Oleh_Slobodeniuk/E+ via Getty Images
አምላክ ፕላኔታችን እንደምትተርፍ ቃል ገብቷል
“ምድር ከምንጠብቀው በላይ ቻይ ነች።”
ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ እዚህ መደምደሚያ ላይ ደርሷል። ለሰው ልጆች የሚያስብ ፈጣሪ እንዳለ የምታምን ከሆነ እነዚህ ሳይንቲስቶች የደረሱበት መደምደሚያ አምላክ ለፕላኔታችን የሰጣትን ራሷን በራሷ የማደስ ችሎታ ያስታውስህ ይሆናል።
ያም ቢሆን፣ የሰው ልጆች በምድር ላይ ያደረሱት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ምድር በራሷ ችሎታ አሁን ካለችበት ደረጃ ማገገም አትችልም። ታዲያ አምላክ እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
በሣጥኑ ውስጥ የተዘረዘሩት ጥቅሶች ምድር እንደምትተርፍ አልፎ ተርፎም ለዘላለም ተስማሚ መኖሪያ ሆና እንደምትቀጥል ዋስትና ይሰጡናል።
ፕላኔታችንን የፈጠራት አምላክ ነው። “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።” —ዘፍጥረት 1:1
ፕላኔታችን የአምላክ ንብረት ናት። “ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ . . . የይሖዋa ነው።”—መዝሙር 24:1
አምላክ ፕላኔታችንን የፈጠራት ለዘላለም መኖር እንድትችል አድርጎ ነው። “ምድርን በመሠረቶቿ ላይ መሠረታት፤ እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም።”—መዝሙር 104:5
አምላክ፣ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ለዘላለም በምድር ላይ እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። “እውነተኛው አምላክ፣ ምድርን የሠራትና ያበጃት፣ . . . መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ [አይደለም።]”—ኢሳይያስ 45:18
አምላክ፣ የሰው ልጆች በፕላኔታችን ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
አምላክ ምድርን የፈጠራት የሰው ልጆች በአግባቡ እስከተጠቀሙባት ድረስ ራሷን በራሷ ማደስ እንድትችል አድርጎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ በምድራችን ላይ የደረሰውን ብዝበዛና በደል እንደሚያስወግድ ይናገራል።—ራእይ 11:18
ከዚያ በኋላ አምላክ ፕላኔታችንን ጤናማና ውብ ገነት እንደሚያደርጋት እንዲሁም “የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት” እንደሚያሟላ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል።—መዝሙር 145:16
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18