የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • od ምዕ. 1 ገጽ 6-11
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል
  • የይሖዋ ድርጅት እየገሰገሰ ነው
  • “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ” እወቁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • የአምላክ ድርጅት ክፍል በመሆን ጥበቃ ማግኘት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ወደፊት ይገሰግሳል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ጋር እኩል ተራመዱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
od ምዕ. 1 ገጽ 6-11

ምዕራፍ 1

የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ

በዓለም ዙሪያ የተለያየ አወቃቀር፣ ዓላማ፣ አመለካከትና ፍልስፍና ያላቸው በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና የንግድ ድርጅቶች አሉ። ይሁን እንጂ ከሁሉም ድርጅቶች ፈጽሞ የተለየ አንድ ድርጅት አለ። ይህም የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት እንደሆነ የአምላክ ቃል በግልጽ ይናገራል።

2 ደስ የሚለው አንተም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ታቅፈሃል። የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ መርምረህ ስላረጋገጥክ በአሁኑ ጊዜ የእሱን ፈቃድ እየፈጸምክ ነው። (መዝ. 143:10፤ ሮም 12:2) በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ አፍቃሪ ወንድሞች ጋር ተባብረህ የምታገለግል ትጉ የአምላክ አገልጋይ ሆነሃል። (2 ቆሮ. 6:4፤ 1 ጴጥ. 2:17፤ 5:9) የአምላክ ቃል በሚናገረው መሠረት እንዲህ ማድረግህ የተትረፈረፈ በረከትና ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልሃል። (ምሳሌ 10:22፤ ማር. 10:30) በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ በታማኝነት መፈጸምህ ወደፊት የሚመጣውን ዘላቂና አስደሳች ሕይወት ለማግኘት ያዘጋጅሃል።—1 ጢሞ. 6:18, 19፤ 1 ዮሐ. 2:17

3 ታላቁ ፈጣሪያችን ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚመራ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት አለው። ይህም ሲባል ድርጅቱን የሚመራው የሁሉ የበላይ የሆነው ይሖዋ ነው ማለት ነው። እኛ ደግሞ በእሱ ላይ ሙሉ እምነት አለን። እሱ ዳኛችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ንጉሣችን ነው። (ኢሳ. 33:22) ይሖዋ የሥርዓት አምላክ እንደመሆኑ መጠን መለኮታዊውን ዓላማ ዳር ለማድረስ በምናከናውነው አገልግሎት ‘ከእሱ ጋር አብረን ለመሥራት’ የሚያስችሉ ዝግጅቶች አድርጎልናል።—2 ቆሮ. 6:1, 2

4 የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየቀረበ ሲሄድ፣ በተሾመው ንጉሥ በክርስቶስ ኢየሱስ አመራር ሥር ሆነን ወደፊት እንጓዛለን። (ኢሳ. 55:4፤ ራእይ 6:2፤ 11:15) ተከታዮቹ እሱ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ካከናወነው የበለጠ ሥራ እንደሚፈጽሙ ኢየሱስ ራሱ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 14:12) እንዲህ ማለቱ ትክክል ነው፤ ምክንያቱም የኢየሱስ ተከታዮች ለረጅም ዓመታት ስለሚሰብኩና ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሚሄድ በጣም ሰፊ ክልል መሸፈን ይችላሉ። በመሆኑም የመንግሥቱን ምሥራች እስከ ምድር ዳር ድረስ ያውጃሉ።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8

5 ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። ይሁንና ኢየሱስ በግልጽ እንደተናገረው ምሥራቹን የማወጁ ሥራ የሚያበቃው ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ነው። በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ውስጥ የሚገኙት ማስረጃዎች በሙሉ ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን በጣም እንደቀረበ በግልጽ ያሳያሉ።—ኢዩ. 2:31፤ ሶፎ. 1:14-18፤ 2:2, 3፤ 1 ጴጥ. 4:7

የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የምናደርገውን ጥረት ማጠናከር ይኖርብናል። ይህ ደግሞ የአምላክ ድርጅት ሥራውን የሚያካሂድበትን መንገድ በሚገባ ማወቅን ይጠይቃል

6 ሥርዓቱ ሊደመደም በተቃረበበት በዚህ ሰዓት፣ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ በመገንዘባችን የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የምናደርገውን ጥረት ማጠናከር ይኖርብናል። ይህ ደግሞ የአምላክ ድርጅት ሥራውን የሚያካሂድበትን መንገድ በሚገባ ማወቅንና ከድርጅቱ አሠራር ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምቶ መኖርን ይጠይቃል። የድርጅቱ አሠራር በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ሲሆን ይህም አምላክ በመንፈስ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኙትን ደንቦች፣ ሕጎች፣ መመሪያዎች፣ ሥርዓቶችና ትምህርቶች ይጨምራል።—መዝ. 19:7-9

