የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • uw ምዕ. 8 ገጽ 62-69
  • ‘ክፉ መንፈሣውያን ኃይሎችን መታገል’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ክፉ መንፈሣውያን ኃይሎችን መታገል’
  • እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በሰማያዊ ስፍራ ያሉ የዓለም ገዥዎች
  • ክፉው የሚጠቀምባቸው ረቂቅ መሣሪያዎች
  • አሸናፊ ለመሆን የሚረዳን ትጥቅ
  • ‘ከርኩሳን መናፍስታዊ ኃይሎች ጋር መጋደል’
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • አጋንንትን እንዴት መቋቋም እንችላለን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ‘በጌታ ጠንክሩ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ዲያብሎስንና መሠሪ ዘዴዎቹን ተቃወም
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
ለተጨማሪ መረጃ
እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት
uw ምዕ. 8 ገጽ 62-69

ምዕራፍ 8

‘ክፉ መንፈሣውያን ኃይሎችን መታገል’

1. ክፉ መናፍስት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እኛን የሚያሳስበው ለምንድን ነው?

ሥጋዊ አስተሳሰብ ብቻ ያላቸው ሰዎች ክፉ መናፍስት አሉ በሚለው ሐሳብ ያሾፉ ይሆናል። ሆኖም ነገሩ የሚሳቅበት አይደለም። ቢያምኑትም ባያምኑትም የአጋንንት እንቅስቃሴዎች በእያንዳንዱ ሰው ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ። ይሖዋን የሚያመልኩትም ቢሆኑ ከዚህ ተጽእኖ ነፃ አይደሉም። እንዲያውም ዋነኞቹ የአጋንንት ዒላማ እነርሱ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ ግጭት እንዳለ ሲያስጠነቅቀን “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከስልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሣውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” ብሏል። (ኤፌሶን 6:12) በዘመናችን ከአጋንንት የሚመጣው ግፊት ከመቼውም ይበልጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ምክንያቱም ሰይጣን ከሰማይ ተጥሏል፤ አጭር ጊዜ እንደቀረውም ስለሚያውቅ በጣም ተናዷል። — ራእይ 12:12

2. ከሰው የበለጠ ኃይል ካላቸው መንፈሣውያን ፍጡሮች ጋር ታግለን እንዴት ማሸነፍ እንችላለን?

2 ታዲያ ከሰው ከሚበልጡ መንፈሣውያን ኃይሎች ጋር ታግለን እንዴት ማሸነፍ እንችላለን? በይሖዋ እርዳታ ላይ ሙሉ ትምክህት በመጣል ብቻ ነው። እርሱ የሚለንን መስማትና ቃሉን መታዘዝ አለብን። እንደዚህ በማድረግ በሰይጣናዊ ቁጥጥር ሥር ያሉት ሰዎች ከሚደርስባቸው የአካል፣ የሥነ ምግባር፣ የስሜትና የአእምሮ ጉዳት እንድናለን። — ኤፌሶን 6:11፤ ያዕቆብ 4:7

በሰማያዊ ስፍራ ያሉ የዓለም ገዥዎች

3. ሰይጣን ምንንና ማንን ክፉኛ ይቃወማል?

3 ይሖዋ ነገሮችን ከሰማይ ሆኖ ሲመለከታቸው ምን እንደሚመስሉ ሕያው በሆነ መንገድ ገልጾልናል። ለሐዋርያው ዮሐንስ በላከው ራእይ ላይ ሰይጣን እንደ “ታላቅ ቀይ ዘንዶ” ሆኖ ተገልጿል። ዘንዶውም ቢችል መሲሐዊቷ መንግሥስት በ1914 በሰማይ ስትቋቋም ወዲያው ሊውጣት ተዘጋጅቶ ነበር። ሰይጣን ይህ ሳይሆንለት ሲቀር በምድር የሚገኙትን የመንግሥቲቱን ተወካዮች ወይም የአምላክን “ሴት” ሁለተኛ ደረጃ ዘሮች ለማጥፋት ኃይለኛ የተቃውሞ ማዕበል አምጥቷል። — ራእይ 12:3, 4, 13, 17

4. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የሰብዓዊ መንግሥታት ምንጭ ማን መሆኑን ገልጾ ያስጠነቅቀናል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የፖለቲካ ገዥዎች ወደ ምን እየተሰበሰቡ ነው? በማንስ ሰብሳቢነት?

