ጥናት 38
በጉጉት ለማዳመጥ የሚጋብዝ መግቢያ
ለማንኛውም ንግግር ቢሆን መግቢያ ወሳኝ ነው። መግቢያህ አድማጮች በጉጉት እንዲያዳምጡ የሚጋብዝ ከሆነ ቀጥሎ የምትናገረውን በጥሞና ይከታተሉሃል። አገልግሎት ላይ የምትጠቀምበት መግቢያ ለመስማት የሚያጓጓ ካልሆነ መናገር የፈለግኸውን ሐሳብ ላያስጨርሱህ ይችላሉ። በመንግሥት አዳራሽ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ አድማጮች በትኩረት እንዲከታተሉህ ማድረግ ካልቻልክ ቃል በቃል አዳራሹን ጥለው ባይወጡም አንዳንዶቹ ስለሌላ ነገር ማሰብ ሊጀምሩ ይችላሉ።
መግቢያህን በምትዘጋጅበት ጊዜ ሦስት ዓላማዎች ሊኖሩህ ይገባል። (1) አድማጮች በትኩረት እንዲከታተሉህ ማድረግ፣ (2) ርዕሰ ጉዳዩ ምን እንደሆነ በግልጽ ማስቀመጥ እንዲሁም (3) ትምህርቱ እንደሚጠቅማቸው መጠቆም ናቸው። ሦስቱንም ዓላማዎች በአንድ ጊዜ የሚያሳካ መግቢያ መጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ ልትሠራባቸውም ትችላለህ። ይህን ለማድረግ የግድ ከላይ ያለውን ቅደም ተከተል መጠበቅ አያስፈልግም።
አድማጮች በትኩረት እንዲከታተሉህ ማድረግ የምትችልበት መንገድ። ሰዎች ንግግሩን ለማዳመጥ በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል ማለት በጥሞና ይከታተላሉ ማለት አይደለም። ለምን? በኑሯቸው ብዙ የሚያሳስቧቸው ጉዳዮች አሉ። ቤታቸው ውስጥ ያለ ችግር ወይም ሌላ ጉዳይ ያስጨንቃቸው ይሆናል። ንግግርህን በምታቀርብበት ጊዜ ትልቁ ፈተና አድማጮች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በትኩረት እንዲከታተሉህ ማድረግ መቻልህ ነው። ለዚህ የሚረዱ በርካታ መንገዶች አሉ።
እስከ ዛሬ ከተሰጡት እጅግ ድንቅ ንግግሮች አንዱ የተራራው ስብከት ነው። የዚህ ንግግር መግቢያ ምን ነበር? በሉቃስ ዘገባ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- ‘እናንተ ድሆች ደስተኞች ናችሁ፣ እናንተ አሁን የምትራቡ ደስተኞች ናችሁ፣ እናንተ አሁን የምታለቅሱ ደስተኞች ናችሁ፣ ሰዎች ሲጠሉአችሁ ደስተኞች ናችሁ።’ (ሉቃስ 6:20-22) ይህ መግቢያ በጉጉት ለማዳመጥ የሚጋብዝ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ የጠቀሰው ሰዎቹ ያሉባቸውን ከባድ ችግሮች ስለሆነ ነው። ቀጥሎ ስለ ችግሮቻቸው በሰፊው ከማተት ይልቅ ችግር እያለባቸውም እንኳ ደስተኛ መሆን እንደሚችሉ ገልጿል። አነጋገሩም ቢሆን አድማጮቹ በጉጉት እንዲከታተሉት የሚጋብዝ ነበር።
ጥያቄ መጠየቅ አድማጮች በጉጉት እንዲያዳምጡ ለማነሳሳት የሚረዳ ግሩም ዘዴ ነው። ሆኖም የምትመርጣቸው ጥያቄዎች ተስማሚ ሊሆኑ ይገባል። ጥያቄውን ስታነሳ ከአሁን ቀደም ስለሚያውቁት ጉዳይ ልትናገር እንደሆነ ከተሰማቸው የማዳመጥ ፍላጎታቸው ሊጠፋ ይችላል። አድማጮችን የሚያሸማቅቁ ወይም የሚያሳጡ ጥያቄዎች አትጠይቅ። ከዚህ ይልቅ የጥያቄዎችህ አቀራረብ አድማጮች እንዲያስቡ የሚያደርግ ሊሆን ይገባል። አድማጮች ለራሳቸው መልስ መስጠት የሚችሉበት ፋታ እንዲያገኙ ትንሽ ቆም በል። በሐሳባቸው ከአንተ ጋር እየተወያዩ እንዳለ እንዲሰማቸው ካደረግህ በትኩረት እየተከታተሉህ ነው ማለት ነው።
አድማጮች በጉጉት እንዲያዳምጡ ማድረግ የሚያስችለው ሌላው ጥሩ ዘዴ ተሞክሮ መናገር ነው። የምትናገረው ተሞክሮ ከአድማጮችህ መካከል አንዳንዶቹን የሚያሸማቅቅ ከሆነ አንድ ታሪክ ተናግረህ መጀመርህ ብቻ ዓላማህን ለማሳካት አይረዳም። አድማጮች ታሪኩን ብቻ አስታውሰው በዚያ አማካኝነት ማስተላለፍ የፈለግኸውን ትምህርት ከረሱት ዓላማህ ግቡን አልመታም። በመግቢያህ ላይ የምትጠቅሰው ተሞክሮ በንግግርህ መሃል ከምታነሳቸው ጉልህ ነጥቦች ጋር ሊያያዝ የሚችል መሆን ይኖርበታል። ተሞክሮውን ሕያው አድርገህ ለመተረክ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን መጥቀስ ሊያስፈልግህ ቢችልም ከልክ በላይ መርዘም የለበትም።
