የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • jy ምዕ. 73 ገጽ 172-ገጽ 173 አን. 2
  • አንድ ሳምራዊ እውነተኛ ባልንጀራ መሆኑን አሳየ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አንድ ሳምራዊ እውነተኛ ባልንጀራ መሆኑን አሳየ
  • ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ደግ ባልንጀራ የሆነ ሳምራዊ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • ደግ ስለመሆን የተሰጠ ትምህርት
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • አንድ ሳምራዊ መልካም ባልንጀራ ሆኖ ተገኘ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
ለተጨማሪ መረጃ
ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
jy ምዕ. 73 ገጽ 172-ገጽ 173 አን. 2
አንድ ሳምራዊ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ለመርዳት ወደ እሱ ሲቀርብ፤ አንድ ካህንና ሌዋዊ ገለል ብለው አልፈውት ሄደዋል

ምዕራፍ 73

አንድ ሳምራዊ እውነተኛ ባልንጀራ መሆኑን አሳየ

ሉቃስ 10:25-37

  • የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ

  • ደግ ሳምራዊ

ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ እያለ የተወሰኑ አይሁዳውያን ወደ እሱ መጡ። አንዳንዶቹ የመጡት ከእሱ ለመማር ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ሊፈትኑት አስበው ነው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድ ሰው ይገኝበታል፤ ይህ ሰው “መምህር፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ?” ብሎ ጠየቀ።—ሉቃስ 10:25

ሰውየው ይህን ጥያቄ ያቀረበው እውቀት ለማግኘት ብሎ እንዳልሆነ ኢየሱስ ተገንዝቧል። ግለሰቡ ጥያቄውን ያነሳው ኢየሱስ አይሁዳውያንን ቅር የሚያሰኝ መልስ እንዲሰጥ ለማድረግ አስቦ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ፣ ሰውየው በዚህ ጉዳይ ላይ የራሱ አመለካከት እንዳለው አውቋል። በመሆኑም ግለሰቡ በልቡ ያለውን እንዲያወጣ የሚያደርግ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምላሽ ሰጠው።

ኢየሱስ “በሕጉ ላይ የተጻፈው ምንድን ነው? አንተስ ምን ትረዳለህ?” በማለት ጠየቀው። ይህ ሰው የአምላክን ሕግ ስላጠና የሰጠው መልስ በቃሉ ላይ የተመሠረተ ነው። ከዘዳግም 6:5 እና ከዘሌዋውያን 19:18 ላይ ጠቅሶ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ ኃይልህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ’፤ እንዲሁም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’” (ሉቃስ 10:26, 27) ታዲያ መልሱ ይህ ነው?

ኢየሱስ ሰውየውን “በትክክል መልሰሃል፤ ዘወትር ይህን አድርግ፤ ሕይወትም ታገኛለህ” አለው። ይሁንና ውይይቱ በዚህ አላበቃም። ሰውየው የፈለገው ቀጥተኛ መልስ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “ጻድቅ መሆኑን ለማሳየት” እንዲሁም አመለካከቱ ትክክለኛ እንደሆነና ሌሎችን የሚይዝበት መንገድ ተገቢ መሆኑን ኢየሱስ እንዲያረጋግጥለት ፈልጓል። ስለዚህ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። (ሉቃስ 10:28, 29) ይህ ቀላል የሚመስል ጥያቄ ጠለቅ ያለ ትርጉም አለው። እንዴት?

አይሁዳውያን “ባልንጀራ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የአይሁዳውያንን ባሕል የሚጠብቁ ሰዎችን ብቻ እንደሆነ ያምናሉ፤ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ ያለው ሐሳብም ይህን የሚደግፍ ሊመስል ይችላል። እንዲያውም አንድ አይሁዳዊ፣ ከሌላ ዘር ጋር ለመቀራረብ “ሕጉ እንደማይፈቅድ” ሊናገር ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 10:28) ስለዚህ ሕግ አዋቂውና ምናልባትም አንዳንድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ለሌሎች አይሁዳውያን ደግነት ካሳዩ ጻድቃን እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥራሉ። ይሁንና አይሁዳዊ ያልሆነን ሰው እንደ “ባልንጀራቸው” ስለማይመለከቱት በደግነት ላይዙት ይችላሉ።

