ትምህርት 18
አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ወንድሞቻችንን የምንረዳው እንዴት ነው?
ዶሚኒካን ሪፑብሊክ
ጃፓን
ሄይቲ
ድንገተኛ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋው የተጎዱ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ወዲያውኑ ዝግጅት ያደርጋሉ። እንዲህ ያለው ጥረት በመካከላቸው ያለው ፍቅር ከልብ የመነጨ መሆኑን ያሳያል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 3:17, 18) ታዲያ ወንድሞቻችንን በየትኞቹ መንገዶች መርዳት እንችላለን?
ገንዘብ እናዋጣለን። በይሁዳ ታላቅ ረሃብ በተከሰተ ጊዜ በአንጾኪያ የነበሩ የጥንት ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸው የገንዘብ እርዳታ ልከው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 11:27-30) በተመሳሳይም በአንድ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ወንድሞቻችን ከባድ ችግር እንዳጋጠማቸው ስናውቅ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት እንዲቻል በጉባኤያችን በኩል የገንዘብ መዋጮ እንልካለን።—2 ቆሮንቶስ 8:13-15
በተግባር የተደገፈ እርዳታ እንሰጣለን። ድንገተኛ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሽማግሌዎች እያንዳንዱ የጉባኤ አባል የት እንዳለና ደህንነቱን ያጣራሉ። የአደጋ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴ ተጎጂዎቹ ምግብ፣ ንጹሕ ውኃ፣ ልብስ፣ መጠለያና የሕክምና አገልገሎት ማግኘት የሚችሉበትን ዝግጅት ያስተባብራል። በዚህ ጊዜ ተፈላጊ የሆኑ ሙያዎች ያሏቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ወጪያቸውን ችለው በእርዳታ አቅርቦት ሥራ ለመካፈል ወይም የተጎዱ ቤቶችንና የስብሰባ አዳራሾችን ለመጠገን ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀርባሉ። አንድነት ስላለንና አብረን በመሥራት ረገድ ልምድ ስላካበትን እንደዚህ ባሉት ጊዜያት የሚያስፈልጉትን የእርዳታ ቁሳቁሶችና ሠራተኞች በፍጥነት ማሰባሰብ እንችላለን። በዋነኝነት የእርዳታ እጃችንን የምንዘረጋው “በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች” ቢሆንም በሚቻለን ጊዜ ሁሉ እገሌ ከገሌ ሳንል የማንኛውም ሃይማኖት አባላት የሆኑ ሰዎችንም እንረዳለን።—ገላትያ 6:10
መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ እንሰጣለን። አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ከሌሎች ይበልጥ ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። እንደነዚህ ባሉት ጊዜያት ብርታት የምናገኘው “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) በጭንቀት ላይ ለሚገኙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋዎች በደስታ በመናገር በቅርቡ የአምላክ መንግሥት የመከራና የሥቃይ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ እንደሚያስወግድ እናረጋግጥላቸዋለን።—ራእይ 21:4
የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ በሚደርስበት ጊዜ አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑት ለምንድን ነው?
ከአደጋ ለተረፉ ሰዎች ምን ዓይነት መንፈሳዊ ማጽናኛ መስጠት እንችላለን?