ጥናት 4
ቅልጥፍና
ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ አንዳንድ ቃላት ላይ ትደነቃቀፋለህ? ወይም ደግሞ ንግግር ስትሰጥ ብዙውን ጊዜ ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ትቸገራለህ? ከሆነ በቅልጥፍና ረገድ ችግር አለብህ ማለት ሊሆን ይችላል። ቅልጥፍና ያለው ተናጋሪ ሲናገርም ሆነ ሲያነብብ ያለ ችግርና ያለምንም መደነቃቀፍ ቃላቱን ማውጣትና ሐሳቡን መግለጽ ይችላል። ይህ ማለት ግን ያለፋታ ያወራል፣ በጣም ይፈጥናል ወይም እንዳመጣለት ይናገራል ማለት አይደለም። ንግግሩ ማራኪና ለዛ ያለው ይሆናል። ይህ የንግግር ባሕርይ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ቅልጥፍና እንዳይኖርህ እንቅፋት የሚሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ምናልባት ከዚህ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት መካከል ለየት ያለ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባህ ነጥብ ይኖር ይሆን? (1) ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ አንዳንድ እንግዳ ቃላት ካጋጠሙህ እየቆጠርህ ማንበብ ትጀምር ይሆናል። (2) አሁንም አሁንም ቆም የምትል ከሆነ ሐሳቡ የተቆራረጠ ይሆናል። (3) የዝግጅት ማነስ ለችግሩ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። (4) ንግግር ስትሰጥ ቅልጥፍና እንዳይኖርህ የሚያደርገው የተለመደ ችግር ነጥቦችህ በቅደም ተከተል ተደራጅተው አለመቀመጣቸው ነው። (5) አንድ ሰው የሚያውቃቸው ቃላት ውስን ከሆኑም ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ሲሞክር ሊደነቃቀፍ ይችላል። (6) አጽንኦት የሚሰጣቸው ቃላት ከበዙም ቅልጥፍና አይኖረውም። (7) የሰዋስው ሕግን በሚገባ አለማወቅም ቅልጥፍና እንዳይኖር እንቅፋት ሊሆን ይችላል።
ቅልጥፍና ከሌለህ አድማጮችህ ቃል በቃል የመንግሥት አዳራሹን ለቅቀው ባይወጡም በሐሳብ ሊባዝኑ ይችላሉ። ከዚህም የተነሣ የምትናገረው አብዛኛው ነገር ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ሊቀር ይችላል።
በሌላ በኩል ደግሞ አድማጮችን ለተግባር የሚቀሰቅስና ቅልጥፍና ያለው እንዲሆን ያሰብከው ንግግር አድማጮችን የሚኮንን አልፎ ተርፎም የሚያሸማቅቅ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብሃል። በአንተና በአድማጮችህ መካከል ካለው የአስተዳደግ ልዩነት የተነሳ አድማጮችህ ለሰዎች ስሜት እንደማትጠነቀቅ ወይም ንግግርህ ቅንነት እንደሚጎድለው ከተሰማቸው የተነሣህበት ዓላማ መና ሊቀር ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ልምድ ያለው ተናጋሪ ቢሆንም እንኳ አላግባብ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ላለመሳብ ሲል የቆሮንቶስ ሰዎችን የቀረባቸው “በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥ” መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው።—1 ቆሮ. 2:3
