ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ይመጣ ይሆን?
በዚህ ትራክት ላይ ያለውን ሥዕል ስትመለከት ምን ይሰማሃል? በዚህ ላይ የምታየው ዓይነት ሰላም፣ ደስታና ብልጽግና ለማግኘት ልብህ አይጓጓም? መጓጓቱ የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በምድር ላይ አንድ ቀን ይመጣል ብሎ ማሰብ እንዲያው ሕልም ወይም ቅዥት ነውን?
አብዛኞቹ ሰዎች እንደዚያ ብለው ያስቡ ይሆናል። በዛሬው ጊዜ ያሉትን ጥቂቶቹን ችግሮች ለመጥቀስ ያክል ጦርነት፣ ወንጀል፣ ረሃብ፣ በሽታና እርጅና ይገኙበታል። ይሁን እንጂ ተስፋ የምናደርግበት ምክንያት አለን። አምላክ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚፈጥርና ‘የቀደሙትም እንደማይታሰቡ ወደ ልብም እንደማይገቡ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይተነብያል።—ኢሳይያስ 65:17
በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት እዚህ ላይ የተገለጹት “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” አዲስ ግዑዝ ሰማይ ወይም ቃል በቃል አዲስ ምድር አይደሉም። ግዑዙ ምድርና ሰማያት ፍጹም ሆነው እንደተሠሩና ለዘላለም እንደሚኖሩ ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ። (መዝሙር 89:36, 37፤ 104:5) እዚህ ላይ የተገለጸው “አዲስ ምድር” በምድር ላይ የሚኖር ጻድቅ የሆነ ኅብረተሰብ ሲሆን “አዲስ ሰማይ” የተባለው ደግሞ በምድራዊው ኅብረተሰብ ላይ የሚገዛ ፍጹም የሆነ ሰማያዊ መንግሥት ወይም መስተዳድር ነው። ይሁን እንጂ “አዲስ ምድር” ወይም በጣም ግሩም የሆነ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ለማመን የሚያስችል ተጨባጭ ምክንያት አለንን?
እንደዚህ ያለው እጅግ ግሩም የሆነ ሁኔታ አምላክ ለዚህ ምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ክፍል መሆኑን መገንዘብ ይገባል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት በምድራዊ ዔደን ገነት ውስጥ ካስቀመጣቸው በኋላ “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም” በማለት ድንቅ የሆነ ሥራ ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 1:28) አዎን፣ አምላክ ለእነርሱ የነበረው ዓላማ ልጆችን እንዲወልዱና ገነታቸውን በምድር ሁሉ እንዲያስፋፉ ነበር። ምንም እንኳን አዳምና ሔዋን ከጊዜ በኋላ አምላክን ላለመታዘዝ ቢመርጡና በዚህ ምክንያት ዘላለም ለመኖር የማይበቁ መሆናቸውን ቢያረጋግጡም የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ አልተለወጠም። ይህ ዓላማ በአዲስ ዓለም ውስጥ መፈጸም ይኖርበታል!—ኢሳይያስ 55:11
እንዲያውም፣ በዚህ አዲስ ዓለም በአምላክ የተሾመ ንጉሥና ገዢ የሚሆነው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ቃል የተገባለት መሲሕ ነው። (መዝሙር 2:2, 6-9፤ ዳንኤል 7:13, 14) መሲሑ ምድርን ከሁሉም ዓይነት ክፋት ካጸዳ በኋላ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው መዝሙር ፍጻሜውን ያገኛል።—መዝሙር 37:29
አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕይወት
የመሲሑ አገዛዝ አምላክ ሕዝቦቹ በምድር ላይ ተደስተው እንዲኖሩ ለማድረግ በመጀመሪያ አስቦት የነበረውን መልካም ነገር ሁሉ በመፈጸም አቻ የማይገኝላቸው ምድራዊ በረከቶችን ያመጣል። ጥላቻና ሌላውን በክፉ መመልከት ስለሚወገድ በመጨረሻ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች እርስ በእርስ እውነተኛ ወዳጅ ይሆናሉ። አምላክ ‘ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ድረስ ጦርነትን እንደሚያስቀር’ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ቃል ገብቷል። “ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ አይማሩም።”—መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4
በመጨረሻ መላዋ ምድር ገነታዊ የአትክልት ስፍራ ትሆናለች። ቅዱሳን ጽሑፎች “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። . . . በምድረ በዳ ውኃ፣ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፣ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች” ይላሉ።—ኢሳይያስ 35:1, 6, 7
ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ እንድንደሰት የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ይኖራሉ። የሚበሉት አጥተው የሚራቡ ሰዎች አይኖሩም። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘ምድር ፍሬዋን እንደምትሰጥ’ ይናገራሉ። (መዝሙር 67:6፤ 72:16) ፈጣሪያችን “ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። . . . ሌላም እንዲበላው አይተከሉም” በማለት በገባው ቃል መሠረት እያንዳንዱ ሰው በሥራው ፍሬ ይደሰታል።—ኢሳይያስ 65:21, 22
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሰዎች ግዙፍ በሆኑ የአፓርታማ ሕንፃዎች ወይም ትርኪምርኪ በሆኑ ሠፈሮች ተጨናንቀው አይኖሩም። ምክንያቱም አምላክ “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ . . . ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም” በማለት ዓላማውን ገልጾልናል። በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች “በከንቱ አይደክሙም” በማለት ተስፋ ይሰጣሉ።—ኢሳይያስ 65:21–23
በመጨረሻም የአምላክ መንግሥት በዔደን ገነት ውስጥ በእንስሳት መካከል እንዲሁም በእንስሳትና በሰዎች መካከል የነበረውን ሰላማዊ ግንኙነት መልሶ ያመጣል። ቅዱሳን ጽሑፎች:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል” በማለት ይገልጻሉ።—ኢሳይያስ 11:6–9፤ ሆሴዕ 2:20
እስቲ አስበው። ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ሁሉም ዓይነት በሽታና የአካል ጉዳተኝነት ይፈወሳል! የአምላክ ቃል “በዚያም የሚቀመጥ ታምሜአለሁ አይልም” በማለት ያረጋግጥልናል። (ኢሳይያስ 33:24) በተጨማሪም የአምላክ ቃል “[አምላክ] ሞትን ለዘላለም ይውጣል” በማለት ቃል ይገባልናል።—ኢሳይያስ 25:8
አንተም ይህን ሕይወት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
ይህ በእርግጥም ድንቅ ተስፋ ነው። አምላክ የገባውን ቃል ሁልጊዜ የሚፈጽም በመሆኑ ይህ ተስፋ ይፈጸማል ብለን ለማመን ሊከብደን አይገባም። (ኢሳይያስ 46:9, 10) እርግጥ ነው፣ በምትመጣዋ ምድራዊት ገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ ብቃቶች አሉ። እነዚህ ብቃቶች ምንድን ናቸው?
እነዚህ ብቃቶች በከፊል ብዙዎች “ብሉይ ኪዳን” ብለው በሚጠሩት በታናክ ውስጥና መሲሑን በሚመለከት ዝርዝር ማብራሪያ በያዙት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይገኛሉ። “አዲስ ኪዳን” በመባል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁት የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ልክ እንደ ታናክ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ናቸው። ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የሚባሉት እነዚህ ሁለት ክፍሎች አንድ ላይ ሆነው ነው። “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው [ከሰዎች ዓይን ላይ] ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” የሚለውን አምላክ የገባውን አስደናቂ ተስፋ ይዘዋል።—ራእይ 21:4፤ በተጨማሪም ሆሴዕ 13:14ን ተመልከት።
የዚህ ትራክት አዘጋጅ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የሕዝበ ክርስትና ወይም የአይሁድ እምነት ክፍል ባይሆኑም እንኳ እነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት የሰፈረባቸው መጻሕፍት መሆናቸውን ይቀበላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር ይችሉ ዘንድ ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ ለሰዎች ለማሳወቅ በሁሉም የምድር ክፍል በትጋት ይመሰክራሉ።—ሚክያስ 4:1-4
ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በእንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።