የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • pe ምዕ. 7 ገጽ 69-75
  • የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?
  • በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዝግመተ ለውጥ ወይስ ፍጥረት
  • አምላክ ሰውን እንዴት ፈጠረው
  • አምላክ ሰውን እዚህ ምድር ላይ ያስቀመጠበት ምክንያት
  • የምናረጅበትና የምንሞትበት ምክንያት
  • የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ምድር ገነት እንደምትሆን የሚያሳይ ማስረጃ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፈጠረ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ከመቃብር ወጥቶ እንደገና መኖር ይቻላል!
    ንቁ!—2008
ለተጨማሪ መረጃ
በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
pe ምዕ. 7 ገጽ 69-75

ምዕራፍ 7

የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?

1. ስለ ሁኔታዎች የሚያስቡ ሰዎች ምን ብለው ደምድመዋል?

ሰዎች በምድር ላይ የመኖሩ ትርጉም ምንድን ነው በማለት ለብዙ ዘመናት ሲጠይቁ ቆይተዋል። በከዋክብት የተሞላውን እጅግ ሰፊ ሰማይ ተመልክተዋል። ፀሐይ ስትጠልቅ የምታሳየውን ኅብራዊ መልክና በገጠር አካባቢ ያለውን ውበት አድንቀዋል። በነገሩ ላይ የሚያስቡ ሰዎች ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች በስተጀርባ አንድ ትልቅ ዓላማ መኖር አለበት ብለው አስበዋል። ይሁን እንጂ በዚያ ዓላማ ውስጥ የእነርሱ ቦታ ምን ስለ መሆኑ ብዙ ጊዜ በመገረም ይጠይቃሉ።—መዝሙር 8:3, 4

2. ሰዎች ምን ጥያቄዎችን ጠይቀዋል?

2 አብዛኞቹ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ:- የተፈጠርነው ለአጭር ጊዜ ለመኖር፣ በሕይወታችንም የቻልነውን ያህል እንድንደሰትና በኋላ እንድንሞት ነውን? በእውነቱ ወዴት እየተጓዝን ነው? ከአጭሩ የመወለድ፣ የመኖርና የመሞት ዑደት በስተቀር ልንጠብቀው የምንችል ሌላ ነገር አለን? (ኢዮብ 14:1, 2) ይህንን ጉዳይ ለማስተዋል የሚረዳን እዚህ ዓለም ላይ እንዴት ተገኘን ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ነው።

ዝግመተ ለውጥ ወይስ ፍጥረት

3. የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ምን ይላል?

3 የምናየው ነገር ሁሉ እንዲሁ በራሱ የመጣ ነው፤ በአጋጣሚ የተገኘ ነው፤ እያሉ ማስተማሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የተለመደ ነገር ነው። ሕይወት በጣም ዝቅተኛ ከሆኑ ሕያዋን ነገሮች ተነሥቶ በሚልዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ እያዘገመ በመለወጥ ወይም በመሻሻል በመጨረሻው ሰው ሊገኝ ቻለ እየተባለ ይነገራል። በብዙ የምድር ክፍሎች ይህ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እንደ እውነት ተደርጎ ትምህርት ይሰጥበታል። ይሁን እንጂ በሚልዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከነበረ ጦጣ ከመሰለ አውሬ ተሻሽለን መጣን የሚለው አባባል እውነት ነውን? ይህ ታላቅ አጽናፈ ዓለም እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ ነውን?

4. “አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” የሚለውን ቃል ለምን ልናምንበት እንችላለን?

4 መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:1) በቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን የያዙት ሰማያትና ምድራችን መጀመሪያ ያላቸው መሆኑን የሳይንስ ማስረጃዎች ይስማማሉ። እነዚህ ነገሮች ተፈጥረዋል። የከዋክብትና የፕላኔቶች እንቅስቃሴ የማይለዋወጥ በመሆኑ ከአያሌ ዓመታት በፊት በየትኛው ቦታ ላይ እንደሚገኙ ያለ አንዳች መሳሳት መናገር ተችሏል። ከዋክብትና ፕላኔቶች የሂሳብን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እየጠበቁ በጠፈር ውስጥ ይበርራሉ። በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ በሂሳብ ፕሮፌሰር የሆኑት ፒ ዲራክ ሳይንቲፊክ አሜሪካን በተባለ መጽሔት ላይ እንዲህ ብለዋል:- “አምላክ እጅግ የላቀ የሂሳብ አዋቂ ነው በማለት ሁኔታውን ምናልባት መግለጽ ይቻላል። አጽናፈ ዓለምን በጣም በተራቀቀ የሂሳብ ስሌት ተጠቅሞ ሠርቶታል።”