አንዳንድ ተናጋሪዎች በቅርቡ በዜና የሰሙትን፣ ጋዜጣ ላይ ያነበቡትን ወይም ከሌላ የታወቀ ምንጭ ያገኙትን ሐሳብ በመጥቀስ ንግግራቸውን ይጀምራሉ። የሚጠቅሱት ነገር ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የሚሄድና ከአድማጮች ሁኔታ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ ጥሩ መግቢያ ሊሆን ይችላል።
ከአገልግሎት ስብሰባ ወይም ከሲምፖዚየም ተከታታይ ንግግሮች አንዱን የምታቀርብ ከሆነ ብዙውን ጊዜ መግቢያህ እጥር ምጥን ያለና ያልተወሳሰበ ቢሆን ይመረጣል። የሕዝብ ንግግር የምታቀርብ ከሆነ በአስተዋጽኦው ላይ ለመግቢያ ከተመደበልህ ጊዜ በላይ ማጥፋት የለብህም። ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ትምህርት ያለው በቀረው የንግግሩ ክፍል ውስጥ ነው።
ተጠራጣሪ አልፎ ተርፎም ተቃዋሚ ለሆኑ አድማጮች ንግግር የምትሰጥበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። ጆሮአቸውን እንዲሰጡህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ‘መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላበት’ መሆኑ የተነገረለት እስጢፋኖስ የተባለው የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያን በአይሁድ የሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት እንዲቀርብ ተደርጎ ነበር። በዚህ ሸንጎ ፊት ቆሞ አሳማኝ በሆነ መንገድ ክርስትናን ደግፎ ተናግሯል። ንግግሩን የጀመረው እንዴት ነበር? በቅድሚያ አክብሮቱን ከገለጸ በኋላ በጋራ የሚያስማማቸውን ጉዳይ ጠቅሷል። ‘ወንድሞችና አባቶች ሆይ፣ ስሙ። የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም ታየ’ ብሏል። (ሥራ 6:3፤ 7:2) ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና አርዮስፋጎስ ለነበሩት የተለየ አመለካከት ያላቸው አድማጮቹ ሲናገር “የአቴና ሰዎች ሆይ፣ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ” በማለት ተስማሚ መግቢያ ተጠቅሟል። (ሥራ 17:22) እስጢፋኖስም ሆነ ጳውሎስ የተጠቀሙበት መግቢያ ጥሩ ስለነበር አድማጮቻቸው ጆሮአቸውን ሰጥተዋቸዋል።
አንተም በአገልግሎት ስትሰማራ ሰዎች በትኩረት እንዲያዳምጡህ ማድረግ መቻል ይኖርብሃል። ቤቱ የሄድከው በቀጠሮ ካልሆነ ሰውዬው ሥራ ላይ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ አካባቢዎች እንግዳ የሆነ ሰው የመጣበትን ዓላማ ቶሎ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የሄድክበትን ዓላማ በቀጥታ ከመግለጽህ በፊት እንደ አካባቢው ልማድ ልታደርገው የሚገባህ ነገር ይኖራል።—ሉቃስ 10:5
