ምዕራፍ 34
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ያለብኝ ለምንድን ነው?
ከሁለት ልጆች ጋር በትምህርት ቤታችሁ ካፊቴሪያ ውስጥ ምሳችሁን እየበላችሁ እያለ በቅርቡ ወደ ትምህርት ቤታችሁ የመጣው ወጣት ወደ ካፊቴሪያው ሲገባ አያችሁት።
በዚህ ጊዜ አንደኛዋ ልጅ “ዮናስ በጣም ወዶሻል፤ አስተያየቱ ራሱ ያስታውቃል” አለችሽ። “ዓይኑን እኮ ከአንቺ ላይ መንቀል አልቻለም!”
ሌላኛዋም ወደ አንቺ ጠጋ ብላ “ደስ የሚለው ደግሞ አልተያዘም!” በማለት ሹክ ትልሻለች።
ለነገሩ አንቺም ይሄን ታውቂያለሽ። ዮናስ ራሱ ቤቱ ባዘጋጀው ፓርቲ ላይ እንድትገኚ ባለፈው ጋብዞሽ ነበር። በእርግጥ ግብዣውን አልተቀበልሽም፤ በውስጥሽ ግን ‘ፓርቲው ምን ይመስል ይሆን?’ ብለሽ ማሰብሽ አልቀረም።
ይህን እያውጠነጠንሽ እያለ የመጀመሪያዋ ልጅ:-
“ወይኔ! ጓደኛ ባይኖረኝ ኖሮ ዮናስ አያመልጠኝም ነበር!” አለች።
ከዚያም ግራ በመጋባት ስሜት ታይሽ ጀመር። ምን ልትልሽ እንደሆነ ገብቶሻል።
“ቆይ አንቺ የወንድ ጓደኛ የማትይዥው ለምንድን ነው?”
የፈራሽው ይህ ጥያቄ እንዳይነሳ ነበር! እውነቱን ለመናገር አንቺም የወንድ ጓደኛ ቢኖርሽ ደስ ይልሻል። ይሁንና ለማግባት ዝግጁ ሳይሆኑ የወንድ ጓደኛ መያዝ ተገቢ እንዳልሆነ ተነግሮሻል። ‘የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ መከተል ባይኖርብኝ ኖሮ ግን . . .’ ብለሽ እያሰብሽ እያለ
ሁለተኛዋ ልጅ “በሃይማኖትሽ ምክንያት ነው አይደል?” ብላ ጠየቀችሽ።
‘የማስበውን እንዴት አወቀች?’ ብለሽ በልብሽ አሰብሽ።
ከዚያም የመጀመሪያዋ ልጅ “አንቺ ደግሞ ነጋ ጠባ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትያለሽ። ምናለበት አንዳንዴ እንኳ ዘና ብትዪ?” በማለት አሾፈችብሽ።
አንተስ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ለመከተል ጥረት በማድረግህ ጓደኞችህ አሹፈውብህ ያውቃሉ? ከሆነ የቀረብህ ነገር እንዳለ ይሰማህ ይሆናል። ዲቦራ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ተሰምቷት ነበር። “የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የማያፈናፍኑ እንደሆኑ አስብ ነበር። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ እንደ ልባቸው ስለሚሆኑ በእነሱ እቀና ነበር” ብላለች።
እውነታውን ገምግም
ሞክሮ ማየትን የመሰለ ነገር እንደሌለ ሲገለጽ የምንሰማ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የማያዋጣበት ጊዜ አለ። መዝሙራዊው አሳፍ እንዳደረገው ከሌሎች ስህተት መማር የጥበብ እርምጃ ከመሆኑም ሌላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው አካሄድ ነው። በአንድ ወቅት አሳፍ የአምላክ መመሪያዎች በጣም ጥብቅ እንደሆኑ ተሰምቶት ነበር። ሆኖም የአምላክን ጎዳና የተዉ ሰዎችን ሕይወት መገምገሙ እውነታውን እንዲረዳ አስችሎታል። አሳፍ፣ እነዚህ ሰዎች “በሚያዳልጥ ስፍራ” ላይ ያሉ ያህል መሆኑን ከጊዜ በኋላ ተገንዝቧል።—መዝሙር 73:18
አንተም ከሌሎች ስህተት መማር እንድትችል በአንድ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ችላ ብለው ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ አንዳንድ ወጣቶች የሰጡትን ሐሳብ እስቲ ተመልከት።
● በአስተሳሰባችሁና በድርጊታችሁ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው ምንድን ነው?
