ምዕራፍ 9
የመንግሥቲቷ ወራሾች ፍጹም አቋማቸውን ይጠብቃሉ
1. (ሀ) ኢየሱስ ከሁሉ የላቀውን ስም የወረሰው ለምንድን ነው? (ለ) እርሱ ካሳየው ምሳሌ እነማን ሊጠቀሙ ይችላሉ? እንዴትስ?
እስከ ሞት ድረስ የታመነ ሆኖ በመገኘቱ ኢየሱስ ከመላእክት የሚበልጥ ስም ወርሷል። አንድ የአምላክ ልጅ አቋሙን ሳያጎድፍ በመኖር ሰይጣንን ውሸታም ማድረግ እንደሚችል የማሰብ ችሎታ ካላቸው ፍጥረታት መካከል በተግባር ያሳየው እርሱ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ከዚህ ጋር በመስማማት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ (ቤዛውን በማቅረብ) በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።” ኢየሱስ የመንግሥቲቱን ‘መምጣት’ ለሚጠባበቁት ሁሉ ይኸውም ሰማያዊውን መንግሥት ለሚወርሱት “ታናሽ መንጋ” እና የዚያች መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች ለሚሆኑት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ ምሳሌ ትቶላቸዋል! ሐዋርያው ጳውሎስ ከዚያ በመቀጠል እንደገለጸው:- “የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል (በመከራ እንጨት ላይ) ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” — ዕብራውያን 1:3, 4፤ 12:1, 2
2–4. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከቱ ሥራ ቀስ በቀስ ያሠለጠናቸውና ያደራጃቸው እንዴት ነው? (ለ) እነርሱስ “ምሥራቹን” ሰዎች ወደሚኖሩባቸው ቤቶች እንዳደረሱ እንዴት እናውቃለን? (ሐ) ይህስ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት የአምላክ አገልጋዮች ምን መልካም ምሳሌ ይሆናል?
2 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ግሩም የሆነ ምሳሌ ከመተዉም በተጨማሪ እርሱ ከሄደ በኋላ የአምላክን ሥራ መቀጠል እንዲችሉ አስተምሮና አሠልጥኗቸው ነበር።
“ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር፤ አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ።” — ሉቃስ 8:1
3 በኋላም ኢየሱስ 12ቱን “የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ” ብቻቸውን ላካቸው። “ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።” (ሉቃስ 9:2, 6) በከተማዎቹና በመንደሮቹ ውስጥ የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ ነበረባቸው፤ ይህንንም በየሰዎቹ ቤት በመሄድ ፈጽመውታል። ይህም ዛሬ ለመልእክቱ ባለው ተቃውሞ ምክንያት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እንደታየው ሁሉ በእነርሱ በኩል በፍጹም አቋማቸው መጽናቱ ድፍረት ጠይቆባቸው ነበር። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።” — ማቴዎስ 10:7, 11–14
4 በኋላም ኢየሱስ ሌሎች 70 ደቀ መዛሙርትን መድቦ ሲልክ “ሂዱ እነሆ፣ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ” አላቸው። እነርሱም ጭምር በየሰዉ ቤት በመሄድ ሰዎቹን በግንባር ማነጋገር ነበረባቸው፤ ምክንያቱም ቀጥሎ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ:- ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፣ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል።” ሰዎቹ “ምሥራቹን” ባይቀበሉም እንኳን የአምላክ መንግሥት ስለ መቅረብዋ ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል። (ሉቃስ 10:3–11) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን የማጽናኛና የማስጠንቀቂያ መልእክት ይዘው ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ለሚያከናውኑት ሥራ ይህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። — ኢሳይያስ 61:1, 2
ስደትን እየተጋፈጡ መስበክ
5. ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ወደፊት ተከታዮቹ የሚያከናውኑትን ሥራ ጎላ አድርጎ የገለጸው በምን መንገዶች ነው?
5 ኢየሱስ ሲሞት ደቀ መዛሙርቱ ተበታተኑ። ይሁን እንጂ መንፈስ ሆኖ ከሞት ከተነሣ በኋላ ልባቸውን ለማረጋጋትና እነርሱን ለማጠናከር ሲል ብዙ ጊዜ ሥጋዊ አካል ለብሶ ተገልጦላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:3–8) ከእነዚህ ጊዜያት በአንዱ ላይ ኢየሱስ እርሱን በእርግጥ ይወደውና ያፈቅረው እንደሆነና እንዳልሆነ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠይቆት ነበር። ጴጥሮስ ይህ ጥያቄ ስለቀረበለት አዘነ፤ ይሁን እንጂ ፍቅር እንዳለው ለማሳየት ‘በጎቹን’ እና ‘ጠቦቶቹን’ መመገብና መምራት እንዳለበት ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ገልጾለታል። (ዮሐንስ 21:15–17) ኢየሱስ በሌላ ጊዜ ሲገለጥ ለ11 የታመኑ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር:-
“ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:18–20)
ከፊታቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር ማለት ነው።
6. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እርሱ ከሠራው የበለጠ ሥራ የሚሠሩት ለምንድን ነው?
