የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • yp2 ምዕ. 17 ገጽ 142-146
  • ስለ ትምህርት ቤት ጓደኝነት ምን ማወቅ ይገባኛል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ ትምህርት ቤት ጓደኝነት ምን ማወቅ ይገባኛል?
  • ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?
  • ምን ማድረግ ትችላለህ?
  • የትምህርት ቤት ጓደኝነት ገደቡ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት?
    ንቁ!—2006
  • ጥሩ ጓደኞች እንዲኖሩኝ ምን ላድርግ?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
  • የተሻሉ ጓደኞች ያስፈልጉኝ ይሆን?
    ንቁ!—2009
  • ጓደኞችህን በጥበብ ምረጥ
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
ለተጨማሪ መረጃ
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
yp2 ምዕ. 17 ገጽ 142-146

ምዕራፍ 17

ስለ ትምህርት ቤት ጓደኝነት ምን ማወቅ ይገባኛል?

“አንዳንድ ጊዜ የተወሰኑ ልጆች አንድ ላይ ሆነው ስመለከት ‘አቤት! እንዴት ደስ የሚሉ ጓደኛሞች ናቸው’ ብዬ አስባለሁ። እኔም እንደ እነሱ ጓደኞች እንዲኖሩኝ እመኛለሁ።”​—ጆ

“በትምህርት ቤት ጓደኞች ለማግኘት ብዙም አልቸገርም። ከሌሎች ጋር ለመግባባት ጊዜ አይወስድብኝም። የእኔ ችግር ይህ ነው።”​—ማሪያ

ሁሉም ሰው ደስታውንም ሆነ ሐዘኑን ሊጋሩት የሚችሉ ጓደኞች ያስፈልጉታል። ኢየሱስ ወዳጆች የነበሩት ሲሆን ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተው ነበር። (ዮሐንስ 15:15) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜም የቅርብ ጓደኛውና ‘የሚወደው ደቀ መዝሙሩ’ ዮሐንስ አጠገቡ ነበር። (ዮሐንስ 19:25-27፤ 21:20) አንተም በተመሳሳይ በደስታህም ሆነ በችግርህ ጊዜ ከጎንህ የሚሆኑ ጓደኞች ያስፈልጉሃል!

ምናልባት አንተም በትምህርት ቤት አብረውህ ከሚማሩት ልጆች መካከል በቀላሉ የምትግባባቸው አንድ ሁለት ጓደኞች አግኝተህ ይሆናል። ከእነዚህ ልጆች ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ ተመሳሳይ አመለካከት ያለህ ከመሆኑም በላይ ከእነሱ ጋር ማውራት ያስደስትሃል። እነዚህ ልጆች ‘መጥፎ ጓደኞች’ ከሚባሉት መካከል እንደማይፈረጁ ይሰማህ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) አን የተባለች ወጣት “በየቀኑ ማለት ይቻላል ከእነዚህ ልጆች ጋር ትገናኛላችሁ” ብላለች። “በመሆኑም ከእነሱ ጋር መሆን አይከብዳችሁም። ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር ስትሆኑ ግን እንደዚህ አይሰማችሁም፤ ምክንያቱም ከእነሱ ጋር ስትሆኑ እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባችሁ የሚሰማችሁ ጊዜ አለ። በትምህርት ቤት ግን ዘና ማለት ትችላላችሁ።” ከዚህም በላይ ሎይስ የተባለችውን ወጣት አመለካከት ትጋራ ይሆናል። እንዲህ ብላለች፦ “እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች እንደሚያስቡት ከሌሎች የተለየን እንዳልሆንን ማለቴ እንደ እነሱ እንደሆንን ለትምህርት ቤት ጓደኞቼ ማሳየት እፈልግ ነበር።” እንደነዚህ ያሉት አመለካከቶች አብረውህ ከሚማሩት ልጆች ጋር የጠበቀ ጓደኝነት ለመመሥረት በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ?

ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ማሪያ ምን እንዳጋጠማት እንመልከት። በቀላሉ የምትግባባ መሆኗ በርካታ ጓደኞች ለማፍራት ያስቻላት ቢሆንም የት ላይ ገደብ እንደምታበጅ ለመወሰን ተቸግራ ነበር። ማሪያ እንዲህ ትላለች፦ “በሴቶችም ሆነ በወንዶች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ያስደስተኝ ነበር። በዚህም ምክንያት በዚህ ዓለም ማጥ ውስጥ ይበልጥ እየተዘፈቅኩ ሄድኩ።” ሎይስም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሟታል። “የሌሎቹ ልጆች አመለካከት ተጋባብኝ። እንደ እነሱ መሆን ጀመርኩ” ብላለች።

ይህ መሆኑ የሚያስገርም ነገር አይደለም። ከአንድ ሰው ጋር የጠበቀ ጓደኝነት እንዲኖራችሁ፣ ፍላጎታችሁና ለነገሮች ያላችሁ አመለካከት ተመሳሳይ መሆን አለበት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነታችሁንና አቋማችሁን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር የቅርብ ጓደኝነት ከመሠረታችሁ እንዲህ ያለው ጓደኝነት በምግባራችሁ ላይ ተጽዕኖ ማድረጉ የማይቀር ነው። (ምሳሌ 13:20) ሐዋርያው ጳውሎስ “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” ብሎ መጻፉ የሚያስደንቅ አይደለም።​—2 ቆሮንቶስ 6:14

