የኑሮ ውድነትን መቋቋም
ለጋስ ሁን
ከኑሮ ውድነት ጋር እየታገልክ ከሆነ ለጋስ መሆን ጨርሶ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና ለሌሎች በልግስና ስትሰጥ የኢኮኖሚ ችግሮችን ጭምር ለመቋቋም እንደሚያግዝህ ትመለከታለህ። አዎ፣ ቆጣቢም ለጋስም መሆን ትችላለህ።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በትናንሽ ነገሮችም እንኳ ለጋስ መሆን ደስታችንና ለራሳችን ያለን ግምት እንዲጨምር ያደርጋል። እንዲያውም ጥናቶች እንደሚያሳዩት መስጠት ለአካላዊ እንዲሁም ለአእምሯዊ ጤንነታችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ጭንቀት፣ ውጥረት፣ የደም ግፊት ሌላው ቀርቶ የሕመም ስሜት ጭምር ይቀንሳል። ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛትም ሊያግዘን ይችላል።
ለሌሎች ገንዘባችንንም ሆነ ሌላ ያለንን ነገር የምንሰጥ ከሆነ እኛም በሚያስፈልገን ጊዜ የሌሎችን እርዳታ መቀበል ቀላል ይሆንልናል። በእንግሊዝ የሚኖረው ሃወርድ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ አጋጣሚ ፈልገን ለሌሎች ስለምንሰጥና መልካም ስለምናደርግ እኛ የሌሎች እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ሸክም እንደሆንን አይሰማንም።” እርግጥ ነው፣ ከልባቸው ለጋስ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች በምላሹ ምንም አይጠብቁም። ያም ቢሆን ለጋስ መሆናቸው በችግር ጊዜ የሚደርሱላቸው እውነተኛ ጓደኞች ያተርፍላቸዋል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ያለህን አካፍል። ልትሰጠው የምትችለው ብዙ ነገር እንዳለህ ባይሰማህም እንኳ ልታካፍለው የምትችለው የሆነ ነገር ይኖርሃል፤ ቀለል ያለ ምግብም ሊሆን ይችላል። በኡጋንዳ የሚኖሩት ደንከንና ቤተሰቡ ድሆች ናቸው፤ ቢሆንም የልግስና መንፈስ አላቸው። ደንከን እንዲህ ብሏል፦ “እሁድ እሁድ እኔና ባለቤቴ ትንሽ ምግብ አዘጋጅተን አንድ ሰው እንጋብዛለን። ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተናል።”
እርግጥ ነው፣ ለሌሎች ስትሰጥ ምክንያታዊ መሆን ይኖርብሃል። ቤተሰብህ ላይ ጫና ላለመፍጠር መጠንቀቅ አለብህ።—ኢዮብ 17:5
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ቀለል ያለ ምግብ ወይም ሻይ ቡና አዘጋጅተህ አንድን ሰው ጋብዝ። የማትጠቀምባቸው ዕቃዎች ካሉህ፣ ብሰጣቸው ይጠቀማሉ ወይም ደስ ይላቸዋል ለምትላቸው ጓደኞችህ ወይም ጎረቤቶችህ መስጠት ትችል ይሆን?
በሌሎች መንገዶች ስጥ። ጥሩ ከሚባሉ ስጦታዎች አንዳንዶቹ ምንም ገንዘብ አያስወጡም። ለምሳሌ ሌሎችን በማገዝ ጊዜያችንንና ትኩረታችንን ልንሰጣቸው እንችላለን። መልካም ቃላት ጭምር ስጦታ ሊሆኑ ይችላሉ! ስለዚህ ሌሎችን ምን ያህል እንደምታደንቃቸውና እንደምትወዳቸው ንገራቸው።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የቤት ውስጥ ሥራ በማገዝ፣ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በመጠገን ወይም በመላላክ ሌሎችን እርዳ። ለጓደኛህ አድናቆትህን የሚገልጽ ካርድ ወይም የጽሑፍ መልእክት ላክ፤ ግለሰቡን እንደምታስበው መግለጽህ ብቻ እንኳ በቂ ሊሆን ይችላል።
አጋጣሚ ፈልገህ ለጋስ ስትሆን ብዙ ወሮታ ታገኛለህ።