6 ኢየሱስ ቀደም ሲል ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፣ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፣ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።” (ዮሐንስ 14:12) እርሱ ከሸፈነው የሚበልጥ ሰፊ አካባቢ በስብከታቸው ይሸፍናሉ፤ እንዲሁም የአምላክን መንግሥት የመስበኩን ሥራ እርሱ ካገለገለበት ለሚበልጥ ጊዜ ያካሄዳሉ ማለቱ ነበር።
7. በጰንጠ ቆስጤ ዕለት የተሟላ ምሥክርነት ወደ መስጠት የመራው ምን አስገራሚ ነገር ነበር? ምን በጣም አስደናቂ ውጤትስ ተገኘ?
7 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሄዶ በአባቱ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ አንድ አስደናቂ ነገር አድርጓል። በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠ ቆስጤ ቀን ከእርሱ አንድ ነገር ይጠባበቁ በነበሩት ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስን በማፍሰስ ከእርሱ ጋር የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ ቀባቸው። በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ ከሰው ዘር መካከል የሚመረጡት በመጨረሻው 144,000 ይሞላሉ። በዚያች ቀን ብቻ በተሰጠው የተሟላ ምሥክርነት ምክንያት 3,000 አይሁዶችና በመገረዝ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀብለው ተጠምቀዋል። — ዮሐንስ 14:2, 3፤ ራእይ 14:1–5፤ 20:4, 6፤ ሥራ 2:1–4, 14, 40, 41
8–11. (ሀ) በዚህ ጊዜ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎቸና በሐዋርያት መካከል ምን ግጭት ተፈጠረ? (ለ) ሐዋርያት ፍጹም አቋም ጠባቂዎች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነበር? (ሐ) በሥራ 5:40–42 መሠረት እነዚህ ሐዋርያት በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት የአምላክ አገልጋዮች ምን ግሩም ምሳሌ ትተዋል?
8 ‘የምሥራቹ’ ስብከት በኢየሩሳሌም ውስጥ ልክ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። በአምላክ መንግሥት ላይ የተነሣው ተቃውሞም የዚያኑ ያህል ተጠናከረ። ወዲያው ሐዋርያት ሳንሄድሪን በሚባለው የአይሁዶች የፍርድ ሸንጎ በኃይል ተወሰዱና በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ ተከለከሉ። በአቋማቸው ይጸኑ ይሆን? ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ ሲሉ መለሱ:- “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደሆነ ቁረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው።” በዚህ ጊዜ ሐዋርያት ተለቀቁ፤ ወዲያውም እነርሱና ጓደኞቻቸው ለአምላክ ምስጋና አቅርበው እንደሚከተለው ብለው ለመኑት:- “አሁንም [ይሖዋ (አዓት)] ሆይ፣ . . . ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።” ስለዚህ በይሖዋ መንፈስ እርዳታ መስበካቸውን ቀጠሉ። — ሥራ 4:19, 20, 29, 31
9 የሃይማኖት መሪዎቹ ሐዋርያትን እንደገና ይዘው ወኅኒ ውስጥ አስገቧቸው። ይሁን እንጂ እዚያው እንዲቆዩ የአምላክ ፈቃድ አልነበረም። ሌሊት የይሖዋ መልአክ አስለቀቃቸው፤ ስለዚህ በማግስቱ እንደገና በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሲያስተምሩ ተገኙ። — ሥራ 5:17–21
10 የሳንሄድሪን ሸንጎ ‘የምሥራቹን’ መስፋፋት ለማስቆም ምን ያደርግ ይሆን? አሁንም እንደገና ሐዋርያት ወደ ፍርድ ሸንጎው ቀረቡ፣ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ በማለት ከሰሳቸው:- “በዚህ [በኢየሱስ] ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው።” እነዚያ ሐዋርያት ከአቋማቸው ዝንፍ ባለማለት የሰጡት መልስ ባለፉት 19 መቶ ዘመናት ሲያስተጋባ ቆይቷል:-
“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።”
አይሁዶች እነዚህን ፍጹም አቋም ጠባቂዎች ምን ያደርጓቸው ይሆን? የሕግ አስተማሪ የነበረው ገማልያል የሚከተለውን ጥበብ ያለበት ምክር ሰጣቸው:- “ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተውአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፣ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።” — ሥራ 5:27–39
11 ከዚያም ሐዋርያት ተገረፉ፣ መናገራቸውን እንዲያቆሙ ታዘዙና ተለቀቁ። በዚህ ምክንያት ምን ተሰማቸው? ስለ ኢየሱስ ስም መከራ ለመቀበል የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ደስ አላቸው።
“ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተውም ነበር።” (ሥራ 5:40–42)
እነዚህ የመንግሥቱ ወራሾች የአምላክን ሥራ ላለማቆም ማንኛውንም መከራ ለመቻል ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ። በዚህ መንገድ መንግሥቲቱን ‘በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት’ መስበካቸውን እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ ለቀጠሉት ለሁሉም እውነተኛ የአምላክ ምሥክሮች ግሩም ምሳሌ ሆነዋል። — ሥራ 20:20, 21
የመንግሥቱ “ምሥራች” ተስፋፋ
12. በሥራ 8:1–4 ላይ እንደተገለጸው ስደት ብዙውን ጊዜ ‘ምሥራቹ’ ይበልጥ እንዲስፋፋ የሚያደርገው እንዴት ነው?
