የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lf ጥያቄ 4 ገጽ 22-29
  • ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከአንድ አካል እየተሻሻለ የመጣ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከአንድ አካል እየተሻሻለ የመጣ ነው?
  • የሕይወት አመጣጥ​—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የዳርዊን ዛፍ ተገነደሰ
  • የቅሪተ አካላት ማስረጃዎችስ?
  • “ማስረጃው” ያሉበት ችግሮች
  • “ፊልሙ” ምን ያሳያል?
  • ዝግመተ ለውጥ
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?
    ንቁ!—2006
  • ዝግመተ ለውጥ በችሎት ፊት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑን አረጋግጧልን?
    መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
ለተጨማሪ መረጃ
የሕይወት አመጣጥ​—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
lf ጥያቄ 4 ገጽ 22-29

ጥያቄ 4

ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከአንድ አካል እየተሻሻለ የመጣ ነው?

ተመሳሳይ ቅደም አያቶች ያሏቸውን ዝርያዎች የሚያሳይ ቻርልስ ዳርዊን ያዘጋጀው የሕይወት ዛፍ

ዳርዊን ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከአንድ አካል እየተሻሻለ የመጣ ነው የሚል አመለካከት ነበረው። በምድር ላይ የሚገኙ ሕይወት ያላቸው ነገሮች አመጣጥ ከአንድ ትልቅ ዛፍ ጋር እንደሚመሳሰል አድርጎ ያስብ ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ ሌሎች ሰዎች፣ ይህ “የሕይወት ዛፍ” መጀመሪያ ላይ አንድ ነጠላ ግንድ እንደነበረና ይህ ግንድ የመጀመሪያዎቹን ውስብስብ ያልሆኑ ሴሎች እንደሚያመለክት አድርገው ማመን ጀመሩ። ከዚህ ግንድ አዳዲስ ዝርያዎች የበቀሉ ሲሆን ቅርንጫፍ ወይም የዕፅዋትና የእንስሳት ቤተሰቦች ሆኑ፤ ከዚያም በአሁኑ ጊዜ ያሉት በዕፅዋትና በእንስሳት ቤተሰቦች ውስጥ የሚመደቡት የተለያዩ ዝርያዎች በሙሉ እንደ ቀንበጥ በቀሉ። በእርግጥ የተፈጸመው እንዲህ ያለ ነገር ነው?

ብዙ ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ? ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ከአንድ አካል ተሻሽለው የመጡ ናቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከቅሪተ አካላት በተገኙ ማስረጃዎች የተደገፈ እንደሆነ ብዙዎቹ ይናገራሉ። በተጨማሪም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ተመሳሳይ “የኮምፒውተር ቋንቋ” ወይም ዲ ኤን ኤ ስለሚጠቀሙ ሕይወት ሁሉ ከአንድ አካል ተሻሽሎ የመጣ መሆን አለበት ይላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የዘፍጥረት ታሪክ ዕፅዋት፣ የባሕር ፍጥረታት፣ የየብስ እንስሳትና አእዋፍ “እንደየወገናቸው” እንደተፈጠሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:12, 20-25) ይህ አገላለጽ በእያንዳንዱ ‘ወገን’ ውስጥ ልዩነት ሊኖር እንደሚችል የሚያሳይ ቢሆንም እያንዳንዱን ወገን ከሌላው የሚለይ ሊጣስ የማይችል ድንበር እንዳለ ያመለክታል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ዘገባ፣ ሙሉ አካል ያላቸው አዲስ ዓይነት ፍጥረታት በቅሪተ አካላት ስብስብ ውስጥ በድንገት ሊገኙ እንደሚችሉ ይጠቁማል።

ማስረጃው ምን ያመለክታል? ማስረጃው መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠውን መግለጫ ይደግፋል? ወይስ ዳርዊን ትክክል ነበር? ባለፉት 150 ዓመታት የተገኙት ማስረጃዎች ምን ያረጋግጣሉ?

የዳርዊን ዛፍ ተገነደሰ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሳይንቲስቶች የበርካታ ባለ አንድ ሴል ነፍሳትን እንዲሁም የዕፅዋትንና የእንስሳትን ጄኔቲክ ኮዶች ማነጻጸር ችለዋል። እንዲህ ያለውን ንጽጽር ማድረጋቸው ዳርዊን ስለ “ሕይወት ዛፍ” የተናገረውን መላምት ያረጋግጣል ብለው አስበው ነበር። ይሁን እንጂ እንዳሰቡት አልሆነም።

ምርምሩ ያስገኘው ውጤት ምንድን ነው? የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ማልኮም ጎርደን በ1999 እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ ይመስላል። ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የሚወክለው ዛፍ ከአንድ ነጠላ ሥር የተገኘ አይመስልም።” ዋነኞቹ የሕይወት ቅርንጫፎች በሙሉ ዳርዊን ያምን እንደነበረው ከአንድ ነጠላ ግንድ የበቀሉ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ? ጎርደን በማከል እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከአንድ አካል ተሻሽለው የመጡ ናቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ዛሬ ከተገኙት ማስረጃዎች አንጻር ሲታይ በኪንግደም ላይ የሚሠራ አይመስልም። ምናልባትም በሁሉም ሊባል ባይችል እንኳ በብዙዎቹ ፋይለሞች እንዲሁም በአንድ ፋይለም ውስጥ በሚገኙ በርካታ መደቦች (classes) ውስጥ ላይሠራ ይችላል።”29a

