አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች—ሱላማጢሷ ወጣት
ሱላማጢሷ ወጣት ከፍቅር ጋር በተያያዘ ስሜቷ እንዳያሸንፋት መጠንቀቅ እንዳለባት ታውቅ ነበር። ጓደኞቿን “ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት አማጥናችኋለሁ” ብላቸዋለች። ሱላማጢሷ ወጣት ስሜቷ የማመዛዘን ችሎታዋን በቀላሉ ሊያዛባው እንደሚችል አስተውላ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ለእሷ የማይሆናት ሰው የሚያቀርብላትን የፍቅር ጥያቄ እንድትቀበል ሌሎች ሊገፋፏት እንደሚችሉ ተገንዝባ ነበር። የራሷ ስሜትም እንኳ የማስተዋል ችሎታዋን ሊያዛባው ይችላል። በመሆኑም ሱላማጢሷ ወጣት እንደ “ቅጥር” ወይም ግንብ ለመሆን ቆርጣ ነበር።—ማሕልየ መሓልይ 8:4, 10
አንቺስ የፍቅር ግንኙነትን በተመለከተ እንደ ሱላማጢሷ በሳል የሆነ አስተሳሰብ አለሽ? በስሜትሽ ብቻ ከመመራት ይልቅ በማሰብ ችሎታሽ መጠቀም ትችያለሽ? (ምሳሌ 2:10, 11) አንቺ የፍቅር ጓደኝነት ለመጀመር ዝግጁ እንደሆንሽ ባይሰማሽም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እንዲህ እንድታደርጊ ይገፋፉሽ ይሆናል። በውስጥሽ የምታብሰለስይው ነገርም እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርብሽ ሊያደርግሽ ይችላል። ለምሳሌ፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ስትመለከቺ አንቺም የፍቅር ጓደኛ እንዲኖርሽ በጣም ትጓጊያለሽ? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነትሽን ከማይጋራ ሰው ጋር እንኳ የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ትሆኛለሽ? ሱላማጢሷ ወጣት ከፍቅር ግንኙነት ጋር በተያያዘ ብስለት እንዳላት አሳይታለች። አንቺም እንደ እሷ መሆን ትችያለሽ!