የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lv ምዕ. 13 ገጽ 144-159
  • አምላክ የማይደሰትባቸው በዓሎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ የማይደሰትባቸው በዓሎች
  • ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ገና​—የፀሐይ አምልኮ አዲስ ስያሜ ተሰጠው
  • መጽሐፍ ቅዱስ የልደት ቀንን ስለ ማክበር ምን ይላል?
  • በዓለ ትንሣኤ​—የክርስቶስ ትንሣኤ እንደሆነ የሚታሰበው የመራባት አምልኮ
  • ሃሎዊን​—ቅዱስ የሆነ በዓል አይደለም
  • ሠርጋችሁ ንጹሕ ይሁን
  • ጽዋ ማንሳት ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው?
  • ‘ይሖዋን የምትወዱ ክፋትን ጥሉ’
  • አምላክን በቃልም ሆነ በድርጊት ማክበር
  • አምላክን የሚያስደስቱት ሁሉም በዓላት ናቸው?
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • በዓላትን ማክበር
    ትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች
  • አምላክን በትክክለኛው መንገድ ለማምለክ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ቁም
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
lv ምዕ. 13 ገጽ 144-159
አንድ ልጅ ወላጆቹ የሰጡትን ስጦታ ሲከፍት

ምዕራፍ 13

አምላክ የማይደሰትባቸው በዓሎች

“በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ።”​—ኤፌሶን 5:10

1. ይሖዋ ወደ ራሱ የሚስበው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው መኖር የሚገባቸውስ ለምንድን ነው?

ኢየሱስ⁠ ‘እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ ምክንያቱም አብ እንዲህ ዓይነት ሰዎች እንዲያመልኩት ይፈልጋል’ ብሏል። (ዮሐንስ 4:23) ይሖዋ አንተን እንዳገኘህ ሁሉ እሱን በመንፈስና በእውነት ማምለክ የሚፈልጉ ሰዎች ሲያገኝ ወደ ራሱና ወደ ልጁ ይስባቸዋል። (ዮሐንስ 6:44) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ይሁን እንጂ ሰይጣን የተዋጣለት አታላይ በመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚወዱ ሁሉ ‘በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምረው ማረጋገጥ’ ይኖርባቸዋል።​—ኤፌሶን 5:10፤ ራእይ 12:9

2. ይሖዋ እውነተኛውን ሃይማኖት ከሐሰተኛው ጋር ለመቀላቀል የሚሞክሩ ሰዎችን እንዴት ይመለከታቸዋል? አብራራ።

2 እስራኤላውያን በሲና ተራራ አቅራቢያ ሳሉ፣ የሚያመልኩት አምላክ እንዲሠራላቸው አሮንን በጠየቁት ጊዜ ምን እንደተከሰተ ተመልከት። አሮን በጥያቄያቸው መሠረት የወርቅ ጥጃ ሠራላቸውና ‘ነገ ለይሖዋ በዓል ይሆናል’ አላቸው፤ ይህም ምስሉ ይሖዋን ይወክላል የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ነበር። በዚህ መንገድ እውነተኛው አምልኮ ከሐሰተኛው አምልኮ ጋር መቀላቀሉን ይሖዋ በቸልታ ተመልክቶታል? በፍጹም። ሦስት ሺህ የሚያክሉ ጣዖት አምላኪዎች እንዲገደሉ አድርጓል። (ዘፀአት 32:1-6, 10, 28) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን ማንኛውንም ‘ርኵስ ነገር መንካት’ አይኖርብንም፤ እንዲሁም እውነት በምንም ነገር እንዳይበከል በቅንዓት መጠበቅ ይገባናል።​—ኢሳይያስ 52:11፤ ሕዝቅኤል 44:23፤ ገላትያ 5:9

3, 4. ተወዳጅ የሆኑ ልማዶችንና በዓሎችን በምንመረምርበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር ልናያቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

3 ክህደት እንዳይስፋፋ አጥብቀው ይከላከሉ የነበሩት ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ለእውነት ምንም ዓይነት ፍቅር ያልነበራቸው ክርስቲያን ነን ባዮች በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት አላቸው በማለት የአረማውያንን ልማዶችና በዓሎች መቀበል ጀመሩ። (2 ተሰሎንቄ 2:7, 10) ከእነዚህ በዓሎች አንዳንዶቹን በምትመረምርበት ጊዜ የአምላክን ሳይሆን የዓለምን መንፈስ እንዴት እንደሚያንጸባርቁ ልብ ብለህ ተመልከት። በአጠቃላይ ሲታይ በዓለም የሚከበሩ በዓሎች የሚያመሳስሏቸው የጋራ ባሕርያት አሏቸው፤ ሥጋዊ ምኞቶችን ይማርካሉ፣ እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖት እምነቶችንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን ያስፋፋሉ። እነዚህ ደግሞ ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ መለያ ባሕርያት ናቸው።a (ራእይ 18:2-4, 23) በተጨማሪም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚዘወተሩት ብዙዎቹ ተወዳጅ ልማዶች የመነጩባቸውን አስጸያፊ የሆኑ የአረማውያን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንደተመለከተ አስታውስ። እንደነዚህ ያሉትን በዓሎች ዛሬም እንደሚጸየፋቸው ጥርጥር የለውም። በዚህ ረገድ ልንቀበል የሚገባን ይሖዋ ያለውን አመለካከት መሆን አይኖርበትም?​—2 ዮሐንስ 6, 7