በቅርቡ የተደረጉ ምርምሮችም ከዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ጋር ይቃረናሉ። ለምሳሌ በኒው ሳይንቲስት መጽሔት ላይ በ2009 የወጣ አንድ ጽሑፍ፣ የዝግመተ ለውጥ ሳይንቲስት የሆኑት ኤሪክ ባቴስት “የሕይወት ዛፍ [ጽንሰ ሐሳብ] እውነትነት እንዳለው የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለንም” እንዳሉ ጠቅሷል።30 ይኸው ጽሑፍ የዝግመተ ለውጥ ባዮሎጂስት የሆኑት ማይክል ሮዝ እንዲህ በማለት እንደተናገሩ ገልጿል፦ “የሕይወት ዛፍ ብዙ ድምፅ ሳያሰማ ወደ መቃብር በመውረድ ላይ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ከባዮሎጂ ጋር በተያያዘ ያለንን መሠረታዊ አመለካከት መለወጥ እንዳለብን ለመቀበል ግን ተቸግረናል።”31b

የቅሪተ አካላት ማስረጃዎችስ?

በርካታ ሳይንቲስቶች ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከአንድ አካል ተሻሽለው የመጡ ናቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በቅሪተ አካላት ማስረጃዎች የተደገፈ እንደሆነ ይናገራሉ። ለምሳሌ፣ የቅሪተ አካላት ማስረጃዎች ዓሦች ተለውጠው አምፊቢያን፣ በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት ደግሞ አጥቢ እንስሳት ሆነዋል የሚለውን ሐሳብ እንደሚደግፉ በመግለጽ ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ከቅሪተ አካላት የተገኘው ማስረጃ ምን ያሳያል?

በቅሪተ አካል ጥናት ላይ የተሠማሩት ዴቪድ ራውፕ የተባሉ የዝግመተ ለውጥ ምሑር እንዲህ ብለዋል፦ “በዳርዊን ዘመን የነበሩ ጂኦሎጂስቶችም ሆኑ የዘመናችን ጂኦሎጂስቶች ያገኙት ነገር ሕይወት ያላቸው ነገሮች ቀስ በቀስ እየተለወጡ እንደመጡ የሚያሳይ ማስረጃ ሳይሆን የተዘበራረቀና ወጥነት የሌለው ነው፤ አንዳንድ ዝርያዎች በቅሪተ አካላት ስብስብ ቅደም ተከተል ውስጥ ድንገት ብቅ ይሉና በኖሩባቸው ዘመናት በሙሉ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳያሳዩ ወይም ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይከሰትባቸው ድንገት ይጠፋሉ።”32

እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኞቹ ቅሪተ አካላት የሚያረጋግጡት፣ የተለያዩ ፍጥረታት ለረጅም ዘመን ምንም ለውጥ ሳይታይባቸው እንደኖሩ ነው። የተገኘው ማስረጃ፣ አንድ ዓይነት ፍጥረት ተሻሽሎ ወደ ሌላ ዓይነት ፍጥረት እንደተለወጠ አያሳይም። ከዚህ ይልቅ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ አካላዊ ንድፎች በድንገት ብቅ ይላሉ። ከዚህም በላይ አዳዲስ ገጽታዎች በድንገት ይከሰታሉ። ለምሳሌ በድምፅ ሞገዶች በመጠቀም የአንድን ነገር አቅጣጫና ርቀት የመለየት ችሎታ ያላቸው የሌሊት ወፎች ቅሪተ አካላት፣ ቀደም ባሉት ዘመናት ከነበሩት እንስሳት ጋር ዝምድና እንዳላቸው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ የለም።

እንዲያውም የእንስሳት ሕይወት ከተከፋፈለባቸው ዋና ዋና ምድቦች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ብቅ ያሉት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመስላል። በዓይነታቸው ለየት ያሉና አዳዲስ የሆኑ በርካታ ሕያዋን ነገሮች በቅሪተ አካላት ስብስብ ውስጥ ብቅ ያሉት በድንገት በመሆኑ የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪዎች ይህ የሆነበትን ዘመን “የካምብሪያን ፍንዳታ” ብለውታል። የካምብሪያን ዘመን የተባለው የትኛው ዘመን ነው?

የተመራማሪዎቹ ግምት ትክክል ነው እንበል። እነሱ እንደሚሉት ቢሆን ምድር የኖረችበት ዘመን የእግር ኳስ ሜዳ ከሚያክል የጊዜ ርዝመት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን (1)። በዚህ መሥፈርት መሠረት የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪዎች የካምብሪያን ዘመን በሚሉት ዘመን ላይ ለመድረስ የሜዳውን ሰባት ስምንተኛ የሚያህል ርቀት መጓዝ ይኖርብሃል (2)። የእንስሳት ሕይወት የተከፋፈለባቸው ዋና ዋና ምድቦች በቅሪተ አካላት ስብስብ ውስጥ ብቅ ማለት የሚጀምሩት በካምብሪያን ዘመን ውስጥ በሚገኝ አጭር ጊዜ ውስጥ ነው። ቅሪተ አካላቱ መታየት የሚጀምሩበት ጊዜ ምን ያህል አጭር ነው? በኳስ ሜዳው ላይ መሄድህን ስትቀጥል እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ፍጥረታት ብቅ የሚሉት ከአንድ እርምጃ በሚያንስ ርቀት ውስጥ ነው!