4 ሰብዓዊ መንግሥታት የኃይላቸውና የሥልጣናቸው ምንጭ ምን እንደሆነ ለዮሐንስ በተላከው በዚህ ራእይ ላይ ገሃድ ወጥቷል። ዮሐንስ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉትን “በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ስልጣን” የተሰጠውን ባለ ብዙ አባላት አውሬ ተመልክቷል። አውሬው አንድን መንግሥት ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ያለውን ጠቅላላ የፖለቲካ ሥርዓት የሚያመለክት ነው። ዮሐንስ “ዘንዶው [ሰይጣን ዲያብሎስ] ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን” ለአውሬው እንደሰጠው ተገልጾለታል። (ራእይ 13:1, 2, 7፤ ከሉቃስ 4:5, 6 ጋር አወዳድር) ፖለቲካዊ መሪዎች ምንም ዓይነት ሃይማኖት አለን ቢሉም የአውሬው ክፍል ከሆኑት ብሔራት መካከል አንዳቸውም ለይሖዋ ሉዓላዊነትና እርሱ ለሾመው ንጉሥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ራሳቸውን አላስገዙም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም የራሳቸውን ሉዓላዊነት እንደያዙ ለመኖር ይጥራሉ። የራእይ መጽሐፍ እንደሚያሳየው ከአጋንንት የሚወጡ መናፍስት እነዚህን መንግሥታት “ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ላይ በሐርማጌዶን ወደሚደረገው ጦርነት” እየሰበሰቧቸው ነው። (ራእይ 16:13, 14, 16) በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው “የዓለም ገዥዎች” ሰዎች ሳይሆኑ “በሰማያዊ ስፍራ ያሉት ክፉ መንፈሣውያን ሠራዊት” ናቸው። (ኤፌሶን 6:12) እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ሆነው የሚቆሙ በሙሉ የዚህን ሙሉ ትርጉም ማስተዋል ያስፈልጋቸዋል።

5. የሰይጣን ሥርዓት ደጋፊዎች ሆነን እንዳንገኝ መጠንቀቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

5 ሰብዓዊውን ቤተሰብ የሚገነጣጥሉት ግጭቶች በየዕለቱ ሕይወታችንን ይነካሉ። ሰዎች የራሳቸውን ብሔር፣ ጎሣ፣ ቋንቋቸውን የሚናገር ቡድን ወይም ማኅበራዊ መደባቸውን እንደሚደግፉ በቃላቸው ወይም በሌላ መንገድ መግለጻቸው የተለመደ ነገር ነው። ራሳቸው ክፍል የሆኑበት ወገን በውጊያው ላይ ባይሆንም ከተዋጊዎቹ የአንዱ ወገን ደጋፊ የሌላውም ተቃዋሚ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ እሮሮአቸው ምንም ዓይነት ይሁን፣ የሚደግፉትም ዓላማ ወይም ሰው ምንም ይሁን ምን በእርግጥ እየደገፉት ያለው ማንን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደተያዘ እናውቃለን” ሲል ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) እንግዲያው አንድ ሰው ሌሎችን ተከትሎ በስህተት ጎዳና እንዳይሄድ ራሱን እንዴት ሊጠብቅ ይችላል? ለአምላክ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ በመስጠትና በልዩ ልዩ የዓለም ወገኖች መካከል በሚደረገው ውጊያ ፍጹም ገለልተኛ በመሆን ብቻ ነው። — ዮሐንስ 17:15, 16

ክፉው የሚጠቀምባቸው ረቂቅ መሣሪያዎች

6. ሰይጣን ሰዎችን ከእውነተኛ አምልኮ ለማስወጣት የተጠቀመባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

6 ባለፉት የታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰይጣን ግለሰቦችን ከእውነተኛ አምልኮ ለማስወጣት ስድብንና አካላዊ ስቃይን እንደ መሣሪያ አድርጎ ሲጠቀምባቸው ቆይቷል። ነገር ግን ከዚያ ይበልጥ በረቀቁ ዘዴዎች ይኸውም መሰሪ በሆኑ ድርጊቶችና አሳሳች መልክ ባላቸው መሣሪያዎችም ተጠቅሟል።

7. በሐሰተኛ ሃይማኖት ረገድ የሰይጣን ብልሃተኝነት የሚታየው እንዴት ነው?