7 የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ያለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አመራር በጥብቅ መከተላቸው ሰላምና አንድነት ያስገኝላቸዋል፤ እንዲሁም በኅብረት እንዲሠሩ ያስችላቸዋል። (መዝ. 133:1፤ ኢሳ. 60:17፤ ሮም 14:19) በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ወንድሞቻችን ጠንካራ ዝምድና እንዲኖራቸው የሚያደርገው ምንድን ነው? ፍቅር ነው። ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያነሳሳን ፍቅር ከመሆኑም ሌላ ፍቅርን ለብሰናል። (ዮሐ. 13:34, 35፤ ቆላ. 3:14) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ይህን መንገድ በመከተል ከይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ጋር እኩል እንራመዳለን።

የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል

8 የአምላክ ነቢያት የሆኑት ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በራእይ ተመልክተዋል። (ኢሳ. ምዕ. 6፤ ሕዝ. ምዕ. 1፤ ዳን. 7:9, 10) በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ የይሖዋ ድርጅት በሰማይ እንዴት እንደተዋቀረ በራእይ የተመለከተ ሲሆን አደረጃጀቱ ምን እንደሚመስል በራእይ መጽሐፍ ላይ ፍንጭ ሰጥቶናል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ይሖዋ አምላክ በመላእክት ታጅቦና ክብር በተጎናጸፈ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ተመልክቷል፤ በዙሪያው ያሉት ፍጥረታትም “የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፣ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው” እያሉ ያውጁ ነበር። (ራእይ 4:8) በተጨማሪም ዮሐንስ ‘በዙፋኑ መካከል፣ አንድ በግ ቆሞ’ ተመልክቷል፤ እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ራእይ 5:6, 13, 14፤ ዮሐ. 1:29

9 በዚህ ራእይ ላይ ይሖዋ በዙፋን ላይ ተቀምጦ መታየቱ ድርጅቱን በበላይነት የሚመራው እሱ መሆኑን ይጠቁማል። አንደኛ ዜና መዋዕል 29:11, 12 ስለ ይሖዋና ስላለው ታላቅ ሥልጣን ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታላቅነት፣ ኃያልነት፣ ውበት፣ ግርማና ሞገስ የአንተ ነው፤ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነው። ይሖዋ ሆይ፣ መንግሥት የአንተ ነው። ከሁሉም በላይ ከፍ ከፍ ያልክ ራስ ነህ። ሀብትና ክብር ከአንተ ነው፤ አንተም ሁሉንም ነገር ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ እጅህ ሁሉንም ታላቅ ማድረግና ለሁሉም ብርታት መስጠት ይችላል።”

10 ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሖዋ ጋር አብሮ የሚሠራ እንደመሆኑ መጠን በሰማይ ከፍ ያለ ቦታ አለው፤ ታላቅ ሥልጣንም ተሰጥቶታል። እንዲያውም አምላክ “ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ ከጉባኤው ጋር በተያያዘም በሁሉ ነገር ላይ ራስ አደረገው።” (ኤፌ. 1:22) ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው፤ ምላስም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በመመሥከር አባት ለሆነው አምላክ ክብር ያመጣ ዘንድ ነው።” (ፊልጵ. 2:9-11) በመሆኑም የኢየሱስ ክርስቶስ አመራር በጽድቅ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን።

11 ነቢዩ ዳንኤል በተገለጠለት ራእይ ላይ ከዘመናት በፊት የነበረውን በሰማይ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የተመለከተው ሲሆን በዚያ ስላያቸው መላእክት ሲናገር “ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም በፊቱ ቆመው ነበር” ብሏል። (ዳን. 7:10) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ የመላእክት ሠራዊት “መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑ መናፍስት” እንደሆኑ ይናገራል። (ዕብ. 1:14) እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት በሙሉ ‘በዙፋኖች፣ በጌትነት፣ በመንግሥታትና በሥልጣናት’ ተደራጅተዋል።—ቆላ. 1:16

12 የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ባሉት በእነዚህ ገጽታዎች ላይ ቆም ብለን ስናሰላስል ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ይሖዋ “በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ” እንዲሁም ‘ሱራፌል ከእሱ በላይ ቆመው’ ባየ ጊዜ የተሰማውን ስሜት መረዳት እንችላለን። ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል፦ “ወዮልኝ! ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ስለሆንኩና የምኖረውም ከንፈራቸው በረከሰ ሕዝብ መካከል ስለሆነ በቃ መሞቴ ነው፤ ዓይኖቼ ንጉሡን፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ራሱን አይተዋልና!” በእርግጥም ኢሳይያስ የይሖዋ ድርጅት እጅግ ሰፊ እንደሆነ መገንዘቡ በአድናቆት እንዲዋጥና ራሱን ዝቅ አድርጎ እንዲመለከት አድርጎታል። ኢሳይያስ ባየው ነገር በጥልቅ በመነካቱ ከሰማይ የይሖዋን ፍርድ የማወጁን ልዩ ሥራ አስመልክቶ ጥሪ በቀረበ ጊዜ “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።—ኢሳ. 6:1-5, 8