የእግር ኳስ ሜዳ የሚያህል ስፋት ያለው የጊዜ ሰንጠረዥ፤ ሰንጠረዡ ከምድር ታሪክ መጀመሪያ እስከ ካምብሪያን ፍንዳታ ያለውን ጊዜ ያሳያል

እነዚህ የተለያዩ ሕያዋን ነገሮች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በድንገት ብቅ ማለታቸው አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎች መደበኛውን የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል። ለምሳሌ የዝግመተ ለውጥ ባዮሎጂስት የሆኑት ስቱዋርት ኒውማን በ2008 በተደረገላቸው ቃለ ምልልስ ላይ፣ አዳዲስ ሕያዋን ነገሮች በድንገት የተገኙበትን ምክንያት የሚያስረዳ አዲስ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። “ቀስ በቀስ የተከናወኑትን ለውጦች በሙሉ ለማስረዳት ሲያገለግል የኖረው የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ወደ ጎን ገሸሽ እንደሚደረግ ይሰማኛል፤ ማክሮኢቮሉሽንን ይኸውም በአካል ክፍሎች ላይ የሚከሰቱትን ትልልቅ ለውጦች ከምናስረዳባቸው በርካታ መንገዶች አንዱ ብቻ እንደሚሆን ምናልባትም ትልቅ ቦታ እንደማይሰጠው አምናለሁ” ብለዋል።33

“ማስረጃው” ያሉበት ችግሮች

በአንዳንድ የመማሪያ መጻሕፍት ላይ የተሳሉ ቅሪተ አካላትና ትክክለኛ መጠናቸው

አንዳንድ የመማሪያ መጻሕፍት በቅደም ተከተል የሚያስቀምጧቸውን ቅሪተ አካላት መጠን የሚለውጡት ለምንድን ነው?

ከላይ በስተ ግራ፦ በአንዳንድ የመማሪያ መጻሕፍት ላይ የቀረበበት መንገድ

ከላይ በስተ ቀኝ፦ ትክክለኛው አንጻራዊ መጠን

ዓሦች ወደ አምፊቢያን፣ በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት ደግሞ ወደ አጥቢ እንስሳት እንደተለወጡ ለማሳየት እንደ ማስረጃ የሚቀርቡት ቅሪተ አካላትስ? ለዝግመተ ለውጥ ሂደት አሳማኝ ማስረጃ ይሆናሉ? ጠለቅ ብለን ስንመረምራቸው በርካታ ችግሮች ገሃድ ይወጣሉ።

አንደኛ፣ በደረታቸው ከሚሳቡ እንስሳት አንስቶ እስከ አጥቢ እንስሳት ድረስ ያለውን ቅደም ተከተል ለማሳየት ሲባል በመማሪያ መጻሕፍት ላይ የሚቀርበው የእነዚህ እንስሳት የመጠን ልዩነት አንዳንድ ጊዜ ትክክል አይደለም። በዚህ ቅደም ተከተል ውስጥ ያሉት እንስሳት መጠናቸው ተመሳሳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳንዶቹ እጅግ ትላልቅ ሌሎቹ ደግሞ ትናንሽ ናቸው።

ሁለተኛውና ይበልጥ ተፈታታኝ የሆነው ጉዳይ እነዚህ ፍጥረታት እርስ በርሳቸው እንደሚዛመዱ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የሌለ መሆኑ ነው። በቅሪተ አካል ስብስብ ውስጥ የተካተቱት እነዚህ ናሙናዎች በተመራማሪዎች ግምት መሠረት በሚሊዮን ዓመታት የሚቆጠር የጊዜ ልዩነት አላቸው። ሄንሪ ጂ የተባሉ የሥነ እንስሳት ተመራማሪ፣ በአብዛኞቹ ቅሪተ አካላት መካከል ስላለው የጊዜ ልዩነት ሲናገሩ “በቅሪተ አካላቱ መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት በጣም ብዙ በመሆኑ ምንም ዓይነት የትውልድም ሆነ የዘር ሐረግ ዝምድና እንዳላቸው በእርግጠኝነት መናገር አንችልም” ብለዋል።34c

የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ማልኮም ጎርደን የዓሦችንና የአምፊቢያኖችን ቅሪተ አካላት አስመልክተው አስተያየት ሲሰጡ፣ የተገኙት ቅሪተ አካላት “በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የተካተተውን በዚያ ዘመን የኖረውን ብዝሐ ሕይወት ናሙና የሚወክሉት [በጥቂቱ ብቻ] ነው፤ ምናልባትም ጨርሶ ላይወክሉ ይችላሉ” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “እነዚህ ሕያዋን ነገሮች ከእነሱ በኋላ ለተገኘው እድገት ያበረከቱት ድርሻ ይኖር እንደሆነ አሊያም እርስ በርሳቸው ምን ዝምድና ሊኖራቸው እንደሚችል ማወቅ የሚቻልበት ምንም መንገድ የለም” ብለዋል።35d

የተለያዩ የእንስሳ ዓይነቶችንና በመካከላቸው አለ ተብሎ የሚታሰበውን ዝምድና የሚያሳይ ሰንጠረዥ

“ፊልሙ” ምን ያሳያል?

