የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ol ክፍል 8 ገጽ 25-28
  • ከሐሰት ሃይማኖት ራቅ፤ እውነተኛውን ሃይማኖት ያዝ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከሐሰት ሃይማኖት ራቅ፤ እውነተኛውን ሃይማኖት ያዝ
  • ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ አግኝተኸዋል?
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሐሰት ሃይማኖት ውጣ
  • ለሐሰት አምልኮ ትጠቀምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን አስወግድ
  • ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ተቀራረብ
  • እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • ሰይጣንን ሳይሆን ይሖዋን አገልግል
    የሙታን መናፍስት—ሊረዱህ ወይም ሊጎዱህ ይችላሉን? ደግሞስ በእርግጥ አሉን?
  • አምላክ የሚቀበለው አምልኮ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ከሐሰት ሃይማኖት ራቅ!
    የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ!
ለተጨማሪ መረጃ
ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ አግኝተኸዋል?
ol ክፍል 8 ገጽ 25-28

ክፍል 8

ከሐሰት ሃይማኖት ራቅ፤ እውነተኛውን ሃይማኖት ያዝ

1. አምልኮን በተመለከተ በዛሬው ጊዜ ሰዎች የትኛውን ምርጫ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

ኢየሱስ “ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ይቃወመኛል” ብሏል። (ማቴዎስ 12:30) ከይሖዋ ጎን ካልቆምን ከሰይጣን ጎን መሰለፋችን አይቀርም። አብዛኞቹ ሰዎች አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ እያገለገሉ እንዳለ ያስባሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰይጣን “መላውን ዓለም እያሳሳተ” እንዳለ ይናገራል። (ራእይ 12:9) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን እያመለኩ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሚያገለግሉት ሰይጣን ዲያብሎስን ነው! በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች አንድ ዓይነት ምርጫ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፦ “የእውነት አምላክ” የሆነውን ይሖዋን ወይም “የውሸት አባት” የሆነውን ሰይጣንን ከማገልገል አንዱን መምረጣቸው የግድ ነው።—መዝሙር 31:5፤ ዮሐንስ 8:44

ከሐሰት ሃይማኖት ውጣ

2. ሰይጣን፣ ሰዎች ይሖዋን እንዳያመልኩ ለማድረግ ከሚሞክርባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?

2 ይሖዋን ለማገልገል መወሰን ጥበብ ያዘለ ምርጫ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ውሳኔ የአምላክን ሞገስ ያስገኛል። ይሁን እንጂ ሰይጣን፣ አምላክን በሚያገለግሉ ሰዎች አይደሰትም፤ ስለሆነም በእንዲህ ዓይነት ሰዎች ላይ ችግር እንዲደርስባቸው ያደርጋል። ሰይጣን ይህን ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ ወዳጆቻቸውንና የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ሰዎች እንዲያፌዙባቸው ወይም እንዲቃወሟቸው ማድረግ ነው። ኢየሱስ “በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ” በማለት አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 10:36

3. የቤተሰብህ አባላት ወይም ወዳጆችህ አምላክን እንዳታመልክ ቢቃወሙህ ምን ታደርጋለህ?

3 እንዲህ ያለ ነገር ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? ብዙ ሰዎች የሚከተሉት ሃይማኖት ስህተት እንደሆነ ያውቃሉ፤ ያም ቢሆን ሃይማኖታቸውን ለመተው ያመነታሉ። ሃይማኖታቸውን መተዋቸው ለቤተሰባቸው ያላቸውን ታማኝነት ማጉደል እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? አንድ የቤተሰብህ አባል አደገኛ ዕፅ እንደሚወስድ ብታውቅ የሚወስደው ዕፅ ጉዳት እንደሚያስከትልበት በመግለጽ ታስጠነቅቀዋለህ እንጂ አብረኸው ዕፅ እንደማትወስድ የታወቀ ነው።

4. ኢያሱ በዘመኑ ይካሄድ ስለነበረው አምልኮ እስራኤላውያንን ምን ብሏቸው ነበር?

