ሙታን ያላቸው አስተማማኝ ተስፋ
አንዲት የ25 ዓመት ሴት እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች፦ “በ1981 እናቴ በካንሰር ምክንያት ሞተች። የእሷ ሞት በእኔና በወንድሜ ላይ ከባድ ሐዘን አስከትሎብን ነበር። በዚያ ጊዜ እኔ 17 ዓመቴ ሲሆን ወንድሜ ደግሞ 11 ዓመቱ ነበር። እናቴን ማጣቴ በጣም ጎዳኝ። በሰማይ እንደምትኖር ተምሬ ስለነበር ከእሷ ጋር ለመሆን ስል ራሴን ለማጥፋት ፈለግሁ። የእሷን ያህል የምወደው ሰው አልነበረም።”
ሞት በጣም የምትወዱትን ሰው ከእናንተ ነጥቆ ለመውሰድ የሚያስችል ኃይል ያለው መሆኑ ኢፍትሐዊ እንደሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ከአሁን በኋላ፣ ከምትወዱት ሰው ጋር መነጋገርና መሳቅ ወይም እሱን እቅፍ ማድረግ እንደማትችሉ ማወቃችሁ ለመሸከም ከምትችሉት በላይ ሊከብዳችሁ ይችላል። የምትወዱት ሰው በሰማይ እንደሚኖር ቢነገራችሁም ይህ ሐዘናችሁን ሊያስወግድላችሁ አይችልም።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በጣም የተለየ ተስፋ ይሰጠናል። ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ቅዱሳን ጽሑፎች፣ በሞት ከተለዩዋችሁ የምትወዷቸው ሰዎች ጋር በቅርቡ እንደገና መገናኘት እንደምትችሉ ይገልጻሉ፤ ይህም የሚሆነው ምን እንደሚመስል በማታውቁት በሰማይ ሳይሆን ሰላምና ጽድቅ በሚሰፍንባት በዚህች ምድር ላይ ነው። በተጨማሪም በዚያን ጊዜ ሰዎች ፍጹም የሆነ ጤንነት ይኖራቸዋል፤ ከዚያ በኋላ የሚሞቱበት ምክንያት አይኖርም። ይሁንና አንዳንዶች ‘ይህ እንኳ የሕልም እንጀራ ነው!’ ይሉ ይሆናል።
ይህ ተስፋ አስተማማኝ መሆኑን አምናችሁ እንድትቀበሉ የሚያስፈልጋችሁ ምን ዓይነት ማስረጃ ነው? በአንድ ተስፋ ማመን እንድንችል፣ ተስፋውን የሰጠው አካል የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም ችሎታውና ፍላጎቱ ሊኖረው ይገባል። ታዲያ ሙታን እንደገና በሕይወት እንደሚኖሩ ተስፋ የሰጠን ማን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ በ31 ዓ.ም. የጸደይ ወራት እንዲህ ሲል በልበ ሙሉነት ቃል ገብቷል፦ “አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸውና ሕያው እንደሚያደርጋቸው ሁሉ ወልድም እንዲሁ የፈለገውን ሰው ሕያው ያደርጋል። በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ [የኢየሱስን ድምፅ] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና።” (ዮሐንስ 5:21, 28, 29) አዎ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ በሞት አንቀላፍተው ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዳግመኛ ሕያው ሆነው ሰላም በሚሰፍንባትና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር አጋጣሚ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16፤ 17:3፤ ከመዝሙር 37:29 እና ከማቴዎስ 5:5 ጋር አወዳድሩ።) ይህን ተስፋ የሰጠው ኢየሱስ በመሆኑ ተስፋውን ለመፈጸም ፈቃደኛ ነው ብሎ ማመን ይቻላል። ይሁን እንጂ ይህን ተስፋ የመፈጸም ችሎታ አለው?
ኢየሱስ ይህን ተስፋ በሰጠ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ሙታንን ለማስነሳት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው በተግባር አሳይቷል።
“አልዓዛር፣ ና ውጣ!”