በ2004 በናሽናል ጂኦግራፊክ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ፣ የቅሪተ አካላትን ስብስብ ፊልም በሚቀናበርበት ክፍል ውስጥ እየተዘጋጀ ካለ የዝግመተ ለውጥ ፊልም ጋር ያመሳሰለው ሲሆን ይህን ፊልም ለማዘጋጀት ከሚያስፈልገው “ከእያንዳንዱ 1,000 ተከታታይ ምስል ውስጥ 999 ያህሉ ጠፍቷል።”36 ይህ ምሳሌ ምን አንድምታ እንደሚኖረው ተመልከት።

የፊልም ክር እና ከፊልሙ የተወሰዱ ጥቂት ምስሎች

በቅሪተ አካላት ስብስብ ውስጥ ያሉት “95ቱ ምስሎች” እንስሳት ቀስ በቀስ ከአንዱ ዓይነት ወደ ሌላው እንደማይለወጡ የሚያሳዩ ከሆነ የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪዎች የተቀሩትን “5 ምስሎች” አዝጋሚ ለውጥን እንደሚያሳዩ አድርገው የሚያቀናብሯቸው ለምንድን ነው?

መጀመሪያ ላይ 100,000 ተከታታይ ምስሎች ከነበሩት አንድ ፊልም ውስጥ 100 የሚሆኑትን ምስሎች አገኘህ እንበል። በእነዚህ ምስሎች ተመሥርተህ የፊልሙን ታሪክ ማወቅ ትችላለህ? ታሪኩ እንዲህ መሆን አለበት ብለህ አስቀድመህ ገምተሃል እንበል፤ ሆኖም ካገኘሃቸው 100 ምስሎች መካከል የአንተን ግምት እንዲደግፉ ተደርገው ሊቀናበሩ የሚችሉት 5ቱ ብቻ ቢሆኑና የቀሩት 95ቱ ምስሎች አንተ ከገመትከው የተለየ ታሪክ የሚናገሩ ቢሆንስ? አምስቱ ምስሎች መጀመሪያ ላይ ስለ ታሪኩ የነበረህን ግምት እንደሚያረጋግጡ በመግለጽ ብትከራከር ምክንያታዊ ይሆናል? አምስቱን ምስሎች በዚህ ቅደም ተከተል ያስቀመጥከው የአንተን ሐሳብ ስለሚደግፍልህ ብቻ ሊሆን አይችልም? አመለካከትህ በተቀሩት 95 ምስሎች ላይ የተመሠረተ ቢሆን ይበልጥ ምክንያታዊ አይሆንም?

ይህ ምሳሌ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች ስለ ቅሪተ አካላት ማስረጃዎች ካላቸው አመለካከት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? አብዛኞቹ ቅሪተ አካላት ማለትም 95ቱ የፊልሙ ምስሎች፣ ዝርያዎቹ በዘመናት ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይታይባቸው የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተመራማሪዎች ለበርካታ ዓመታት ሳይቀበሉ ቆይተዋል። እንዲህ ያለ አሳማኝ ማስረጃ እያለ ዝምታን የመረጡት ለምንድን ነው? ሪቻርድ ሞሪስ የተባሉት ደራሲ እንዲህ ብለዋል፦ “የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪዎች ሥር የሰደደውን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የተቀበሉ ሲሆን ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ የሚጠቁም ማስረጃ ባገኙበት ጊዜም እንኳ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ሙጭጭ አድርገው የያዙ ይመስላል። የቅሪተ አካላት ማስረጃዎችን ተቀባይነት ካገኘው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አንጻር ለመተርጎም ሲሞክሩ ቆይተዋል።”37

“በቅደም ተከተል የተቀመጡ ቅሪተ አካላትን ወስዶ የዘር ሐረግን ያመለክታሉ ማለት በሙከራ ሊረጋገጥ የሚችል ሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሕፃናትን ለማስተኛት ከሚነበብ ተረት ተለይቶ አይታይም፤ አዝናኝ ምናልባትም ትምህርት ሰጪ ሊሆን ቢችልም ሳይንሳዊ አይደለም።”—ኢን ሰርች ኦቭ ዲፕ ታይም—ቢዮንድ ዘ ፎሲል ሪከርድ ቱ ኤ ኒው ሂስትሪ ኦቭ ላይፍ፣ በሄንሪ ጂ የተዘጋጀ ከገጽ 116-117

በአሁኑ ጊዜ ስላሉት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆችስ ምን ማለት ይቻላል? ዛሬም ቅሪተ አካላትን በተወሰነ ቅደም ተከተል ማስቀመጣቸውን የቀጠሉት፣ እንዲህ ያለው ቅደም ተከተል በቅሪተ አካላትና በጄኔቲክ ማስረጃዎች የተደገፈ ስለሆነ ሳይሆን እንዲህ ማድረጋቸው በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ካገኘው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ስለሆነ ብቻ ይሆን?e

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከማስረጃው ጋር ይበልጥ የሚስማማው የትኛው መደምደሚያ ነው? እስካሁን የተመለከትናቸውን እውነታዎች ልብ በል።

