የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lr ምዕ. 14 ገጽ 77-81
  • ይቅር ማለት ያለብን ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይቅር ማለት ያለብን ለምንድን ነው?
  • ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይቅር ባይ የመሆን አስፈላጊነት
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ስለ ይቅር ባይነት የተሰጠ ትምህርት
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ‘ምንጊዜም በጉን ይከተሉታል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
ከታላቁ አስተማሪ ተማር
lr ምዕ. 14 ገጽ 77-81

ምዕራፍ 14

ይቅር ማለት ያለብን ለምንድን ነው?

ሰው በድሎህ ያውቃል?— አንድ ሰው መጥፎ ድርጊት ፈጽሞብህ ወይም ደስ የማይል ነገር ተናግሮህ ያውቃል?— እሱ ያደረገብህን አንተም መልሰህ ልታደርግበት ይገባል?—

ብዙ ሰዎች አንድ ሰው መጥፎ ነገር ካደረገባቸው እነሱም መልሰው መጥፎ ነገር ያደርጉበታል። ኢየሱስ ግን የበደሉንን ይቅር ማለት እንዳለብን አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:12) አንድ ሰው ብዙ ጊዜ ቢበድለንስ? ይህን ሰው ይቅር ማለት ያለብን ስንት ጊዜ ነው?—

ጴጥሮስ የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ አንድ ቀን ኢየሱስን ‘እስከ ሰባት ጊዜም ቢበድለኝ ይቅር ማለት አለብኝ ማለት ነው?’ ብሎ ጠየቀው። ሆኖም ሰባት ጊዜም እንኳ በቂ አይደለም። ኢየሱስ ሰውየው ሰባ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ ‘ሰባ ሰባት ጊዜ ይቅር ማለት እንዳለብህ’ ተናግሯል።

ጴጥሮስ ኢየሱስን አንድ ጥያቄ ሲጠይቀው

ጴጥሮስ ስለ ይቅር ባይነት ለማወቅ የፈለገው ነገር ምንድን ነው?

ይህ በጣም ብዙ ነው! አንድ ሰው ሰባ ሰባት ጊዜ በድሎኛል ወይም መጥፎ ድርጊት ፈጽሞብኛል ብለን ለማስታወስ እንኳ ይከብደናል፣ አይደል? ኢየሱስም ቢሆን ሊነግረን የፈለገው ይህን ነው:- ሌሎች ምን ያህል ጊዜ በደል እንደፈጸሙብን ለማስታወስ መሞከር የለብንም። ይቅር እንድንላቸው ከጠየቁን ይቅር ልንላቸው ይገባናል።

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይቅር ማለት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ማድረግ ፈለገ። ስለዚህ የጴጥሮስን ጥያቄ ከመለሰ በኋላ አንድ ታሪክ ነገራቸው። ታሪኩን መስማት ትፈልጋለህ?—

በአንድ ወቅት አንድ ጥሩ ንጉሥ ነበር። ይህ ንጉሥ በጣም ደግ ነበር። ለባሪያዎቹ እንኳን ሳይቀር ሲቸግራቸው ገንዘብ ያበድራቸው ነበር። አንድ ቀን ግን ይህ ንጉሥ ባሪያዎቹ የተበደሩትን ገንዘብ እንዲመልሱለት ፈለገ። በዚህ ጊዜ ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ዕዳ የነበረበት አንድ ባሪያ ንጉሡ ፊት ቀረበ። ይህ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ነው!

አንድ ባሪያ ዕዳውን ለመክፈል ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጌታውን ሲለምን፤ በኋላ ላይ ግን እንደ እሱ ባሪያ የሆነውን ሰው አንቆ ሲያስጨንቀው

ባሪያው ዕዳውን ለመክፈል ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን በለመነው ጊዜ ምን አደረገለት?

ነገር ግን ይህ ባሪያ የንጉሡን ገንዘብ በሙሉ ተጠቅሞበት ስለጨረሰው ብድሩን ሊመልስ አልቻለም። ስለዚህ ንጉሡ ይህ ባሪያ እንዲሸጥ ትእዛዝ አስተላለፈ። በተጨማሪም ንጉሡ የባሪያው ሚስት፣ ልጆቹ እንዲሁም ያለው ነገር ሁሉ እንዲሸጥ አዘዘ። ከዚህ ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ለንጉሡ ይከፈላል። በዚህ ጊዜ ባሪያው ምን የተሰማው ይመስልሃል?—

በንጉሡ ፊት ተንበርክኮ ‘እባክህ ትንሽ ጊዜ ስጠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍልሃለሁ’ ሲል ለመነው። አንተ ንጉሡን ብትሆን ኖሮ ባሪያውን ምን ታደርገው ነበር?— ንጉሡ ለባሪያው አዘነለት። ስለዚህ ዕዳውን ተወለት። ንጉሡ ለባሪያው ከ60 ሚሊዮኑ ገንዘብ ውስጥ አንዱንም ቢሆን መመለስ እንደማያስፈልገው ነገረው። በዚህ ጊዜ ባሪያው ምን ያህል ተደስቶ ይሆን!

ከዚያ በኋላ ግን ያ ባሪያ ምን ያደረገ ይመስልሃል? ከዚያ ወጥቶ ሲሄድ ከእሱ ላይ ወደ አንድ መቶ የሚጠጋ ገንዘብ ብቻ የተበደረ አንድ ሌላ ባሪያ አገኘ። እንደ እሱ ባሪያ የሆነውን ይህን ሰው አንገቱን አንቆ ‘የተበደርከኝን ገንዘብ መልስልኝ!’ አለው። ይህ ባሪያ ንጉሡ ያን ሁሉ ዕዳ ትቶለት እሱ እንዲህ ማድረጉ አይገርምም?—

አንድ ባሪያ እንደ እሱ ባሪያ የሆነውን ሰው እስር ቤት ሲያስገባው

ዕዳው የተተወለት ባሪያ፣ እንደ እሱ ባሪያ የሆነው ሰው ያለበትን ዕዳ መክፈል ሲያቅተው ምን አደረገው?