ሊወገዱ የሚገባቸው ልማዶች። ብዙ ሰዎች በሚናገሩበት ጊዜ “እ-እ-እ” የማለት ልማድ አላቸው። ሌሎች ደግሞ አንድ ሐሳብ ከመጀመራቸው በፊት “አሁን” የሚለውን ቃል ወይም በተናገሩ ቁጥር “እንግዲያው” ወይም “ስለዚህ” የሚሉትንና እነዚህን የመሳሰሉ ማያያዣዎች ይደጋግማሉ። ምናልባት እንደነዚህ ያሉትን መግለጫዎች ምን ያህል ደጋግመህ እንደምትጠቀም አይታወቅህ ይሆናል። አንድ ሰው ስትናገር እንዲያዳምጥህና እነዚህን ቃላት በጠራህ ቁጥር እንዲደግምልህ ልታደርግ ትችላለህ። ቃላቱን ምን ያህል እንደምትደጋግማቸው ስታስተውል ትገረም ይሆናል።
አንዳንድ ሰዎች ሲያነብቡም ሆነ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ወደኋላ እየተመለሱ ያሉትን ነገር የመድገም ልማድ አላቸው። ይህም አንድ ዓረፍተ ነገር ጀምረው መሃል ከደረሱ በኋላ አቋርጠው ወደኋላ በመመለስ ቢያንስ የተወሰነውን ክፍል እንደገና ይደግማሉ ማለት ነው።
ሌሎች ደግሞ የሚናገሩበት ፍጥነት በቂ ሆኖ ሳለ አንድ ሐሳብ ይጀምሩና ዓረፍተ ነገሩን ሳይቋጩ ወደ ሌላ ሐሳብ ይሸጋገራሉ። ቃላቱ ያለ አንዳች እንቅፋት የሚንቆረቆሩ ቢሆንም ድንገተኛ የሐሳብ ለውጥ መደረጉ ለንግግሩ ቅልጥፍና እንቅፋት ይሆናል።
ማሻሻል የሚቻልበት መንገድ። እየተናገርህ ሳለ ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት የምትቸገር ከሆነ የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ለመጨመር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች እንዲሁም ሌሎች ጽሑፎች ስታነብብ ለአንተ አዲስ የሆኑ ቃላትን ልብ ለማለት ሞክር። የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምን እንደሆነ ለማወቅ መዝገበ ቃላት ተመልከት። ከዚያም አንዳንዶቹን ከአሁን ቀደም ከምታውቃቸው ቃላት ጋር ተጠቀምባቸው። በቋንቋህ መዝገበ ቃላት የማይገኝ ከሆነ ቋንቋውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው እንዲረዳህም ልትጠይቅ ትችላለህ።
ድምፅን ከፍ አድርጎ የማንበብ ልማድ ማዳበር በዚህ ረገድ ለማሻሻል ይረዳል። አስቸጋሪ ሆነው ያገኘሃቸውን ቃላት ድምፅህን ከፍ አድርገህ ደጋግመህ ተለማመዳቸው።
ንባብህ ቅልጥፍና ያለው እንዲሆን ቃላቱ በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ያላቸውን አገባብ መረዳት ይኖርብሃል። የጸሐፊውን መልእክት በትክክል ለማስተላለፍ በርከት ያሉ ቃላትን አንድ ላይ ማንበብ ያስፈልጋል። አንድ ላይ መሆን ያለባቸውን ቃላት ልብ በል። ምልክት ማድረግ እንደሚሻል ከተሰማህ እንደዚያ ማድረግ ትችላለህ። ግብህ ቃላቱን በትክክል ማንበብ ብቻ ሳይሆን ሐሳቡን ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተላለፍም ነው። ከአንቀጹ ጋር በደንብ እስክትተዋወቅ ድረስ ዓረፍተ ነገሮቹን አንድ በአንድ አጥናቸው። የሐሳቡን ቅደም ተከተል በደንብ ተረዳ። ከዚያም ድምፅህን ከፍ አድርገህ ተለማመድ። ሳትደነቃቀፍና አለቦታው ሳትቆም ማንበብ እስክትችል ድረስ አንቀጹን ደግመህ ደጋግመህ አንብበው። ከዚያ ወደሚቀጥለው አንቀጽ ተሻገር።
