የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • yp2 ምዕ. 18 ገጽ 150-155
  • ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
  • ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሥራ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ
  • ሚዛንህን ጠብቅ
  • ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—1999
  • ገንዘቤን በቁጠባ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ
    ንቁ!—2015
  • ሥራ ለማግኘት የሚረዱ አምስት ቁልፍ ሐሳቦች
    ንቁ!—2005
ለተጨማሪ መረጃ
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
yp2 ምዕ. 18 ገጽ 150-155

ምዕራፍ 18

ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

“መኪና ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ማግኘት እፈልጋለሁ።”​—ሰርዞ

“ገበያ መውጣት ደስ ይለኛል።”​—ሎሪአን

“እንዲኖሩኝ የምፈልጋቸው ምርጥ ምርጥ ነገሮች አሉ፤ ወላጆቼ ግን እነዚህን ነገሮች የመግዛት አቅም የላቸውም።”​—ሚካኤል

አንተም ገንዘብ ማግኘት የምትፈልግበት ተመሳሳይ ምክንያት ሊኖርህ ይችላል። አሊያም ደግሞ ቤተሰብህን ለመደገፍ ገንዘብ ማግኘት ይኖርብህ ይሆናል። ለቤት ወጪ ገንዘብ መስጠት ባያስፈልግህም እንኳ ልብስህን ራስህ መግዛትህ ወይም ሌሎች የግል ወጪዎችህን መሸፈንህ ወላጆችህ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ጭንቀት ሊቀንስ ይችላል።

በሌላ በኩል ግን ከላይ ያለው ሐሳብ አንተን እንደማይመለከት ይሰማህ ይሆናል፤ ዞሮ ዞሮ ለራስህም ሆነ ለቤተሰብህ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለሟሟላት ገንዘብ ያስፈልጋል። ኢየሱስ፣ ‘ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥት ለሚፈልጉ’ ሁሉ አምላክ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚሰጣቸው ቃል የገባ ቢሆንም አንድ ክርስቲያን እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት የራሱን ጥረት ማድረግ አለበት። (ማቴዎስ 6:33፤ የሐዋርያት ሥራ 18:1-3፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10) ታዲያ ገንዘብ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ከምንም በላይ ደግሞ፣ ምንጊዜም ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ሥራ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ

ወላጆችህ አንተ በጣም የምትፈልገውን ነገር ለመግዛት አቅማቸው የማይፈቅድ ከሆነ ያንን ነገር አንተ ራስህ ለመግዛት የሚያስችልህ ገንዘብ እንዲኖርህ ሥራ ማግኘት ትችል ይሆናል። ስለ ጉዳዩ ወላጆችህን አማክራቸው። እንዲህ ለማድረግ በመነሳሳትህ ደስ ሊላቸው ይችላል። ወላጆችህ በሐሳብህ እንደተስማሙና ሕጉም ለመሥራት እንደሚፈቅድልህ እናስብና ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ሥራ ለማግኘት የሚረዱ አራት ሐሳቦች እንመልከት።

በሰው በሰው አፈላልግ። ሥራ እየፈለግህ እንደሆነ ለጎረቤቶችህ ለአስተማሪዎችህና ለዘመዶችህ ተናገር። ይህን ጉዳይ በቀጥታ ማንሳቱ የሚያሳፍርህ ከሆነ በአንተ ዕድሜ ላይ እያሉ ምን ዓይነት ሥራ ይሠሩ እንደነበር ልትጠይቃቸው ትችላለህ። ሥራ እየፈለግህ መሆንህን ብዙ ሰዎች ባወቁ መጠን ሥራ የማግኘት አጋጣሚህም የዚያኑ ያህል ሰፊ ይሆናል።

ማንኛውንም አጋጣሚ አትለፍ። በጋዜጣ ወይም በኢንተርኔት ላይ የሚወጡ እንዲሁም በገበያ ማዕከሎች፣ በትምህርት ቤትህና በሌሎች ቦታዎች በሚገኙ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎችን ተከታተል። “ሥራ ያገኘሁት በዚህ መንገድ ነው” ሲል ዴቭ የተባለ አንድ ወጣት ይናገራል። “ማስታወቂያውን ጋዜጣ ላይ አነበብኩ፤ ከዚያም በፋክስ ሲቪዬን ከላኩላቸው በኋላ ስልክ ደወልኩላቸው።” በዚህ መንገድ ሥራ ማግኘት ካልቻልክ ወደ ተለያዩ ድርጅቶች ሄደህ መሥራት ስለምትችላቸው ነገሮች በሚያሳምን መንገድ በመግለጽ እንዲቀጥሩህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ።