ያም ሆነ ይህ በወዳጅነት መቅረብህ ጥሩ ውይይት ማድረግ የምትችሉበትን በር ይከፍትልሃል። ብዙውን ጊዜ ሰውዬው የሚያሳስበውን ጉዳይ በቀጥታ በመጥቀስ መጀመሩ ጠቃሚ ይሆናል። ይህንን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ሰውዬውን ስታገኘው ምን እያደረገ እንደነበር ልብ በል። እርሻ ላይ ሆኖ፣ ግቢውን ሲያሰማምር፣ መኪናውን ሲጠግን፣ ምግብ ሲያበስል፣ ልብስ ሲያጥብ ወይም ልጆቹን ሲንከባከብ አግኝተኸው ይሆናል። ጋዜጣ ሲያነብብ ወይም በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ቆሞ ሲመለከት ነው ያገኘኸው? ዓሣ ማጥመድ፣ ስፖርት፣ ሙዚቃ፣ ጉዞ፣ ኮምፒውተር ወይም ሌላ ነገር እንደሚወድድ የሚጠቁም ምን ነገር አስተውለሃል? ሰዎች ብዙውን ጊዜ በራዲዮ የሚሰሙት ወይም በቴሌቪዥን የሚያዩት ዜና ያሳስባቸዋል። ከእነዚህ ጉዳዮች ስለ አንዱ ጥያቄ በማንሳት ወይም አጭር አስተያየት በመሰንዘር ጥሩ ውይይት ማድረግ ትችላለህ።
ኢየሱስ በሲካር የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር እንደተነጋገረ የሚገልጸው ታሪክ ለሰዎች ለመመስከር በማሰብ እንዴት ውይይት መጀመር እንደሚቻል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው።—ዮሐ. 4:5-26
በተለይ የጉባኤያችሁ የአገልግሎት ክልል በተደጋጋሚ የሚሸፈን ከሆነ በደንብ የታሰበበት መግቢያ ማዘጋጀት ያስፈልግሃል። አለዚያ ሰዎችን ማወያየት አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል።
ርዕሰ ጉዳዩን ግልጽ ማድረግ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የመድረክ ሊቀ መንበር ሆኖ የሚያገለግለው ወይም ከአንተ በፊት ክፍል የሚያቀርበው ወንድም የንግግርህን ርዕስና ስምህን ማስተዋወቁ አይቀርም። ያም ሆኖ መግቢያህ ላይ ከምትናገረው ሐሳብ ጋር አያይዘህ ርዕስህን መጠቆምህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይህን ስታደርግ ጭብጡን በቀጥታ መጥቀስ ትችል ይሆናል፤ ግን የግድ እንደዚያ መደረግ አለበት ማለት አይደለም። ያም ሆነ ይህ ንግግሩን እያብራራህ ስትሄድ ጭብጡ ይበልጥ ግልጽ ሊሆን ይገባል። በተቻለ መጠን መግቢያህ ላይ ለርዕሰ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ይኖርብሃል።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲሰብኩ ሲልካቸው “ሄዳችሁም:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ” በማለት የሚናገሩትን መልእክት በግልጽ አስቀምጦላቸዋል። (ማቴ. 10:7) ስለ እኛ ዘመንም ሲናገር “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ብሏል። (ማቴ. 24:14) ‘ቃሉን እንድንሰብክ’ ተመክረናል። ይህም በምንመሰክርበት ጊዜ የምንናገረው ነገር ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ማለት ነው። (2 ጢሞ. 4:2) ይሁን እንጂ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ከመሄድህ ወይም ስለ አምላክ መንግሥት መናገር ከመጀመርህ በፊት ሰውዬውን ስለሚያሳስበው ወቅታዊ ጉዳይ መጥቀስህ አስፈላጊ ነው። ሆኖም መልእክታችን ምሥራች ስለሆነ በዓለም ላይ ስላሉት ችግሮች ብዙ መዘርዘር አያስፈልግም። ውይይታችሁ በአምላክ ቃልና በመንግሥቱ ተስፋ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ጥረት አድርግ።
