የኑሮ ውድነትን መቋቋም
ተስፋ ይኑርህ
በምትኖርበት አገር የገበያ ዋጋ የሚጨምርበት መጠን ከገቢህ ጋር አልሄድ ብሎሃል? ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን ማስተዳደር መቻልህ ያሳስብሃል? ከሆነ ነገን ስታስብ ስጋት ያድርብህ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ባለው ከባድ ሁኔታ ውስጥም እንኳ ተስፋ የራስህ ልታደርገው የሚገባ ውድ ነገር ነው።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ተስፋ ማድረግ ሲባል እንዲሁ ቁጭ ብሎ ጥሩ ነገር እንዲከሰት መመኘት ማለት አይደለም። ተስፋ ለሥራ እንድንነሳሳና ያለንበትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት አቅም ይሰጠናል። ለምሳሌ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች በአብዛኛው . . .
መንፈሰ ጠንካራ ናቸው
ከሁኔታዎች ጋር በቀላሉ ይላመዳሉ
ጥበብ የሚንጸባረቅበት የአኗኗር ዘይቤ ይከተላሉ፤ ይህም ጥሩ የጤና አጠባበቅ ልማዶችን ያካትታል
ምን ማድረግ ትችላለህ?
በመጀመሪያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ላይ እንዴት እንደሚረዳህ ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን ይጠቁምሃል። እነዚህም ሆኑ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ሕይወትህን ለማሻሻል ማድረግ በምትችላቸው ነገሮች ላይ እንድታተኩር ይረዱሃል፤ እንዲሁም ወደፊት ለሚያጋጥሙህ ፈተናዎች ዝግጁ ያደርጉሃል።
ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን እንደሚል ተማር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ስትረዳ ይህ መጽሐፍ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የያዘውን ሐሳብ ለመመርመር መነሳሳትህ አይቀርም። ለምሳሌ፣ አምላክ “የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን” እንደሚመኝልህ ትማራለህ፤ ይህ ተስፋ እውን እንዲሆን ደግሞ አስተማማኝ መሠረት እንደጣለ ትረዳለህ። (ኤርምያስ 29:11) ይህ አስተማማኝ መሠረት የአምላክ መንግሥት ነው።
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ምንስ ያከናውናል?
የአምላክ መንግሥት ወደፊት መላዋን ምድር የሚገዛ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10) ከሰማይ ሆኖ የሚገዛው ይህ መንግሥት መከራን እንዲሁም ድህነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወግዳል፤ በምትኩ ሰላምና ብልጽግና እንዲሰፍን ያደርጋል። የሚከተሉት ጥቅሶች ይህን ያሳያሉ፦
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ አይጠራጠሩም፤ ምክንያቱም አምላክ ‘ሊዋሽ እንደማይችል’ ይተማመናሉ። (ቲቶ 1:2) ታዲያ አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን ለምን አትመረምርም? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ዛሬ ላይ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለማሸነፍ ውስጣዊ ጥንካሬ ይሰጥሃል፤ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ደግሞ ብሩህ አመለካከት እንዲኖርህ ያደርጋል።