የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 44 ገጽ 236-ገጽ 239 አን. 5
  • ጥያቄዎችን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥያቄዎችን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የማስተማርን ችሎታ ማዳበር
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ጥያቄዎችን መጠቀም
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • በአገልግሎት ረገድ ክህሎታችንን ማዳበር—ጥያቄዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2018
  • ታላቁን አስተማሪ ምሰሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 44 ገጽ 236-ገጽ 239 አን. 5

ጥናት 44

ጥያቄዎችን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ጥያቄዎችን የምትጠቀመው የተነሳህበትን ዓላማ በሚያሳካ መንገድ መሆን ይኖርበታል። ዓላማህ አድማጮች መልሱን እንዲነግሩህ ወይም ለራሳቸው እንዲያስቡበት ማድረግ ሊሆን ይችላል። የተሳካ ውጤት ለማግኘት የምታነሳው ጥያቄም ሆነ የምትጠይቅበት መንገድ ትልቅ ድርሻ አለው።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ጥያቄዎችን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም አድማጮች በውይይቱ እንዲመሰጡ ለማድረግ ይረዳል። አንድ ሰው ሲያስተምር በደንብ የታሰበበት ጥያቄ የሚጠይቅ ከሆነ የሚያገኘው መልስ ስለ አድማጩ ብዙ ነገር እንዲያስተውል ሊረዳው ይችላል።

አንድ ጥያቄ ከጠየቅህ አድማጮች ለአንተም ይሁን ለራሳቸው መልስ መስጠታቸው ስለማይቀር ውይይቱን በተመስጦ እንዲከታተሉ ይረዳቸዋል። ጥያቄዎች ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመርም ይሁን ውይይቱን ሕያው ለማድረግ ሊረዱህ ይችላሉ። ንግግር ስትሰጥም ይሁን ስታስተምር አድማጮችህ በጉጉት እንዲከታተሉህ፣ ጉዳዩን እንዲያመዛዝኑ ወይም ነጥቡ አጽንዖት እንዲሰጠው ለማድረግ ጥያቄዎችን ልትጠቀም ትችላለህ። ሰዎችን በምታነጋግርበት ጊዜ ጥያቄዎችን ጥሩ አድርገህ የምትጠቀም ከሆነ አእምሮአቸውን እንዲያሠሩ ስለምታደርጋቸው እንዲሁ አዳማጭ ብቻ አይሆኑም። አንድ ጥያቄ ስታነሣ ዓላማ ሊኖርህና አጠያየቅህም ይህንኑ ዓላማህን የሚያሳካ ሊሆን ይገባል።

ውይይት ለመጀመር። በምታገለግልበት ጊዜ ሰዎቹ ፈቃደኛ ሆነው ከተገኙ በተቻለ መጠን ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ለማበረታታት ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።

ብዙ ወንድሞችና እህቶች ከሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት ለመጀመር “ለመሆኑ . . . ብለው አስበው ያውቃሉ?” በማለት ይጠይቃሉ። የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አብዛኞቹን ሰዎች የሚያሳስቡ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ከሆነ በአገልግሎታቸው ተደስተው እንደሚመለሱ ምንም ጥርጥር የለውም። ጥያቄው ለሰውዬው አዲስ ቢሆንበት እንኳ የማወቅ ጉጉት ሊያሳድርበት ይችላል። “ምን ይመስልዎታል? . . .” “ስለዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አለዎት?” እንዲሁም “. . . ብለው ያምናሉ?” ብሎ በመጀመር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መወያየት ይቻላል።

ወንጌላዊው ፊልጶስ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብብ አግኝቶ “በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲል ጠየቀው። (ሥራ 8:​30) ፊልጶስ ይህን ጥያቄ በማንሳቱ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን እውነት ለዚህ ሰው ለማብራራት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝቷል። ዛሬ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን በማንሳት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በግልጽ ለመረዳት ከሚጓጉ ሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል።