ትምህርቱ እንደሚጠቅማቸው ግልጽ ማድረግ። በጉባኤ ውስጥ ንግግር ስትሰጥ አብዛኞቹ አድማጮች ደስ ብሏቸው እንደሚሰሙ በተወሰነ መጠን እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ይሁንና አንድ ሰው እርሱን በቀጥታ ስለሚመለከት ጉዳይ ሲነገረው እንደሚያዳምጠው በጥሞና ያዳምጣሉ? ትምህርቱ እነርሱን እንደሚመለከት ተሰምቷቸው ምን ማድረግ ይኖርብኝ ይሆን በሚል ጉጉት በትኩረት ይከታተሉሃል? አድማጮች በዚህ መልኩ እንዲከታተሉ ማነሳሳት የምትችለው በዝግጅትህ ወቅት ስለ እነርሱ ሁኔታ፣ ስለሚያሳስባቸው ጉዳይ እንዲሁም ስለ አመለካከታቸውና ዝንባሌያቸው በጥሞና ካሰብክ ብቻ ነው። ከዚያም መግቢያህ እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ አስገብተህ እንደተዘጋጀህ የሚጠቁም ሊሆን ይገባል።
ንግግር ስትሰጥም ይሁን ለአንድ ሰው ስትመሰክር አድማጮች ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉህ ማድረግ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው ዘዴ እነርሱን እንደሚመለከት አድርገህ ማቅረብ ነው። እነርሱን የሚያሳስባቸው ችግር ወይም ጥያቄ ከምትወያዩበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር ያለውን ዝምድና ግልጽ አድርግላቸው። ጉዳዩን እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ሳይሆን በጥልቀት እንደምታብራራ ግልጽ ከሆነላቸው ይበልጥ በአንክሮ ሊያዳምጡህ ይችላሉ። በጥልቀት ለማብራራት ግን ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብሃል።
መግቢያህን የምትናገርበት መንገድ። መግቢያህ ላይ የምትናገረው ነገር በጣም ወሳኝ ነው። ይሁን እንጂ የምትናገርበትም መንገድ የአድማጮችህን ፍላጎት ለማነሳሳት የራሱ ድርሻ አለው። ስለዚህ መዘጋጀት ያለብህ ምን እንደምትል ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምትናገርም ጭምር ነው።
መግቢያህ ላይ የምትጠቀምባቸውን ቃላት መምረጥ ዓላማህን ለማሳካት ስለሚረዳ የመጀመሪያዎቹን ሁለትና ሦስት ዓረፍተ ነገሮች በጥንቃቄ መዘጋጀትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙውን ጊዜ አጭርና ቀላል ዓረፍተ ነገሮችን መጠቀምህ የተሻለ ይሆናል። በጉባኤ ንግግር ስታቀርብ በመግቢያህ ላይ የምትጠቀምባቸው ቃላት ተፈላጊው ኃይል እንዲኖራቸው ስትል እነዚህን ዓረፍተ ነገሮች በማስታወሻ ጽፈህ ልትይዝ ወይም በቃልህ ልታጠናቸው ትችላለህ። መግቢያህን ሳትጣደፍ በጥሩ መንገድ መናገር ከቻልክ ቀሪውን የንግግሩን ክፍል ተረጋግተህ ማቅረብ ትችላለህ።
መግቢያህን መዘጋጀት ያለብህ መቼ ነው? በዚህ ረገድ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት የተለያየ ነው። አንዳንድ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች አንድ ሰው መግቢያውን መዘጋጀት ያለበት መጀመሪያ ላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ አንድ ሰው መግቢያውን መዘጋጀት ያለበት ንግግሩን ተዘጋጅቶ ሲጨርስ ነው የሚል አመለካከት አላቸው።
ለንግግርህ ተስማሚ መግቢያ ከመዘጋጀትህ በፊት ርዕሰ ጉዳዩንና የምታብራራቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ማወቅ እንዳለብህ ምንም ጥርጥር የለውም። ንግግሩን የምታቀርበው ተዘጋጅቶ ከተሰጠህ አስተዋጽኦ ቢሆንስ? አስተዋጽኦውን ካነበብህ በኋላ ለመግቢያ የምትጠቀምበት አንድ ሐሳብ ከመጣልህ ልትጽፈው ትችላለህ። ጥሩ መግቢያ ለመዘጋጀት አድማጮችህንም ሆነ አስተዋጽኦው ላይ ያለውን ትምህርት ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለብህ አትዘንጋ።