ከሰዎች ጋር የመወያየት ችሎታህን ማሻሻል
ብዙውን ጊዜ ከሰዎች ጋር ዘና ብለህ መወያየት ትችላለህ? ብዙዎች ከሌላ ሰው ጋር በተለይም ከማያውቁት ሰው ጋር መጫወት ገና ሲያስቡት ያስፈራቸዋል። እንዲህ ያሉት ሰዎች ዓይን አፋር ሊሆኑ ይችላሉ። ‘ምን አወራለሁ? ምንስ ብዬ እጀምራለሁ? ደግሞስ ጭውውቱ እንዲቀጥል ምን ላወራ እችላለሁ?’ ብለው ሊጨነቁ ይችላሉ። ደፋርና ተግባቢ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ጭውውቱን ብቻቸውን ይቆጣጠሩት ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሌላው ሰው ሐሳቡን እንዲገልጽ ማድረግና አዳማጭ መሆን ይቸግራቸዋል። እንግዲያው ዓይን አፋርም ሆንን ተግባቢ ሁላችንም ከሰዎች ጋር የመወያየት ችሎታችንን ማሻሻል ይኖርብናል ማለት ነው።
ከቤትህ ጀምር
ከሰዎች ጋር የመወያየት ችሎታህን ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት ለምን ከቤትህ አትጀምርም? ገንቢ የሆኑ ጭውውቶች ለአንድ ቤተሰብ ደስታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
እርስ በርስ መተሳሰብ እንዲህ ዓይነቱ ጭውውት እንዲኖር የሚረዳ ወሳኝ ባሕርይ ነው። (ዘዳ. 6:6, 7፤ ምሳሌ 4:1-4) እርስ በርስ የምንተሳሰብ ከሆነ ስሜታችንን እንገልጻለን እንዲሁም ሌሎችም ሲናገሩ እናዳምጣለን። በተጨማሪም ገንቢ ውይይት ለማድረግ ለሌሎች የምናካፍለው ቁም ነገር ሊኖረን ይገባል። ቋሚ ፕሮግራም አውጥተን መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን የምናነብብና የምናጠና ከሆነ ለሌሎች ልናካፍለው የምንችለው ብዙ ነገር ይኖረናል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት በሚገባ የምንጠቀም ከሆነም ለውይይት የሚረዳ ሐሳብ እናገኛለን። ምናልባት ቀን ስናገለግል ደስ የሚል ተሞክሮ አጋጥሞን ሊሆን ይችላል። ግንዛቤ የሚያሰፋ ወይም የሚያስቅ ነገር አንብበን ይሆናል። ቤተሰቡ ሰብሰብ ብሎ በሚጫወትበት ጊዜ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ማካፈል ሊዳብር የሚገባው ልማድ ነው። እንዲህ ካደረግን ከቤተሰባችን ውጭ ካሉ ሰዎችም ጋር መወያየት አይቸግረንም።
ከማታውቀው ሰው ጋር መወያየት
ብዙ ሰዎች ከማያውቁት ሰው ጋር ውይይት ለመጀመር አይደፍሩም። የይሖዋ ምሥክሮች ግን ለአምላክና ለጎረቤቶቻቸው ፍቅር ስላላቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማካፈል ሲሉ ከሰዎች ጋር ውይይት ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ለመማር ይጥራሉ። በዚህ ረገድ ማሻሻያ እንድታደርግ ምን ሊረዳህ ይችላል?