4 ኢያሱ፣ እስራኤላውያን የአባቶቻቸውን የተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ልማዶችና ወጎች እንዲተዉ አሳስቦ ነበር። “ይሖዋን ፍሩ፤ በንጹሕ አቋምና በታማኝነትም አገልግሉት፤ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶና በግብፅ ምድር ያገለገሏቸውን አማልክት አስወግዱ፤ ይሖዋን አገልግሉ” ብሏቸዋል። (ኢያሱ 24:14) ኢያሱ ለይሖዋ ታማኝ ነበር፤ ይሖዋም ባርኮታል። እኛም ለይሖዋ ታማኝ ብንሆን ይባርከናል።—2 ሳሙኤል 22:26

ሃይማኖታዊ ትምህርት—እውነተኛውና ሐሰተኛው

  • አንዲት የይሖዋ ምሥክር አንዲትን ሴትና ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠናቸው

    ሥላሴ፦ ብዙ ሃይማኖቶች አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ያስተምራሉ። “አብ አምላክ ነው፤ ወልድ [ኢየሱስ] አምላክ ነው፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው፤ ሆኖም ሦስት አማልክት ሳይሆኑ አንድ አምላክ ናቸው” ይላሉ።

    “ሥላሴ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም፤ እንዲሁም የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ አንድም ሦስትም እንደሆነ አያስተምርም። ከይሖዋ በቀር ሌላ አምላክ የለም። አንደኛ ቆሮንቶስ 8:6 “አንድ አምላክ አብ አለን” ይላል። ይሖዋ የሁሉ የበላይ ነው። ኢየሱስ “የአምላክ ልጅ” እንጂ አምላክ አይደለም። (1 ዮሐንስ 4:15) በተመሳሳይም መንፈስ ቅዱስ አምላክ አይደለም። ሌላው ቀርቶ መንፈስ ቅዱስ አካል ያለው ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የሚጠቀምበት ኃይል ነው።—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ኤፌሶን 5:18

  • ነፍስ፦ ብዙ ሃይማኖቶች ነፍስ በሰው ውስጥ የምትኖርና ፈጽሞ የማትሞት ነገር እንደሆነች ያስተምራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰው ራሱ ነፍስ እንደሆነ ይገልጻል፤ ሰው ደግሞ እንደሚሞት ግልጽ ነው።—ዘፍጥረት 2:7 የግርጌ ማስታወሻ፤ ሕዝቅኤል 18:4

  • የሲኦል እሳት፦ የሐሰት ሃይማኖቶች፣ ክፉ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች ነፍስ በሲኦል ለዘላለም እንደምትሠቃይ ያስተምራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ‘ሙታን ምንም እንደማያውቁ’ ያስተምራል። (መክብብ 9:5) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር” እንደሆነ ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 4:8) አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ሰዎችን በእሳት እያቃጠለ አያሠቃይም።

ሣጥን፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥላሴ፣ ስለ ነፍስና ስለ ሲኦል እሳት ምን ብሎ ያስተምራል?

ለሐሰት አምልኮ ትጠቀምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን አስወግድ

አንዲት ሴት ከአስማት ጋር የተያያዙ ዕቃዎቿን ስታቃጥል

5. ምትሃታዊ ኃይል እንዳላቸው ተደርገው የሚቆጠሩ ቁሳቁሶችን ማስወገድ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

5 ከሐሰት ሃይማኖት ነፃ መውጣት፣ እንደ ክታብ ወይም ድግምት እንደተደረገበት ቀለበትና አምባር ያሉ ምትሃታዊ ኃይል እንዳላቸው ተደርገው የሚቆጠሩ ቁሳቁሶችን በሙሉ ማስወገድን ይጨምራል። እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን ያሳያል።

6. አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች የጥንቆላ መጽሐፎቻቸውን ምን አድርገው ነበር?

6 አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች እውነተኛውን ሃይማኖት ለመከተል ሲወስኑ ምን እንዳደረጉ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ” በማለት ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 19:19

7. አጋንንት ጥቃት የሚሰነዝሩብን ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?

7 የጥንቆላና የአስማት ድርጊቶችን ይፈጽሙ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ይሖዋን ማገልገል ሲጀምሩ ከአጋንንት ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ የይሖዋን ስም ጮክ ብለህ በመጥራት ጸልይ። እሱም ይረዳሃል።—ምሳሌ 18:10፤ ያዕቆብ 4:7

8. ክርስቲያኖች ከሐሰት አምልኮ ጋር የተያያዙ ሥዕሎችን፣ ምስሎችንና ጣዖታትን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው?