4 እውነተኛ ክርስቲያኖች በመሆናችን ይሖዋ የማይደሰትባቸው በዓሎች እንዳሉ እናውቃለን። ይሁንና ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ ነገር አለ፤ ይኸውም ከእነዚህ በዓሎች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይገባናል። ይሖዋ እንደነዚህ ባሉት በዓሎች የማይደሰተው ለምን እንደሆነ መመርመራችን በአምላክ ፍቅር ውስጥ ለመኖር እንቅፋት የሚሆንብንን ማንኛውንም ነገር ለማስወገድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።

ገና​—የፀሐይ አምልኮ አዲስ ስያሜ ተሰጠው

5. ኢየሱስ ታኅሣሥ 25 ቀን (በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) እንዳልተወለደ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የልደት በዓሉ እንደተከበረለት የሚናገረው ነገር የለም። እንዲያውም የተወለደበት ቀን በትክክል አይታወቅም። ይሁንና ኢየሱስ በተወለደበት የዓለም ክፍል የክረምቱ ቅዝቃዜ በጣም በሚያይልበት ወቅት ማለትም በታኅሣሥ 25 ቀን (በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) እንዳልተወለደ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።b እንዲህ የምንልበት አንደኛው ምክንያት ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ “ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች” እንደነበሩ ሉቃስ ዘግቧል። (ሉቃስ 2:8-11) እነዚህ ሰዎች ዓመቱን ሙሉ ‘ሜዳ ላይ የማደር’ ልማድ ቢኖራቸው ኖሮ ይህ ሐሳብ ተለይቶ መጠቀስ አያስፈልገውም ነበር። ይሁን እንጂ ቤተልሔም በክረምት ወራት ዝናብና በረዶ የሚበዛበት በመሆኑ መንጎች በቤት ውስጥ ይጠለላሉ፤ ስለሆነም እረኞች በዚህ ወቅት ‘ሜዳ አያድሩም።’ በተጨማሪም ዮሴፍና ማርያም ወደ ቤተልሔም የሄዱት አውግስጦስ ቄሳር የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ ስላዘዘ ነው። (ሉቃስ 2:1-7) ቄሳር የሮማውያንን አገዛዝ ይጠሉ የነበሩትን ሕዝቦች በኃይለኛው ክረምት ለቆጠራ ወደየትውልድ ቦታቸው እንዲሄዱ ያዝዛል ማለት የማይመስል ነገር ነው።

6, 7. (ሀ) ብዙዎቹ የገና በዓል አከባበር ልማዶች ምንጫቸው ምንድን ነው? (ለ) ሰዎች በገና በዓል ሰሞን ስጦታ የሚለዋወጡበት መንገድ ክርስቲያኖች ስጦታ ከሚሰጡበት መንገድ የሚለየው በምንድን ነው?

6 የገና በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም፤ ከዚህ ይልቅ በጥንት ጊዜ ይከበሩ ከነበሩ የአረማውያን በዓሎች የመነጨ ነው። ከእነዚህ በዓሎች መካከል ሮማውያን የግብርና አምላክ የሚሉትን ሳተርንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሲሉ የሚያከብሩት የሳተርናሊያ በዓል ይገኝበታል። እንዲሁም ሚትራ የሚባለው አምላክ አምላኪዎች ታኅሣሥ 25ን “የማትበገረው ፀሐይ የልደት ቀን” ብለው ያከብሩት እንደነበረ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። “የገና በዓል መከበር የጀመረው በተለይ የፀሐይ አምልኮ በሮም በጣም በገነነበት” ይኸውም ክርስቶስ ከሞተ ከሦስት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ ነው።

እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚሰጡት በፍቅር ተነሳስተው ነው

7 አረማውያን እነዚህን በዓሎች በሚያከብሩበት ጊዜ ስጦታ ይለዋወጡና ትልቅ ድግስ ይደግሱ ነበር። እንዲህ ያለው ልማድ በዛሬው የገና በዓል አከባበር ላይም ይታያል። ልክ በዛሬው ጊዜ እንደሚታየው፣ በሮማውያን ዘመን ሰዎች የገና ስጦታዎችን የሚለዋወጡት “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ” በሚለው በ⁠2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ በሚገኘው መንፈስ አልነበረም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ስጦታ የሚሰጡት በፍቅር ተነሳስተው ነው። ስጦታ ለመስጠት አንድ የተለየ ቀን የማይጠብቁ ከመሆኑም በላይ በምላሹ ስጦታ እናገኛለን ብለው ተስፋ አያደርጉም። (ሉቃስ 14:12-14፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35) እንዲያውም ክርስቲያኖች በገና በዓል ሰሞን ከሚኖረው ግርግር እንዲሁም ብዙዎች እንደሚያጋጥማቸው በዓሉን ለማክበር ሲሉ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ከመግባት ነፃ በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው።​—ማቴዎስ 11:28-30፤ ዮሐንስ 8:32

8. ኮከብ ቆጣሪዎቹ ለኢየሱስ ያመጡለት ስጦታ የልደት ስጦታ ነበር? አብራራ።

8 ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት ኮከብ ቆጣሪዎቹ ለኢየሱስ ያመጡለት የልደት ስጦታ ነው? በፍጹም! በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ሰው አክብሮትን ለመግለጽ ስጦታ መስጠት የተለመደ ነበር፤ ኮከብ ቆጣሪዎቹም ያደረጉት ይህንኑ ነው። (1 ነገሥት 10:1, 2, 10, 13፤ ማቴዎስ 2:2, 11) እንዲያውም ስጦታውን ያመጡት ኢየሱስ በተወለደበት ምሽት አልነበረም። እነሱ በመጡበት ጊዜ ኢየሱስ በግርግም ውስጥ የተኛ አራስ ሕፃን ሳይሆን በቤት ውስጥ ይኖር የነበረ የወራት ዕድሜ ያለው ልጅ ነበር።

በበዓሉ ላይ ልካፈል?