በጣም ልብ የሚነካ ትዕይንት ነው። አልዓዛር በጠና ታሞ ነበር። ሁለቱ እህቶቹ ማርያምና ማርታ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ይገኝ ለነበረው ለኢየሱስ “ጌታ ሆይ፣ የምትወደው ሰው ታሟል” የሚል መልእክት ላኩ። (ዮሐንስ 11:3) ኢየሱስ አልዓዛርን እንደሚወደው ያውቁ ነበር። ኢየሱስ የታመመ ወዳጁን ለማየት መፈለጉ ይቀራል? ኢየሱስ ግን ወዲያውኑ ወደ ቢታንያ ከመሄድ ይልቅ በነበረበት ቦታ ለሁለት ቀናት ቆየ።—ዮሐንስ 11:5, 6
ለኢየሱስ መልእክት ከተላከ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አልዓዛር ሞተ። ኢየሱስ አልዓዛር መሞቱን አውቆ ስለነበረ አንድ ነገር ለማድረግ አሰበ። ቢታንያ በደረሰ ጊዜ ወዳጁ ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። (ዮሐንስ 11:17, 39) ታዲያ ኢየሱስ ከሞተ ይህን ያህል ጊዜ ያለፈውን ሰው ሊያስነሳ ይችላል?
የተግባር ሰው የሆነችው ማርታ የኢየሱስን መምጣት ስትሰማ ልትቀበለው እየሮጠች ወጣች። (ከሉቃስ 10:38-42 ጋር አወዳድሩ።) ኢየሱስ በሐዘኗ ልቡ ተነክቶ “ወንድምሽ ይነሳል” የሚል ማረጋገጫ ሰጣት። ማርታ ወደፊት በሚፈጸመው ትንሣኤ እንደምታምን በነገረችው ጊዜም ኢየሱስ በግልጽ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። በእኔ የሚያምን ሁሉ ቢሞት እንኳ እንደገና ሕያው ይሆናል” አላት።—ዮሐንስ 11:20-25
ኢየሱስ አልዓዛር ወደተቀበረበት ቦታ ሲደርስ፣ የመቃብሩ በር የተዘጋበት ድንጋይ እንዲነሳ አዘዘ። ከዚያም ጮክ ብሎ ከጸለየ በኋላ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” አለ።—ዮሐንስ 11:38-43
በዚያ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ዓይን በመቃብሩ ላይ ተተክሎ ነበር። ከጨለማው ውስጥ አንድ ሰው ብቅ አለ። እግሮቹና እጆቹ በመግነዝ፣ ፊቱም በጨርቅ ተጠምጥሞ ነበር። ኢየሱስ “ፍቱትና ይሂድ” ሲል አዘዛቸው። እነሱም ሰውየው የተጠመጠመበትን ጨርቅ በሙሉ ከሰውነቱ ላይ አነሱት። በእርግጥም ሰውየው ለአራት ቀናት ያህል ሞቶ የቆየው አልዓዛር ነበር!—ዮሐንስ 11:44
ይህ ተአምር እውነት ተፈጽሟል?
አልዓዛር ከሙታን ስለመነሳቱ የሚገልጸው ዘገባ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እንደ አንድ ታሪካዊ ሐቅ ሆኖ ሰፍሯል። ዝርዝር ሁኔታዎቹ በሙሉ በማያሻማ ሁኔታ ስለተገለጹ ይህ ዘገባ ተራ ተረት ነው ማለት አይቻልም። ይህ ዘገባ ሐቅ መሆኑን መጠራጠር፣ የራሱን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን መነሳት ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ተአምራት በሙሉ መጠራጠር ማለት ነው። ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱን መካድ ደግሞ መላውን የክርስትና እምነት መካድ ማለት ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:13-15
እንደ እውነቱ ከሆነ የአምላክን መኖር የምትቀበሉ ከሆነ በትንሣኤ ማመን አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ አይገባም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ሰው ኑዛዜውን በቪዲዮ ቀድቶ ሊያስቀምጥ ይችላል፤ ከዚያም እሱ ከሞተ በኋላ ዘመዶቹና ወዳጆቹ ንብረቱ ምን መደረግ እንዳለበት ሲገልጽ ሊመለከቱና ሊሰሙ ይችላሉ። ከመቶ ዓመታት በፊት ይህ ነገር ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር። አሁንም ቢሆን ራቅ ባሉ የዓለም ክፍሎች ለሚኖሩ ሰዎች የቪዲዮ ቀረጻ ቴክኖሎጂ፣ ለመረዳት የሚያስቸግር ተአምር ሆኖ ይታያቸው ይሆናል። ሰዎች፣ አምላክ ያቋቋማቸውን ሳይንሳዊ ሕጎች ተጠቅመው፣ የሚታይና የሚሰማ ምስል መቅረጽ ከቻሉ ፈጣሪ ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ አይችልም? ሕይወትን የፈጠረው አምላክ፣ ቀድሞ የነበረውን ሕይወት እንደገና መልሶ መፍጠር አይሳነውም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም?