8 ይሖዋን ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ከሐሰት አምልኮ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ዓይነት ሥዕል፣ ምስል ወይም ጣዖት ማስወገድ ይኖርባቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚመላለሱት “በእምነት እንጂ በማየት አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 5:7) ማንኛውንም ዓይነት ምስል ለአምልኮ መጠቀምን የሚከለክለውን የአምላክን ሕግ ያከብራሉ።—ዘፀአት 20:4, 5

ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ተቀራረብ

አንዲት እናት ከልጇ ጋር ሆና ምግብ ስትሠራ

9. መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጥበበኛ ስለ መሆን ምን ምክር ይሰጣል?

9 መጽሐፍ ቅዱስ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) ጥበበኛ መሆን ከፈለግን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሄድ ወይም መቀራረብ ያስፈልገናል። ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዙ ያሉት እነሱ ናቸው።—ማቴዎስ 7:14

10. የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን እንድታገለግል ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?

10 የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ከልብ ያስባሉ። የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስችለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ያስተምራሉ። ለአንተም መጽሐፍ ቅዱስን ያለምንም ክፍያ ሊያስተምሩህ ይችላሉ። ለጥያቄዎችህ መልስ ይሰጡሃል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት በሕይወትህ ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድታውቅ ይረዱሃል።—ዮሐንስ 17:3

11. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚረዱህ እንዴት ነው?

11 አብዛኛውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ በሚደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ስለ ይሖዋ መንገዶች ተጨማሪ እውቀት ታገኛለህ። የምታገኘው እውቀት እውነተኛውን ሃይማኖት ለመከተል ያደረግከውን ውሳኔ ይበልጥ ያጠናክርልሃል። በተጨማሪም ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር የሚያስችል ሥልጠና ታገኛለህ።—ዕብራውያን 10:24, 25

በይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄድ የጉባኤ ስብሰባ

12. ጸሎት አምላክን እንድታገለግል የሚረዳህ እንዴት ነው?

12 ስለ ይሖዋ ዓላማና ፈቃድ ይበልጥ ባወቅክ መጠን ፍቅር ስለሚንጸባረቅባቸው መንገዶቹ ያለህ ግንዛቤና አድናቆት እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። በተጨማሪም ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግና እሱን ከሚያሳዝነው ነገር ለመራቅ ያለህ ፍላጎት ይጨምራል። ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግና ስህተት ከሆነው ነገር መራቅ ትችል ዘንድ እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ እንደምትችል አስታውስ።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ፊልጵስዩስ 4:6

የአንድ ቤተሰብ አባላት አብረው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ

እውነተኛውን ሃይማኖት መከተል የምትችለው እንዴት ነው?

13. የይሖዋን ልብ ማስደሰት የምትችለው እንዴት ነው?

13 በመንፈሳዊ እያደግክ ስትሄድ፣ ራስህን ለአምላክ ወስነህ በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደሚያስፈልግህ መገንዘብህ አይቀርም። የይሖዋ ምሥክር ስትሆን ደግሞ የይሖዋን ልብ ታስደስታለህ። (ምሳሌ 27:11) አምላክ “በመካከላቸው እኖራለሁ፤ ከእነሱም ጋር እሄዳለሁ፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፣ እነሱ ደግሞ ሕዝቤ ይሆናሉ” በማለት ከተናገረላቸው ደስተኛ ሕዝቦች አንዱ ትሆናለህ።—2 ቆሮንቶስ 6:16

ከአጋንንት ተጽዕኖ ተላቀቅሁ

ጆሴፊን ኢኬዙ ከተወሰኑ ልጆቿ ጋር

አንድ ቀን ሌሊት ከባለቤቴ ጋር ተኝቼ ሳለሁ አንድ ድምፅ ሦስት ጊዜ ሲጠራኝ ሰማሁ። ከዚያም ጣሪያው ለሁለት ተሰነጠቀና ኳስ የሚመስል እሳታማ ነገር ሆዴ ላይ ወደቀ። እርግጥ፣ ባለቤቴ የሚያየው አንድም ነገር አልነበረም። እኔ ግን ከዚያ በኋላ ለበርካታ ወራት ከፍተኛ የማቃጠል ስሜት ይሰማኝ ነበር።