አንዲት ክርስቲያን የሥራ ቦታዋን ለበዓል እንድታስጌጥ ለቀረበላት ጥያቄ ፈቃደኛ አለመሆኗን ስትገልጽ

መሠረታዊ ሥርዓት:- “‘ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር መንካት አቁሙ’፤ ‘እኔም እቀበላችኋለሁ።’”​—2 ቆሮንቶስ 6:17

አንድን በዓል ወይም ልማድ በተመለከተ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:-

  • መናፍስትነትን ጨምሮ ከሐሰት ሃይማኖት ልማድ ወይም ትምህርት የመነጨ እንደሆነ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ አለ?​—ኢሳይያስ 52:11፤ 1 ቆሮንቶስ 4:6፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14-18፤ ራእይ 18:4

  • ለአንድ ሰው፣ ድርጅት ወይም ብሔራዊ አርማ አምልኮ አከል ክብር የሚሰጥ ነው?—ኤርምያስ 17:5-7፤ የሐዋርያት ሥራ 10:25, 26፤ 1 ዮሐንስ 5:21

  • አንድን ብሔር ወይም ጎሳ ከሌላው ከፍ የሚያደርግ ነው?​—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ 17:26

  • የአምላክን ቅዱስ መንፈስ የሚቃረነው ‘የዓለም መንፈስ’ የሚንጸባረቅበት ነው?​—1 ቆሮንቶስ 2:12፤ ኤፌሶን 2:2

  • በሥነ ሥርዓቱ ላይ ብካፈል ሌሎች ይሰናከላሉ?​—ሮም 14:21

  • በሥነ ሥርዓቱ ላይ ላለመካፈል ከወሰንኩ ምክንያቴን ለሌሎች አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?​—ሮም 12:1, 2፤ ቆላስይስ 4:6

ቀጥሎ የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ በዓሎችን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሊረዱ ይችላሉ:-

  • “[ታማኝ ያልነበሩት እስራኤላውያን] ከሕዝቦቹ ጋር ተደባለቁ፤ ልማዳቸውንም ቀሠሙ።”​—መዝሙር 106:35

  • “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ ሰው በብዙ ነገርም ታማኝ ነው፤ በትንሽ ነገር ዓመፀኛ የሆነ ሰው ደግሞ በብዙ ነገርም ዓመፀኛ ነው።”​—ሉቃስ 16:10

  • “የዓለም ክፍል [አይደላችሁም።]”​—ዮሐንስ 15:19

  • “‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም።”—1 ቆሮንቶስ 10:21

  • “የብልግና ተግባሮችን በመፈጸም፣ ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ፈንጠዝያ፣ በፉክክር ብዙ በመጠጣትና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ እየፈጸማችሁ ትመላለሱበት የነበረው ያለፈው ጊዜ በቂ ነው።”​—1 ጴጥሮስ 4:3

መጽሐፍ ቅዱስ የልደት ቀንን ስለ ማክበር ምን ይላል?

9. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው በምናገኛቸው የልደት በዓሎች ላይ ምን ተፈጽሟል?

9 ልጅ መወለዱ ምንጊዜም ደስ የሚያሰኝ ነገር ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች የልደት በዓላቸውን እንዳከበሩ የሚገልጽበት አንድም ቦታ የለም። (መዝሙር 127:3) ይህ የሆነው ተረስቶ ይሆን? አይደለም፤ ምክንያቱም ሁለት የልደት በዓሎች፣ ማለትም የግብጹ ፈርዖንና የሄሮድስ አንቲጳስ የልደት በዓሎች ተጠቅሰዋል። (ዘፍጥረት 40:20-22፤ ማርቆስ 6:21-29) ይሁን እንጂ ሁለቱም የተጠቀሱት በመጥፎ ነው፤ በተለይ የሄሮድስ የልደት በዓል በተከበረበት ዕለት የአጥማቂው ዮሐንስ ራስ ተቆርጧል።

10, 11. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የልደት በዓልን ስለማክበር ምን አመለካከት ነበራቸው? ለምንስ?

10 ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች . . . የማንኛውንም ሰው የልደት ቀን ማክበር የአረማውያን ልማድ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱ ነበር” ይላል። ለምሳሌ የጥንቶቹ ግሪኮች እያንዳንዱ ሰው ሲወለድ አንዲት መንፈስ እንደምትገኝና ያንን ግለሰብ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እንደምትጠብቀው ያምኑ ነበር። ይህች መንፈስ “ግለሰቡ በተወለደበት ቀን የልደት በዓሉ ከሚከበርለት አምላክ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት ነበራት” በማለት ዘ ሎር ኦቭ በርዝዴይስ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። በተጨማሪም የልደት በዓል ከኮከብ ቆጠራ ጋር ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት አለው።

በዓሎችና የሰይጣን አምልኮ

ሳታኒዝም ወይም የሰይጣን አምልኮ በሚባለው ሃይማኖት ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ቀን የአንድ ሰው የልደት ቀን መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ለምን? ምክንያቱም የሰይጣን አምላኪዎች እያንዳንዱ ሰው ራሱን እንደ አምላክ አድርጎ ለማየት ከፈለገ አምላክ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው የራሱን የልደት ቀን ሲያከብር የአንድን አምላክ የልደት ቀን ማክበሩ ነው ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ ብዙዎች እንዲህ ያለ ከልክ ያለፈ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ዝንባሌ የላቸውም። ይሁን እንጂ ዘ ሎር ኦቭ በርዝዴይስ የተባለው መጽሐፍ “ሌሎች በዓሎች ልብን ደስ የሚያሰኙ ናቸው፤ የልደት በዓል ግን ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ ያደርጋል” ይላል።