ዲቦራ፦ “ትምህርት ቤት ሳለሁ ሁሉም ልጆች የፍቅር ጓደኛ ነበራቸው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ሲታዩ ደስተኛ ይመስሉ ነበር። ከእነሱ ጋር በምሆንበት ጊዜ ሲሳሳሙና ሲተቃቀፉ እመለከት ነበር፤ ይህ ደግሞ የቅናት ስሜት የፈጠረብኝ ከመሆኑም ሌላ ብቻዬን እንደቀረሁ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። ብዙውን ጊዜ ስለወደድኩት ልጅ ቁጭ ብዬ በማሰብ ረጅም ሰዓት አሳልፍ ነበር። ይህ ደግሞ ከእሱ ጋር ለመሆን ያለኝ ፍላጎት እያየለ እንዲሄድ አደረገ።”
ማይክ፦ “የማነባቸው ጽሑፎችና የምከታተላቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የፆታ ስሜትን የሚያነሳሱ ነበሩ። ከጓደኞቼ ጋር ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራቴ ድርጊቱን ለመፈጸም ይበልጥ እንድነሳሳ አደረገኝ። ከአንዲት ልጅ ጋር ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ ‘የፆታ ግንኙነት ባንፈጽምም በመተቃቀፍ ወይም በሌላ መልኩ ፍቅራችንን መግለጽ እንችላለን’ ብዬ አስብ ነበር፤ የፆታ ግንኙነት የምፈጽምበት ደረጃ ላይ ሳልደርስ ማቆም እንደምችል ይሰማኝ ነበር።”
አንድሩ፦ “ኢንተርኔት ላይ የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ነበረኝ። ከዚያም የአልኮል መጠጥ በብዛት መጠጣት ጀመርኩ። እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ደንታ ከሌላቸው ልጆች ጋር ፓርቲዎች ላይ እገኝ ነበር።”
ትሬሲ፦ “ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ስህተት መሆኑን ባውቅም ድርጊቱን አልጠላውም ነበር። ከማግባቴ በፊት የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ሐሳብ አልነበረኝም፤ ይሁንና ስሜቴ አስተሳሰቤን አዛባው። ለተወሰነ ጊዜ ሕሊናዬ ደንዝዞ ስለነበር ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜት አልተሰማኝም።”
● የመረጣችሁት ጎዳና ደስታ አስገኝቶላችኋል?
ዲቦራ፦ “መጀመሪያ ላይ ነፃነት እንዳገኘሁ ስለተሰማኝ ፈነደቅሁ፤ እንደ እኩዮቼ መሆን በመቻሌ ተደስቼ ነበር። ደስታዬ ግን አልዘለቀም። እንደቆሸሽኩ፣ ንጽሕናዬን እንዳጣሁና ባዶ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ርካሽ በሆነ መንገድ ድንግልናዬን በማጣቴ ከፍተኛ የጸጸት ስሜት አደረብኝ።”
አንድሩ፦ “አንዴ ከገባሁበት በኋላ መጥፎ ድርጊቶችን መፈጸም እየቀለለኝ መጣ። በዚያው መጠን ደግሞ በጥፋተኝነት ስሜት እሠቃይ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በራሴ እበሳጭ ነበር።”
ትሬሲ፦ “የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸሜ የወጣትነት ሕይወቴ ተበላሸ። ከወንድ ጓደኛዬ ጋር ዓለማችንን የምንቀጭ መስሎኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንዳሰብኩት አልሆነም። የተረፈን ነገር ቢኖር የስሜት ቁስል እንዲሁም ሐዘንና ሥቃይ ብቻ ነው። ‘ምናለ የይሖዋን ምክር በተከተልኩ ኖሮ’ ብዬ ስለምቆጭ ማታ ማታ ሥራዬ ማልቀስ ሆኖ ነበር።”
ማይክ፦ “ጨርሶ ደስታ ራቀኝ። ያደረግኳቸው ነገሮች በሌሎች ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ ላለማሰብ ብሞክርም አልተሳካልኝም። ራሴን ለማስደሰት ስል ሌሎችን መጉዳቴ ያንገበግበኛል።”
● የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎች የማያፈናፍኑ እንደሆኑ ለሚሰማቸው ወጣቶች ምን ምክር ትሰጣላችሁ?