በፊልጵስዩስ 2:4 ላይ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ። ‘እያንዳንዳችን የራሳችንን ሳይሆን የባልንጀራችንን ጥቅም እንድንመለከት’ ተመክረናል። እስቲ ራስህን በሌላው ሰው ቦታ አድርገህ አስብ። ከሰውዬው ጋር ከዚህ በፊት ተገናኝታችሁ የማታውቁ ከሆነ እንግዳ እንደምትሆንበት የታወቀ ነው። ታዲያ ዘና እንዲል ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ሞቅ ያለ ፈገግታ ልታሳየውና ወዳጃዊ ሰላምታ ልትሰጠው ትችላለህ። ይሁን እንጂ ሌላም ሊታሰብበት የሚገባ ነገር አለ።
ምናልባት ሐሳብ ውስጥ እያለ ድንገት አነጋግረኸው ሊሆን ይችላል። እርሱ እያሰበ ስላለው ነገር ምንም ግድ ሳይሰጥህ አንተ የምታስበውን ልታወያየው ብትሞክር ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ ይመስልሃል? ኢየሱስ በሰማርያ በሚገኝ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አንዲት ሴት ባገኘ ጊዜ ያደረገው ምን ነበር? ሴትዮዋ ሐሳቧ ያለው ውኃ ቀድታ መሄዷ ላይ ነበር። ኢየሱስም ከሴትዮዋ ጋር ውይይቱን የጀመረው ይህንኑ ጉዳይ መሠረት አድርጎ ሲሆን ጥሩ መንፈሳዊ ውይይት ማድረግ ችለዋል።—ዮሐ. 4:7-26
አንተም ልብ ብለህ የምታስተውል ከሆነ ሰዎች ስለምን ነገር እያሰቡ እንዳለ መረዳት ትችላለህ። ሰውዬው ደስተኛ ይመስላል ወይስ አዝኗል? አረጋዊ ናቸው? ቤት ውስጥ ልጆች እንዳሉ የሚጠቁም ነገር ይታይሃል? ሰውዬው ጥሩ ኑሮ ያለው ይመስላል ወይስ ኑሮ የደቆሰው? ቤቱ ውስጥ የሚታዩት ነገሮች ወይም ያደረጋቸው ጌጦች ሃይማኖታዊ ዝንባሌ እንዳለው ይጠቁማሉ? ሰላምታ ስትለዋወጡ እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ ካስገባህ ግለሰቡ በጋራ የሚያግባባችሁ ነገር እንዳለ ሊያስብ ይችላል።
ሰውዬውን በግንባር ካላገኘኸውና ምናልባትም የሚያነጋግርህ በሩን ሳይከፍት ከሆነ ምን ልትገምት ትችላለህ? ፍርሃት ይኖርበት ይሆናል። በሩን ባይከፍትልህም ይህንኑ ጉዳይ መሠረት በማድረግ ውይይት መጀመር ትችል ይሆን?
አንዳንድ ጊዜ ማንነትህን፣ ወደቤቱ የመጣህበትን ምክንያት፣ በአምላክ ለምን እንደምታምን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ያነሳሳህ ምን እንደሆነ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደጠቀመህ በመግለጽ ሰውዬውን ወደ ውይይት ማስገባት ይቻል ይሆናል። (ሥራ 26:4-23) እርግጥ ይህንን የምታደርገው በጥበብና በዓላማ መሆን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ግለሰቡ ስለ ራሱም ሆነ ስላለው አመለካከት አንዳንድ ነገር እንዲነግርህ ሊያነሳሳው ይችላል።
በአንዳንድ አካባቢዎች እንግዶችን ተቀብሎ የማስተናገድ ባሕል አለ። ሰዎች ገና ሲያዩህ ቤታቸው ገብተህ አረፍ እንድትል ይጋብዙህ ይሆናል። ገብተህ እንደተቀመጥህ ስለ ቤተሰቡ ደህንነት በአክብሮት ብትጠይቅና የሚሰጡትን ምላሽ ከልብህ ብታዳምጥ የቤቱ ባለቤት አንተ የምትናገረውንም እንደዚያው በጥሞና ለማዳመጥ ሊነሳሳ ይችላል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ቤታቸው ለመጣ እንግዳ የሚኖራቸው ግምት ከዚህም ከፍ ያለ ስለሆነ የሰላምታ ልውውጡ ሰፋ ያለ ሊሆን ይችላል። በዚህ መሃል የሚያግባባችሁ ነገር እንዳለ ያስተውሉ ይሆናል። ይህም ግሩም መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ በር ሊከፍት ይችላል።