የሰይጣን አምላኪዎች በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ግምት የሚሰጧቸው በዓሎች ቫልፑርጊስ ናይት እና ሃሎዊን ናቸው። የዌብስተር መዝገበ ቃላት ቫልፑርጊስ ናይትን “ጠንቋዮች ወደ አንድ ቦታ የሚሰበሰቡበት ቀን እንደሆነ የሚታመነው የሜይ ዴይ ዋዜማ” በማለት ፈቶታል።

11 የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች የልደት በዓልን ያላከበሩት ከአረማውያን አምልኮ ስለመነጨና ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ስለነበረው ብቻ ሳይሆን ካላቸው አቋም አንጻርም ተመልክተውት ሊሆን ይችላል። ይህ ምን ማለት ነው? እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ትሑት ስለነበሩ መወለዳቸው በራሱ እንደ ትልቅ ነገር ተቆጥሮ እንዲከበርላቸው አልፈለጉም።c (ሚክያስ 6:8፤ ሉቃስ 9:48) ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ክብር የሰጡ ከመሆናቸውም በላይ ውድ የሆነውን የሕይወት ስጦታ በማግኘታቸውም አመስግነውታል።d​—መዝሙር 8:3, 4፤ 36:9፤ ራእይ 4:11

12. የምንሞትበት ቀን ከተወለድንበት ቀን የተሻለ የሚሆነው እንዴት ነው?

12 እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ታማኝነታቸውን የጠበቁ ሰዎችን አምላክ የሚያስባቸው ሲሆን የወደፊት ሕይወታቸው ዋስትና ያለው ነው። (ኢዮብ 14:14, 15) መክብብ 7:1 “መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል” ይላል። እዚህ ላይ “ስም” የተባለው አምላክን በታማኝነት በማገልገል ያተረፍነውን ጥሩ ዝና ያመለክታል። ክርስቲያኖች እንዲያከብሩ የታዘዙት ብቸኛው በዓል ልደት ሳይሆን የኢየሱስ ሞት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ኢየሱስ ያተረፈው መልካም “ስም” ለመዳናችን ቁልፍ ሚና ይጫወታል።​—ሉቃስ 22:17-20፤ ዕብራውያን 1:3, 4

በዓለ ትንሣኤ​—የክርስቶስ ትንሣኤ እንደሆነ የሚታሰበው የመራባት አምልኮ

13, 14. በአንዳንድ አገሮች የተለመዱት በበዓለ ትንሣኤ ላይ የሚደረጉ ነገሮች ምንጫቸው ምንድን ነው?

13 እንደ እውነቱ ከሆነ የክርስቶስ ትንሣኤ ነው ተብሎ የሚከበረው በዓለ ትንሣኤ ምንጩ የሐሰት ሃይማኖት ነው። በዓለ ትንሣኤ ተብሎ የተተረጎመው ኢስተር የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል፣ አንግሎ ሳክሰን ይባሉ የነበሩት ሕዝቦች ከሚያመልኳት የንጋትና የጸደይ አምላክ ማለትም ከኢስትሬ ወይም ኦስታራ ጋር ግንኙነት አለው። ታዲያ በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየው እንቁላሎችና ጥንቸል ከበዓለ ትንሣኤ አከባበር ጋር መያያዝ የጀመሩት እንዴት ነው? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንቁላሎቹ “የአዲስ ሕይወትና የትንሣኤ ዋነኛ ምሳሌ” ሲሆኑ ጥንቸል ደግሞ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ የመራባት ምሳሌ ሆኖ እንዳገለገለ ይገልጻል። በመሆኑም በዓለ ትንሣኤ የክርስቶስ ትንሣኤ በሚል ሽፋን የሚከበር የመራባት አምልኮ ነው።e

14 ይሖዋ የልጁ ትንሣኤ ጸያፍ በሆነ የመራባት አምልኮ ሥርዓት እንዲታሰብ ይፈቅዳል? በፍጹም! (2 ቆሮንቶስ 6:17, 18) በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ትንሣኤ እንድናከብር ትእዛዝም ሆነ ፈቃድ አይሰጥም። ስለሆነም የአምላክን ፈቃድ በመተላለፍ በበዓለ ትንሣኤ ስም የክርስቶስን ትንሣኤ ማክበር ከባድ ጥፋት ይሆናል።

ሃሎዊን​—ቅዱስ የሆነ በዓል አይደለም

15. የሃሎዊን አመጣጥ ምንድን ነው? ይህን በዓል ለማክበር ስለተመረጠው ቀን ምን ማለት ይቻላል?