7 ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት አማካይነት አብዛኞቹን የሰው ዘሮች በዘዴ ጨለማ ውስጥ አጉሯቸዋል። ሰዎቹ የአምልኮት ፍላጎት ካላቸውም አምላክን በማገልገል ላይ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል። ለእውነት ልባዊ ፍቅር ስለሌላቸው ምስጢራዊና ስሜታዊ የሃይማኖት ሥነ ስርዓቶችና ቅዳሴዎች ወይም ተአምራት በጣም ይማርኳቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10) ይሁን እንጂ በእውነተኛ አምልኮ ውስጥ ተሳትፎ ከነበራቸው መካከልም ቢሆን “አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንት ትምህርት እያደመጡ” እንደሚሳሳቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

8. ሰይጣን ይሖዋን ሲያመልኩ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦችን ሳይቀር አታልሎ ወደ ሐሰት ሃይማኖት ያስገባው እንዴት ነው?

8 ሰይጣን አንድን ሰው ቀስ ብሎ በድክመቱ ይገባበታል። ሰውየው አሁንም የሰው ፍርሃት አለበትን? እንግዲያው ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ በሐሰት አምልኮ ሥርዓቶች እንዲሳተፍ ሲጫኑት እሺ ይላቸዋል። ግለሰቡ ኩራት አለበትን? ይህ ከሆነ ምክር ሲሰጠው ወይም ሐሳቡ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር ስሜቱ ይጐዳል። (ምሳሌ 29:25፤ 15:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:3, 4) በመስክ አገልግሎት የሚሳተፈው በፍቅር ተገፋፍቶ ካልሆነስ? አስተሳሰቡን አስተካክሎ ከክርስቶስ አስተሳሰብ ጋር በማስማማት ፈንታ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና “በጎ መሥራት” ብቻ በቂ ነው እያሉ አንዳንዶች ወደሚሰጡት ‘ጆሮን ወደሚያሳክክ ትምህርት’ ሊያዘነብል ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 4:3) ሰውየው አምላክ በቃሉና በድርጅቱ በኩል በሰጠው መመሪያ መሠረት ይሖዋን አያምልክ እንጂ ወደ ሌላ ሃይማኖት ቢገባ ወይም የራሱን ሃይማኖት ቢፈጥር ሰይጣን ግድ የለውም።

9. ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት በፆታ ግንኙነት የሚያስተው እንዴት ነው?

9 ከዚህም በላይ ሰይጣን ሰዎች የተፈጥሮ ፍላጎቶችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዲያረኩ በተንኮል ያስታቸዋል። ለምሳሌ ሩካቤ ሥጋን ለዚህ ዓላማ ተጠቅሞበታል። በዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር አቋም ባለመቀበል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚደረገው የፆታ ግንኙነት ትክክል ነው፣ ወይም ለአካለ መጠን እንደደረስን የምናሳይበት መንገድ ነው ይላሉ። ትዳር ያላቸው ሰዎች ሁኔታስ እንዴት ነው? ዓለማውያን በትዳራቸው ችግር ካጋጠማቸው ይፋቱና ሌላ ያገባሉ ወይም እንዲሁ ብቻ ይለያዩና ከሌላ ጋር ይኖራሉ። ይህንን ዓይነት አኗኗር ስንመለከት አንድ ነገር እንደቀረብን ወይም የክርስትና መንገድ ከሚገባው በላይ ጥብቅ እንደሆነ ይሰማናልን? ሰይጣን በረቀቀ ዘዴ በመቅረብ ይሖዋ አንድ ጥሩ ነገር እንዳስቀረብን አድርገን እንድናስብ ይጥራል። ድርጊቱ በራሳችንና በሌሎች ላይ ወይም ከይሖዋና ከልጁ ጋር ባለን ዝምድና ላይ የሚያመጣው የረጅም ጊዜ መዘዝ ሳይሆን የዚያች ሰዓት ደስታ ብቻ እንዲታየን ይገፋፋናል። — ገላትያ 6:7, 8፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