5. ሰብዓዊው አካላችን የዝግመተ ለውጥ ውጤት ከመሆን ይልቅ በመፈጠር የተገኘ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 100:3) ሰብዓዊ አካላችን እንደዚህ ያለ አስደናቂ ንድፍ ስለሚያንጸባርቅ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ለአምላክ እንዲህ ለማለት ተገፋፍቷል:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ . . . እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ . . . አጥንቶቼ ከአንተ አልተሠወሩም። ያለተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ . . . አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።” (መዝሙር 139:14–16) አንድ ሕፃን በእናቱ ውስጥ በሚያስደንቅ መንገድ ያድጋል። የኒውስዊክ መጽሔት ስለዚሁ ሲናገር:- “ባጭር አገላለጽ ነገሩ ተአምር ነው” ብሏል። ከዚያም ሐሳቡን በመጨመር “ጽንሱ የሚጀምርበትን ወሳኝ ጊዜ በየትኛውም ዘዴ ተጠቅሞ ለይቶ ማወቅ አይቻልም። ከዚያ በኋላ ለዚያ ሰብዓዊ ጽንስ ልዩ ልዩ የሰውነት ክፍሎችና አእላፋት የነርቭ አውታሮች የሚፈጥሩለት አስደናቂ ኃይሎች ምን እንደሆኑ የትኛውም ሳይንቲስት ለመናገር አይችልም” ብሏል።

6. ከዝግመተ ለውጥ ይልቅ በፍጥረት ማመኑ ምክንያታዊ እንደሆነ የሚሰማን ለምንድን ነው?

6 እስቲ ስለ ታላቁ አጽናፈ ዓለማችንና አስደናቂ አሠራርና ንድፍ ስላለው ስለ ራሳችን አካል እናስብ። ነገሩን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ብናስብበት እነዚህ ነገሮች ቀስ እያሉ በመሻሻል ወይም እንዲሁ በራሳቸው እንዳልተገኙ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። ንድፍ አውጥቶ የሚሠራቸው ወይም ፈጣሪ ያስፈልጋቸዋል። በዙሪያችን የምናያቸውንም ሌሎች ነገሮች እንውሰድ። እቤትህ ውስጥ ስትቀመጥ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- የራሴ ጠረጴዛ፣ መብራት፣ አልጋ፣ ወንበር፣ የቤቱ ግድግዳ ወይም ቤቱ ራሱ ቀስ እያሉ በመሻሻል የተገኙ ናቸውን? ወይስ ሠሪ ያስፈልጋቸው ነበር? አእምሮ ባላቸው ሰዎች መሠራት እንዳስፈለጋቸው የተረጋገጠ ነው። ታዲያ ከዚያ ይልቅ በጣም ውስብስብ የሆነው አጽናፈ ዓለማችንና እኛ ራሳችን ሠሪ አላስፈለገንም ለማለት የሚቻለው በምን መንገድ ነው? እዚህ ምድር ላይ ያስቀመጠን አምላክ ከሆነ ደግሞ እንደዚያ ሲያደርግ ምክንያት እንዳለው የተረጋገጠ ነው።

7. (ሀ) ኢየሱስ በፍጥረት እንደሚያምን እንዴት አሳየ? (ለ) አዳም በእርግጥ የነበረ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላው ማስረጃ ምንድን ነው?

7 ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ስለ መጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ሲናገር:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ አለም፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሏል። (ማቴዎስ 19:4, 5) እዚህ ላይ ኢየሱስ የጠቀሰው ስለ አዳምና ሔዋን አፈጣጠር ከሚናገረው ከዘፍጥረት 1:27 እና 2:24 ነው። በዚህ መንገድ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውነት መሆኑን ማመልከቱ ነበር። (ዮሐንስ 17:17) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ” መሆኑን ይናገራል። (ይሁዳ 14) አዳም በእርግጥ የነበረ ሰው ባይሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መንገድ ማንነቱን ለይቶ ባልተናገረ ነበር።—ሉቃስ 3:37, 38

8. ስለ ሰው አመጣጥ የትኛውን አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም?