15 በጥቅምት 31 ምሽት ላይ የሚከበረው ሃሎዊን ከጠንቋዮች፣ ከአስፈሪ ፍጥረታት እንዲሁም ከአስቂኝና አስደናቂ አለባበሶች ጋር የተያያዘ በዓል ሲሆን የሁሉም ቅዱሳን ቀን ዋዜማ በመባልም ይታወቃል። በዓሉ የመነጨው ኬልት ከሚባሉት የጥንት የብሪታንያና የአየርላንድ ሕዝቦች ነው። እነዚህ ሕዝቦች ኅዳር 1 አካባቢ ጨረቃ ሙሉ በምትሆንበት ጊዜ “የበጋ ፍጻሜ” የሚል ትርጉም ያለውን ሳውሄን የሚባል በዓል ያከብሩ ነበር። ሳውሄን በሚከበርበት ጊዜ ሰዎችን ከመንፈሳዊው ዓለም የሚለየው መጋረጃ ስለሚከፈት በዚህ ጊዜ ክፉዎቹም ሆኑ ጥሩዎቹ መናፍስት በምድር ላይ ይዘዋወራሉ ብለው ያምኑ ነበር። የሞቱ ሰዎች ነፍሳት ወደየቤታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ቤተሰቦቻቸው እነሱን ለማስደሰት የሚበላና የሚጠጣ ነገር አዘጋጅተው ያስቀምጡላቸዋል። በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ልጆች ጣረ ሞት ወይም ጠንቋይ የሚያስመስል ልብስ ለብሰው ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ስጦታ ካልተሰጣቸው በተንኮል አንድ ነገር እንደሚያደርጉ ሲያስፈራሩ ሳይታወቃቸው የሳውሄን ክብረ በዓል ተጠብቆ እንዲቆይ እያደረጉ ነው።

ሠርጋችሁ ንጹሕ ይሁን

16, 17. (ሀ) ለመጋባት ያቀዱ ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው ያሉትን ከሠርግ ጋር የተያያዙ ልማዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር መመርመር የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ሩዝ ወይም ሌሎች ነገሮችን እንደመበተን ያሉ ልማዶችን በተመለከተ ክርስቲያኖች ግምት ውስጥ ሊያስገቡት የሚገባቸው ነገር ምንድን ነው?

16 ‘የሙሽራና የሙሽሪት ድምፅ ዳግመኛ በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ከቶ የማይሰማበት’ ጊዜ ቀርቧል። (ራእይ 18:23) እንዲህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ጋብቻን ከሠርጉ ዕለት ጀምሮ ሊያረክሱ የሚችሉ መናፍስታዊ ድርጊቶችን የምትፈጽም በመሆኗ ነው።​—ማርቆስ 10:6-9

17 ባሕሎችና ልማዶች ከአገር አገር ይለያያሉ። ምንም ክፋት የሌላቸው የሚመስሉ አንዳንድ ልማዶች፣ ለሙሽሮቹ ወይም ለእንግዶቻቸው መልካም “ዕድል” ያስገኛሉ ከሚባሉ ባቢሎናዊ ልማዶች የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 65:11) እንደነዚህ ካሉት ልማዶች መካከል አንዱ ሩዝ ወይም ሌላ ነገር ሙሽሮቹ ላይ መበተን ነው። ይህ ልማድ ምግብ የክፉ መናፍስትን ቁጣ ስለሚያበርድ በሙሽሮቹ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ያደርጋል ከሚል እምነት የመነጨ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ሩዝ ከመራባት፣ ከደስታ እንዲሁም ከረጅም ዕድሜ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት እንዳለው ለዘመናት ሲታመን ኖሯል። ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ ለመኖር የሚፈልጉ ሁሉ እንዲህ ካለው ርኩስ ልማድ እንደሚርቁ ግልጽ ነው።​—2 ቆሮንቶስ 6:14-18

18. ሠርግ ለሚደግሱ ተጋቢዎችም ሆነ ለታዳሚዎች የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመሪያ ሊሆኗቸው ይገባል?

18 የይሖዋ አገልጋዮችም በተመሳሳይ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችና የሠርግ ድግሶች ሊኖራቸው የሚገባውን ክርስቲያናዊ ክብር ዝቅ ሊያደርጉ ወይም የአንዳንዶችን ሕሊና ሊጎዱ ከሚችሉ ዓለማዊ ልማዶች ይርቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በግብዣው ሰዓት ስለ ሙሽሮቹ አስተያየት መስጠት ከፈለጉ አሽሙር የተቀላቀለበት ወይም በተዘዋዋሪ ስለ ጾታ ግንኙነት መልእክት የሚያስተላልፍ ነገር ከመናገር ይቆጠባሉ። በተጨማሪም ሙሽሮቹንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ሊያሳፍር የሚችል ቀልድ አይቀልዱም። (ምሳሌ 26:18, 19፤ ሉቃስ 6:31፤ 10:27) ከዚህም በላይ “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” የሚንጸባረቅበትና ልከኝነት የጎደለው ድል ያለ ድግስ አይደግሱም። (1 ዮሐንስ 2:16) ሠርግ ለመደገስ የምታስብ ከሆነ ይሖዋ ይህን ልዩ ቀን መለስ ብለህ ስታስብ የምትጸጸትበት ሳይሆን የምትደሰትበት እንዲሆን እንደሚፈልግ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብህም።f

ጽዋ ማንሳት ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው?

19, 20. ጽዋ የማንሳት ልማድ አጀማመርን በተመለከተ አንድ መጽሐፍ ምን ብሏል? እንዲህ ያለው ልማድ በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የማይኖረው ለምንድን ነው?