በአካባቢህ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ቢኖሩስ? ከእነዚህ ሰዎች ጋር መወያየት የምትችለው እንዴት ነው? የአንዳንዶቹን ቋንቋዎች የሰላምታ ልውውጥ ብቻ እንኳ ብታጠና ሰዎቹ ለእነርሱ ጥሩ አመለካከት እንዳለህ ይገነዘባሉ። ይህም ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ በር ይከፍታል።
ውይይቱ እንዲቀጥል ማድረግ
ውይይቱ እንዲቀጥል ማድረግ እንድትችል የሰውዬውን ሐሳብ ለማወቅ ሞክር። ፈቃደኛ ከሆነ ሐሳቡን እንዲገልጽ አበረታታው። የታሰበባቸው ጥያቄዎች ማቅረብ በዚህ ረገድ ሊረዳ ይችላል። ብዙውን ጊዜ አንድ ግለሰብ አመለካከቱን እንዲገልጽ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ አዎን ወይም አይደለም የሚል ብቻ ስለማይሆን ሐሳቡን እንዲገልጽ የሚጋብዙ ጥያቄዎችን መጠቀም የተሻለ ነው። ለምሳሌ ያህል በአካባቢው ያሉ ሰዎችን የሚያሳስብ አንድ ችግር ከጠቀስክ በኋላ “ለዚህ ችግር መንስኤው ምን ይመስልሃል?” ወይም “ምን መፍትሔ የሚኖር ይመስልሃል?” እያልክ ልትጠይቀው ትችላለህ።
አንድ ጥያቄ ከጠየቅህ በኋላ ግለሰቡ የሚሰጠውን መልስ በጥሞና አዳምጥ። አንዳንድ ቃላት በመሰንዘር፣ ጭንቅላትህን በመነቅነቅ ወይም ሌሎች አካላዊ መግለጫዎችን በመጠቀም ንግግሩን እየተከታተልክ እንዳለህ አሳይ። ንግግሩን አቋርጠህ ጣልቃ አትግባ። እየተናገረ ያለውን ነገር ከልብህ አዳምጥ። ‘ለመስማት የፈጠንህ ለመናገርም የዘገየህ’ ሁን። (ያዕ. 1:19) በተራህ ሐሳብ ስትሰጥ የምትናገረው ነገር በጥሞና ስታዳምጠው እንደነበር የሚያሳይ መሆን አለበት።
ይሁንና ሁሉም ሰው ለምታቀርበው ጥያቄ መልስ ይሰጣል ማለት እንዳልሆነ አስታውስ። አንዳንድ ሰዎች ምላሻቸውን የሚገልጹት በቅንድባቸው ወይም ፈገግ በማለት ብቻ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ አዎ ወይም አይደለም ብቻ ይሉ ይሆናል። ተስፋ አትቁረጥ። ታገሥ። ውይይቱን በግድ መቀጠል እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ግለሰቡ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ከሆነ የሚገነባ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ አካፍለው። ቀስ በቀስ እየተግባባችሁ ልትሄዱና ሐሳቡን በነፃነት መግለጽ ሊጀምር ይችላል።
በውይይታችሁ ወቅት በቀጣዩ ጊዜ የምትነጋገሩበትን ነገር ከወዲሁ አስብ። አንድ ሰው በርከት ያሉ ጥያቄዎችን ካነሳ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ከመመለስ ይልቅ አንድ ሁለቱን በሚቀጥለው ጊዜ እንደምትወያዩበት ግለጽለት። ምርምር አድርገህ ለጥያቄዎቹ መልስ ይዘህለት እንደምትመጣ ንገረውና ተመልሰህ ስትሄድ ያገኘኸውን ሐሳብ አካፍለው። እርሱ ያነሳው ጥያቄ ከሌለ የሚቀጥለውን ውይይታችሁን በጉጉት እንዲጠብቅ ያደርገዋል ብለህ የምታስበውን ጥያቄ ጠይቀውና እንደገና ስትገናኙ እንደምትወያዩበት በመግለጽ መደምደም ትችላለህ። ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ፣ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹርና በቅርብ ከወጡት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ ብዙ ሐሳቦች ማግኘት ይቻላል።