ወደ አንድ መቶ የሚጠጋ ገንዘብ ብቻ የተበደረው ባሪያ ድሃ ነበር። ገንዘቡን ወዲያውኑ መክፈል አይችልም። ስለዚህ በአበዳሪው ባሪያ እግር ላይ ወድቆ ‘እባክህ ትንሽ ጊዜ ስጠኝ፣ ያለብኝን ዕዳ እከፍልሃለሁ’ ብሎ ለመነው። ይህ ሰው ለዚህ ባሪያ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም?— አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?—

ይህ ሰው እንደ ንጉሡ ደግ አልነበረም። ገንዘቡን ወዲያው ማግኘት ፈልጓል። ከእሱ የተበደረው ባሪያ ዕዳውን ሊከፍለው ስላልቻለ እስር ቤት እንዲገባ አደረገው። ሌሎቹ ባሪያዎች ይህ ሰው ያደረገውን ሲያዩ ደስ አላላቸውም። እስር ቤት ለገባው ባሪያ አዘኑለት። ስለዚህ ለንጉሡ ሄደው ነገሩት።

ንጉሡም ቢሆን የተደረገውን ነገር ሲሰማ አልተደሰተም። ያ ባሪያ ይቅርታ ባለማድረጉ ንጉሡ በጣም ተቆጣ። ስለዚህ አስጠራውና ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ እኔ ያንተን ዕዳ አልተውኩልህም? ታዲያ አንተም ልክ እንዳንተው ባሪያ የሆነውን ሰው ዕዳ ልትተውለት አይገባም ነበር?’ አለው።

ይቅር ያላለው ባሪያ ከደጉ ንጉሥ ትምህርት ሊያገኝ ይገባ ነበር። ነገር ግን አልተማረም። ስለዚህ ንጉሡ ይህ ባሪያ ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋውን ገንዘብ ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ እስር ቤት እንዲገባ አደረገ። እስር ቤት ሆኖ ደግሞ ለንጉሡ የሚከፍለው ገንዘብ ሊያገኝ አይችልም። ስለዚህ እስኪሞት ድረስ እዚያው ታስሮ ይኖራል።

ንጉሡ ይቅር ያላለውን ባሪያ እስር ቤት አስገባው

ንጉሡ ይቅር ያላለውን ባሪያ ምን አደረገው?

ኢየሱስ ታሪኩን ተናግሮ ሲጨርስ ተከታዮቹን እንዲህ አላቸው:- “እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።”—ማቴዎስ 18:21-35

ሁላችንም የአምላክ ዕዳ አለብን። ሕይወታችንም እንኳ ሳይቀር ከአምላክ የተገኘ ነው! ስለዚህ እኛ በአምላክ ላይ ካለብን ዕዳ ጋር ሲነፃፀር ሌሎች በእኛ ላይ ያለባቸው ዕዳ ትንሽ ነው። እነሱ በእኛ ላይ ያለባቸው ዕዳ አንዱ ባሪያ ከሌላው ባሪያ ከተበደረው ወደ መቶ የሚጠጋ ገንዘብ ጋር የሚነፃፀር ነው። እኛ በምንሠራው በደል የተነሳ በአምላክ ላይ ያለብን ዕዳ ግን ባሪያው ከንጉሡ እንደተበደረው ወደ 60 ሚሊዮን እንደሚጠጋው ገንዘብ ብዙ ነው።

አምላክ በጣም ደግ ነው። ስህተት ብንሠራም እንኳ ይቅር ይለናል። ሕይወታችንን ለዘላለሙ ከእኛ በመውሰድ ዕዳችንን እንድንከፍል አያደርግም። ሆኖም የሚከተለውን ትምህርት ማስታወስ ይኖርብናል:- አምላክ ይቅር የሚለን እኛ የበደሉንን ይቅር የምንል ከሆነ ብቻ ነው። ይህ በጣም ጠቃሚ ትምህርት ነው፣ አይደል?—

አንድ ልጅ የሌላውን ልጅ መጫወቻ አውሮፕላን ስለሰበረበት ይቅርታ ሲጠይቀው

አንድ ሰው ይቅር እንድትለው ቢጠይቅህ ምን ታደርጋለህ?

ስለዚህ አንድ ሰው መጥፎ ነገር ቢሠራብህና ይቅርታ ቢጠይቅህ ምን ታደርጋለህ? ይቅር ትለዋለህ?— ደጋግሞ ቢበድልህስ? በዚህ ጊዜም ይቅር ትለዋለህ?—

ይቅርታ እንዲደረግልን የምንጠይቀው እኛ ብንሆን የበደልነው ሰው ይቅር እንዲለን እንደምንፈልግ የታወቀ ነው፣ አይደል?— ስለዚህ እኛም ለሌላው እንዲሁ ማድረግ አለብን። ይቅርታ እንዳደረግንለት መናገር ብቻ ሳይሆን ከልባችን ይቅር ልንለው ይገባናል። ይህን ስናደርግ በእውነት የታላቁ አስተማሪ ተከታዮች መሆን እንደምንፈልግ እናሳያለን።

ይቅር ባይ የመሆንን አስፈላጊነት ለመረዳት እንድንችል ምሳሌ 19:11፤ ማቴዎስ 6:14, 15 እና ሉቃስ 17:3, 4ን​ም እናንብብ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