ብዙ ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አጋጣሚ የምትሰጣቸው ከሆነ አንተ የምትናገረውንም ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆናቸው አይቀርም። ጥያቄ ከጠየቅህ በኋላ የሚናገሩትን በጥሞና አዳምጥ። ሰውዬው ለሰነዘረው አስተያየት የምትሰጠው ምላሽ ነቀፋ ያዘለ ሳይሆን ደግነት የሚንጸባረቅበት ሊሆን ይገባል። ከልብ እንድታመሰግነው የሚያስችል ምክንያት ካለ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትበል። ኢየሱስ በአንድ ወቅት አንድ ጸሐፊ “በማስተዋል እንደ መለሰለት” ባየ ጊዜ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” በማለት አመስግኖታል። (ማር. 12:​34) በተናገረው ነገር ባትስማማም እንኳ ሐሳቡን ስለገለጸልህ ብቻ ልታመሰግነው ትችላለህ። ሰውዬው የሰነዘረው አስተያየት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስትነግረው ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብህን ነገር እንድትገነዘብ ሊረዳህ ይችላል።

ቁልፍ የሆኑ ነጥቦችን ለማስተዋወቅ። ንግግር ስትሰጥም ይሁን ከግለሰቦች ጋር ስትወያይ ወደ አንድ ቁልፍ ነጥብ ሊመሩ የሚችሉ ጥያቄዎችን ለመጠቀም ሞክር። የምታነሳው ጥያቄ አድማጮችህን ከልብ የሚያሳስባቸውን ጉዳይ የሚመለከት መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም አድማጮች ለማወቅ እንዲጓጉ የሚያደርግ ትንሽ የሚያመራምር ጥያቄ ልታነሳ ትችላለህ። አንድ ጥያቄ ጠይቀህ ቆም ካልክ አድማጮችህ ቀጥሎ የምትናገረውን ነገር የመስማት ጉጉት ያድርባቸዋል።

በአንድ ወቅት ነቢዩ ሚክያስ ይሖዋ ከአምላኪዎቹ ስለሚፈልገው ነገር ከጠየቀ በኋላ አራት ተጨማሪ ጥያቄዎችን በተከታታይ አንስቷል። እነዚህ ጥያቄዎች በሐሳቡ መቋጫ ላይ ለሰጠው ጥልቅ ትርጉም ያዘለ መልስ የአድማጮቹን አእምሮ የሚያዘጋጁ ነበሩ። (ሚክ. 6:​6-8) አንተስ በምታስተምርበት ጊዜ ተመሳሳይ ዘዴ ልትጠቀም ትችላለህ? ለምን አትሞክረውም?

ስለ ጉዳዩ እንዲያመዛዝኑ ለመርዳት። አንድን ሐሳብ አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማስረዳት ጥያቄዎችን መጠቀም ይቻላል። በ⁠ሚልክያስ 1:​2-10 ላይ እንደምናነበው ይሖዋ በእስራኤል ሕዝብ ላይ መቆጣቱን ሲገልጽ ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሟል። በመጀመሪያ “ወድጃችኋለሁ” ብሏቸዋል። ሆኖም ፍቅሩን ማስተዋል ስለተሳናቸው “ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን?” ሲል ጠይቋቸዋል። ከዚያም ኤዶም ያለችበትን ሁኔታ እንደ ማስረጃ በመጥቀስ በክፋታቸው ምክንያት እንደጠላቸው ተናግሯል። እስራኤላውያን ለፍቅሩ ምላሽ ሳይሰጡ መቅረታቸውን ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ምሳሌዎችን ከጥያቄዎች ጋር አቀናጅቶ ተጠቅሟል። አንዳንዶቹን ጥያቄዎች ያቀረባቸው ከሃዲዎቹ ካህናት ራሳቸው እንደጠየቁ አድርጎ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ይሖዋ ለካህናቱ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ናቸው። ውይይቱ የቀረበበት መንገድ ስሜት የሚነካና የሚመስጥ ነው። ማስረጃው ምንም ማስተባበያ ሊቀርብበት የማይችል መልእክቱም ከአእምሮ የማይጠፋ ነው።