ከስድስት ወር በኋላ ያ ድምፅ እንደገና ጠራኝ። ወዲያውኑ ቤቱ ጥልቅ በሆነ ውኃ ውስጥ የሰጠመ መሰለኝ። ከውኃውም ውስጥ አንድ ትልቅ ዘንዶ ወጣና እጄ ላይ ተጠመጠመ። ዘንዶውን ከእጄ ለማላቀቅ ብሞክርም አልቻልኩም። በፍርሃት ተዋጥኩ። ከዚያ በኋላ ውኃውም፣ ዘንዶውም ጠፉ፤ እኔ ግን መሬት ላይ ተዘረርኩ። ለበርካታ ሰዓታት ራሴን ስቼ ቆየሁ። ከዚያም ያ ድምፅ በመንደሩ ወደሚገኝ መናፍስታዊ ፈውስ ወደሚሰጥበት ቤተ መቅደስ እንድሄድ ነገረኝ። ያናግረኝ የነበረውን መንፈስ ስሙን ስጠይቀው “የልጅ ሳይሆን የሀብት ባለቤት” የሚል ትርጉም ያለው ስም ነገረኝ። ሰዎችን የመፈወስ ኃይል በመስጠት ባለጠጋ እንደሚያደርገኝ ቃል ገባልኝ።

የታመሙ ሰዎች ከሩቅም ሆነ ከቅርብ ወደ እኔ ይመጡ ጀመር። ሰዎቹ ቤቴ ከመድረሳቸው በፊት ልዩ በሆነው መስታወቴ አያቸው ነበር። ከዚያም በሚደርሱበት ጊዜ በእጄ መዳፍ የእጃቸውን መዳፍ ስመታ በሽታቸው ወይም ችግራቸው ከነመድኃኒቱ ይገለጥልኛል። በተጨማሪም መንፈሱ፣ ሰዎቹ ምን ያህል ገንዘብ መክፈል እንዳለባቸው ይነግረኝ ነበር።

ወደ እኔ የሚመጡት ሰዎች ይፈወሱ ስለነበር ገንዘብና ስጦታ ይጎርፍልኝ ነበር። “የሀብት ባለቤት” ሆንኩ፤ ይሁን እንጂ ‘የልጅ ባለቤት’ እንደማልሆን የተነገረኝ ለምን እንደሆነም ተገነዘብኩ። ልጅ በወለድኩ ቁጥር ከእሱ በፊት የተወለደው ይሞትብኝ ነበር። ከዚህም የተነሳ በጣም አዝን ነበር። ይህን መንፈስ ባገለገልኩባቸው 12 ዓመታት ውስጥ ስድስት ልጆቼን በሞት አጥቻለሁ።

አምላክ እንዲረዳኝ መጸለይ ጀመርኩ። አጥብቄ እጸልይ ነበር። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች በሬን አንኳኩ። ከዚያ ቀደም የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ ሲመጡ አባርራቸው የነበረ ቢሆንም ያን ቀን ግን የሚናገሩትን ለማዳመጥ ወሰንኩ። ከእነሱ ጋር መወያየቴን ስቀጥል አጋንንትን እያገለገልኩ እንደሆነ ተረዳሁ! በመሆኑም ከአስማታዊ ድርጊቶች ለመራቅ ወሰንኩ።

ውሳኔዬን ለሚያነጋግረኝ መንፈስ ስነግረው ማስጠንቀቂያ ሰጠኝ። ሆኖም “የእኔና የአንተ ግንኙነት አብቅቶለታል” አልኩት።

ለጥንቆላ እጠቀምባቸው የነበሩትን ነገሮች በሙሉ አቃጠልኩ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ቀጠልኩ፤ ከዚያም በ1973 ተጠምቄ ይሖዋን ማገልገል ጀመርኩ። አሁን አምስት ጤነኛ ልጆች አሉኝ። ባለቤቴም ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል።—ጆሴፊን ኢኬዙ እንደተናገረችው

ሣጥን፦ አንዲት ሴት ከአጋንንት ተጽዕኖ መላቀቅ የቻለችው እንዴት ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