አልዓዛር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ወደ ሕይወት መመለሱ፣ ሰዎች በኢየሱስና በትንሣኤ ላይ ያላቸውን እምነት አጠናክሮታል። (ዮሐንስ 11:41, 42፤ 12:9-11, 17-19) በተጨማሪም ይሖዋና ልጁ ሙታንን ለማስነሳት ፈቃደኞች እንደሆኑና ፍላጎቱ እንዳላቸው ልብ በሚነካ መንገድ አሳይቷል።
‘አምላክ የእጁን ሥራ ይናፍቃል’
ኢየሱስ አልዓዛር በሞተበት ጊዜ ያደረገው ነገር በጣም ሩኅሩኅ መሆኑን ያሳያል። በዚህ ጊዜ ያሳየው ጥልቅ ስሜት፣ ሙታንን ለማስነሳት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ያመለክታል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ማርያምም ኢየሱስ የነበረበት ቦታ ደርሳ ባየችው ጊዜ እግሩ ላይ ተደፋች፤ ከዚያም ‘ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር’ አለችው። ኢየሱስ እሷ ስታለቅስና አብረዋት የመጡት አይሁዳውያን ሲያለቅሱ ሲያይ እጅግ አዘነ፤ ተረበሸም። እሱም ‘የት ነው ያኖራችሁት?’ አለ። እነሱም ‘ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ’ አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። በዚህ ጊዜ አይሁዳውያኑ ‘እንዴት ይወደው እንደነበር ተመልከቱ!’ አሉ።”—ዮሐንስ 11:32-36
“እጅግ አዘነ፣” “ተረበሸ” እና “እንባውን አፈሰሰ” የሚሉት ሦስት መግለጫዎች ኢየሱስ ከልብ የመነጨ ርኅራኄ እንዳሳየ ይጠቁማሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ልብ የሚነካ ትዕይንት ለመመዝገብ የተጠቀመባቸው የበኩረ ጽሑፉ ቃላት፣ ኢየሱስ በጣም በሚወደው ጓደኛው በአልዓዛር ሞት እንዲሁም የአልዓዛር እህት ስታለቅስ በማየቱ ስሜቱ በጣም ተነክቶ እንባው እንደፈሰሰ ያመለክታሉ።a
በጣም የሚያስገርመው ነገር ኢየሱስ ቀደም ሲል ሌሎች ሁለት ሰዎችን ከሞት አስነስቶ የነበረ መሆኑ ነው። አሁንም ቢሆን አልዓዛርን ለማስነሳት አቅዶ ነበር። (ዮሐንስ 11:11, 23, 25) ያም ሆኖ ‘እንባውን አፍስሷል።’ ስለዚህ ኢየሱስ ሙታንን የሚያስነሳው ግዴታውን ለመወጣት ሲል አይደለም። በዚህ ጊዜ ያሳየው ከአንጀት የመነጨ የርኅራኄ ስሜት፣ ሞትን ፈጽሞ ለመሻር ጥልቅ የሆነ ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ያመለክታል።
ኢየሱስ አልዓዛርን ባስነሳበት ጊዜ ያሳየው ልባዊ ርኅራኄ፣ ሞትንና ሞት ያስከተላቸውን ውጤቶች ፈጽሞ ለማስወገድ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል
ኢየሱስ የይሖዋ አምላክ ማንነት “ትክክለኛ አምሳያ ነው”፤ በመሆኑም ሰማያዊ አባታችንም ከዚህ ያነሰ ርኅራኄ እንደማያሳይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዕብራውያን 1:3) ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ፈቃደኛ መሆኑን በተመለከተ ታማኙ ኢዮብ እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት ሊኖር ይችላል? . . . አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ።” (ኢዮብ 14:14, 15) እዚህ ላይ “ትናፍቃለህ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል፣ አምላክ ይህን ለማድረግ እንደሚጓጓ ያመለክታል። (ዘፍጥረት 31:30፤ መዝሙር 84:2) ይሖዋ ሙታንን የሚያስነሳበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት እንደሚጠባበቅ ግልጽ ነው።
በእርግጥ በትንሣኤ ተስፋ ማመን እንችላለን? አዎ፣ ይሖዋና ልጁ ይህን ተስፋ እውን ለማድረግ ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው አላቸው። ታዲያ ይህ ለእናንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ከአሁኑ በጣም የተለየ ሁኔታ በሚኖራት ምድር ላይ፣ በሞት ከተለዩዋችሁ የምትወዷቸው ሰዎች ጋር መኖር ትችላላችሁ!