ከዚያ ደግሞ ፍጥነትህን ጨምር። ቃላቱ በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ያላቸውን አገባብ ከተረዳህ በአንድ ጊዜ በርከት ያሉ ቃላትን መመልከት ከመቻልህም ሌላ ቀጥሎ ያለውን ሐሳብ አስቀድመህ መገመት ትችላለህ። ይህም ለንባብህ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
አንድን ጽሑፍ ያለ ቅድሚያ ዝግጅት ማንበብን ልማድ ማድረግ ጠቃሚ ሥልጠና ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አስቀድመህ ሳትዘጋጅ የዕለቱን ጥቅስና አብሮ የተሰጠውን ሐሳብ ድምፅህን ከፍ አድርገህ የማንበብ ልማድ አዳብር። አንድን ቃል በተናጠል ከማየት ይልቅ የተወሰነ መልእክት የሚያስተላልፉ በርከት ያሉ ቃላትን ለማየት ሞክር።
ከሰዎች ጋር ስትወያይ ንግግርህ ቅልጥፍና እንዲኖረው፣ ከመናገርህ በፊት ምን እንደምትል ማሰብ ይኖርብሃል። ዕለት ተዕለት ከሰዎች ጋር ስትነጋገር ይህን ልማድ አዳብር። መናገር ከመጀመርህ በፊት ምን መልእክት ማስተላለፍ እንደምትፈልግና በምን ቅደም ተከተል እንደምትናገረው አስብ። አትጣደፍ። መሃል ላይ ሳትቆም ወይም የሐሳብ ለውጥ ሳታደርግ በአንድ ጊዜ አንድ የተሟላ መልእክት ለማስተላለፍ ሞክር። ዓረፍተ ነገሮችህ አጭርና ቀላል መሆናቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል።
ምን ማለት እንደፈለግህ ጠንቅቀህ የምታውቅ ከሆነ ቃላቱ በቀላሉ ይመጡልሃል። አብዛኛውን ጊዜ የምትጠቀምባቸውን ቃላት አስቀድሞ መምረጥ አያስፈልግም። እንዲያውም ሐሳቡ ብቻ ግልጽ እንዲሆንልህ ካደረግህ በኋላ የምትጠቀምባቸውን ቃላት እየተናገርህ ሳለህ ማሰቡ ጥሩ ልምምድ ሊሆንልህ ይችላል። ይህን ካደረግህና አእምሮህ በቃላቱ ላይ ሳይሆን በሐሳቡ ላይ ካተኮረ ቃላቱ ብዙም ሳትጨነቅ ሊመጡልህ ይችላሉ። ይህም በውስጥህ ያለውን ስሜት በሚገባ ለመግለጽ ያስችልሃል። ይሁን እንጂ ስለምትናገረው ሐሳብ ሳይሆን ስለ ቃላቱ ማሰብ ከጀመርህ ንግግርህ ሊደነቃቀፍ ይችላል። ብዙ ልምምድ ባደረግህ መጠን ጥሩ ተናጋሪና አንባቢ ለመሆን የሚረዳውን የቅልጥፍና ባሕርይ ልታዳብር ትችላለህ።
ሙሴ ይሖዋን በመወከል ወደ እስራኤል ሕዝብና ወደ ግብጹ ፈርዖን እንዲሄድ ሲላክ ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር። ለምን? አንደበተ ርቱዕ ሰው ስላልነበረ ነው። ምናልባትም የመኮላተፍ ችግር ኖሮበት ሊሆን ይችላል። (ዘጸ. 4:10፤ 6:12) ሙሴ የራሱን ምክንያቶች ቢያቀርብም አምላክ አልተቀበለውም። ይሖዋ አሮንን እንደ ቃል አቀባይ አድርጎ ከመላክም በተጨማሪ ሙሴ ራሱ መናገር እንዲችል ረድቶታል። ሙሴ ለግለሰቦች ወይም ጥቂት ቁጥር ላላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጭምር በተደጋጋሚ ጥሩ አድርጎ ለመናገር በቅቷል። (ዘዳ. 1:1-3፤ 5:1፤ 29:2፤ 31:1, 2, 30፤ 33:1) በይሖዋ በመታመን አቅምህ የሚፈቅድልህን ሁሉ ካደረግህ አንተም አንደበትህን አምላክን ለማክበር ልትጠቀምበት ትችላለህ።