19 በሠርግና በሌሎች ግብዣዎች ላይ መልካም ምኞትን ለመግለጽ ጽዋን ማንሳት የተለመደ ነው። በ1995 የተዘጋጀው ኢንተርናሽናል ሃንድቡክ ኦን አልኮሆል ኤንድ ካልቸር የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በአሁኑ ጊዜ ጽዋን ማንሳት . . . ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚሠራበት ባይሆንም ለአማልክት . . . ቅዱስ ፈሳሾች ይቀርቡበት ከነበረው ጥንታዊ የመጠጥ መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ ጋር የተቆራኘ ሊሆን ይችላል። የመጠጥ መሥዋዕቱ የሚቀርበው መልካም ምኞትን ለመግለጽ ሲሆን ‘ረጅም ዕድሜ ለእገሌ!’ አሊያም ‘ለጤንነትህ!’ የሚል አጭር ጸሎት ይቀርብ ነበር።”

20 እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች ጽዋ ማንሳትን ከሃይማኖት ወይም ከአጉል እምነት ጋር ግንኙነት ያለው ድርጊት እንደሆነ አድርገው አይመለከቱት ይሆናል። ቢሆንም የወይን ጽዋን ወደ ላይ ማንሳት ከሰው በላይ ከሆነ ኃይል እርዳታ ይፈልጉ ይመስል “ከሰማይ” በረከትን እንደመጠየቅ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ይህ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ነው።​—ዮሐንስ 14:6፤ 16:23g

‘ይሖዋን የምትወዱ ክፋትን ጥሉ’

21. ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ይዘት ባይኖራቸውም በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ በሆኑ እንዴት ባሉ ክብረ በዓሎች ላይ አይገኙም? ለምንስ?

21 አንዳንድ አገሮች ወሲባዊ ስሜት የሚቀሰቅስ ጭፈራ የሚጨፈርባቸውና የግብረ ሰዶማውያን የአኗኗር ዘይቤ የሚወደስባቸው ካርኒቫል ወይም ማርዲ ግራስ የሚባሉ ዓመታዊ ክብረ በዓሎችን ያዘጋጃሉ። ታላቂቱ ባቢሎን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የምትደግፋቸው እነዚህ ዓመታዊ በዓሎች የዛሬው ዓለም የደረሰበትን የሥነ ምግባር ዝቅጠት የሚያንጸባርቁ ናቸው። አንድ ‘ይሖዋን የሚወድ’ ሰው እንዲህ ባለው በዓል ላይ ቢገኝ ወይም በዓሉን ቢመለከት ተገቢ ይሆናል? እንዲህ ማድረጉ ክፉ የሆነውን ሁሉ ከልቡ እንደሚጠላ ያሳያል? (መዝሙር 1:1, 2፤ 97:10) “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” ሲል የጸለየውን መዝሙራዊ ዝንባሌ መኮረጅ ምንኛ የተሻለ ነው!​—መዝሙር 119:37

22. አንድ ክርስቲያን በሕሊናው ተመርቶ በአንድ ክብረ በዓል ላይ ለመካፈል ወይም ላለመካፈል ሊወስን የሚችለው መቼ ነው?

22 አንድ ክርስቲያን፣ የተለያዩ በዓሎች በሚከበሩባቸው ቀናት ሌሎች በዓሉን እንደሚያከብር እንዲሰማቸው የሚያደርግ ምንም ዓይነት ድርጊት ላለመፈጸም ይጠነቀቃል። ጳውሎስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:31፤ “ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በሌላ በኩል ግን አንድ ልማድ ወይም ክብረ በዓል ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በግልጽ የሚታወቅና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት የማይጥስ ከሆነ እንዲሁም የአገር ፍቅር ስሜት የሚንጸባረቅበት ወይም የፖለቲካ በዓል ካልሆነ እያንዳንዱ ክርስቲያን በበዓሉ ለመካፈል ወይም ላለመካፈል በግሉ ሊወስን ይችላል። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ ግን ሌሎችን እንዳያሰናክል ስሜታቸውን ከግምት ውስጥ ያስገባል።

አምላክን በቃልም ሆነ በድርጊት ማክበር

23, 24. ስለ ይሖዋ የጽድቅ ሕጎች ጥሩ ምሥክርነት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

23 ብዙ ሰዎች አንዳንድ የታወቁ በዓሎች የሚከበሩባቸውን ቀናት የሚመለከቷቸው ቤተ ዘመድ የሚሰባሰብባቸው አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርገው ነው። በዚህ ምክንያት አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው አቋማችን ፍቅር የጎደለው ወይም ጽንፈኛ ሆኖ ከታየው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ተሰባስበው ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስታቸው በደግነት ልናስረዳው እንችላለን። (ምሳሌ 11:25፤ መክብብ 3:12, 13፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7) በማናቸውም የዓመቱ ቀናት ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ተገናኝተን እንጨዋወታለን። ይሁን እንጂ ለአምላክና ለጽድቅ ሕጎቹ ባለን ፍቅር ምክንያት እንደነዚህ ያሉትን አስደሳች አጋጣሚዎች እሱን በሚያሳዝኑ ልማዶች መበከል አንፈልግም።​—“እውነተኛ አምልኮ የላቀ ደስታ ያስገኛል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

እውነተኛ አምልኮ የላቀ ደስታ ያስገኛል

ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው፤ አገልጋዮቹም ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ይህ ሐቅ በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ተንጸባርቋል:-

  • “በደስታ የተሞላ ልብ . . . የማይቋረጥ ፈንጠዝያ አለው።”​—ምሳሌ 15:15

  • “ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ [የአምላክ] ችሮታ ነው።”​—መክብብ 3:12, 13

  • “ለጋስ ሰው ደግሞ፣ ልግስናን በተመለከተ ምክር ይሰጣል፤ እንዲሁም የልግስናን ተግባር ደግፎ ይቆማል።”​—ኢሳይያስ 32:8 NW

  • “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። . . . ምክንያቱም ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነው።”​—ማቴዎስ 11:28, 30