የሰውን ልጅ ፈጥሮ በተዋበ የአትክልት ስፍራ እንዲኖር ያደረገው ይሖዋ አምላክ፣ በአሁኑ ጊዜ ታላቅ ክብር በተቀዳጀው በኢየሱስ ክርስቶስ በሚተዳደረው ሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት በዚህች ምድር ላይ ገነትን መልሶ ለማቋቋም ቃል ገብቷል። (ዘፍጥረት 2:7-9፤ ማቴዎስ 6:10፤ ሉቃስ 23:42, 43) ዳግመኛ በሚቋቋመው ገነት ውስጥ የሰው ልጅ ከማንኛውም ዓይነት ሕመምና በሽታ ነፃ ሆኖ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የመምራት አጋጣሚ ያገኛል። (ራእይ 21:1-4፤ ከኢዮብ 33:25 እና ከኢሳይያስ 35:5-7 ጋር አወዳድሩ።) ማንኛውም ዓይነት ጥላቻ፣ የዘር መድልዎ፣ የጎሣ ግጭትና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል። ይሖዋ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ሙታንን የሚያስነሳው እንደዚህ ባለችው የጸዳች ምድር ላይ ነው።
በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት እውን የሚሆነው ትንሣኤ ለሁሉም ሕዝቦች ደስታ ያመጣል
በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው ሴት ስለዚህ ተስፋ ተምራለች። እናቷ ከሞተች ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት እንድታጠና ረዷት። “ስለ ትንሣኤ ተስፋ ከተማርኩ በኋላ አለቀስኩ። እናቴን ዳግመኛ ማግኘት እንደምችል ማወቄ በጣም አስደሰተኝ” በማለት ታስታውሳለች።
እናንተም እንዲሁ፣ የሞተባችሁን ሰው ዳግመኛ ለማግኘት የምትጓጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ የተረጋገጠ ተስፋ ሲፈጸም በዓይናችሁ ማየት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ሊያስተምሯችሁ ፈቃደኞች ናቸው። በአቅራቢያችሁ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ በመሄድ ወይም በገጽ 32 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች ወደ አንዱ በመጻፍ ከእነሱ ጋር መገናኘት ትችላላችሁ።
a “እጅግ አዘነ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥልቅ የሐዘን ስሜትን ከሚያመለክት ግስ (ኤምብሪማኦሜ) የተወሰደ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “እዚህ ላይ ቃሉ የሚያመለክተው ኢየሱስ የጠለቀ የሐዘን ስሜት ተሰምቶት ከልቡ እንደቃተተ ነው” ብለዋል። “ተረበሸ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል መታወክን ከሚያመለክት ቃል (ታራሶ) የተወሰደ ነው። አንድ የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ እንዳሉት ቃሉ “አንድ ሰው ውስጡ እንደተረበሸ እንዲሁም ከፍተኛ ሥቃይ ወይም ሐዘን እንደተሰማው” ይጠቁማል። “እንባውን አፈሰሰ” የሚለው አገላለጽ “ምንም ድምፅ ሳያሰሙ ማልቀስ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ግስ (ዳክሪኦ) የተወሰደ ነው።