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ጳውሎስ የሰጠው ምክር አብረውህ ከሚማሩት ልጆች ሙሉ በሙሉ በመራቅ ራስህን ልታገል እንደሚገባ የሚጠቁም ነው? በፍጹም! ክርስቲያኖች ‘ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት’ እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም የተለያየ ዘር፣ ሃይማኖትና ባሕል ካላቸው ወንዶችና ሴቶች ጋር እንዴት መግባባት እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው።​—ማቴዎስ 28:19

በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። እምነቱን የማይጋሩት ቢሆኑም እንኳ ‘ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር’ እንዴት መነጋገር እንደሚችል ያውቅ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:22, 23) አንተም የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። ከእኩዮችህ ጋር ስትሆን የማትከብድ ሰው ለመሆን ጥረት አድርግ። ከእነሱ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ተማር። ይህን ስታደርግ ግን አብረውህ የሚማሩትን ልጆች አነጋገርና ምግባር እንዳትኮርጅ ተጠንቀቅ። ከዚህ በተቃራኒ ከእነሱ ጋር ስትጨዋወት በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት ለመኖር የመረጥከው ለምን እንደሆነ በተቻለ ፍጥነት ንገራቸው፤ ይህን የምታደርገው ግን በአክብሮት ሊሆን ይገባል።​—2 ጢሞቴዎስ 2:25

እንዲህ ማድረግህ ከሌሎች ለየት ብለህ እንድትታይ ስለሚያደርግህ ቀላል እንደማይሆንልህ የታወቀ ነው። (ዮሐንስ 15:19) ይሁን እንጂ ነገሩን እስቲ በዚህ መንገድ ተመልከተው፦ ያለኸው ሕይወት አድን ጀልባ ላይ ቢሆንና እርዳታ የሚሹ በርካታ ሰዎች በዙሪያህ ብትመለከት ምን ታደርጋለህ? እነሱን ለመርዳት ስትል ጀልባውን ትተህ ውኃው ውስጥ ትገባለህ? እንዲህ እንደማታደርግ ምንም ጥርጥር የለውም!

በተመሳሳይም አብረውህ የሚማሩት አብዛኞቹ ልጆች የይሖዋ ወዳጅ በመሆን የሚገኘውን ጥበቃ አያገኙም። (መዝሙር 121:2-8) ከእነዚህ ልጆች ጋር ለመቀራረብ ስትል የይሖዋን መመሪያዎች ብትተው መንፈሳዊ ጤንነትህንና ደስታህን በማጣት ራስህን ችግር ውስጥ ከማስገባት ሌላ የምትፈይደው ነገር አይኖርም። (ኤፌሶን 4:14, 15፤ ያዕቆብ 4:4) ከዚህ ይልቅ አብረውህ የሚማሩት ልጆች ይሖዋን እንዴት ማገልገል እንደሚችሉ ብታሳያቸው፣ በምሳሌያዊ አነጋገር አንተ ወዳለህበት ሕይወት አድን ጀልባ እንዲገቡ ብትረዳቸው ምንኛ የተሻለ ይሆናል! በእርግጥም እውነተኛ ጓደኛ መሆን የሚቻልበት ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖራል?

ቁልፍ ጥቅስ

“ምሥራቹን ከሌሎች ጋር እካፈል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።”​—1 ቆሮንቶስ 9:23

ጠቃሚ ምክር

አብረውህ ከሚማሩት ልጆች መካከል አንዳንዶቹ ስለ እምነትህ ለማወቅ የሚፈልጉ ከሆነ እነሱም አመለካከታቸውን እንዲገልጹ ዕድል ስጣቸው። ሲናገሩ በጥሞና አዳምጣቸው። አንተም ሐሳብህን ስትገልጽ “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ተናገር።​—1 ጴጥሮስ 3:15

ይህን ታውቅ ነበር?

በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑ ብዙዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተማሩት ስለ እምነታቸው በድፍረት ከተናገሩ የክፍል ጓደኞቻቸው ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አብሮኝ ከሚማር አንድ ልጅ ጋር በጣም እንደተቀራረብኩ ከተሰማኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

አብሮኝ የሚማር ልጅ በእምነቴ ምክንያት ካሾፈብኝ ሁኔታውን ለመቋቋም እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጓደኞች ከማፍራት ይልቅ በትምህርት ቤት ካሉት ልጆች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ቀላል ሊሆን የሚችለው ለምን ይመስልሃል?

● እምነትህን ከማይጋሩ የክፍል ጓደኞችህ ጋር ከትምህርት ሰዓት ውጪ ጊዜ ማሳለፍ ምን አደጋዎች አሉት?

● የይሖዋ ምሥክር መሆንህን አብረውህ ለሚማሩት ልጆች ማሳወቅህ ምን ጥቅሞች አሉት?

[በገጽ 143 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በትምህርት ቤት ሌሎቹ ልጆች የሚያደርጉትን ሁሉ አደርግ ስለነበር ጓደኞች ለማግኘት ብዙም አልተቸገርኩም። ሆኖም ከስህተቴ ተማርኩ። በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ልተማመንባቸው የምችል ጓደኞች አሉኝ።”​—ዳንኤል

[በገጽ 146 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እየሰመጠ ያለን ሰው ለመርዳት የተሻለው መንገድ የትኛው ነው? ውኃው ውስጥ ዘሎ መግባት ወይስ ግለሰቡ ሕይወት አድን ጀልባ ላይ እንዲወጣ መርዳት?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