  • “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”​—ዮሐንስ 8:32

  • “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።”​—2 ቆሮንቶስ 9:7

  • “የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ . . . ደግነት፣ ጥሩነት [ነው]።”​—ገላትያ 5:22

  • “የብርሃን ፍሬ ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት፣ ጽድቅና እውነት የያዘ ነው።”​—ኤፌሶን 5:9

24 አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በቅን ልቦና ተነሳስተው ጥያቄ ለሚጠይቁ ሰዎች ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?h በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ላይ የሚገኙትን ነጥቦች በማስረዳት ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ዓላማችን ልባቸው በእውነት እንዲማረክ መርዳት እንጂ በክርክር መርታት እንዳልሆነ አስታውስ። ስለዚህ በአክብሮትና በረጋ መንፈስ ተናገር፤ ‘ንግግርህ ምንጊዜም ለዛ ያለውና በጨው የተቀመመ ይሁን።’​—ቆላስይስ 4:6

25, 26. ወላጆች ልጆቻቸው ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግና እምነታቸው እንዲጎለብት ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

25 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን በሚገባ ተምረናል። አንዳንድ ነገሮችን ለምን እንደምናምንና እንደምናደርግ፣ ሌሎችን ደግሞ ለምን እንደማናደርግ እናውቃለን። (ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲያገናዝቡ አስተምሯቸው። እንዲህ ስታደርጉ እምነታቸውን ትገነባላችሁ፤ ስለ እምነታቸው ለሚጠይቋቸው ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ መስጠት እንዲችሉ ታሠለጥኗቸዋላችሁ፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚወዳቸው እርግጠኞች እንዲሆኑ ትረዷቸዋላችሁ።​—ኢሳይያስ 48:17, 18፤ 1 ጴጥሮስ 3:15

26 አምላክን “በመንፈስና በእውነት” የሚያመልኩ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውን በዓሎች ባለማክበር ብቻ አይወሰኑም። ከዚህ ይልቅ በሁሉም የኑሯቸው ዘርፎች ሐቀኛ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ሐቀኛ መሆን የማይቻል ነገር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይሁንና በሚቀጥለው ምዕራፍ እንደምንመለከተው የአምላክ መንገዶች ምንጊዜም ትክክል ናቸው።

a “በበዓሉ ላይ ልካፈል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት። በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) ላይ የበርካታ በዓሎች ዝርዝር ይገኛል።

b በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠርና በዓለም ታሪክ መሠረት ኢየሱስ የተወለደው በ2 ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በዛሬው የቀን አቆጣጠር መስከረምና ጥቅምት ላይ በሚውለው ኤታኒም በሚባለው የአይሁዶች ወር ላይ እንደሆነ ይታመናል።​—በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 56-57ን ተመልከት።

c “በዓሎችና የሰይጣን አምልኮ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

d የሕጉ ቃል ኪዳን አንዲት ሴት ከወለደች በኋላ የኃጢአት መሥዋዕት እንድታቀርብ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 12:1-8) ኃጢአት ከወላጅ ወደ ልጅ እንደሚተላለፍ የሚያስታውሰው ይህ ሕግ፣ እስራኤላውያን ስለ ልጅ መውለድ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸውና አረማውያን ከልደት ቀን ጋር በተያያዘ የነበሯቸውን ልማዶች እንዳይከተሉ ሳያሳስባቸው አልቀረም።​—መዝሙር 51:5

e በተጨማሪም ኦስትሬ (ወይም ኢስትሬ) የመራባት አምላክ ነበረች። ዘ ዲክሽነሪ ኦቭ ሚቶሎጂ እንደሚለው “እንቁላሎችን የምትወድ በጨረቃ ላይ ያለች ጥንቸል ነበረቻት፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የጥንቸል ጭንቅላት እንዳላት ተደርጋ ትገለጽ ነበር።”

f በጥቅምት 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 18-31 ላይ የጋብቻ ሥነ ሥርዓትንና የሠርግ ድግሶችን በሚመለከት የወጡትን ሦስት ርዕሶች ተመልከት።

g የየካቲት 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 30-31ን ተመልከት።

h በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ማድረግ

ለይሖዋ ያለን ፍቅርና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ስለምናውልበት መንገድ ያለን ግንዛቤ የሚፈተንበት ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የአንዲት ክርስቲያን የማያምን የትዳር ጓደኛ በአንድ የበዓል ቀን ከዘመዶቹ ጋር አብረው ምሳ ወይም ራት እንዲመገቡ ሊጋብዛት ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ሕሊናቸው ግብዣውን እንዲቀበሉ ሲፈቅድላቸው ሌሎቹ ግን አይፈቅድላቸው ይሆናል። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን ግብዣ ከተቀበለ፣ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በዓሉን እንደማያከብርና እዚያ የተገኘው ከዘመዶቹ ጋር አብሮ ምግብ በመመገብ ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ብቻ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳዩ መሆን አለባቸው።

አንድ ክርስቲያን እንዲህ ወዳለው ግብዣ ከመሄዱ በፊት ሊያጋጥም ስለሚችለው ሁኔታ ከትዳር ጓደኛው ጋር በአክብሮት መነጋገሩ አስተዋይነት ነው። ቤተ ዘመዶቹ አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ማከናወን ቢፈልጉና የይሖዋ ምሥክር የሆነው ወገን ግን በዚህ ለመካፈል ፈቃደኛ ባይሆን የትዳር ጓደኛው ሊሸማቀቅ እንደሚችል ሊገልጽ ይችላል። የማያምነው የትዳር ጓደኛ ከዘመዶቹ ጋር በሌላ ቀን ቢገናኙ የተሻለ እንደሚሆን ሊወስን ይችላል።​—1 ጴጥሮስ 3:15

