የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g21 ቁጥር 3 ገጽ 10-13
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?
  • ንቁ!—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን አይልም?
  • አምላክ ጽንፈ ዓለምን መፍጠር የጀመረው መቼ ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?
    ንቁ!—2006
  • ያልተነገረው የፍጥረት ታሪክ
    ንቁ!—2014
  • ሳይንስና የዘፍጥረት ዘገባ
    ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2021
g21 ቁጥር 3 ገጽ 10-13

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?

“ሰማያትና ምድር በተፈጠሩበት ጊዜ፣ . . . የተከናወነው ነገር ይህ ነው።” (ዘፍጥረት 2:4) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፕላኔታችን አጀማመር የሚገልጸውን ታሪክ የሚደመድመው በእነዚህ ቃላት ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር በሳይንስ ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር ይስማማል? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

በመጀመሪያ፦ ሰማያትና ምድር ተፈጠሩ

ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ አለው?

ዘፍጥረት 1:1 “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል።

እስከ 1950ዎቹ ዓመታት ድረስ በርካታ ታዋቂ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንደሌለው ያምኑ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ጽንፈ ዓለም በእርግጥም መጀመሪያ እንዳለው አምነዋል።

ምድር መጀመሪያ ላይ ምን ትመስል ነበር?

ዘፍጥረት 1:2, 9 እንደሚገልጸው ምድር መጀመሪያ ላይ “ቅርጽ አልባና ባድማ” እንዲሁም በውኃ የተሸፈነች ነበረች።

ይህ መግለጫ ዘመናዊ ሳይንስ ከደረሰበት ነገር ጋር ይስማማል። ፓትሪክ ሺ የተባሉት የባዮሎጂ ባለሙያ ምድራችን መጀመሪያ ላይ ስለነበራት ሁኔታ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ኦክስጅን የሌለውና ለመተንፈስ የማይሆን ከባቢ አየር ነበራት። . . . በጥቅሉ ሲታይ የምድራችን መልክ ሳይንስ ፊክሽን (ሳይንሳዊ ልብ ወለድ) ላይ የሚታየውን ይመስል ነበር።” አስትሮኖሚ መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “አዳዲስ የምርምር ውጤቶች እንደሚያሳዩት የጥንቷ ምድር የውኃ ዓለም ነበረች፤ የብስ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር።”

ከባቢ አየር በጊዜ ሂደት የተቀየረው እንዴት ነው?

ዘፍጥረት 1:3-5 ብርሃን ወደ ከባቢ አየር እንደደረሰ ይናገራል፤ ሆኖም መጀመሪያ ላይ፣ ምድር ላይ ሆኖ የብርሃኑን ምንጭ መለየት አይቻልም ነበር። ከምድር ሆኖ ፀሐይን እና ጨረቃን በግልጽ ማየት የተቻለው የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ነበር።—ዘፍጥረት 1:14-18

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በምድር ላይ ያለው ሕይወት ሁሉ የተፈጠረው የ24-ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ አይናገርም

የስሚዝሶኒያን የአካባቢ ምርምር ማዕከል እንደሚገልጸው መጀመሪያ ላይ ከባቢ አየሩን አልፎ ወደ ምድር መድረስ የሚችለው ደብዛዛ ብርሃን ብቻ ነበር። ማዕከሉ ያወጣው ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “የሜቴን ቅንጣቶች እንደ ጉም ምድርን ጥቅጥቅ አድርገው ሸፍነዋት ነበር።” ውሎ አድሮ ግን “ይህ የሜቴን ጉም እየጠራ ሄደና ሰማያዊ ሰማይ ታየ።”

ሕይወት ያላቸው ነገሮች ምድር ላይ የታዩት በየትኛው ቅደም ተከተል ነው?

1​—አንደኛ ቀን፦ የምድርን ከባቢ አየር አልፎ የመጣ ደብዘዝ ያለ ብርሃን ታየ።—ዘፍጥረት 1:3-5

2​—ሁለተኛ ቀን፦ ምድር በውኃና ጥቅጥቅ ባለ ተን የተሸፈነች ነበረች። ተኑና ውኃው ተለያዩና በመካከላቸው ክፍተት ተፈጠረ።—ዘፍጥረት 1:6-8

3​—ሦስተኛ ቀን፦ የብስ ላይ ያለው ውኃ አንድ ቦታ ተሰበሰበና ደረቅ መሬት ታየ።—ዘፍጥረት 1:9-13

4​—አራተኛ ቀን፦ ፀሐይና ጨረቃ ከምድር መታየት ጀመሩ።—ዘፍጥረት 1:14-19

5​—አምስተኛ ቀን፦ አምላክ በውኃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በሰማይ የሚበርሩ ሕያዋን ፍጥረታትን ፈጠረ፤ እነዚህ ፍጥረታት በየወገናቸው የመራባት ችሎታ ተሰጥቷቸዋል።—ዘፍጥረት 1:20-23

6​—ስድስተኛ ቀን፦ ትላልቅ እና ትናንሽ የየብስ እንስሳት ተፈጠሩ። በስድስተኛው ቀን ማብቂያ ላይ የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ተፈጠሩ።—ዘፍጥረት 1:24-31

ዘፍጥረት 1:20-27 ዓሦች፣ ወፎች፣ የየብስ እንስሳት፣ በመጨረሻም ሰዎች እንደተፈጠሩ ይናገራል። ሳይንቲስቶች የመጀመሪያው አጥቢ እንስሳ የታየው የመጀመሪያው ዓሣ ከታየ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ያምናሉ፤ የሰው ልጆች ምድር ላይ የታዩት ደግሞ ከዚያ በጣም ቆይቶ እንደሆነ ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጊዜ ሂደት ለውጥ አያደርጉም ብሎ አይናገርም

“በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አጠር ያለ ቢሆንም የተጠቀሱት ክንውኖችና የተፈጸሙበት ጊዜ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ያላቸው ስምምነት በጣም አስገራሚ ነው።”—ጄራልድ ሽሮደር፣ የፊዚክስ ሊቅ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን አይልም?

አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናዊ ሳይንስ ከደረሰባቸው ነገሮች ጋር እንደማይስማማ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ በአብዛኛው የሚመነጨው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የጽንፈ ዓለም ወይም የምድር ዕድሜ 6,000 ዓመት ብቻ እንደሆነ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ምድርም ሆነች ጽንፈ ዓለም “በመጀመሪያ” እንደተፈጠሩ ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 1:1) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነው መቼ እንደሆነ በቀጥታ አይናገርም።

መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ያለው ሕይወት ሁሉ የተፈጠረው የ24-ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ “ቀን” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት የተለያየ ርዝማኔ ያለውን ጊዜ ለማመልከት ነው። ለምሳሌ ፕላኔታችንና ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተፈጠሩበትን ጊዜ (በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ የተገለጹትን ስድስት የፍጥረት “ቀናት” ማለት ነው) “ይሖዋa አምላክ ምድርንና ሰማይን [የሠራበት] ቀን” ብሎ ይጠራዋል። (ዘፍጥረት 2:4) በመሆኑም አምላክ ምድርን ለመኖሪያነት ያመቻቸባቸውና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረባቸው ስድስት የፍጥረት “ቀናት” እያንዳንዳቸው በጣም ረጅም ጊዜን የሚያመለክቱ ሊሆኑ ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጊዜ ሂደት ለውጥ አያደርጉም ብሎ አይናገርም። የዘፍጥረት መጽሐፍ እንስሳት “እንደየወገናቸው” እንደተፈጠሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:24, 25) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው “ወገን” የሚለው ቃል ሳይንሳዊ ትርጉም ያለው ቃል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰፋ ያለ ምድብን የሚያመለክት ቃል ይመስላል። በመሆኑም አንድ “ወገን” በውስጡ ብዙ ዝርያዎችን ሊያካትት ይችላል። ይህ ቃል በአንድ ወገን ውስጥ የዝርያ ለውጥ ሊካሄድ የሚችልበት ክፍተት ይሰጣል፤ ከዚህ አንጻር የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ዝርያዎች በጊዜ ሂደት ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚለው ሐሳብ ጋር አይጋጭም።

ታዲያ ምን ይመስልሃል?

ቀደም ብለን እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጽንፈ ዓለም አጀማመር፣ ምድር መጀመሪያ ላይ ስለነበረችበት ሁኔታ እንዲሁም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ምድር ላይ ስለታዩበት ቅደም ተከተል የያዘው ሐሳብ ቀላልና ትክክለኛ ነው። ታዲያ ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ነገሮች የፈጠረ አካል እንዳለ የሚናገረው ሐሳብስ ትክክል ሊሆን አይችልም? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወት የተገኘው ከሰው በላይ በሆነ ኃይል ጣልቃ ገብነት ነው የሚለው ሐሳብ በጥቅሉ ሲታይ ዘመናዊ ሳይንስ ከደረሰበት ጋር የሚጋጭ አይደለም።”b

እስቲ አስበው፦

ዘፍጥረት 1:1 እስከ 2:4⁠ን አንብብ። ይህን ዘገባ፣ ስለ ፍጥረት ከሚገልጹ ጥንታዊ አፈታሪኮች ጋር አወዳድር። ለምሳሌ ያህል፣ ባቢሎናውያን ጽንፈ ዓለምና የሰው ልጆች የተሠሩት ከአንዲት እንስት አምላክ አስከሬን እና ከአንድ ተባዕት አምላክ ደም እንደሆነ ያምኑ ነበር። የጥንቶቹ ግብፃውያን ራ የተባለው አምላክ የሰው ልጆችን ከእንባ እንደሠራቸው ያስቡ ነበር። ቻይና ውስጥ ደግሞ አንዳንዶች የአንድ ግዙፍ አካል አስከሬን ምድር ወደተሠራችባቸው ንጥረ ነገሮች እንደተቀየረ፣ የሰው ልጆች የተገኙትም በዚህ አስከሬን ላይ ከነበሩ ቁንጫዎች እንደሆነ ይናገሩ ነበር። ታዲያ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ታሪክ ከእነዚህ አፈታሪኮች ተርታ እንደሚመደብ ይሰማሃል? ወይስ ከሳይንስ አንጻር ትርጉም የሚሰጥ ሐሳብ ይዟል?

ጽንፈ ዓለም የተገኘው በፍጥረት ነው? የተባለውን የአራት ደቂቃ ቪዲዮ ተመልከት። የቪዲዮውን ርዕስ jw.org ላይ ፈልግ።

a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።

b ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው የሚል አቋም አያራምድም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