  • በመጀመሪያ በምድር ላይ የነበረው ሕይወት ያለው ነገር “ያልተወሳሰበ” አልነበረም።

  • የአንድ ሴል የተለያዩ ክፍሎች እንኳ በአጋጣሚ ሊገኙ የሚችሉበት ዕድል እጅግ የመነመነ ነው።

  • ሴሎች ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያደርግ “የኮምፒውተር ፕሮግራም” ወይም ኮድ የሆነው ዲ ኤን ኤ እጅግ በጣም ውስብስብ በመሆኑ የትኛውም ዓይነት ሰው ሠራሽ የኮምፒውተር ፕሮግራም ወይም መረጃ የሚይዝ መሣሪያ ሊወዳደረው የማይችል ከፍተኛ ጥበብ የታየበት ነው።

  • የጄኔቲክ ምርምር ሕይወት ያለው ነገር ከአንድ አካል ተሻሽሎ የመጣ አለመሆኑን አረጋግጧል። በተጨማሪም የእንስሳት ሕይወት የተከፋፈለባቸው ዋና ዋና ምድቦች በቅሪተ አካል ስብስብ ውስጥ ብቅ ያሉት በድንገት ነው።

ከእነዚህ እውነታዎች አንጻር ሲታይ ማስረጃዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ ከሚሰጠው ማብራሪያ ጋር ይስማማሉ ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይመስልህም? ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው አብዛኛው የፍጥረት ዘገባ ከሳይንስ ጋር እንደሚጋጭ ይናገራሉ። ይህ እውነት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ምን ይላል?

a ፋይለም የሚለው የባዮሎጂ ቃል አንድ ዓይነት አካላዊ ንድፍ ያላቸውን በርካታ እንስሳት ያቀፈ ቡድን ያመለክታል። ሳይንቲስቶች ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ከሚከፋፍሉባቸው ዘዴዎች አንዱ ሰባት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ደረጃዎቹ ከላይ ወደታች እየጠበቡ ይሄዳሉ። የመጀመሪያው ደረጃ በስፋቱ ከሁሉ የሚበልጠው ኪንግደም የተባለው ክፍል ነው። ከዚያም ፋይለም፣ ክላስ፣ ኦርደር፣ ፋሚሊ፣ ጂነስ እና ስፒሽስ የተባሉት ክፍሎች ይከተላሉ። ለምሳሌ ፈረስ በሚከተለው መንገድ ይመደባል፦ ኪንግደም፣ አኒማልያ፤ ፋይለም፣ ኮርዳታ፤ ክላስ፣ ማማልያ፤ ኦርደር፣ ፐሪሶዳክቲላ፤ ፋሚሊ፣ ኤክዊዴ፤ ጂነስ፣ ኤክዉስ፤ ስፒሽስ፣ ካባለስ።

b ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔትም ሆነ ባቴስትና ሮዝ ይህን የገለጹት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ስህተት ነው ለማለት ፈልገው እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ሊያስገነዝቡ የፈለጉት የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ዋነኛ ክፍል የሆነው የሕይወት ዛፍ በማስረጃ የተደገፈ አለመሆኑን ነው። እንደነዚህ ያሉ ሳይንቲስቶች ስለ ዝግመተ ለውጥ ሌላ ማብራሪያ ለማግኘት አሁንም ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

c ሄንሪ ጂ ይህን የተናገሩት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ስህተት እንደሆነ ለማመልከት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን አስተያየት የሰጡት ከቅሪተ አካላት ስብስብ የሚገኘው ግንዛቤ ውስን እንደሆነ ለመግለጽ ነው።

d ማልኮም ጎርደን የዝግመተ ለውጥን ትምህርት የሚደግፉ ሰው ናቸው።

e ለዚህ ምሳሌ እንዲሆንህ “ስለ ሰው ዝግመተ ለውጥ ምን ማለት ይቻላል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ጥያቄ የሚያስነሱ አንዳንድ እውነታዎች

  • እውነታው፦ መሠረታዊ የሆኑት ሁለት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳቦች ይኸውም ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከአንድ አካል እየተሻሻለ የመጣ ነው የሚለውና ትልልቅ አካላዊ ለውጦች የተከሰቱት ቀስ በቀስ የተከናወኑ ትንንሽ ለውጦች አንድ ላይ ተዳምረው ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የመጽሐፍ ቅዱስን የፍጥረት ዘገባ በማይደግፉ ተመራማሪዎች ዘንድ ተቃውሞ እየገጠማቸው ነው።

    ጥያቄ፦ ለዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ዋና መሠረት በሆኑት በእነዚህ እሳቤዎች ላይ ተቃውሞ ከተነሳ እሱ ያስተማረው የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ሳይንሳዊ ሐቅ ነው ሊባል ይችላል?

  • እውነታው፦ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ተመሳሳይ ንድፍ ያለው ዲ ኤን ኤ ይኸውም የሴላቸውን ወይም የሴሎቻቸውን ቅርጽና ተግባር የሚቆጣጠር ኮድ አሊያም “የኮምፒውተር ቋንቋ” አላቸው።

    ጥያቄ፦ እንዲህ ያለው ተመሳሳይነት ሊኖር የቻለው ከአንድ አካል ተሻሽለው ስለመጡ ሳይሆን የሁሉንም ንድፍ ያወጣ አንድ አካል ስላለ ሊሆን አይችልም?

ስለ ሰው ዝግመተ ለውጥ ምን ማለት ይቻላል?