አንዳንድ ተናጋሪዎችም ጥያቄዎችን በተመሳሳይ መንገድ ጥሩ አድርገው ይጠቀማሉ። አድማጮች መልስ እንዲሰጡ ባይጠበቅባቸውም እንኳ ጥያቄ ስትጠይቅ መልሱን ማሰባቸው ስለማይቀር እያወያየሃቸው እንዳለ ያክል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ጊዜ ተማሪው መልስ የሚሰጥባቸውን ጥያቄዎች እንጠይቃለን። እርግጥ ተማሪው የተሻለ ጥቅም የሚያገኘው በራሱ አባባል ቢመልስ ነው። ተጨማሪ ጥያቄዎችን በደግነት በማንሳት ነጥቡ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንለት እርዳው። ቁልፍ ነጥቦችን በተመለከተ መልስ ሲሰጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንደማስረጃ እንዲጠቀም አበረታታው። በተጨማሪም እንዲህ እያልክ ልትጠይቀው ትችላለህ:- “አሁን እየተወያየንበት ያለው ነገር እስካሁን ካጠናነው ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ይህን ማጥናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በሕይወታችን ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይገባል?” አንተ ስለ ጉዳዩ ያለህን ጠንካራ እምነት ከምትገልጽ ወይም የራስህን ሰፊ ማብራሪያ ከምትሰጥ ይልቅ ይህንን ዘዴ መጠቀምህ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል። ይህም ተማሪው የራሱን ‘የማመዛዘን ችሎታ’ ተጠቅሞ አምላክን እንዲያገለግል ይረዳዋል።​—⁠ሮሜ 12:​1 NW 

ተማሪው ያልተረዳው ነገር ካለ ቶሎ ተስፋ አትቁረጥ። አሁን የምትነግረውን ሐሳብ ለብዙ ዓመታት ሲያምንበት ከኖረው ነገር ጋር እያወዳደረ ሊሆን ይችላል። ነጥቡን ከሌላ አቅጣጫ ማብራራት ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ከመሠረቱ ጀምሮ ማስረዳት ሊያስፈልግ ይችላል። በርከት ያሉ ጥቅሶችን ተጠቀም። በምሳሌዎች ለማስረዳት ሞክር። ከዚህም በተጨማሪ ስላቀረብከው ማስረጃ እንዲያስብ የሚያደርጉትን ጥያቄዎች ጠይቀው።

ስሜቱን እንዲገልጽ ለማበረታታት። ሰዎች ለሚቀርብላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ሁልጊዜ እውነተኛ ስሜታቸውን ይገልጻሉ ማለት አይደለም። አንተ የምትጠብቀውን ምላሽ ካወቁ ያንኑ መልስ ሊሰጡህ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ አስተዋይ መሆን ይኖርብሃል። (ምሳሌ 20:​5) ኢየሱስ እንዳደረገው ‘ይህን ታምንበታለህ?’ ብለህ ልትጠይቀው ትችል ይሆናል።​—⁠ዮሐ. 11:​26

ኢየሱስ ብዙ ደቀ መዛሙርቱ በተናገረው ነገር ተከፍተው ትተውት በሄዱ ጊዜ ሐዋርያቱ ምን እንደተሰማቸው ለማወቅ “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” ሲል ጠይቋቸዋል። ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ምን እንደሚሰማቸው ገልጿል:- “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም።” (ዮሐ. 6:​67-69) በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱን ‘ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?’ ሲል ጠየቃቸው። ከዚያም በማስከተል እነርሱ በልባቸው ያለውን እንዲናገሩ የሚያበረታታ ጥያቄ አቀረበላቸው። ‘እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።’ ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ሲል መልሷል።​—⁠ማቴ. 16:​13-16

መጽሐፍ ቅዱስ በምታስጠናበት ጊዜ ተማሪው ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ይህንን ዘዴ ብትጠቀም ጥሩ ሊሆን ይችላል። “አብረውህ የሚማሩት ልጆች (ወይም የሥራ ባልደረቦችህ) ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት አላቸው?” ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ከዚያም “የአንተስ አስተያየት ምንድን ነው?” ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። በምታስተምርበት ጊዜ አንድ ሰው ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው በትክክል ካወቅህ ጥሩ አድርገህ የመርዳት አጋጣሚ ይኖርሃል።

