የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • jy ምዕ. 106 ገጽ 246-ገጽ 247 አን. 1
  • ስለ ወይን እርሻ የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ ወይን እርሻ የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች
  • ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በወይን አትክልት ምሳሌዎች ተጋለጡ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • ከዳተኛ ለሆነው የወይን ቦታ ወዮ!
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
  • የወይኑ እርሻ ሠራተኞች ምሳሌ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • የወይኑ አትክልት ሠራተኞች
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
ለተጨማሪ መረጃ
ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
jy ምዕ. 106 ገጽ 246-ገጽ 247 አን. 1
ገበሬዎቹ የወይን እርሻውን ባለቤት ልጅ ሲገድሉት

ምዕራፍ 106

ስለ ወይን እርሻ የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች

ማቴዎስ 21:28-46 ማርቆስ 12:1-12 ሉቃስ 20:9-19

  • ስለ ሁለት ልጆች የተነገረ ምሳሌ

  • ስለ ወይን እርሻ ገበሬዎች የተነገረ ምሳሌ

ኢየሱስ የፈጸማቸውን ነገሮች የሚያከናውነው በምን ሥልጣን እንደሆነ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እያለ ለጠየቁት የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ግራ የሚያጋባ መልስ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ የሰጠው መልስ አፋቸውን አስያዛቸው። ከዚያም እውነተኛ ማንነታቸውን የሚያጋልጥ ምሳሌ ተናገረ።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ ‘ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ወይኑ እርሻ ሄደህ ሥራ’ አለው። ልጁም መልሶ ‘አልሄድም’ አለው፤ በኋላ ግን ጸጸተውና ሄደ። ሁለተኛውንም ቀርቦ እንደዚሁ አለው። ልጁም መልሶ ‘እሺ አባዬ፣ እሄዳለሁ’ አለው፤ ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” (ማቴዎስ 21:28-31) መልሱ ግልጽ ነው፤ በኋላ ላይ የአባቱን ፈቃድ ያደረገው የመጀመሪያው ልጅ ነው።

ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች ወደ አምላክ መንግሥት በመግባት ረገድ ይቀድሟችኋል።” ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አምላክን ለማገልገል በመጀመሪያ ፈቃደኞች አልነበሩም። ይሁንና እንደ መጀመሪያው ልጅ በኋላ ላይ ንስሐ የገቡ ሲሆን አሁን እያገለገሉት ነው። በሌላ በኩል ግን የሃይማኖት መሪዎቹ እንደ ሁለተኛው ልጅ ናቸው፤ አምላክን እናገለግላለን ቢሉም ተግባራቸው ሌላ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “[መጥምቁ] ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ መጣ፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም። ይሁን እንጂ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አመኑት፤ እናንተ ይህን አይታችሁም እንኳ ጸጸት ተሰምቷችሁ እሱን ለማመን አልፈለጋችሁም።”—ማቴዎስ 21:31, 32

ኢየሱስ በመቀጠል ሌላም ምሳሌ ተናገረ። በዚህ ምሳሌ ላይ የሃይማኖት መሪዎቹ ጥፋት አምላክን አለማገልገላቸው ብቻ እንዳልሆነ አመልክቷል። እነዚህ ሰዎች ክፉ ናቸው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ አለማ፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ ጉድጓድ ቆፍሮም የወይን መጭመቂያ አዘጋጀ፤ ማማም ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን ከገበሬዎቹ እንዲያመጣለት አንድ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ። እነሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ፤ እሱንም ራሱን ፈነከቱት፤ ደግሞም አዋረዱት። ሌላም ባሪያ ላከ፤ እሱን ደግሞ ገደሉት፤ ሌሎች ብዙዎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ገደሉ።”—ማርቆስ 12:1-5

ኢየሱስን የሚያዳምጡት ሰዎች ምሳሌውን ይረዱ ይሆን? ኢሳይያስ የተናገረውን የሚከተለውን ውግዘት አዘል ሐሳብ ያስታውሱ ይሆናል፦ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋ የወይን እርሻ የእስራኤል ቤት ነውና፤ የይሁዳ ሰዎች እሱ ይወደው የነበረው የአትክልት ቦታ ናቸው። ፍትሕን ሲጠብቅ እነሆ፣ ግፍ ይፈጸማል።” (ኢሳይያስ 5:7) የኢየሱስ ምሳሌም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ባለ ርስቱ ይሖዋ ሲሆን የወይን እርሻው ደግሞ የአምላክ ሕግ እንደ አጥር ከለላ የሆነለት የእስራኤል ብሔር ነው። ይሖዋ፣ ሕዝቡን ለማስተማርና መልካም ፍሬ እንዲያፈሩ ለመርዳት ነቢያት ልኳል።

ይሁንና “ገበሬዎቹ” ወደ እነሱ ከተላኩት “ባሪያዎች” አንዳንዶቹን አሠቃዩአቸው፤ ሌሎቹንም ገደሏቸው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “[የወይን እርሻው ባለቤት] የቀረው የሚወደው ልጁ ነበር። ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት በመጨረሻ እሱን ላከው። እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ኑ እንግደለው፤ ርስቱም የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ። ስለዚህ ይዘው ገደሉት።”—ማርቆስ 12:6-8

ኢየሱስ “እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” በማለት ጠየቀ። (ማርቆስ 12:9) የሃይማኖት መሪዎቹም እንዲህ አሉ፦ “ክፉዎች ስለሆኑ ከባድ ጥፋት ያደርስባቸዋል፤ ከዚያም የወይን እርሻውን፣ ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል።”—ማቴዎስ 21:41

ይህን ሲናገሩ ሳያውቁት የፈረዱት በራሳቸው ላይ ነው፤ ምክንያቱም የይሖዋ “የወይን እርሻ” የሆነውን የእስራኤልን ብሔር ከሚያስተዳድሩት “ገበሬዎች” መካከል እነሱም ይገኙበታል። ይሖዋ ከእነዚህ ገበሬዎች ከሚጠብቃቸው ፍሬዎች አንዱ፣ በልጁ ማለትም በመሲሑ ማመን ሲሆን ይህን መጠበቁም ተገቢ ነው። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን ትኩር ብሎ በመመልከት እንዲህ አለ፦ “እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ። ይህ የይሖዋ ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’” (ማርቆስ 12:10, 11) ከዚያም ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል የምላችሁ ለዚህ ነው” በማለት ነጥቡን ግልጽ አደረገ።—ማቴዎስ 21:43

“በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና የካህናት አለቆች ይህን ምሳሌ የተናገረው እነሱን አስቦ እንደሆነ” ተረዱ። (ሉቃስ 20:19) ስለዚህ ሕጋዊ ‘ወራሽ’ የሆነውን ኢየሱስን ለመግደል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠው ተነሱ። ይሁንና ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለሚያየው ሕዝቡን ፈሩ፤ በመሆኑም በዚህ ወቅት ሊገድሉት አልሞከሩም።

  • በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ልጆች እነማንን ያመለክታሉ?

  • በሁለተኛው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው “ባለ ርስት” እና “የወይን እርሻ” እንዲሁም “ገበሬዎቹ፣” “ባሪያዎቹ” እና “ወራሹ” እነማንን ያመለክታሉ?

  • “ገበሬዎቹ” ወደፊት ምን ያጋጥማቸዋል?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