ቀውስ ባለበት ጊዜ ከሌሎች ጋር ያለህን ግንኙነት ለመጠበቅ እነዚህን እርምጃዎች ውሰድ
ትዳርህን አጠናክር
ትዳርህን አጠናክር
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤ . . . አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና።” (መክብብ 4:9, 10) ባልና ሚስት በተቃራኒ ጎራ ያሉ ሁለት ተዋጊ ጄቶችን እንደሚያበርሩ አብራሪዎች መሆን የለባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አንድን አውሮፕላን ተባብረው እንደሚያበርሩ ዋና አብራሪና ረዳት አብራሪ እንደሆኑ ማስታወስ አለባቸው።
ሁለታችሁም ብስጭታችሁን በሌላው ላይ ላለመወጣት ጥረት አድርጉ። መታገሥና ችሎ ማለፍ በጣም አስፈላጊ ነው።
ቢያንስ በሳምንት አንዴ፣ መነጋገር የሚፈልጉ ጉዳዮችን አንስታችሁ ከትዳር አጋራችሁ ጋር ተወያዩ። እርስ በርስ ከመወቃቀስ ይልቅ ችግሩን በመፍታት ላይ ትኩረት አድርጉ።
ሁለታችሁንም የሚያስደስቷችሁን ነገሮች ለማድረግ ጊዜ መድቡ።
አብራችሁ ያሳለፋችሁትን አስደሳች ጊዜ መለስ ብላችሁ አስቡ፤ የሠርጋችሁን ወይም አስደሳች ትዝታ የሚፈጥሩባችሁን ሌሎች ፎቶዎች መመልከታችሁ ለዚህ ሊረዳችሁ ይችላል።
“ባልና ሚስት በሁሉ ነገር ይስማማሉ ማለት አይደለም፤ ሆኖም ለአንድ ዓላማ ተባብረው መሥራት ይችላሉ። አብረው ውሳኔ ማድረግና ውሳኔያቸው እንዲሳካ በጋራ መሥራት ይችላሉ።”—ዴቪድ
ከወዳጆችህ አትራቅ
ከወዳጆችህ አትራቅ
የወዳጆችህን ድጋፍ መቀበል ብቻ ሳይሆን አንተም ለእነሱ ድጋፍ መስጠት ስለምትችልባቸው መንገዶች አስብ። ሌሎችን ስታበረታታ አንተም ትበረታታለህ።
በየቀኑ የተወሰኑ ጓደኞችህን መርጠህ ደህንነታቸውን ጠይቃቸው።
ዛሬ አንተን ያጋጠሙህን ችግሮች እንዴት እንዳለፏቸው ጓደኞችህን ጠይቃቸው።
“ጓደኞች በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ አሻግረህ እንደምታየው ምልክት ናቸው። የት እንዳለህና የትኛውን አቅጣጫ ይዘህ መጓዝ እንዳለብህ ይጠቁሙሃል፤ ደግሞም አንዳንድ ጊዜ የሚያስፈልግህ የምታውቀውን ነገር የሚያስታውስህ ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል። ወዳጆችህ ያስቡልሃል፤ አንተም እንደምታስብላቸው በደንብ ያውቃሉ።”—ኒኮል
ለልጆችህ አስፈላጊውን ድጋፍ ስጥ
ለልጆችህ አስፈላጊውን ድጋፍ ስጥ
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት።” (ያዕቆብ 1:19) መጀመሪያ ላይ ልጆችህ፣ የሚያስፈራቸውንና የሚያሳስባቸውን ነገር መናገር ላይፈልጉ ይችላሉ። ሆኖም በትዕግሥት በማዳመጥ ስሜታቸውን አውጥተው እንዲነግሩህ ልትረዳቸው ትችላለህ።
ልጆችህ ስሜታቸውን አውጥተው መናገር እንዲቀላቸው የሚያደርግ አመቺ ሁኔታ እንዲኖር አድርግ። አንዳንድ ልጆች በጠረጴዛ ዙሪያ ፊት ለፊት ከማውራት ይልቅ ዘና ባለ ሁኔታ ማውራት ሊቀላቸው ይችላል፤ ለምሳሌ በመኪና አብራችሁ ስትሄዱ ወይም በእግር ስትጓዙ።
ልጆችህ ለሚረብሹ ዜናዎች ብዙ እንዳይጋለጡ ጥረት አድርግ።
የቤተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ስትሉ ምን እርምጃዎች እንደወሰዳችሁ ለልጆችህ ንገራቸው።
የአደጋ ጊዜ ዕቅድ ይኑራችሁ፤ ከልጆቻችሁ ጋርም ምን እንደምታደርጉ አስቀድማችሁ ተለማመዱ።
“ልጆቻችሁን አዋሯቸው፤ ስሜታቸውን እንዲገልጹም ዕድል ስጧቸው። ምናልባትም የሚሰማቸውን ፍርሃት፣ ጭንቀት ወይም ቁጣ አምቀውት ይሆናል። እናንተም እንዲህ የሚሰማችሁ ጊዜ እንዳለና እንዴት መወጣት እንደቻላችሁ ንገሯቸው።”—ቤታኒ