃችሁ ጥፋት ቢያጠፋ፣ ለምሳሌ ሳያስበው የሌላን ሰው ንብረት ቢያበላሽ ጥፋቱን ልትሸፋፍኑለት አትሞክሩ። ከዚህ ይልቅ ይቅርታ እንዲጠይቅ አልፎ ተርፎም የማካካሻ እርምጃ እንዲወስድ አድርጉ። ልጆች ድርጊታቸው ያስከተለውን መዘዝ እንዲቀበሉ ማድረግ ስህተት አይደለም።

ልጆች ጥፋታቸውን አምነው የሚቀበሉና ለድርጊታቸው ኃላፊነት የሚወስዱ ከሆነ የሚከተሉትን ነገሮች ይማራሉ፦

  • ሐቀኛ መሆንን

  • ጥፋትን በሌሎች ላይ ከማላከክ መቆጠብን

  • ሰበብ አስባብ ከመደርደር መራቅን

  • አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ይቅርታ መጠየቅን

አንድ አባት አትክልቶችን ውኃ እንዲያጠጣ ልጁን ሲያስተምረው

ከወዲሁ አሠልጥኗቸው

ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ተደርገው ያደጉ ልጆች አዋቂ ሲሆኑ ሕይወታቸውን በተሻለ መንገድ መምራት ይችላሉ

ምሳሌ በመሆን አስተምሩ

  • ታታሪ፣ የተደራጀሁና ሰዓት አክባሪ ነኝ?

  • ልጆቼ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ስሠራ ያዩኛል?

  • ጥፋቴን አምኜ እቀበላለሁ? አስፈላጊ ሲሆንስ ይቅርታ እጠይቃለሁ?

አንዳንድ ወላጆች ያደረጉት ነገር

“ከትንሽነታቸው አንስቶ ልጆቼ ራት ስሠራ አብረውኝ ይሠራሉ። ልብስ ሳጣጥፍ እነሱም ያጣጥፋሉ። ቤት ሳጸዳ እነሱም ያጸዳሉ። ሥራ ለእነሱ አስደሳች ነገር ነበር። ከእኔ ጋር ሆነው እኔ የምሠራውን ነገር መሥራታቸው በራሱ ያስደስታቸው ነበር። ልጆቼ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆንን የተማሩት በዚህ መንገድ ነው።”—ሎራ

“በአንድ ወቅት ልጃችን ትንሽ ሳለ፣ የቤተሰባችን ወዳጅ የሆነችን አንዲት ሴት በንግግሩ ስላስቀየማት ስልክ ደውሎ ይቅርታ እንዲጠይቅ አድርጌው ነበር። ከዚያ በኋላም ቢሆን፣ ትክክል የሆነ ግን ደግነት የጎደለው ንግግር በመናገሩ በተደጋጋሚ ይቅርታ እንዲጠይቅ አድርጌዋለሁ፤ አሁን ሲያጠፋ ይቅርታ መጠየቅ አይከብደውም።”—ዴብራ

ልጆች ድርጊታቸው ያስከተለውን ውጤት እንዲቀበሉ ማድረግ ያለው ጥቅም

ጄሲካ ሌሂ የተባሉ መምህርት አትላንቲክ በተባለው መጽሔት ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ልጆች ጥፋት ያጠፋሉ፤ በዚህ ጊዜ የጥፋታቸውን ውጤት እንዲቀበሉ መደረጋቸው ትልቅ ትምህርት እንደሚያስተምራቸው ወላጆች ሊያስታውሱ ይገባል።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “በየዓመቱ፣ በጣም ‘ምርጥ’ የምላቸው ማለትም ደስተኛና ስኬታማ የሆኑት ተማሪዎቼ በፈተና የሚወድቁበት ዕድል የተሰጣቸው፣ ለጥፋታቸው ኃላፊነት እንዲወስዱ የተደረጉና ስህተታቸውን ማረም እንዲችሉ እገዛ የተደረገላቸው ተማሪዎች ናቸው።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