ትሬሲ፦ “የይሖዋን መመሪያዎች ተከተሉ፤ እንዲሁም እንደዚያ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ተቀራረቡ። ይበልጥ ደስተኛ መሆን የምትችሉት እንዲህ ካደረጋችሁ ነው።”
ዲቦራ፦ “ስለ ራሳችሁና ስለምትፈልጉት ነገር ብቻ አታስቡ። የምታደርጉት ነገር እናንተን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይነካል። የአምላክን መመሪያዎች ችላ የምትሉ ከሆነ ራሳችሁን ትጎዳላችሁ።”
አንድሩ፦ “ተሞክሮ ስለሚጎድላችሁ እኩዮቻችሁ የሚመሩት ሕይወት አስደሳች እንደሆነ ይሰማችኋል። የእኩዮቻችሁ አመለካከት ሊጋባባችሁ ይችላል። በመሆኑም ጓደኞቻችሁን በጥበብ መምረጥ ይኖርባችኋል። በይሖዋ የምትታመኑ ከሆነ ከጸጸት ትድናላችሁ።”
ማይክ፦ “ይሖዋ ከሰጣችሁ በጣም ውድ የሆኑ ስጦታዎች መካከል ክብራችሁና ንጽሕናችሁ ይገኙበታል። ራሳችሁን መግዛት ባለመቻላችሁ እነዚህን ስጦታዎች አሽቀንጥራችሁ ስትጥሉ ራሳችሁን ታዋርዳላችሁ። በመሆኑም ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ወላጆቻችሁንና ሌሎች የጎለመሱ ሰዎችን አማክሯቸው። ስህተት ከሠራችሁ ጉዳዩን በግልጽ ለመናገርና ሁኔታውን ለማስተካከል ዛሬ ነገ አትበሉ። ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ካከናወናችሁ እውነተኛ ሰላም ይኖራችኋል።”
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ እንዴት ታየዋለህ?
ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ስለሆነ አንተም ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ መክብብ 11:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን መመሪያዎች ብትከተል ጥቅሙ ለአንተው ነው። እርግጥ ነው፣ ይህን መመሪያ እንደ ልብህ እንዳትሆን ጠፍሮ እንዳሰረህ ነገር አድርገህ ትመለከተው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያ ከአደጋ እንደሚጠብቅህ የመኪና ቀበቶ ነው።
በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ። በውስጡ የሰፈሩትን መመሪያዎች የምትከተል ከሆነ ይሖዋን የምታስደስት ከመሆኑም በላይ ራስህም ትጠቀማለህ።—ኢሳይያስ 48:17
የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ። እንዴት?
ቁልፍ ጥቅስ
“እኔ ይሖዋ የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . አምላክህ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17 NW
ጠቃሚ ምክር
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል የጥበብ አካሄድ መሆኑን ለታናናሾችህ እንዴት ማስረዳት እንደምትችል አስብ። ስለምታምንባቸው ነገሮች ለሌሎች መናገርህ ለእነዚህ ነገሮች ያለህ አቋም ጥብቅ እንዲሆን ለማድረግ የሚረዳ ግሩም መንገድ ነው።
ይህን ታውቅ ነበር?
ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት በአንድ ጀንበር ልታበላሸው ትችላለህ፤ ወዳጅነትህን ለማደስ ግን ዓመታት ሊፈጅብህ ይችላል።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል የጥበብ አካሄድ መሆኑን መገንዘብ እንድችል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች የማይመሩ ሰዎች ሕይወት ካስቀናኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● የአምላክን ሕግጋት መጣስ ምን መዘዝ እንደሚያስከትል በራስ ሕይወት ሞክሮ ማየት የማያዋጣው ለምንድን ነው?
● ዲቦራ፣ ማይክ፣ አንድሩና ትሬሲ ከሰጧቸው ሐሳቦች ምን ትምህርት አግኝተሃል?
● አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ጠፍሮ እንደሚያስር ነገር አድርገው የሚመለከቷቸው ለምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ ያለው አመለካከት አርቆ ማስተዋል የጎደለው ነው የምንለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 285 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለፈጸምከው መጥፎ ድርጊት ከምትቀበለው ተግሣጽ ይልቅ ድርጊቱን ለመደበቅ መሞከር የሚያስከትልብህ ሥቃይ ይብሳል።”—ዶና
[በገጽ 288 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች መፈናፈኛ የሚያሳጡህ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ጥበቃ ያደርጉልሃል