የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • yp1 ምዕ. 25 ገጽ 178-182
  • የማስተርቤሽን ልማድን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የማስተርቤሽን ልማድን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?
  • ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጥፋተኝነት ስሜትን ማሸነፍ
  • ማስተርቤሽን—ምን ያህል አሳሳቢ ችግር ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • ማስተርቤሽንና ግብረ ሰዶም
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
  • ይህን ልማድ ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2006
  • የማስተርቤሽንን ልማድ ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
ለተጨማሪ መረጃ
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
yp1 ምዕ. 25 ገጽ 178-182

ምዕራፍ 25

የማስተርቤሽን ልማድን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

“ማስተርቤሽን መፈጸም የጀመርኩት በስምንት ዓመቴ ነው። ከጊዜ በኋላ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት አወቅሁ። በዚህ ልማድ በተሸነፍኩ ቁጥር በራሴ በጣም አዝናለሁ። ‘አምላክ እንደ እኔ ያለውን ሰው እንዴት ሊወደው ይችላል?’ ብዬ አስባለሁ።”—ሉዊዝ

የጉርምስና ዕድሜ የፆታ ስሜት በጣም የሚያይልበት ወቅት ነው። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች ማስተርቤሽን መፈጸም ይጀምሩ ይሆናል።a ብዙ ሰዎች ይህ ልማድ ምንም ችግር እንደሌለው ይናገራሉ። “እንዲህ ብታደርግ ማንንም አትጎዳም” ይሉ ይሆናል። ይሁንና ከእንዲህ ዓይነቱ ልማድ ለመራቅ የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ” ብሏል፤ ጳውሎስ ይህን ሲል ከጠቀሳቸው ነገሮች መካከል “የፆታ ምኞት” ይገኝበታል። (ቆላስይስ 3:5) ማስተርቤሽን የፆታ ምኞትን ከመግደል ይልቅ ጭራሹኑ ያባብሰዋል። ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦችም ልብ በል፦

● ማስተርቤሽን አንድ ሰው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዲያድርበት ያደርጋል። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ይህን ድርጊት ሲፈጽም የራሱን ሥጋዊ ፍላጎት በማርካት ላይ ያተኩራል።

● የማስተርቤሽን ልማድ የተጠናወተው ግለሰብ፣ ተቃራኒ ፆታ ያላቸውን ሰዎች የእሱን የፆታ ፍላጎት ለማርካት እንደተፈጠሩ አድርጎ መመልከት ሊጀምር ይችላል።

● የማስተርቤሽን ልማድ የሚያስከትለው የራስ ወዳድነት አስተሳሰብ የትዳር ጓደኛሞች በፆታ ግንኙነት መርካት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ሊያደርግ ይችላል።

በውስጥህ የሚታገልህን የፆታ ስሜት ለማርካት ማስተርቤሽን ከመፈጸም ይልቅ ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማዳበር ጥረት አድርግ። (1 ተሰሎንቄ 4:4, 5) መጀመሪያውኑ የፆታ ስሜትህ እንዲቀሰቀስ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መራቅህ በዚህ ረገድ እንደሚረዳህ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 5:8, 9) ይሁንና ማስተርቤሽን የመፈጸም ልማድ ተጠናውቶህ ከሆነስ? ይህን ልማድ ለማሸነፍ ብትጥርም አልተሳካልህ ይሆናል። በመሆኑም ‘ለውጥ ማድረግና ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቼ መኖር አልችልም’ ብለህ ትደመድም ይሆናል። ፔድሮ የተባለ ወጣት እንደዚህ ይሰማው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ልማድ ሲያገረሽብኝ በራሴ በጣም አዝናለሁ። ለሠራሁት ስህተት ፈጽሞ ይቅርታ ሊደረግልኝ እንደማይችል ይሰማኝ እንዲሁም መጸለይ እንኳ ይከብደኝ ነበር።”

አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ አይዞህ! ጨርሶ ልትለወጥ እንደማትችል አታስብ። በርካታ ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች ይህን ልማድ ማሸነፍ ችለዋል። አንተም ልታሸንፈው ትችላለህ!