12 ስደቱ አሁንም እንደገና እየተባባሰ ሄደ። በዚህም ምክንያት ከሐዋርያት በቀር ሁሉም በቅርብ ወደሚገኙት የይሁዳና የሰማርያ አካባቢዎች ተበታተኑ። መበታተናቸው ምሥክርነቱን ለማስፋፋት ጠቅሟል፤ ምክንያቱም:- “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ።” (ሥራ 8:1–4) የሚገርመው በዘመናችንም ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሟል። አምባገነናዊ መንግሥታት የይሖዋ ምሥክሮችን ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በመበተን ሥራቸውን ለማቆም ሲሞክሩ እነርሱ በዚያው ቦታ ስብከታቸውን ቀጠሉ፤ በዚህም ምክንያት “ምሥራቹ” ተስፋፋ።
13, 14. (ሀ) አምላክ ለአይሁዳውያን መድቦት የነበረው የልዩ ሞገስ ሳምንት ያበቃው መቼ ነበር? በዚያን ጊዜስ የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው እነማን ናቸው? (ለ) በሥራ 13 እና በሮሜ 11 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ይህንን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?
13 ይሁን እንጂ በዚያን ጊዜ ይኸውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመንግሥቲቷ መልእክት መድረስ የነበረበት ለአይሁዶችና አጐራባች ለሆኑት ሳምራውያን ብቻ ነበርን? የሰማያዊ መንግሥቱ አባላት ሙሉ በሙሉ ከእነርሱ ብቻ ይሰበሰቡ ይሆን? ይሰጥ የነበረው ምሥክርነት አስደናቂ ቢሆንም ነገሩ እንደዚያ አልነበረም። ለአይሁዳውያን ተመድቦ የነበረው የአምላክ የሞገስ “ሳምንት” በ36 እዘአ ሲያልቅ ጴጥሮስ የኢጣልያ ጦር ሠራዊት መኮንን የሆነውን ቆርኔሌዎስን ወደ መኖሪያው ወደ ቂሣሪያ ሄዶ እንዲያነጋግረው ይሖዋ መራው። ጴጥሮስ አይሁዳዊ ላልሆነው ለዚህ ሰውና ለቤተሰቡ ሲሰብክላቸው በእነርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ በመውረድ የመንግሥቲቱ ወራሾች እንዲሆኑ ቀባቸው። የመጀመሪያዎቹ ወደ ክርስትና የተለወጡ ያልተገረዙ አሕዛብ በመሆን ተጠመቁ። — ሥራ 10:1–48
14 ከዚያ ቆየት ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኞቹ በጲስድያ በምትገኘው አንጾኪያ ከሚኖሩት አይሁዶች ረብሻ ሲፈጠርባቸው ጳውሎስ ለእነዚህ አይሁዶች እንዲህ አለ:- “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፣ እነሆ፣ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። እንዲሁ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ።” (ሥራ 13:46, 47) ጳውሎስ በሌላ ጊዜ በአንድ ምሳሌ ላይ እንደገለጸው የማያምኑት አይሁዶች ከአንድ የወይራ ዛፍ ላይ ተቆርጠው እንደተጣሉ ተፈጥሯዊ ቅርንጫፎች ነበሩ። የመንግሥቲቱ ወራሾች ቁጥር ሙሉ በሙሉ በአይሁዳውያን ይሞላ ነበር። ይሁን እንጂ በእነርሱ ቦታ ‘ከአሕዛብ የሆኑ ሰዎች’ እንደ በረሀ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች በመሆን ተጨምረዋል፤ በዚህም ምክንያት “ሁሉም [መንፈሳዊ] እስራኤል” የመንግሥቲቱ አባሎች ቁጥር ተሟልቶ “ይድናል።” — ሮሜ 11:13–26፤ ገላትያ 6:16
‘በመከራ’ ጊዜ ፍጹም አቋም መያዝ
15, 16. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘መከራን’ በተመለከተ ምን አለ? ምንስ አደረገ? ይህስ ለእኛ ምን ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል? (ለ) ከመንግሥታት ወይም ከቤተሰብ ለሚመጣብን ተቃውሞ ሊኖረን የሚገባው አቋም ምን መሆን ይኖርበታል? ምን ውጤት እንደምናገኝስ ቃል ተገብቶልናል?