የራስ ቅል

በብዙ የመማሪያ መጻሕፍትና በኢንሳይክሎፒዲያዎች ላይ ስለ ሰው ዝግመተ ለውጥ የሚገልጽ ርዕስ አውጥተህ ብትመለከት ጎበጥ ካለ ዝንጀሮ የሚመስል ፍጡር አንስቶ ቀና እያሉና ጭንቅላታቸው ተለቅ እያለ የመጡ ፍጥረታት የሚታዩበት ሥዕል ትመለከታለህ። መጨረሻ ላይ በዚህ ዘመን ያለ ሰው ሥዕል ታያለህ። እንደነዚህ ያሉት ሥዕላዊ መግለጫዎችና በቅሪተ አካላቱ ስብስብ መሃል አለ የሚባለውን ክፍተት የሚሞላ አዲስ ግኝት ተገኘ የሚሉ የሰዎችን ቀልብ የሚስቡ የመገናኛ ብዙኃን ሪፖርቶች ሰው ዝንጀሮ ከሚመስሉ ፍጥረታት ተሻሽሎ የመጣ ስለመሆኑ በቂ መረጃ የተገኘ ያስመስላሉ። እንዲህ ያሉት መግለጫዎች በጠንካራ ማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ናቸው? የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎች በሚከተሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምን እንዳሉ ተመልከት።f

የቅሪተ አካላት ማስረጃ የሚያሳየው ምንድን ነው?

እውነታው፦ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሰዎችና ዝንጀሮዎች ከአንድ አካል ተሻሽለው የመጡ ናቸው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ይደግፋሉ የሚባሉ ቅሪተ አካላት አንድ ላይ ቢሰበሰቡ በአንድ የከረንቡላ መጫወቻ ጠረጴዛ ላይ ሊደረደሩ የሚችሉ ነበሩ። ከዚያ ወዲህ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ይደግፋሉ የሚባሉ ቅሪተ አካላት ብዛት ጨምሯል። በአሁኑ ጊዜ አንድ የባቡር ፉርጎ ሊሞሉ እንደሚችሉ ይነገርላቸዋል።38 ይሁን እንጂ ከእነዚህ ቅሪተ አካላት አብዛኞቹ ከሌሎቹ የአካል ክፍሎች ተነጥለው የተገኙ አጥንቶችና ጥርሶች ብቻ ናቸው። ሙሉ አፅም ይቅርና ሙሉ የራስ ቅል እንኳ ማግኘት በጣም ብርቅ ነው።39

ጥያቄ፦ የሰው “የዘር ግንድ” ክፍል ናቸው የሚባሉ ቅሪተ አካላት በብዛት መገኘታቸው የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎች፣ ሰዎች ዝንጀሮ መሰል ከሆኑ ፍጥረታት ተሻሽለው የተገኙት መቼና እንዴት እንደሆነ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ አስገኝቷል?

መልስ፦ ፈጽሞ አላስገኘም። እንዲያውም እውነታው ከዚህ ተቃራኒ ነው። በአውስትራሊያ የኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሮቢን ዴሪኮርት በ2009 ስለ እነዚህ ቅሪተ አካላት አመዳደብ ሲጽፉ “በአሁኑ ጊዜ የተደረሰበት የጋራ መግባባት ቢኖር ምንም ዓይነት የጋራ መግባባት አለመኖሩ ነው” ብለዋል።40 በ2007 ኔቸር የተባለው ሳይንሳዊ መጽሔት፣ በዝግመተ ለውጥ ሂደት መካከል አለ የሚባለውን ክፍተት የሚሞላ አዲስ ግኝት አግኝተዋል የተባሉ ተመራማሪዎች የሰው ዝርያ ከዝንጀሮ የተገኘው መቼና እንዴት እንደሆነ ጨርሶ እንደማይታወቅ በመግለጽ የሰጡትን አስተያየት ይዞ ወጥቶ ነበር።41 በሃንጋሪ በኦየትቮየሽ ሎራንት ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂካል አንትሮፖሎጂ ክፍል ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ድዩላ ድየኒሽ በ2002 እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የሆሚኒድ ቅሪተ አካላት አመዳደብና በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ የሚገኙበት ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል።”g በተጨማሪም እኚሁ ጸሐፊ፣ እስካሁን የተሰባሰቡት የቅሪተ አካላት ማስረጃዎች የሰው ልጆች ዝንጀሮ መሰል ከሆኑ ፍጥረታት መቼ፣ የትና እንዴት እየተሻሻሉ እንደመጡ እንድናውቅ አላስቻሉንም ብለዋል።42

“ክፍተቱን የሚሞላ” ግኝት መገኘቱን የሚገልጹ ዘገባዎች

እውነታው፦ ብዙውን ጊዜ መገናኛ ብዙኃን “ክፍተቱን የሚሞላ” አዲስ ግኝት መገኘቱን የሚገልጽ ዜና በሠፊው ሲያሰራጩ ይስተዋላል። ለምሳሌ በ2009 አይዳ የሚል ስያሜ የተሰጣት ቅሪተ አካል አንድ የዜና መጽሔት “ለእውቅ ዘፋኝ እንደሚደረገው ዓይነት ያለ የተጋጋለ ዘገባ” ሲል በገለጸው መንገድ ይፋ ሆናለች።43 እንዲህ ያለ ዘገባ ካሰራጩት መገናኛ ብዙኃን መካከል “ቅሪተ አካል አይዳ፦ በሰው ዝግመተ ለውጥ ሰንሰለት ውስጥ የነበረውን ‘ክፍተት የምትሞላ’ ልዩ ግኝት” የሚል ርዕሰ ዜና ይዞ የወጣው ዘ ጋርዲያን የተባለ በእንግሊዝ የሚታተም ጋዜጣ ይገኝበታል።44 ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኒው ሳይንቲስት የተባለው በእንግሊዝ የሚታተም ሳይንሳዊ መጽሔት “አይዳ በሰው ዝግመተ ለውጥ ሰንሰለት ውስጥ ያለውን ‘ክፍተት አትሞላም’” ብሏል።45

