ጥናት 1
ጥርት ያለ ንባብ
አምላክ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ‘የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ’ እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጢሞ. 2:4) ስለሆነም ትክክለኛውን እውቀት ለማስተላለፍ ያለን ፍላጎት መጽሐፍ ቅዱስን ለሌሎች ጥርት አድርገን እንድናነብብ ሊያነሳሳን ይገባል።
ወጣቶችም ሆንን አዋቂዎች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎችን ለሌሎች ጥሩ አድርገን ማንበብ መቻላችን በጣም አስፈላጊ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ስለ ይሖዋ እና ስለ መንገዶቹ ያገኘነውን እውቀት ለሌሎች የማካፈል ኃላፊነት ተጥሎብናል። ይህም ብዙውን ጊዜ ለአንድ ግለሰብም ይሁን ለተሰበሰቡ ሰዎች ማንበብን የሚጠይቅ ነው። በቤተሰብ መልክ ሆነን የምናነብባቸው አጋጣሚዎችም ይኖራሉ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ወጣት አዋቂ ሳይል ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ለሌሎች የማንበብ ችሎታቸውን ለማሻሻል የሚረዳ ምክር ያገኛሉ።
ለአንድ ግለሰብም ይሁን ለጉባኤ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ አጋጣሚ ስናገኝ ይህንን ኃላፊነት አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ነው። “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም . . . ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብ. 4:12) የአምላክ ቃል የትም ሊገኝ የማይችል ውድ እውቀት ይዟል። እውነተኛውን አንድ አምላክ እንድናውቅና ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንድንመሠርት ይረዳናል። እንዲሁም በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንወጣ ሊያግዘን ይችላል። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስን በተቻለን መጠን ጥሩ አድርገን የማንበብ ግብ ሊኖረን ይገባል።—መዝ. 119:140፤ ኤር. 26:2
ጥርት አድርጎ ማንበብ የሚቻልበት መንገድ። አንድ ንባብ ጥሩ እንዲሆን የሚያስፈልጉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም መጀመሪያ ሊዳብር የሚገባው በትክክል የማንበብ ችሎታ ነው። ይህም ጽሑፉ ላይ ያለውን ምንም ሳትገድፍ ወይም ሳትጨምር ማንበብ ማለት ነው። ቃላትና ፊደላትን ላለመግደፍ ወይም ተቀራራቢነት ያላቸውን ቃላት አሳስተህ ላለማንበብ መጠንቀቅ ይኖርብሃል።
ቃላቱን በትክክል ማንበብ እንድትችል የጽሑፉን መልእክት መረዳትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃል። በደንብ በተለማመድህ መጠን የሐሳቡ ፍሰት ስለሚገባህ የንባብህ ጥራትም ይሻሻላል።
በጽሑፍ ቋንቋ ውስጥ ሥርዓተ ነጥቦች ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። ሥርዓተ ነጥቦች የት ቦታ ላይ ቆም እንደምንል፣ ምን ያህል ቆም ማለት እንዳለብንና የድምፃችንን ቃና መቀየር ያስፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ ሊጠቁሙን ይችላሉ። በአንዳንድ ቋንቋዎች ሥርዓተ ነጥቡ የድምፅን ቃና መለወጥ የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ በተመሳሳይ የድምፅ ቃና ማንበብ ጥያቄውን በአራት ነጥብ የሚደመደም ዓረፍተ ነገር ሊያስመስለው ወይም ከነጭራሹ ትርጉሙን ሊለውጠው ይችላል። እርግጥ ሥርዓተ ነጥቦች በአብዛኛው ከሰዋስው ጋር ብቻ የተያያዘ ተግባር የሚያከናውኑባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። ሥርዓተ ነጥቦች በቋንቋህ ውስጥ ስለሚጫወቱት ሚና ጠንቅቀህ ልታውቅ ይገባል። ይህም ትርጉም በሚሰጥ መንገድ ለማንበብ የሚረዳ ወሳኝ ነገር ነው። ዓላማህ አንድ የሚጨበጥ መልእክት ማስተላለፍ እንጂ እንዲሁ ቃላትን ማነብነብ ብቻ ሊሆን እንደማይገባ አስታውስ።
አጥርተህ የማንበብ ችሎታህን ለማዳበር ልምምድ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። መጀመሪያ አንድ አንቀጽ ብቻ አንብብ። ይህንን አንቀጽ ምንም ሳትሳሳት ማንበብ እስክትችል ድረስ ደግመህ ደጋግመህ ተለማመደው። ከዚያ ወደሚቀጥለው አንቀጽ ታልፋለህ። በመጨረሻ አንድም ቃል ሳትገድፍ፣ ሳትደግም ወይም ሳትሳሳት የተወሰኑ ገጾችን ለማንበብ ሞክር። ይህንን ካደረግህ በኋላ አንድ ሰው ስታነብብ እየተከታተለ ምናልባት የምትሳሳትባቸው ቦታዎች ካሉ እንዲጠቁምህ አድርግ።
በአንዳንድ አካባቢዎች ለንባብ ችግር ምክንያት የሚሆኑት የዓይን ሕመምና በቂ ብርሃን ማጣት ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ከተስተካከሉ ንባቡ እንደሚሻሻል የታወቀ ነው።
ጥሩ የማንበብ ችሎታ ያላቸው ወንድሞች ውሎ አድሮ በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት እና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት አንባቢ ሆነው ይመደቡ ይሆናል። ይሁንና ቃላቱን አስተካክሎ መጥራት መቻል ብቻውን ይህን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይረዳል ማለት አይደለም። በጉባኤ ጥሩ አንባቢ ለመሆን በግልህ ስታነብ ጥሩ አድርገህ የማንበብ ልማድ ማዳበር ይኖርብሃል። ይህም እያንዳንዱ ቃል በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ያለውን ድርሻ መገንዘብን የሚጠይቅ ነው። አንዳንዶቹን ቃላት ቸል ካልክ ሐሳቡን በግልጽ ለመረዳት ትቸገራለህ። ለራስህም ስታነብ ቢሆን ቃላቱን አሳስተህ የምታነብብ ከሆነ የዓረፍተ ነገሩ መልእክት ይዛባል። ቃላቱን በተሳሳተ መንገድ የምናነብበው በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ሳንገነዘብ ስንቀር ነው። እያንዳንዱ ቃል በዚያ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ምን ትርጉም እንዳለው ለመረዳት ሞክር። ሥርዓተ ነጥቦች በዓረፍተ ነገሩ ትርጉም ላይ ስለሚያስከትሉትም ለውጥ አስብ። ብዙውን ጊዜ የተሟላ መልእክት ያለው ሐሳብ ለማስተላለፍ ከአንድ በላይ ቃላት እንደሚያስፈልጉ አትዘንጋ። በምታነብበት ጊዜ አንድን ቃል በተናጠል ከማየት ይልቅ በርከት ያሉ ቃላትን አንድ ላይ ለማንበብ ሞክር። የምታነብበውን ነገር በግልጽ ከተረዳኸው ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ ትክክለኛ እውቀት ለማስተላለፍ ትችላለህ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለማንበብ ትጋ’ የሚለውን ምክር የጻፈው ተሞክሮ ላለው ክርስቲያን ሽማግሌ ነበር። (1 ጢሞ. 4:13) በዚህ ረገድ ሁላችንም ማሻሻያ ማድረግ እንችላለን።