15 ያ የታመነ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሐዋርያው ጳውሎስ ተጨማሪ ስደቶች ቢደርሱበትም እንኳን ደቀ መዛሙርትን ለማበረታታትና ጉባኤውን በይበልጥ ለማደራጀት ወደ አንጾኪያ ተመለሰ። የሚከተለውን ቃል የተናገረው በዚህ ጊዜ ነበር:-
“ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል።” — ሥራ 14:21–23
16 ጳውሎስ ድርሻውን መከራና ፈተና መቀበሉን ቀጠለ፤ ይሁን እንጂ ንጹሕ አቋምን አጥብቆ በመያዝ በኩል ጥሩ ምሳሌ ሆኗል። በዘመናችን ከባድ የእምነት ተጋድሎ ለማድረግ ለተገደዱት ለብዙዎች ጥሩ አብነት ትቷል። ከእነዚህም አንዳንዶቹ መደብደብን፣ መታሰርንና በሕይወት ላይ የመጣን አደጋ እንኳ ሳይቀር መቋቋም አስፈልጓቸዋል። ከአምባገነናዊ መንግሥታት ወይም ደግሞ በጣም ከሚወደዱ ዘመዶች ተቃውሞ መጥቶባቸዋል። አንዳንዶች “ይህን የመንግሥት ምሥራች” በመቀበላቸውና በመታዘዛቸው ቤተሰቦቻቸው በይፋ ክደዋቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በሚቀጥሉት የኢየሱስ ቃላት ተጽናንተዋል:- “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እህቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” (ማርቆስ 10:29, 30) ከይሖዋ አምላክና ከልጁ ጋር ባላቸው የቅርብ ዝምድናና ከይሖዋ ምድር አቀፍ ቤተሰብ ጋር ባገኙት አስደሳች ኅብረት በእርግጥም “መቶ እጥፍ” አጭደዋል።
17. (ሀ) የጥንት ክርስቲያኖች ምን አሳች ፈተናዎችን ጭምር መቋቋም አስፈልጓቸው ነበር? (ለ) ጳውሎስ ምን ግሩም የሆነ ምሳሌና ምክር ሰጥቶናል?
17 ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኞቹ የዓለምን የብልግናና የፍቅረ ንዋይ ፈተናዎችንም መታገል ነበረባቸው። ልክ እንደኛው ያሉ ሰዎች ነበሩ። እንደነዚህ ያሉ አሳች ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ልክ እንደ ጳውሎስ “ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ደግሞ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” ማለት ይኖርብናል። በተጨማሪም እንደ ጳውሎስ እኛም ለጎረቤቶቻችን ስለ አምላክ መንግሥት መናገራችን ጥበቃ ሊሆንልን ይችላል። ይህን ቅዱስ አገልግሎት በሚመለከት ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ” ብሏል። — 1 ቆሮንቶስ 9:16, 17
‘ሙሉ በሙሉ ድልን መቀዳጀት’
18. ጳውሎስ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ምን ማበረታቻ ሰጥቷል? ለዚህስ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
18 ሐዋርያው ጳውሎስ ቅቡዓን ባልንጀሮቹ ለሆኑት ክርስቲያኖች የአምላክ “ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፣ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን” ብሎ ነግሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ ቀጥሎ የተናገረው ነገር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ክብራማ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት በዛሬው ጊዜ በመዘጋጀት ላይ ላሉት የ“ሌሎች በጎች” ክፍል ለሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች”ም ይሠራል። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) ጳውሎስ ሁሉንም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት ያበረታታል:-
“ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን? . . . በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8:17, 35–39፤ በተጨማሪም 2 ቆሮንቶስ 11:22–28 ተመልከት።)
በአምላክ ፍቅርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ‘መምጣት’ ላይ ይህን የመሰለ ትምክህት እያዳበርህ ነውን? ይገባሃል!
19. ጳውሎስ ሞትን ሊያመጣ ስለሚችል ስለ ሌላ አደጋ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጠ?
19 ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ አቋምህን በማጠናከር ልትዋጋው የሚያስፈልግህ ሌላው ነገር የሐሰት ትምህርት ነው። ጳውሎስ ስለዚህም ጉዳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) የሐሰት አስተማሪዎች የሚመጡት ከየት ነው? ራሳችንንስ ከእነርሱ ልንጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?