የአንዲት ክርስቲያን ባል የሚስቱን ማብራሪያ ከሰማ በኋላም አብራው እንድትሄድ ቢወተውታትስ? ባሏ የቤተሰቡ ራስ እንደመሆኑ መጠን ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት ልታስብ ትችላለች። (ቆላስይስ 3:18) በዚህ ዕለት ቤተሰቡ በዘመዶቻቸው ቤት እንዲመገቡ ዝግጅት አድርጓል። ይህን አጋጣሚ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ልትጠቀምበት ትችል ይሆናል። ምግቡ በበዓል ቀን ስለተበላ ብቻ የረከሰ አይሆንም። (1 ቆሮንቶስ 8:8) ይህች ክርስቲያን ምግቡን በማንኛውም ቀን እንደሚበላ ምግብ ቆጥራ ልትበላ የምትችል ቢሆንም በበዓሉ የመልካም ምኞት መግለጫዎች፣ መዝሙሮችና ሌሎች ሥርዓቶች አትካፈልም፤ ወይም ጽዋ አታነሳም።

ሌላው ከግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው ጉዳይ ደግሞ እንዲህ ባለው ግብዣ ላይ መገኘት በሌሎች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት ነው። አንዲት ክርስቲያን ሚስት በዚያ ቀን የማያምኑ ዘመዶችን ለመጠየቅ መሄዷን ሌሎች ቢያውቁ ሊሰናከሉ እንደሚችሉ ማሰብ ይኖርባታል።​—1 ቆሮንቶስ 8:9፤ 10:23, 24

በተጨማሪም ይህች ክርስቲያን ሚስት በበዓል ቀን ከዘመድ አዝማድ ጋር ለመገናኘት ብትወስን አቋሟን እንድታላላ ተጽዕኖ ያደርጉባት ይሆን? ባሏንም ሆነ ራሷን የሚያሳፍር ሁኔታ እንዳይፈጠር ያላት ፍላጎት አቋሟን እንድታላላ ተጽዕኖ ሊያደርግባት ይችላል። ስለሆነም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናዋን ጨምሮ እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ ከግንዛቤ በማስገባት ስለ ጉዳዩ ቀደም ብላ በጥንቃቄ ማሰቧ አስፈላጊ ነው።​—የሐዋርያት ሥራ 24:16

በገና በዓል ሰሞን የሚሰጥ ጉርሻ መቀበል ይገባኛል?

የአንድ ክርስቲያን አሠሪ በገና በዓል ሰሞን ለሠራተኞቹ ስጦታ ወይም ጉርሻ ለመስጠት ሊወስን ይችላል። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን ስጦታ ወይም ክፍያ አልቀበልም ማለት ይኖርበታል? እንዲህ ማለት ላያስፈልገው ይችላል። አሠሪው፣ ተቀጣሪው ይህን ስጦታ በመቀበሉ ገናን ያከብራል ብሎ ላያስብ ይችላል። ከዚህ ይልቅ ኩባንያው ካገኘው ትርፍ ለሁሉም ሠራተኞቹ የተወሰነ ጉርሻ መስጠት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ወይም ጉርሻ ለመስጠት የተነሳሳው ሠራተኞቹ ዓመቱን በሙሉ ለሰጡት አገልግሎት አመስጋኝነቱን ለመግለጽና ተግተው መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ ለማበረታታት ሊሆንም ይችላል። አሠሪው ስጦታ የሰጠው ገናን አከበሩም አላከበሩ ለሁሉም ሠራተኞች ማለትም ለአይሁዶች፣ ለሙስሊሞች ወይም ለሌሎች ነው። ስለዚህ ስጦታው የተሰጠበት ጊዜ የበዓል ሰሞን መሆኑ ወይም ስጦታው የበዓሉን ስም መያዙ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዳይቀበል ምክንያት ይሆናል ማለት አይቻልም።

ስጦታው በሃይማኖታዊ በዓል ምክንያት የተሰጠ እንኳን ቢሆን ስጦታውን የሚቀበለው ሰው ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ አመለካከት እንዳለው ተደርጎ ይቆጠራል ማለት አይደለም። አንድ የሥራ ባልደረባ ወይም ዘመድ ለአንድ የይሖዋ ምሥክር “ይህን በዓል እንደማታከብር አውቃለሁ፣ ቢሆንም ይህን ስጦታዬን እንድትቀበል እፈልጋለሁ” ሊለው ይችላል። ክርስቲያኑ ሕሊናው የማይረብሸው ከሆነ ስጦታውን ለመቀበልና ስለ በዓሉ ምንም ነገር ሳያነሳ ምስጋናውን ለመግለጽ ሊመርጥ ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 23:1) ምናልባት ሌላ አመቺ አጋጣሚ ሲያገኝ ስጦታውን የሰጠውን ሰው ሳያስቀይም በዘዴ አቋሙን ሊያስረዳ ይችል ይሆናል።

ይሁን እንጂ ስጦታውን የሚሰጠው ሰው ክርስቲያኑ ለእምነቱ ጥብቅ እንዳልሆነና ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ሲል አቋሙን ከመለወጥ ወደኋላ እንደማይል ለማሳየት ፈልጎ ቢሆንስ? በዚህ ጊዜ ስጦታውን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አይኖርበትም። አምልኳችን ለይሖዋ አምላክ ብቻ የተወሰነ እንዲሆን እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው።​—ማቴዎስ 4:8-10

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