ታዲያ ኢየሱስ ይህንን ሰውም ሆነ ሌሎች አይሁዳውያንን ቅር ሳያሰኝ አመለካከታቸውን ማስተካከል የሚችለው እንዴት ነው? አንድ ታሪክ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በዘራፊዎች እጅ ወደቀ፤ እነሱም ከገፈፉትና ከደበደቡት በኋላ በሞትና በሕይወት መካከል ጥለውት ሄዱ።” ኢየሱስ አክሎም እንዲህ አለ፦ “እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲወርድ ሰውየውን አየውና ራቅ ብሎ አልፎት ሄደ። በተመሳሳይም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና ገለል ብሎ አልፎት ሄደ። ሆኖም አንድ ሳምራዊ በዚያ መንገድ ሲጓዝ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ በጣም አዘነለት።”—ሉቃስ 10:30-33

ኢየሱስ ይህን ታሪክ የነገረው ሕግ አዋቂ፣ በርካታ ካህናትና በቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚረዷቸው ሌዋውያን በኢያሪኮ እንደሚኖሩ ያውቃል። እነዚህ ሰዎች ከቤተ መቅደሱ ሲመለሱ 23 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ቁልቁለት መንገድ መጓዝ አለባቸው። መንገዱ ላይ ዘራፊዎች ስላሉ ይህ ጉዞ አደገኛ ሊሆን ይችላል። አንድ ካህንና ሌዋዊ፣ አደጋ የደረሰበት አይሁዳዊ ቢመለከቱ ሊረዱት አይገባም? ኢየሱስ በተናገረው ታሪክ ላይ እንዲህ አላደረጉም። አይሁዳዊውን የረዳው አንድ ሳምራዊ ነው፤ ሳምራውያን ደግሞ አይሁዳውያን የሚጠሏቸው ሕዝቦች ናቸው።—ዮሐንስ 8:48

ሳምራዊው የተጎዳውን አይሁዳዊ ለመርዳት ምን አደረገ? ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “ወደ ሰውየው ቀርቦ በቁስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ በጨርቅ አሰረለት። ከዚያም በራሱ አህያ ላይ ካስቀመጠው በኋላ ወደ አንድ የእንግዶች ማረፊያ በመውሰድ ተንከባከበው። በማግስቱ ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዶች ማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠውና ‘ይህን ሰው አስታመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውን ተጨማሪ ወጪ ሁሉ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው።”—ሉቃስ 10:34, 35

ታላቅ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ ታሪኩን ከተናገረ በኋላ “ታዲያ ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ ሆኖ የተገኘው የትኛው ይመስልሃል?” በማለት ሕግ አዋቂው እንዲያስብ የሚያደርግ ጥያቄ አቀረበ። ሕግ አዋቂው “ሳምራዊው” ብሎ በቀጥታ መመለስ ስለከበደው ሳይሆን አይቀርም “ምሕረት በማሳየት የረዳው ነው” በማለት መለሰ። ኢየሱስም ከታሪኩ የሚገኘውን ትምህርት ቁልጭ አድርጎ ለማስቀመጥ ሲል “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” ብሎ አሳሰበው።—ሉቃስ 10:36, 37

ይህ እንዴት ያለ ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴ ነው! ኢየሱስ፣ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎችም ባልንጀሮቹ እንደሆኑ ለሕግ አዋቂው በቀጥታ ቢነግረው ኖሮ እሱም ሆነ ውይይቱን የሚያዳምጡ ሌሎች አይሁዳውያን ትምህርቱን ይቀበሉ ነበር? ላይቀበሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ አድማጮቹ በሚያውቁት ሁኔታ ላይ የተመሠረተና ለመረዳት የማይከብድ ታሪክ መናገሩ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ መልስ ቁልጭ ብሎ እንዲታይ አድርጓል። እውነተኛ ባልንጀራ የሆነው፣ ቅዱሳን መጻሕፍት በሚያዙት መሠረት ፍቅርና ደግነት ያሳየው ሰው ነው።

  • አንድ ሰው የዘላለም ሕይወት ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ኢየሱስን የጠየቀው ለምን ሊሆን ይችላል?

  • አይሁዳውያን ባልንጀሮቻቸው እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቱት እነማንን ነው? ለምንስ?

  • ኢየሱስ፣ እንደ ባልንጀራችን ልንቆጥረው የሚገባው ማንን እንደሆነ ለተነሳው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ የሰጠው እንዴት ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