10. ሰይጣን አካላዊ ጉዳት ለሚያመጣ የዓመጽ ድርጊት ያለንን አመለካከት በምን አማካይነት ለመጠምዘዝ ይሞክራል?

10 ሌላው የተፈጥሮ ፍላጎት የሚያዝናና ጨዋታ ማየት ነው። ነገሩ ለዛ ያለው ከሆነ አካላችንን፣ አእምሮአችንንና ስሜታችንን ሊያነቃቃልን ይችላል። ነገር ግን ሰይጣን የመዝናናትን ጊዜ አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ለማራቅ በዘዴ ሊጠቀምበት ቢሞክርስ? ለምሳሌ ይሖዋ በሰው ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረስ የሚወዱትን እንደሚጠላ እናውቃለን። (መዝሙር 11:5) ነገር ግን በሲኒማ፣ በቴሌቪዥን ወይም በቲያትር ይህ ዓይነቱ ድርጊት ቢቀርብልን ቁጭ ብለን ሁሉንም እንከታተለዋለንን? ወይም ነገሩ በስፖርት ስም ቢቀርብልን እንቀበለዋለንን? ደግሞስ እየጮኽን ተጫዋቾቹን እናበረታታለንን? — ከዘፍጥረት 6:13 ጋር አወዳድር።

11. ስለ መናፍስትነት እውነቱን የሚያውቅ ሰውም ቢሆን ካልተጠነቀቀ በዚህ ወጥመድ ሊያዝ የሚችለው በምን መንገዶች ነው?

11 በማንኛውም ዓይነት መናፍስትነት ተካፋይ የሚሆኑ ይኸውም የሚያሟርቱ፣ የሚጠነቍሉ፣ ወይም ከሙታን ጋር ለመገናኘት የሚሞክሩ ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ መሆናቸውንም እናውቃለን። ጠንቋዮችን ለመጠየቅ ሐሳቡም እንኳ ወደ አእምሮአችን አይመጣም። ወደ ቤታችንም መጥተው አጋንንታዊ ሥራቸውን እንዲሠሩ አንፈቅድላቸውም። ይሁን እንጂ በቴሌቪዥን ቢታዩ እነርሱ የሚናገሩትን እናዳምጣለንን? ወይም በተመስጦ እንከታተላቸዋለንን? ከሕመም ለመዳን የጠንቋይ መድኃኒት ባንቀበልም ልጅ ሲወለድልን ከክፉ ይጠብቀዋል ብለን በማሰብ እጁ ላይ ክር እናስራለንን? ወይም መጽሐፍ ቅዱስ በድግምት ሰውን ማፍዘዝን እንደሚያወግዝ እያወቅን አንድ ድግምተኛ ወይም ሒፕኖቲስት አእምሮአችንን ለትንሽ ጊዜም ቢሆን እንዲቆጣጠር እንፈቅድለታለንን? — ዘዳግም 18:10–12፤ ገላትያ 5:19–21

12. (ሀ) ሙዚቃ ስሕተት መሆናቸውን የምናውቃቸውን ነገሮች ወደ አእምሮአችን ለማስገባት ሰይጣን የሚጠቀምበት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሰው ይሖዋ የማይቀበለው ዓይነት አኗኗር የሚከተሉትን ሰዎች እንደሚያደንቅ በአለባበሱ፣ በአበጣጠሩ ወይም በአነጋገሩ እንዴት ሊያሳይ ይችላል? (ሐ) ስውር የሆኑ የሰይጣን መሣሪያዎች እንዳይጥሉን በእኛ በኩል ምን ማድረግ ይፈለግብናል?