13 የይሖዋ ሕዝቦችም ድርጅቱን እያወቁና እያደነቁ ሲሄዱ ተመሳሳይ ምላሽ ለመስጠት ይገፋፋሉ። ድርጅቱ ወደፊት እየገሰገሰ በሄደ መጠን እኛም እኩል ለመጓዝ ጥረት እናደርጋለን። በዛሬው ጊዜ እኛም በይሖዋ ድርጅት እንደምንተማመን በተግባር ከማሳየት ወደኋላ አንልም።

የይሖዋ ድርጅት እየገሰገሰ ነው

14 በሕዝቅኤል ትንቢት የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ይሖዋ በሰማይ አንድ ትልቅ ሠረገላ እየነዳ እንዳለ ተደርጎ ተገልጿል። ይህ ክብር የተላበሰ ሠረገላ በዓይን የማይታየውን የይሖዋን ድርጅት ክፍል ይወክላል። ይሖዋ ይህን ሠረገላ የሚነዳ መሆኑ ድርጅቱን ከዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ እንደሚመራውና እንደሚጠቀምበት ያሳያል።—መዝ. 103:20

15 የዚህ ሠረገላ እያንዳንዱ መንኮራኩር፣ ተመሳሳይ ስፋት ያለው ሌላ መንኮራኩር በውስጡ ይዟል፤ ሁለተኛው መንኮራኩር መሃል ለመሃል ስለሚሰካ መንኮራኩሮቹ መስቀለኛ ቅርጽ ይሠራሉ። መንኮራኩሮቹ “በአራቱም ጎን በፈለጉበት አቅጣጫ መሄድ ይችላሉ” ሊባል የሚችለው ይህ ከሆነ ብቻ ነው። (ሕዝ. 1:17) መንኮራኩሮቹ አቅጣጫቸውን በቅጽበት መቀየር ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሲባል ሠረገላውን የሚቆጣጠረው ወይም የሚመራው አካል የለም ማለት አይደለም። ይሖዋ ድርጅቱ ባሻው መንገድ እንዲሄድ አይፈቅድም። ሕዝቅኤል 1:20 “መንፈሱ ወደመራቸው አቅጣጫ . . . ይሄዳሉ” ይላል። በመሆኑም በመንፈሱ አማካኝነት ድርጅቱን ወደሚፈልግበት አቅጣጫ እንዲጓዝ የሚያደርገው ይሖዋ ነው። ስለዚህ ‘ከድርጅቱ እኩል እየተጓዝኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

16 ከይሖዋ ድርጅት እኩል መጓዝ ሲባል በስብሰባዎች ላይ መገኘትና በመስክ አገልግሎት መሳተፍ ማለት ብቻ አይደለም። ይህ አባባል በዋነኝነት የሚያመለክተው ወደፊት መግፋትንና መንፈሳዊ እድገት ማድረግን ነው። “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ለይቶ ማወቅና በየጊዜው የሚቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ መመገብ ይጠይቃል። (ፊልጵ. 1:10፤ 4:8, 9፤ ዮሐ. 17:3) በተጨማሪም መደራጀት ካለ ጥሩ ቅንጅትና የትብብር መንፈስ እንደሚኖር የታወቀ ነው። በመሆኑም ይሖዋ፣ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን እንድንችል ሲል በአደራ የሰጠንን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት ከሁሉ በተሻለ መንገድ የመጠቀምን አስፈላጊነት ቸል ማለት አይኖርብንም። በሰማይ ካለው የይሖዋ ሠረገላ እኩል ለመጓዝ ጥረት ስናደርግ አኗኗራችን ከምናውጀው መልእክት ጋር የሚስማማ ይሆናል።

17 ሁላችንም በይሖዋ ድርጅት እርዳታ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ወደፊት እየገሰገስን ነው። በሰማይ ያለውን ይህን ሠረገላ የሚነዳው ይሖዋ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ስለዚህ ከሠረገላው እኩል ለመጓዝ የምናደርገው ጥረት ለይሖዋ አክብሮት እንዳለንና ዓለታችን በሆነው አምላክ እንደምንታመን ያሳያል። (መዝ. 18:31) መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ለሕዝቡ ብርታት ይሰጣል። ይሖዋ ሰላም በመስጠት ሕዝቡን ይባርካል” የሚል ተስፋ ይዟል። (መዝ. 29:11) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት ክፍል በመሆናችን እሱ ከሚሰጠው ብርታት ተጠቃሚ መሆን ችለናል፤ እንዲሁም ለተደራጀው ሕዝቡ የሰጠውን ሰላም አግኝተናል። በእርግጥም ዛሬም ሆነ ለዘላለም የይሖዋን ፈቃድ ማድረጋችንን በቀጠልን መጠን የተትረፈረፈ በረከት ማግኘታችን የማይታበል ሐቅ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