የጥፋተኝነት ስሜትን ማሸነፍ

ከላይ እንዳየነው ማስተርቤሽን የመፈጸም ልማድ ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት ይዋጣሉ። እርግጥ ነው፣ “አምላካዊ በሆነ መንገድ ማዘን” ይህን ልማድ ለማሸነፍ ኃይል ይሰጥሃል። (2 ቆሮንቶስ 7:11) በሌላ በኩል ግን ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። እንዲህ ያለው ስሜት በጣም ተስፋ ስለሚያስቆርጥህ ይህን ልማድ ለማሸነፍ የምታደርገውን ጥረት እርግፍ አድርገህ ልትተወው ትችላለህ።—ምሳሌ 24:10 NW

ስለዚህ ስለ ጉዳዩ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖርህ ይገባል። ማስተርቤሽን ርኩስ ከሆኑ ድርጊቶች የሚፈረጅ ነው። “ለተለያየ ምኞትና ሥጋዊ ደስታ [እንድትገዛ]” እንዲሁም ጤናማ ያልሆነ ዝንባሌ እንዲኖርህ ያደርጋል። (ቲቶ 3:3) በሌላ በኩል ግን ማስተርቤሽን እንደ ዝሙት ያለ ከባድ የፆታ ብልግና አይደለም። (ይሁዳ 7 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም ይህ ችግር ካለብህ ‘ይቅር የማይባል ኃጢአት ሠርቻለሁ’ ብለህ አትደምድም። ዋናው ነገር ይህን ድርጊት እንድትፈጽም የሚገፋፋህን ኃይለኛ ስሜት መቋቋምህና ጥረት ማድረግህን ፈጽሞ አለማቆምህ ነው!

ልማዱ በሚያገረሽብህ ወቅት በቀላሉ ተስፋ ትቆርጥ ይሆናል። በዚህ ጊዜ በምሳሌ 24:16 ላይ የሚገኘውን “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣልና፤ ክፉዎች ግን በጥፋት ይወድቃሉ” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ። ይህ ልማድ አንዳንድ ጊዜ ቢያገረሽብህ ክፉ ሰው ነህ ማለት አይደለም። በመሆኑም ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ ይህ ልማድ እንዲያገረሽብህ ያደረገውን ነገር ለማወቅና ያንን ደግመህ ላለመፈጸም ጥረት አድርግ።

ጊዜ ወስደህ በይሖዋ ፍቅርና ምሕረት ላይ አሰላስል። በድክመቱ ተሸንፎ የነበረው መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።” (መዝሙር 103:13, 14) አዎን፣ ይሖዋ ፍጹማን አለመሆናችንን ግምት ውስጥ የሚያስገባ ከመሆኑም ሌላ “ይቅር ባይ” ነው። (መዝሙር 86:5) በሌላ በኩል ግን ለመሻሻል ጥረት እንድናደርግም ይፈልጋል። ታዲያ የማስተርቤሽን ልማድን ለማሸነፍ ምን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?

መዝናኛህን ገምግም። የፆታ ስሜት እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉ ፊልሞችን ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ትመለከታለህ? አሊያም እንዲህ ዓይነት ድረ ገጾችን ትቃኛለህ? መዝሙራዊው “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” በማለት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ጸሎት አቅርቧል።b—መዝሙር 119:37

አእምሮህ በሌሎች ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ዊልያም የተባለ ክርስቲያን እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል፦ “ከመተኛታችሁ በፊት መንፈሳዊ ነገሮችን አንብቡ። ስለ መንፈሳዊ ነገሮች እያሰባችሁ መተኛታችሁ በጣም ጠቃሚ ነው።”—ፊልጵስዩስ 4:8

የሌሎችን እርዳታ ጠይቅ። ነገሩ ስለሚያሳፍርህ ለምትቀርበው ሰው መናገር ይከብድህ ይሆናል። ይሁንና ይህን ማድረግህ የማስተርቤሽን ልማድን ለማሸነፍ ሊረዳህ ይችላል! ዴቪድ የተባለ ክርስቲያን ይህ እውነት መሆኑን ከራሱ ተሞክሮ ተመልክቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ከአባቴ ጋር ብቻችንን ሆነን ስለ ጉዳዩ ነገርኩት። አባቴ ምን እንዳለኝ መቼም አልረሳውም። እንድረጋጋ በሚያደርግ መንገድ ፈገግ ብሎ፣ ጉዳዩን ስለነገርኩት ደስ እንዳለው ገለጸልኝ። ያለብኝን ችግር ለእሱ ለመናገር ምን ያህል እንደተጨነቅሁ ተረድቶልኝ ነበር። በወቅቱ የሚያስፈልገኝ እንዲህ ዓይነት ማበረታቻ ነበር።