ሲቪህን አዘጋጅተህ ወደ ተለያዩ ድርጅቶች በትን። አድራሻህን እንዲሁም መሥራት የምትችላቸውን ነገሮችና የሥራ ልምድህን በወረቀት ላይ አስፍር። ምንም የምትጽፈው ነገር እንደሌለህ ይሰማሃል? እስቲ በደንብ አስብበት። ወላጆችህ ቤት በሌሉበት ወቅት ታናናሾችህን ወይም ደግሞ የሌሎች ሰዎችን ልጆች ጠብቀህ ታውቃለህ? ይህ ኃላፊነት ሊጣልብህ የሚችል ሰው እንደሆንክ ያሳያል። አባትህ መኪናውን ሲጠግን አግዘኸው ታውቃለህ? ይህ የጥገና ዝንባሌ እንዳለህ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። በታይፕ መጻፍ አሊያም በኮምፒውተር መጠቀም ትችላለህ? ወይም ደግሞ በትምህርት ቤት የፈጠራ ሥራዎችን እንድትሠሩ በምትታዘዙበት ጊዜ ጥሩ ውጤት ታገኛለህ? እንደነዚህ ያሉት ችሎታዎች በቀጣሪዎች ዘንድ ተፈላጊ ናቸው። እነዚህን ነገሮች በሲቪህ ላይ አካትታቸው። ከዚያም ሲቪህን ሊቀጥሩህ ለሚችሉ ሰዎች አሰራጭ፤ እንዲሁም ጓደኞችህና ዘመዶችህ ሠራተኛ እንደሚፈልግ ለሚያውቁት ሰው እንዲሰጡልህ ጠይቃቸው።

ሥራ ፈጣሪ ሁን። በአካባቢህ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮችን አስብ። ሌሎች ነጋዴዎች ያልያዙትን ዕቃ መሸጥ ወይም ብዙም ያልተለመዱ አገልግሎቶችን መስጠት ትችላለህ? ለምሳሌ አትክልት ትወዳለህ እንበል። አትክልት የመንከባከብና ግቢ የማሳመር አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ እንደምትሰጥ ለሌሎች መናገር ትችላለህ። ወይም ደግሞ ልጆች ማስጠናት ትችል ይሆናል። አሊያም እንደ ልብስ አጠባ፣ ጫማ ማሳመር ወይም መኪና ማጠብ ያሉ ብዙዎች ሊሠሯቸው የማይፈልጓቸውን ሥራዎች ማከናወን ትችል ይሆናል። አንድ ክርስቲያን በእጆቹ መሥራት አያሳፍረውም። (ኤፌሶን 4:28) እርግጥ ነው፣ የግልህን ሥራ ለመሥራት የራስ ተነሳሽነትና ሥርዓታማ መሆን እንዲሁም ሥራው ወደ አንተ እንዲመጣ ከመጠበቅ ይልቅ አንተው ራስህ ወደ ሥራው መሄድ ያስፈልግሃል።

ልትጠነቀቅበት የሚገባ ነገር፦ የራስህን ሥራ ለመጀመር ካሰብክ ከሥራው ጋር በተያያዘ የሚኖሩህን ወጪዎችና ሥራው የሚጠይቀውን ነገር በደንብ ሳታስብ ዘው ብለህ አትግባበት። (ሉቃስ 14:28-30) መጀመሪያ በጉዳዩ ላይ ከወላጆችህ ጋር ተማከር። እንዲሁም አንተ ባሰብከው የሥራ መስክ የተሰማሩ ሰዎችን አነጋግር። ግብር መክፈል ይጠበቅብሃል? የሥራ ፈቃድ ማውጣት ያስፈልግሃል? ይህን ለማጣራት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መሥሪያ ቤቶች ጠይቅ።​—ሮም 13:1

ሚዛንህን ጠብቅ

የትምህርት ቤት ቦርሳህን፣ ኳስህንና ከገበያ የገዛሃቸውን የተለያዩ ነገሮች ተሸክመህ ብስክሌት ለመንዳት ስትሞክር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የምትሸከማቸው ዕቃዎች በበዙ ቁጥር ሚዛንህን መጠበቅ ይበልጥ ከባድ ይሆንብሃል! ከአቅምህ በላይ ለመሥራት የምትሞክር ከሆነም ተመሳሳይ ነገር ያጋጥምሃል። ከትምህርት ሰዓት ውጪ ባለው ጊዜ የምትሠራው ሥራ አብዛኛውን ጊዜህንና ጉልበትህን የሚወስድብህ እንዲሁም አእምሮህን የሚያዝለው ከሆነ ጤንነትህ ሊቃወስ ብሎም የትምህርት ቤት ውጤትህ ሊበላሽ ይችላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አድካሚና ረጅም ሰዓት የሚወስድ ሥራ መሥራት በስብሰባዎች ላይ እንደ መገኘት፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማጥናት እንዲሁም በአገልግሎት እንደ መካፈል ያሉትን ክርስቲያናዊ ልማዶች በሚገባ እንዳታከናውን እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። ሚሼል የተባለች አንዲት ወጣት “ትምህርት ቤትና ሥራ ውዬ ስመለስ በጣም ስለሚደክመኝ ስብሰባ እቀር ነበር” ብላለች።