12 ‘የዝሙት ወሬ ወይም ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ተገቢ ላልሆነ ዓላማ ከአፋችን እንዳይወጣ’ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡትን ትእዛዝ አንብበናል። (ኤፌሶን 5:3–5) ነገር ግን አንድ ደስ የሚል ዘፈን ወይም የሚነሽጥ ውዝዋዜ ወይም ቀስቃሽ ሙዚቃ ይህንን መልእክት እንዲያስተላልፍ ሆኖ በብልሃት ተቀነባብሮ ቢቀርብስ? ሳይጋቡ የፆታ ግንኙነት ማድረግን፣ ለደስታ ዕፅ መውሰድን ወይም የመሳሰሉትን የሚያበረታቱ ዜማዎችን ሳይታወቀን እናንጐራጉር ይሆን? ወይም እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉትን ሰዎች አኗኗር መከተል እንደሌለብን ብናውቅም አለባበሳቸውን፣ የፀጉር አበጣጠራቸውን ወይም አነጋገራቸውን በመኮረጅ ከእነርሱ ጋር ለመመደብ እንደምንፈልግ እናሳያለንን? ሰይጣን እንዴት ብልሃተኛ ነው! የሰው ልጆች ብልሹ በሆነው አስተሳሰቡ እንዲመሩ ለማታለል እንዴት በረቀቁ መንገዶች ይጠቀማል! (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) በሰይጣን ስውር መሣሪያዎች ላለመያዝ ከፈለግን ዓለምን እየተከተልን አብረን እንዳንጓዝ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ‘የዚህ ጨለማ ዓለም ገዥዎች’ እነማን እንደሆኑ ዘወትር ማስታወስና የእነርሱን ግፊት በቁርጠኝነት መታገል ያስፈልገናል። — ኤፌሶን 6:12፤ 1 ጴጥሮስ 5:8

አሸናፊ ለመሆን የሚረዳን ትጥቅ

13. አለፍጽምና እያለብን ሰይጣን የሚገዛውን ዓለም ለማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ለሐዋርያቱ “አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎአቸዋል። ስለዚህ እነርሱም አሸናፊ ለመሆን ይችላሉ ማለቱ ነበር። በኋላም ከ60 ዓመት በላይ ቆይቶ ሐዋርያው ዮሐንስ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?” ሲል ጽፎአል። (ዮሐንስ 16:33፤ 1 ዮሐንስ 5:5) እንደዚህ ያለውን እምነት የምናሳየው የኢየሱስን ትእዛዞች በማክበርና እርሱ እንዳደረገው በአምላክ ቃል ላይ በመደገፍ ነው። ሌላስ ምን ያስፈልጋል? ክርስቶስ ራስ ወደሆነለት ጉባኤ መጠጋት አለብን። ኃጢአት ብንሠራ ከልብ ንስሐ መግባትና በኢየሱስ መስዋዕት መሠረት አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግልን መጠየቅ አለብን። አለፍጽምናም ቢኖረን እንደዚሁ በማድረግ አሸናፊ ለመሆን እንችላለን።

14. (ሀ) ኤፌሶን 6:13–18ን አንብብ። (ለ) በጥያቄዎቹና በጥቅሶቹ መሠረት እያንዳንዱ መሣሪያ የሚሰጠውን ጥቅም ግለጽ።

14 ለማሸነፍ ከፈለግን ‘ከአምላክ የሚገኘውን የተሟላ የጦር ትጥቅ’ መያዝ ይኖርብናል። አንዱንም መሣሪያ መተው የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ በኤፌሶን 6:13–18 ላይ ስለዚያ ትጥቅ የተሰጠውን ዝርዝር መግለጫ አንብብ። ከዚያም ቀጥሎ ያሉትን ጥያቄዎች በመመለስ እያንዳንዱ መሣሪያ ከሚሰጠው ጥበቃ እንዴት ልትጠቀም እንደምትችል መርምር:-

“ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ”