8 አንዳንድ ሰዎች አምላክ ሰውን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ነው ይላሉ። አምላክ ሰውን ቀስ እያለ እየተሻሻለ እንዲሄድ ካደረገው በኋላ አንድ ነጥብ ላይ ሲደርስ በውስጡ ነፍስ አኖረለት ይላሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ሐሳብ በየትኛውም ቦታ ላይ አይገኝም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ዕፀዋትና እንስሳት “እንደ ወገኑ” መፈጠራቸውን ይነግረናል። (ዘፍጥረት 1:11, 21, 24) አንዱ ዓይነት ተክል ወይም እንስሳ ከጊዜ በኋላ ተሻሽሎ ሌላ ዓይነት እንደማይሆን ማስረጃዎቹ ያሳዩናል። ሕይወት እንዴት መጣ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በመፈጠር በሚለው መጽሐፍ ላይ እኛ የዝግመተ ለውጥ ውጤት ያለመሆናችንን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል።

አምላክ ሰውን እንዴት ፈጠረው

9. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን አፈጣጠር እንዴት ይገልጸዋል? (ለ) አምላክ ወደ ሰውየው አፍንጫ “የሕይወትን እስትንፋስ” እፍ ባለ ጊዜ ምን ሆነ?

9 ሰው በምድር ላይ እንዲኖር አምላክ ከምድር ፈጠረው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም አምላክ ሰውን ፈጠረ መሬት ከምድር። በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 እትም) ሰው በአምላክ በቀጥታ የተፈጠረ መሆኑን ከዚህ ለመረዳት እንችላለን። ልዩ በሆነ የአፈጣጠር ሥራ አምላክ ሰውን የተሟላ ወይም ፍጹም አድርጎ ሠራው። አምላክ በሰውየው አፍንጫ ላይ “የሕይወትን እስትንፋስ” እፍ ባለ ጊዜ የሰውየው ሳንባዎች በአየር ተሞሉ። ይሁን እንጂ ከዚያም የበለጠ ነገር ተከናውኗል። አምላክ በዚህ መንገድ ለሰውየው አካል ሕይወት ሰጠው። ይህ የሕይወት ኃይል ለመቀጠል የሚችለው በመተንፈስ ነው።

10. የሰው ነፍስ ምንድን ነች? እንዴትስ ተፈጠረች?

10 ይሁን እንጂ አምላክ ለሰውየው ነፍስ ሰጠው ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ አለመናገሩን ልብ በለው። ከዚህ ይልቅ አምላክ ሰውየውን ማስተንፈስ ካስጀመረ በኋላ “ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ ” ይላል። ስለዚህ ዶክተር የሆነ ሰው ዶክተር ነው እንደሚባል ሁሉ ሰውየውም ነፍስ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ሰብዓዊው አካል የተሠራበት “የመሬት አፈር” ነፍስ አይደለም። ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “የሕይወቱ እስትንፋስ” ነፍስ ነው አይልም። ከዚህ ይልቅ እነዚህን ሁለት ነገሮች ማዋሐዱ ‘ሰውን ሕያው ነፍስ እንዳደረገው’ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።

11. የሰው ነፍስ ከሰውየው ተለይታ ልትኖር የምትችል እንደ ጥላ ያለች ነገር እንዳልሆነች የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች ያሳያሉ?