ገንዘብ ለማግኘት ያለህ ፍላጎት ከአቅምህ በላይ በመሥራት ሚዛንህን እንድትስት እንዳያደርግህ ተጠንቀቅ! ኢየሱስ እውነተኛ ደስታ የሚያገኙት “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ” ሰዎች እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3) ከዚህም በተጨማሪ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ [እንዳልሆነ]” ገልጿል። (ሉቃስ 12:15) ናኦሚ የተባለች አንዲት ወጣት ይህን ምክር ተግባራዊ አድርጋለች። “ቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ግብ እንዲኖረኝ አልፈልግም” ብላለች። “ገንዘብን በማሳደድ ከተጠመድኩ መንፈሳዊነቴ እንደሚጎዳ በሚገባ አውቃለሁ።”

እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ወጣቶች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለማሟላት ሲሉ ረጅም ሰዓት ለመሥራት ይገደዳሉ። ያለህበት ሁኔታ እንደዚህ ካልሆነ ግን ሚዛንህን እስክትስት ድረስ ረጅም ሰዓት የምትሠራበት ምን ምክንያት አለ? በርካታ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ትምህርት እየተማሩ በሳምንት ውስጥ ከ20 ሰዓት በላይ መሥራት ከአቅም በላይ ከመሆኑም ሌላ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። አንዳንድ ባለሙያዎች፣ ወጣቶች በሳምንት ውስጥ በሥራ ላይ የሚያሳልፉት ሰዓት ከስምንት እስከ አሥር ባይበልጥ ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል” ብሏል።​—መክብብ 4:6

“ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለህን ፍላጎት ሊያንቀው እንደሚችል አትዘንጋ። (ማርቆስ 4:19) ስለዚህ ገንዘብ ለማግኘት ከትምህርት ሰዓት ውጪ ለመሥራት ከወሰንክ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ለመስጠት የሚያስችል ፕሮግራም ይኑርህ። ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ አምላክ ጸልይ። ይሖዋ፣ ሁኔታው የሚያስከትልብህን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ሊሰጥህ እንዲሁም መንፈሳዊ ሚዛንህን እንድትጠብቅ ሊረዳህ ይችላል።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 21 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

አንተ ገንዘብን ትቆጣጠረዋለህ ወይስ እሱ አንተን ይቆጣጠርሃል? ገንዘብ ጌታህ እንዳይሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ጥሩ ትምህርት ታገኛለህ።

ቁልፍ ጥቅስ

“ሰነፍ አጥብቆ ይመኛል፤ አንዳችም አያገኝም፤ የትጉዎች ምኞት ግን ይረካል።”​—ምሳሌ 13:4

ጠቃሚ ምክር

ድርጅቶች ክፍት የሥራ ቦታ እንዳላቸው ማስታወቂያ እስኪያወጡ ሳትጠብቅ ሲቪህን አስገባ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በአንዳንድ አካባቢዎች፣ ካሉት ክፍት የሥራ ቦታዎች መካከል በማስታወቂያ የሚወጡት 15 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ሥራ የማግኘት አጋጣሚዬን ለማስፋት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

በየሳምንቱ በሥራ የማሳልፈው ጊዜ ከ ․․․․․ ሰዓት እንዳይበልጥ አደርጋለሁ።

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ገንዘብ ማግኘት ያስፈለገህ ለምንድን ነው?

● ሥራ መሥራት ብትጀምር ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ?

● ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 153 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ደስታህ የተመካው የተለያዩ ነገሮችን በማግኘት ላይ ብቻ ከሆነ በፍጹም ደስተኛ አትሆንም። ምክንያቱም ምንጊዜም አዲስ ነገር ማግኘት ትፈልጋለህ። ስለዚህ ባለህ ነገር መደሰትን መማር ያስፈልግሃል።”​—ዮናታን

[በገጽ 155 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ገንዘብን አክብረው እንጂ አትውደደው

በምግብ ዝግጅት ለተካነ ሰው የሰላ ቢላ ጠቃሚ መሣሪያ ነው። ይኸው ቢላ ልምድ በሌለው ወይም ጥንቁቅ ባልሆነ ሰው እጅ ቢገባ ግን ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ገንዘብ እንደ ሰላ ቢላ ነው። አጠቃቀሙን ካወቅህበት ጠቃሚ መሣሪያ ነው። ካልተጠነቀቅህ ግን ጉዳት ሊደርስብህ ይችላል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ የገንዘብ ፍቅር እንዳያድርብን አስጠንቅቆናል። አንዳንዶች ሀብትን ሲያሳድዱ ከጓደኞቻቸው፣ ከቤተሰባቸው አልፎ ተርፎም ከአምላክ ጋር ያላቸው ግንኙነት ተበላሽቷል። በዚህ ምክንያት “ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም ተማር። ገንዘብን አክብረው እንጂ አትውደደው!

[በገጽ 153 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በርካታ ኃላፊነቶችን መሸከም ሚዛንን መጠበቅ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