ጥያቄ፦ “ክፍተቱን የሚሞላ” አዲስ ግኝት በተገኘ ቁጥር በመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን እየተሰጠው ይኸው ቅሪተ አካል ከሰው “የዘር ሐረግ” እንዲወገድ ሲደረግ ግን ዝም የሚባለው ለምንድን ነው?

ቅሪተ አካል

መልስ፦ ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሮቢን ዴሪኮርት እንደነዚህ ያሉ ግኝቶችን ስለሚያገኙ ሰዎች ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የአንድ ምርምር ቡድን መሪ፣ ከታወቁት የትምህርት ተቋማት ውጭ ለምርምር የሚውል ገንዘብ ለማግኘት ሲል ‘ግኝቱ’ በዓይነቱ ልዩ እንደሆነ አድርጎ መናገርና ከግኝቱ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን አጋንኖ መግለጽ ሊያስፈልገው ይችላል። ምንጊዜም ትኩረት የሚስብ ዜና ለማግኘት የሚያነፈንፉት የኅትመትና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች ደግሞ እንዲህ እንዲያደርጉ ያበረታቷቸዋል።”46

በመማሪያ መጻሕፍት ላይ የሚወጡ የዝንጀሮ መሰል ሰዎች ሥዕሎችና ናሙናዎች

እውነታው፦ በመማሪያ መጻሕፍት ላይና በሙዚየሞች ውስጥ የሚገኙ የሰዎችን ቅድመ አያቶች ያሳያሉ የሚባሉ ሥዕሎችና ምስሎች ብዙውን ጊዜ የራሳቸው የሆነ የተለየ መልክ፣ የቆዳ ቀለምና የፀጉር ብዛት አላቸው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ሥዕሎችና ምስሎች የጥንቶቹን የሰው “ቅድመ አያቶች” ጦጣ አስመስለው፣ ወደ ሰው የቀረቡ ናቸው የሚባሉትን ደግሞ ይበልጥ የሰው ዓይነት የፊት ገጽታ፣ የቆዳ ቀለምና ፀጉር እንዳላቸው አድርገው ያቀርቧቸዋል።

ጥያቄ፦ ሳይንቲስቶች ያገኟቸውን ቅሪተ አካላት መሠረት በማድረግ እንደነዚህ ያሉትን አካላዊ ገጽታዎች በትክክል መሥራት ይችላሉ?

መልስ፦ አይችሉም። በአውስትራሊያ በአድሌድ ዩኒቨርሲቲ የአናቶሚካል ሳይንስ የትምህርት ክፍል የፎሬንሲክ ኤክስፐርት የሆኑት ካርል ስቲቨን በ2003 “የጥንቶቹን የሰው ቅድመ አያቶች የፊት ገጽታ በትክክል መሥራትም ሆነ ምን እንደሚመስል ማረጋገጥ አይቻልም” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም በዘመናችን ያሉትን ዝንጀሮዎች መሠረት አድርጎ የሰዎችን ቅድመ አያቶች ምስል ለመሥራት የሚደረገው ሙከራ “ወደ አንድ ወገን ያዘመመ፣ በእጅጉ የተዛባና ዋጋ ቢስ መሆኑ አይቀርም” ብለዋል። ታዲያ እኚህ ሰው ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? “የጥንቱን ሆሚኒድ የፊት ገጽታ አስመስሎ ‘ለመሥራት’ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ሙከራ አሳሳች ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።”47

የማሰብ ችሎታን በአንጎል መጠን መለካት

እውነታው፦ የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎች የሰዎች ቅድመ አያት ነው የሚሉት አንድ ፍጥረት ከሰዎች ጋር ምን ያህል የቅርብ ዝምድና እንዳለው ለመወሰን ከሚጠቀሙባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ የአንጎል መጠን ነው።

ጥያቄ፦ የማሰብ ችሎታን በአንጎል መጠን መለካት አስተማማኝ ዘዴ ነው?

