ጥናት 39
ግቡን የሚመታ መደምደሚያ
የንግግርህን ነጥቦች ለመምረጥ ጥሩ ምርምር አድርገህ እንዲሁም በታሰበበት መንገድ አዋቅረሃቸው ሊሆን ይችላል። አድማጮች በጉጉት እንዲያዳምጡ የሚጋብዝ መግቢያም ተዘጋጅተህ ይሆናል። ሆኖም ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ግቡን የሚመታ መደምደሚያ ያስፈልግሃል። የዚህን አስፈላጊነት አቅልለህ ልትመለከተው አይገባም። ብዙውን ጊዜ መጨረሻ የምትናገረው ነገር ቶሎ አይረሳም። መደምደሚያህ ጥሩ ካልሆነ ከዚያ በፊት የተናገርኸው ነገር ሁሉ መና ሊቀር ይችላል።
አንድ ምሳሌ እንመልከት:- ኢያሱ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ለእስራኤል ሽማግሌዎች የማይረሳ ንግግር ሰጥቶ ነበር። ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ከዘረዘረ በኋላ ንግግሩን የደመደመው ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች በመከለስ ብቻ ነበርን? አይደለም። ከዚህ ይልቅ “እግዚአብሔርን ፍሩ፣ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት” ሲል ሕዝቡን ከልቡ አጥብቆ አሳስቧል። ኢያሱ 24:14, 15ን አውጣና የተጠቀመበትን መደምደሚያ አንብብ።
ሌላው ምሳሌ ደግሞ በሥራ 2:14-36 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውና ሐዋርያው ጴጥሮስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች የሰጠው ንግግር ነው። በመጀመሪያ አምላክ መንፈሱን እንደሚያፈስስ በኢዩኤል አማካኝነት የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም እንዳዩ አስረድቷል። ከዚያም ይህ ክንውን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እንደሚያገኝና በአምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ እንደሚል ከሚናገሩት በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ መሲሐዊ ትንቢቶች ጋር ያለውን ዝምድና አብራርቷል። ከዚያም ጴጥሮስ ሲደመድም በዚያ የተገኙ ሁሉ ሊቀበሉት የሚገባውን አንድ ሐቅ እንዲህ ሲል ጠቅሷል:- “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” በዚህ ጊዜ ሰዎቹ “ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?” አሏቸው። ጴጥሮስም መልሶ “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” ሲል ተናገረ። (ሥራ 2:37, 38) በዚያኑ ዕለት 3, 000 የሚያክሉ ሰዎች በሰሙት ነገር ተነክተው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት ተቀብለዋል።
ልታስብባቸው የሚገቡ ነጥቦች። መደምደሚያህ ላይ የምትጠቅሰው ሐሳብ ከንግግርህ ጭብጥ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ መሆን ይኖርበታል። ስታብራራቸው የነበሩትን ዋና ዋና ነጥቦች የሚቋጭ ሊሆን ይገባል። በመደምደሚያህ ውስጥ የጭብጡን አንዳንድ ቁልፍ ቃላት ማካተት ትፈልግ ይሆናል። ጭብጡን በቀጥታ መጥቀስም ከፈለግህ ትችላለህ።
በመሠረቱ ንግግር ስታቀርብ ዓላማህ አድማጮች ትምህርቱን ሰምተው አንድ እርምጃ እንዲወስዱ ማበረታታት ነው። የመደምደሚያ አንዱ ዓላማ አድማጮች ሊወስዱት የሚገባውን እርምጃ ማስገንዘብ ነው። ጭብጡንና ዋና ዋና ነጥቦቹን ስትመርጥ ትምህርቱ ለአድማጮችህ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያትና ንግግሩን የምታቀርብበትን ዓላማ በጥሞና አስበህበታልን? ከሆነ አድማጮችህ እንዲወስዱት የምትፈልገው አንድ እርምጃ አለ ማለት ነው። ስለዚህ ሊወስዱት የሚገባው እርምጃ ምን እንደሆነና ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማብራራት ይኖርብሃል።
መደምደሚያህ አድማጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁም ብቻ ሳይሆን ለሥራ የሚቀሰቅስ መሆን ይኖርበታል። ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸው ለምን እንደሆነ አሳማኝ ምክንያት የሚያቀርብና በመታዘዛቸው የሚያገኙትን ጥቅም የሚገልጽ ሊሆን ይገባል። የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር በደንብ የታሰበበትና በተመረጡ ቃላት የተዋቀረ ከሆነ ንግግርህ በአድማጮች ላይ የሚኖረውን በጎ ውጤት ይበልጥ የሚያጠናክር ይሆናል።