አጽንዖት ለመስጠት። ጥያቄ መጠየቅ ለአንዳንድ ነጥቦች አጽንዖት ለመስጠትም ሊረዳ ይችላል። በ⁠ሮሜ 8:​31, 32 ላይ እንደምናነበው ሐዋርያው ጳውሎስም ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሟል። “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?” ብሏል። እያንዳንዱ ጥያቄ አንድ መልእክት አዘል ሐረግ በማስቀደም እንደሚጀምር ልብ በል።

ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋ በባቢሎን ንጉሥ ላይ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ ከዘገበ በኋላ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው?” በማለት በመልእክቱ ላይ ያለውን እርግጠኝነት ገልጿል። (ኢሳ. 14:​27) ጥያቄዎቹ የቀረቡበት መንገድ ራሱ፣ ጉዳዩ ምንም አጠያያቂ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ጥያቄው መልስ የሚያሻው አይደለም።

የተሳሳተ አመለካከትን ለማጋለጥ። የታሰበባቸው ጥያቄዎች የሰዎችን የተሳሳተ አመለካከት ለማጋለጥም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ኢየሱስ ታምሞ የነበረውን ሰው ከመፈወሱ በፊት ፈሪሳውያንንና አንዳንድ የሕግ አዋቂዎችን “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” ሲል ጠየቃቸው። ሰውዬውን ከፈወሰ በኋላ ደግሞ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው?” (ሉቃስ 14:​1-6) ይህን ጥያቄ ሲጠይቃቸው መልስ እንዲሰጡት አልጠበቀም፤ እነርሱም መልስ አልነበራቸውም። ጥያቄው የተሳሳተ አመለካከታቸውን የሚያጋልጥ ነበር።

አንዳንድ ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖችም የተሳሳተ አመለካከት ሊይዙ ይችላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ችግራቸውን በመካከላቸው መፍታት ሲችሉ ወንድሞቻቸውን ችሎት ፊት ያቆሙ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ችግር በሚመለከት ምን አደረገ? አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት ሲል በቀጥታ ጉዳዩን የሚመለከቱ ተከታታይ ጥያቄዎች አቅርቦላቸዋል።​—⁠1 ቆሮ. 6:1-8

አንተም ልምምድ ካደረግህ ጥያቄዎችን ልክ እንደዚሁ በጥሩ ሁኔታ መጠቀም ትችላለህ። ይሁን እንጂ ሁሉንም ሰው በተለይም በዕድሜ የሚበልጡህን፣ የማታውቃቸውን ሰዎች እንዲሁም ባለ ሥልጣኖችን ስታነጋግር አክብሮት ማሳየት እንዳለብህ አትዘንጋ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ማራኪ አድርገህ ለማቅረብ ጥያቄዎችን ጥሩ አድርገህ ተጠቀም።

ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

  • ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመር ይበልጥ የሚያሳስባቸውን ጉዳይ የሚመለከት ጥያቄ ጠይቅ።

  • አንድ ቁልፍ ሐሳብ ከመናገርህ በፊት ለመስማት እንዲጓጉ የሚያደርግ ጥያቄ አንሳ።

  • ለምትናገረው ሐሳብ መሠረቱ ምን እንደሆነ፣ የነጥቡን አሳማኝነት እንዲሁም ለሕይወታቸው እንዴት እንደሚጠቅማቸው እንዲያስተውሉ ለመርዳት ጥያቄዎችን ተጠቀም።

  • ተማሪው ያጠናውን መልሶ እንዲደግም ሳይሆን ስለ ትምህርቱ ምን እንደተሰማው የልቡን አውጥቶ እንዲናገር የሚያበረታቱ ጥያቄዎችን ጠይቀው።

መልመጃ፦ (1) የአገልግሎት ክልልህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት ለማድረግ በር የሚከፍቱ ጥቂት ጥያቄዎችን አዘጋጅ። (2) ሮሜ ምዕራፍ 3⁠ን በማንበብ አይሁዳውያንም ሆኑ አሕዛብ በአምላክ ፊት ስላላቸው ቦታ ለማስረዳት ጳውሎስ ጥያቄዎችን እንዴት እንደተጠቀመ ለማስተዋል ሞክር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