የሰው እና የጦጣ የራስ ቅል

መልስ፦ አይደለም። የአንጎል መጠንን በማየት፣ ከሕልውና ውጭ ከሆኑ እንስሳት መካከል ከሰዎች ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው የትኛው እንደሆነ ለመገመት የሚሞክር አንድ የተመራማሪዎች ቡድን “አብዛኛውን ጊዜ ግምቱ አስተማማኝ እንዳልሆነ” አምኗል።48 ለምን? በ2008 ሳይንቲፊክ አሜሪካን ማይንድ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣውን መግለጫ ልብ በል፦ “ሳይንቲስቶች በሰዎችና በእንስሳት ዝርያዎች ላይ [ባደረጉት ጥናት] በትክክለኛውም ሆነ አንጻራዊ በሆነው የአንጎል መጠንና በብልህነት መካከል ዝምድና መኖሩን ማረጋገጥ አልቻሉም። በተጨማሪም የሰዎችን የመናገር ችሎታ የሚቆጣጠረውን ብሮካስ ኤሪያ የተባለውን የአንጎል ክፍል ሳይጨምር የተለያዩ የአንጎል ክፍሎች መኖርም ሆነ የእነዚህ ክፍሎች መጠን ከብልህነት ጋር ዝምድና እንዳለው የሚጠቁም ማስረጃ ማግኘት አልቻሉም።”49

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ሳይንቲስቶች የማሰብ ችሎታን በአንጎል መጠን መለካት አስተማማኝ ዘዴ እንዳልሆነ እያወቁ “ከዝንጀሮ ወደ ሰው የተደረገውን ሽግግር” በሚያሳየው ሂደት ላይ ቅሪተ አካላቱን በአንጎል መጠን ቅደም ተከተል የሚደረድሯቸው ለምንድን ነው? ማስረጃው ጽንሰ ሐሳባቸውን በግድ እንዲደግፍላቸው ለማድረግ ብለው ይሆን? ተመራማሪዎች በሰው “የዘር ግንድ” ውስጥ መካተት የሚኖርባቸው ቅሪተ አካላት የትኞቹ ናቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ሁልጊዜ የሚከራከሩት ለምንድን ነው? የሚያጠኗቸው ቅሪተ አካላት በእርግጥም ከሕልውና ውጭ የሆኑ የዝንጀሮ ዝርያዎች ስለሆኑ ይሆን?

ብዙውን ጊዜ ዝንጀሮ የሚመስሉ ሰዎች በአንድ ወቅት ይኖሩ እንደነበር ለማሳየት እንደ ማስረጃ ስለሚቀርቡት ኒያንደርታል ስለሚባሉት ሰው መሰል ቅሪተ አካላትስ ምን ማለት ይቻላል? ተመራማሪዎች ስለ እነዚህ ቅሪተ አካላት ምንነት የነበራቸውን አመለካከት መለወጥ ጀምረዋል። በ2009 ሚልፈርድ ዉልፖፍ፣ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ፊዚካል አንትሮፖሎጂ በተሰኘው ጽሑፍ ላይ “ኒያንደርታሎች እውነተኛ የሰው ዘሮች ሳይሆኑ አይቀሩም” ሲሉ ጽፈዋል።50

ተመራማሪዎች ለራሳቸው የሚሰጡት ከፍተኛ ግምት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረትና ገንዘብ ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት ሰው የመጣው በዝግመተ ለውጥ ነው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ለመደገፍ “ማስረጃ” በሚያቀርቡበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሐቀኛ የሆኑ ታዛቢዎች በቀላሉ መገንዘብ ይችላሉ። ታዲያ አንተ እንዲህ ባለው ማስረጃ ላይ እምነት ለመጣል ፈቃደኛ ነህ?

f ማሳሰቢያ፦ በዚህ ሣጥን ውስጥ ከተጠቀሱት ተመራማሪዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚያስተምረውን ትምህርት አያምኑም። ሁሉም የዝግመተ ለውጥን ትምህርት የሚቀበሉ ናቸው።

g “ሆሚኒድ” የሚለው ቃል የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎች የሰውን ዘርና በቅድመ ታሪክ ዘመናት የኖሩትን ሰው መሰል ዝርያዎች ለማመልከት የሚጠቀሙበት ቃል ነው።

በዚህ ሥዕል ላይ የሚታየው ጉድለት ምንድን ነው?

በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ጦጣ እየተሻሻለ ሰው የሆነበት ሂደት
  • እንዲህ ዓይነቶቹ ሥዕሎች የተመሠረቱት በእውነታ ላይ ሳይሆን በተመራማሪዎችና በሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ግምት ብሎም የተዛባ አመለካከት ላይ ነው።51

  • የጥርስ ቅሪተ አካል

    ከእነዚህ ሥዕሎች ውስጥ አብዛኞቹ የተሳሉት በከፊል የተገኙ የራስ ቅሎችንና ተነጥለው የተገኙ ጥርሶችን መሠረት በማድረግ ነው። ሙሉ አፅም ይቅርና ሙሉ የራስ ቅል እንኳ ማግኘት በጣም ብርቅ ነው።

  • የተለያዩ ፍጥረታት ቅሪተ አካላት አመዳደብ እንዴት መሆን እንዳለበት በተመራማሪዎች መካከል የጋራ ስምምነት የለም።

  • ከምድር ገጽ የጠፋ ፍጥረትን የፊት ገጽታ፣ የቆዳ ቀለምና ፀጉር የሚያሳይ ሥዕል

    የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ከሕልውና ውጭ የሆኑ ፍጥረታትን የፊት ገጽታ፣ የቆዳ ቀለምና ፀጉር በትክክል መሳል አይችሉም።

  • እስከ ዘመናዊው ሰው ድረስ ያለው እያንዳንዱ ፍጥረት የሚቀመጥበት ቅደም ተከተል የሚወሰነው በራስ ቅሉ መጠን መሠረት ነው። እንዲህ የሚደረገው የማሰብ ችሎታን በአንጎል መጠን መለካት አስተማማኝ ዘዴ እንዳልሆነ እየታወቀ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