11 ሰብዓዊው ነፍስ ሰውየው ራሱ ስለ ሆነ ነፍስ በሰውነት ውስጥ የሚኖር ወይም ሰውነትን ለቆ ሊሄድ የሚችል እንደ ጥላ ያለ ነገር ሊሆን አይችልም። ቁም ነገሩን በቀላሉ ለመግለጽ ነፍስህ አንተ ራስህ እንደሆንክ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ በበኩረ ጽሑፉ ላይ “ነፍስህ ሥጋን ለመብላት ብትመኝ” በማለት ነፍስ ግዑዝ የሆነውን ምግብ ለመብላት ስለመፈለጓ ይናገራል። (ዘዳግም 12:20 አዓት) በተጨማሪም “በደል የሌላቸው የድሆች ነፍሳት ደም” በማለት ነፍሳት በደም ሥሮቻቸው ውስጥ የሚዘዋወር ደም እንዳላቸው ይናገራል።—ኤርምያስ 2:34 የ1879⁠ን እትም ተመልከት።

አምላክ ሰውን እዚህ ምድር ላይ ያስቀመጠበት ምክንያት

12. አምላክ በምድር ላይ ለሚኖሩት ሰዎች ዓላማው ምን ነበር?

12 አዳምና ሔዋን ከጊዜ በኋላ ሞተው በሌላ ስፍራ እንዲኖሩ የአምላክ ዓላማ አልነበረም። ምድርንና በእርሷ ላይ ያሉትን ሕያዋን ነገሮች በሙሉ እየተንከባከቡ እዚሁ እንዲኖሩ ታስቦ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15) አዳምና ሔዋን እንዲሁም በኋላ የሚወልዷቸው ልጆች በሙሉ አምላክ እንዲሠሯቸው የፈለጋቸውን ነገሮች እያደረጉ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ለመኖር ይችሉ ነበር።

13. (ሀ) እንዴት ደስተኞች መሆን እንችላለን? (ለ) ለሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም የሚሰጠው ምንድን ነው?

13 “እግዚአብሔርም ባረካቸው” መባሉን አስተውል። ስለ ምድራዊ ልጆቹ በእርግጥ አስቧል። ስለዚህ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት በመሆን የሚጠቅሟቸውን መመሪያዎች ሰጣቸው። እነዚያን መመሪያዎች መታዘዙ ደስታ ያስገኝላቸው ነበር። ኢየሱስ ይህንን ያውቅ ነበር። ስለዚህም “የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት” ደስተኞች ናቸው ብሎ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:28) ኢየሱስ የአምላክን ቃል ጠብቋል። “ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 8:29) እዚህ ምድር ላይ የተቀመጥንበትን ምክንያት የሚገልጽልን ቁልፍ ይህ ነው። እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበት ምክንያት ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖርን የተሟላ ኑሮና ደስታ ያለበት ሕይወት እንድናገኝ ነው። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን ማገልገላችን ለሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም ይሰጠዋል። እንደዚህም በማድረጋችን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ከሚሰለፉት መካከል እንሆናለን።—መዝሙር 37:11, 29

የምናረጅበትና የምንሞትበት ምክንያት

14. አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ በማፍረስ ምን አደረጉ?

14 ይሁንና ሁላችንም እናረጃለን ደግሞም እንሞታለን። ለምን? ቀደም ሲል ባጠናነው ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸው በአዳምና ሔዋን ዓመፅ ምክንያት ነው። አምላካቸውን መታዘዝ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳይ አንድ ፈተና ይሖዋ በፊታቸው አስቀምጦ ነበር። ለአዳም እንዲህ አለው:- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርስዋ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳምና ሔዋን ከዚች ዛፍ በመብላታቸው ለሰማያዊ አባታቸው ጀርባቸውን አዞሩበት ፤ አመራሩንም አንቀበልም አሉ። ትእዛዝ አፈረሱ፤ የራሳቸው ያልሆነውንም ወሰዱ። ድህነት ወይም ሌሎች መከራዎች ሳይደርሱባችው በገነቲቱ ምድር ውስጥ ለዘላለም በደስታ መኖር ይችሉ ነበር። አሁን ግን በራሳቸው ላይ የኃጢአትን ቅጣት አመጡ። ይህ ቅጣት አለፍጽምናና ሞት ነው።—ሮሜ 6:23

15. አዳም ላይ የነበረው ኃጢአት ወደ እኛ የመጣው እንዴት ነው?