እውነትን ብናውቅም ዘወትር ማጥናት፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ማሰላሰልና በስብሰባ መገኘት የሚጠብቀን እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 3:1፤ 4:8, 9፤ 1 ቆሮንቶስ 10:12, 13፤ 2 ቆሮንቶስ 13:5፤ 1 ጴጥሮስ 1:13 ኪንግደም ኢንተርሊንያር)

“የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ ”

በማን የአቋም ደረጃ መሠረት ጽድቅ የሆነውን ማለቱ ነው? (ራእይ 15:3)

አንድ ሰው ለአምላክ መንገዶች ፍቅርን ሳይኮተኩት ቀርቶ የይሖዋን ትእዛዞች ቢጥስ አድራጎቱ ለትልቅ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያጋልጠው እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ። (1 ሳሙኤል 15:22, 23ንና ዘዳግም 7:3, 4ን ተመልከት)

“በሰላም ወንጌል በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ ”

አምላክ ስለ ሰላም ያለውን ዝግጅት ለሌሎች እንድንነግር እግሮቻችን ሁልጊዜ ወደ ሰዎች የሚወስዱን ከሆነ ከአደጋ የምንጠበቀው እንዴት ነው? (ሮሜ 10:15፤ መዝሙር 73:2, 3፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:13)

“የእምነትን [ትልቅ ] ጋሻ አንሱ ”

መሠረቱ ጥብቅ የሆነ እምነት ካለን ጥርጥር እንዲያድርብን ወይም እንድንፈራ ሙከራ ቢደረግ ምን እናደርጋለን? (ከ2 ጢሞቴዎስ 1:12ና ከ2 ነገሥት 6:15–17 ጋር አወዳድር።)

“የመዳንንም ራስ ቁር ” ጫኑ

የመዳን ተስፋ አንድን ሰው ከልክ ያለፈ የሥጋዊ ነገሮች ሐሳብ ወጥመድ እንዳይሆንበት የሚጠብቀው እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 6:7–10, 19)

“የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ ”

በራሳችን ወይም በሌሎች መንፈሳዊነት ላይ የሚቃጡትን ክፉ ሙከራዎች ለመመከት መታመኛችን ሁልጊዜ ምን መሆን አለበት? (መዝሙር 119:98፤ ምሳሌ 3:5, 6፤ ከማቴዎስ 4:3, 4 ጋር አወዳድር።)

ከዚህ ጋር በመስማማት በኤፌሶን 6:18, 19 ላይ በመንፈሳዊ ውጊያ ድል ለማድረግ ያስፈልጋል ተብሎ የተጠቀሰው ሌላው ነገር ምንድን ነው? ይህንንስ ምን ያህል ጊዜ ማድረግ አለብን? ስለ እነማንስ?

15. (ሀ) ሁላችንም የተሰለፍንበት መንፈሳዊ ውጊያ በተናጠል የምናካሄደው ነውን? (ለ) በውጊያው የማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ክርስቲያን ወታደሮች እንደመሆናችን መጠን መንፈሳዊ ውጊያ የሚያካሂድ የአንድ ትልቅ ሠራዊት አባሎች ነን። ዘወትር ንቁ ከሆንና የተሟላውን የአምላክ የጦር ትጥቅ በደንብ ከተጠቀምንበት በጦርነቱ ከሚወድቁት ተሸናፊዎች መካከል አንሆንም። ከዚህ ይልቅ አብረውን አምላክን ለሚያገለግሉት የብርታት ምንጭ እንሆንላቸዋለን። በውጊያው የማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ይኸውም ሰይጣን በጣም የሚቃወመውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማስፋፋት ዝግጁና ቅን ፍላጎት ያለን እንሆናለን።

የክለሳ ውይይት

● ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ በዓለማውያን ወገኖች መካከል በሚደረግ ግጭት ፍጹም ገለልተኛ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

● ሰይጣን በክርስቲያኖች ላይ መንፈሳዊ ውድቀት ለማምጣት የሚጠቀምባቸው አንዳንዶቹ ረቂቅ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

● ከአምላክ የሚገኘው የጦር ትጥቅ በዚህ መንፈሳዊ ውጊያ ለማሸነፍ ወሳኝነት ባላቸው መንገዶች የሚጠብቀን እንዴት ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