ከእምነት ወንድሞችህ ጋር መወያየት
ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትገናኝ ለመተዋወቅ ትጥራለህ? ወይስ ዝም ዝም ትባባላላችሁ? ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እነርሱን ለማወቅ ሊገፋፋን ይገባል። (ዮሐ. 13:35) ታዲያ ምን ብለህ ልትጀምር ትችላለህ? ስምህን ልትነግረውና ስሙን ልትጠይቅ ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ እውነትን እንዴት እንደሰማ መጠየቁ ወደ ጥሩ ውይይት የሚመራ ከመሆኑም ሌላ እርስ በርስ ለመተዋወቅ ይረዳል። ሐሳብህን አቀነባብረህ መግለጽ ባትችልም እንኳ ከእርሱ ጋር ለመተዋወቅ ያደረግኸው ጥረት አሳቢነት እንዳሳየኸው እንዲሰማው ያደርጋል። ደግሞም የሚፈለገው ይኸው ነው።
በጉባኤህ ውስጥ ካለ ሰው ጋር የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ስለ ግለሰቡም ሆነ ስለ ቤተሰቡ ከልብ እንደምታስብ አሳይ። ስብሰባ እንደጨረሳችሁ ከሆነ ከስብሰባው ያገኘኸውን ጠቃሚ ነጥብ በተመለከተ አንዳንድ ሐሳብ ማንሳት ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ለሁለታችሁም ጥቅም አለው። በቅርቡ ከወጣ መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! መጽሔት ላይ ያገኘኸውን ጥሩ ነጥብ ልትጠቅስ ትችላለህ። ይህን የምታደርገው የነካህን ነጥብ ለማካፈል እንጂ ለጉራ ወይም አዋቂ ለመባል መሆን የለበትም። ከሁለት አንዳችሁ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ካላችሁ ልትነጋገሩበትና እንዴት ሊቀርብ እንደሚችል ሐሳብ ልትለዋወጡ ትችላላችሁ። ወይም ከመስክ አገልግሎት ያገኘሃቸውን ተሞክሮዎች አካፍለው።
እርግጥ ሰዎች ስለተናገሩት ወይም ስላደረጉት ነገር በውይይታችን መሃል መጥቀሳችን አይቀርም። በጨዋታችን መካከል አንዳንድ የሚያስቁ ነገሮችንም መናገር እንችላለን። ሆኖም የምንናገረው ነገር የሚያንጽ ነው? የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር ልብ የምንል ከሆነና ለአምላክ ፍቅር ካለን ውይይታችን የሚያንጽ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 16:27, 28፤ ኤፌ. 4:25, 29፤ 5:3, 4፤ ያዕ. 1:26
ወደ አገልግሎት ከመሄዳችን በፊት እንደምንዘጋጅ ሁሉ ከወዳጆችህ ጋር በምትጨዋወትበት ጊዜ ጣል የምታደርገው አንድ ደስ የሚል ሐሳብ ለምን አታዘጋጅም? ስታነብብ ወይም ስታዳምጥ ለሌሎች ልታካፍለው የምትፈልገውን ጥሩ ሐሳብ በአእምሮህ ያዝ። ከጊዜ በኋላ ብዙ ሐሳብ ይኖርህና ከዚያ መሃል መምረጥ ትችላለህ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ከሌሎች ጋር ስትወያይ የምትሰጠው ሐሳብ ከዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ ውጭ ያሉ ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስ ይሆናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ጭውውትህ ለአምላክ ቃል ትልቅ ግምት እንዳለህ የሚያሳይ ይሁን።—መዝ. 139:17