ንግግርህን ወደ መቋጨቱ እየተቃረብህ እንዳለ አትዘንጋ። የምትናገረው ነገር ይህንኑ የሚጠቁም መሆን ይኖርበታል። ፍጥነትህም ቢሆን ተስማሚ ሊሆን ይገባል። እስከ መጨረሻው ድረስ በፍጥነት ስትናገር ቆይተህ ድንገት ማቆም የለብህም። በሌላ በኩል ደግሞ የድምፅህም መጠን ቢሆን በጣም ማነስ ወይም መብዛት የለበትም። መጨረሻ ላይ የምትናገራቸው ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ንግግርህን መደምደምህ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ የሚያረጋግጡ መሆን ይኖርባቸዋል። እነዚህን ዓረፍተ ነገሮች የምትናገረው በእርግጠኝነት መሆን ይኖርበታል። ንግግርህን እንዴት እንደምታቀርብ በምትለማመድበት ጊዜ መደምደሚያህንም መለማመድ እንዳለብህ አትዘንጋ።
የመደምደሚያህ ርዝማኔ ምን ያህል መሆን ይኖርበታል? ይህ በጊዜ ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። መደምደሚያህ መንዛዛት የለበትም። ርዝማኔው ተስማሚ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን የሚረዳው አንዱ ነገር ግቡን የሚመታ መሆኑ ነው። የአንድ ንግግር መደምደሚያ ቀላል፣ ቀጥተኛና የሚያበረታታ ቢሆን ይመረጣል። በደንብ ታስቦበት የተዘጋጀ እስከሆነ ድረስ ረዘም ያለ መደምደሚያ ጥሩ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው መደምደሚያ አጠር ያለ ምሳሌ ያካተተም ሊሆን ይችላል። መክብብ 12:13, 14ን እና ማቴዎስ 7:24-27ን በማንበብ ሰፊ በሆነው የመክብብ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን አጭር መደምደሚያ ከተራራው ስብከት ረዘም ያለ መደምደሚያ ጋር አወዳድር።
በአገልግሎት። በተደጋጋሚ መደምደሚያ መጠቀም የሚያስፈልግህ አገልግሎት ላይ ነው። በደንብ የምትዘጋጅና ስለ ሰዎች ከልብ የምታስብ ከሆነ ጥሩ ውጤት ታገኛለህ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱትን ምክሮች ከአንድ ግለሰብ ጋር በምታደርገው ውይይትም ልትጠቀምባቸው ትችላለህ።
ከሰውዬው ጋር ረዘም ያለ ውይይት ለማድረግ በቂ ጊዜ ላይኖር ይችላል። ግለሰቡ ሥራ ላይ ይሆንና ውይይታችሁ በአጠቃላይ ከአንድ ደቂቃ የማይበልጥ ይሆናል። አመቺ ሆኖ ካገኘኸው እንዲህ ልትል ትችላለህ:- “ሥራ ላይ እንደሆኑ ይገባኛል። አንድ የሚያበረታታ ሐሳብ ብነግርዎ ደስ ይለኛል። ፈጣሪ የሰው ልጅ ወደፊት ገነት በምትሆነው በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር ዓላማ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እኛም በዚህ ገነት ውስጥ መኖር እንችላለን። ይሁን እንጂ በቅድሚያ አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ መማር ይኖርብናል።” አለዚያም እርሱ በሚመቸው ሌላ ጊዜ እንደምትመጣ ልትነግረው ትችላለህ።
ሰውዬው አልፈልግም ቢል አልፎ ተርፎም ቢያመናጭቅህና ውይይቱ ቢቋረጥ እንኳ መጨረሻ ላይ የምትናገረው ነገር አንድ መልካም ውጤት ሊኖረው ይችላል። በማቴዎስ 10:12, 13 እንዲሁም በሮሜ 12:17, 18 ላይ የሚገኘውን ምክር አስታውስ። የለዘበ መልስ መስጠትህ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያለውን አመለካከት እንዲያስተካክልም ሊረዳው ይችላል። ይህ ደግሞ አንድ ጥሩ ውጤት ነው።
በሌላ በኩል ከሰውዬው ጋር ጥሩ ውይይት አድርገህ ሊሆን ይችላል። እንዲያስታውሰው የምትፈልገውን ዋና ነጥብ ልትደግምለት ትችላለህ። እርምጃ እንዲወስድ በሚያነሳሳ መንገድ መናገር ይኖርብሃል።
በድጋሚ ተገናኝታችሁ መወያየት የምትችሉበት አጋጣሚ ካለ ቀጠሮአችሁን በጉጉት እንዲጠብቅ የሚያደርገው አንድ ጥያቄ ልታነሳ ትችላለህ። ምናልባት ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር ከተባለው መጽሐፍ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ተብለው ከተዘጋጁት ጽሑፎች ከአንዱ መምረጥ ትችል ይሆናል። ግብህ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ኢየሱስ እንደተናገረው ደቀ መዝሙር ማድረግ እንደሆነ አትዘንጋ።
መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠናስ? ጭብጡን ደግመህ መጥቀስህ ተማሪው የተወያያችሁበትን ነገር እንዲያስታውስ ይረዳዋል። ሳትጣደፍ በክለሳ ጥያቄዎቹ ላይ መወያየት ቁልፍ የሆኑት ነጥቦች በተማሪው አእምሮ እንዲቀረጹ ይረዳል። የተማረው ነገር እንዴት እንደሚጠቅመው ወይም ለሌሎች ሊያካፍላቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ መጠየቃችን ትምህርቱ ያለውን ጠቀሜታ እንዲያስብ ሊረዳው ይችላል።—ምሳሌ 4:7
ንግግርህ የተዋጣለት እንዲሆን መደምደሚያህ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ፈጽሞ መዘንጋት የለብህም!