“አባቴ፣ አንዳንድ ጥቅሶችን አውጥቶ ካነበበልኝ በኋላ ይህን ድርጊት በመፈጸሜ መጥፎ ሰው እንዳልሆንኩ አረጋገጠልኝ፤ ከዚያም ድርጊቱን አቅልዬ እንዳልመለከተው ደግሞ ሌሎች ጥቅሶችን አሳየኝ። በዚህ ልማድ ሳልሸነፍ የተወሰነ ጊዜ ለመቆየት ጥረት እንዳደርግ ያበረታታኝ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ሌላ ጊዜ ለመነጋገር ተስማማን። በመሃል ቢያገረሽብኝ እንኳ ተስፋ እንዳልቆርጥ ከዚህ ይልቅ በልማዱ ሳልሸነፍ ረዘም ላለ ጊዜ ለመቆየት ጥረት እንዳደርግ አበረታታኝ።” ታዲያ ዴቪድ ምን ተሰምቶት ይሆን? “ችግሬን የሚያውቅና እርዳታ የሚሰጠኝ ሰው መኖሩ ከምንም በላይ ጠቅሞኛል” ብሏል።c

በሚቀጥለው ምዕራፍ

“አብሮ መውጣት” ችግር አለው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ማስተርቤሽን የፆታ ስሜትን ለማነሳሳትና ለማርካት ብሎ የራስን የፆታ አካል የማሻሸት ልማድ ነው፤ በመሆኑም አንድ ሰው ሳያስበው ከሚያጋጥመው የፆታ ስሜት መነሳሳት ጋር ሊምታታ አይገባም። ለምሳሌ አንድ ልጅ እንቅልፍ ላይ እያለ ዘሩ ሊፈስ ወይም የፆታ ስሜቱ በመነሳሳቱ ከእንቅልፉ ሊነቃ ይችላል። በተመሳሳይም አንዳንድ ሴቶች ልክ የወር አበባ ዑደት ከመጀመሩ በፊት ወይም እንዳበቃ ሳያስቡት የፆታ ስሜታቸው ሊነሳሳ ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ ማስተርቤሽን የሚያመለክተው ሆን ብሎ የፆታ ስሜትን ማነሳሳትን ነው።

b ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 33 ተመልከት።

c ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ከገጽ 239-241 ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ምኞቶች ሽሽ፤ ከዚህ ይልቅ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋር ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ለማግኘት ተጣጣር።”—2 ጢሞቴዎስ 2:22

ጠቃሚ ምክር

የፆታ ስሜትህ እያየለ ከመሄዱ በፊት ጸልይ። ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችልህ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንዲሰጥህ ይሖዋ አምላክን ጠይቀው።—2 ቆሮንቶስ 4:7

ይህን ታውቅ ነበር?

ለፆታ ስሜት በቀላሉ መሸነፍ የድክመት ምልክት ነው። በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው ብቻውን እያለም እንኳ ራሱን መቆጣጠር መቻሉ ውስጣዊ ጥንካሬ እንዳለው ያሳያል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አእምሮዬ ንጹሕ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ለስሜቴ ከመሸነፍ ይልቅ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ይሖዋ “ይቅር ባይ” እንደሆነ ማስታወስ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?—መዝሙር 86:5

● የፆታ ፍላጎትን የፈጠረው አምላክ ራሱ ሆኖ ሳለ ራስን የመግዛት ባሕርይን እንድታዳብር ትእዛዝ መስጠቱ በአንተ ላይ ምን እምነት እንዳለው ያሳያል?

[በገጽ 182 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ችግሩን ማሸነፌ በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝ ረድቶኛል፤ ይህን ደግሞ በምንም ነገር ልለውጠው አልፈልግም!”—ሣራ

[በገጽ 180 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እየሮጥክ እያለ ብትወድቅ እንደገና ወደ ኋላ እንደማትመለስ ሁሉ የማስተርቤሽን ልማድ ቢያገረሽብህም እስካሁን ያደረግኸው ጥረት መና ይቀራል ማለት አይደለም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