15 ኃጢአት ከአዳም ወደ እኛ እንዴት እንደተላለፈ ታውቃለህን? አዳም ፍጽምናውን ካጣ በኋላ ይህንን አለፍጽምናና ሞት ለሁሉም ልጆቹ አስተላለፈ። (ኢዮብ 14:4፤ ሮሜ 5:12) ሁኔታውን ለመረዳት ያህል አንዲት ዳቦ ጋጋሪ መሀሉ ላይ በተሰረጎደ የብረት ምጣድ ዳቦ ስትጋግር ምን እንደሚፈጠር አስብ። በዚያ የብረት ምጣድ የተጋገረ ዳቦ ሁሉ አንድ ምልክት ያወጣል። አዳም እንደዚያ ብረት ምጣድ ሆነ፤ እኛም እንደ ዳቦው። የአምላክን ሕግ ሲያፈርስ ፍጽምና የጎደለው ሆነ። ሰርጎድ ያለ ወይም አንድ ዓይነት መጥፎ ምልክት እንደ ወጣበት ያህል ሆነ። ስለዚህ ልጆች ሲወልድ ሁሉም ይህ የኃጢአትና የአለፍጽምና ምልክት ተላለፈባቸው።

16, 17. በሽታ በሰው ልጆች ላይ የመጣው በኃጢአት ምክንያት መሆኑን ኢየሱስ ካደረጋቸው ተአምራት አንዱ የሚያሳየው እንዴት ነው?

16 በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም የምንታመመውና የምናረጀው ከአዳም በወረስነው ኃጢአት ምክንያት ነው። ኢየሱስ ካደረጋቸው ተአምራት አንዱ ይህንን ያሳያል። ኢየሱስ ባረፈበት ቤት ውስጥ ሆኖ ሲያስተምር ማንም ሌላ ሰው ተጋፍቶ መግባት እስከማይችል ድረስ ቤቱ በብዙ ሕዝብ ታጭቆ ነበር። አንድን ሽባ የሆነ ሰው በአልጋ የተሸከሙ አራት ሰዎች በቦታው ሲደርሱ ወደ ውስጥ መግባት እንደማይችሉ አዩ። ስለዚህ ወደ ጣሪያው ወጡና በሱት። ከዚያም አልጋውን ሽባውን እንደ ያዘ አወረዱትና በኢየሱስ አጠገብ አኖሩት።

17 ኢየሱስ የቱን ያህል ትልቅ እምነት እንዳላቸው ባየ ጊዜ ለሽባው “ኃጢአትህ ተሠረየችልህ አለው።” ይሁን እንጂ ከተሰበሰቡት ሰዎች አንዳንዶቹ ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ለማለት አይችልም ብለው አሰቡ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሠርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ሽባውን አንተን እልሃለሁ ተነሣ፣ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ።”—ማርቆስ 2:1–12

18. የአምላክ አገልጋዮች ወደፊት ምን ዓይነት ጊዜ ይመጣል ብለው ሊጠብቁ ይችላሉ?

18 ኢየሱስ ያለው ይህ ኃይል ለእኛ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! የአምላክ መንግሥት በምትገዛበት ጊዜ ክርስቶስ አምላክን የሚያፈቅሩና የሚያገለግሉ ሰዎች በሙሉ ያለባቸውን ኃጢአት ይቅር ለማለት ይችላል። ይህም ማንኛውም ሥቃይ ወይም ሕመም ወይም በሽታ ይወገዳል ማለት ነው። ከዚያ በኋላ ማንም ሰው አያረጅም፤ አይሞትም። ይህ ወደፊት የሚመጣ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! አዎን፣ ሰው ተወልዶ ለአጭር ጊዜ ከኖረ በኋላ ይሞታል ከሚለው አስተሳሰብ ይልቅ ልንጠብቀው የምንችል ሌላ ብዙ ነገር አለ። ስለ አምላክ መማራችንን በመቀጠልና እርሱን በማገልገል ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ በእርግጥ ለዘላለም መኖር እንችላለን።

[በገጽ 69 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች የሕይወት ትርጉም ምን ይሆን እያሉ ይገረማሉ

[በገጽ 70 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እነዚህ ነገሮች እያዘገሙ በመለወጥ የተገኙ ናቸው ወይስ በሰው የተሠሩ?

[በገጽ 75 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ አንድን ሽባ እንደፈወሰ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሰዎች የሚታመሙት በአዳም ኃጢአት ምክንያት መሆኑን ያሳያል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