ምዕራፍ 4
ጉባኤው የተደራጀበትና አመራር የሚያገኝበት መንገድ
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ አምላክን በተመለከተ ትልቅ ትርጉም ያዘለ እውነታ ገልጿል። ጳውሎስ “አምላክ የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ሲል ጽፏል። አክሎም ስለ ጉባኤ ስብሰባዎች ሲናገር “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ብሏል።—1 ቆሮ. 14:33, 40
2 ሐዋርያው በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ መከፋፈል በመከሰቱ በደብዳቤው መግቢያ ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ምክር ሰጥቷል። ጳውሎስ በዚያ የነበሩት ወንድሞች ‘ንግግራቸው አንድ እንዲሆን’ እንዲሁም “በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት” እንዲኖራቸው አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 1:10, 11) ከዚያ በመቀጠል በጉባኤው አንድነት ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ የተለያዩ ጉዳዮችን አስመልክቶ ምክር ሰጥቷል። የሰውን አካል እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም አንድነትና ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ በግልጽ አስረድቷል። በመሆኑም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ፣ የሥራ ድርሻቸው ምንም ይሁን ምን አንዳቸው ለሌላው ፍቅራዊ አሳቢነት እንዲያሳዩ አጥብቆ መክሯቸዋል። (1 ቆሮ. 12:12-26) በጉባኤው ውስጥ ባሉት መካከል እንዲህ ዓይነት የትብብር መንፈስ መኖሩ ጉባኤው የተደራጀ እንደሆነ ይጠቁማል።
3 ይሁን እንጂ የክርስቲያን ጉባኤ የተደራጀው እንዴት ነው? የሚያደራጀውስ ማን ነው? ምን ዓይነት መዋቅር ይኖረዋል? በኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚያገለግሉትስ እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያችን አድርገን በመጠቀም ለእነዚህ ጥያቄዎች ግልጽ የሆነ መልስ ማግኘት እንችላለን።—1 ቆሮ. 4:6
በቲኦክራሲያዊ መንገድ የተደራጀ
4 የክርስቲያን ጉባኤ የተቋቋመው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረው ጉባኤ ምን ማወቅ እንችላለን? የተደራጀውና የሚመራው ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ ነበር፤ በሌላ አነጋገር በአምላክ (በግሪክኛ ቴኦስ) አገዛዝ (ክራቶስ) ሥር ነበር። እነዚህ ሁለት ቃላት በ1 ጴጥሮስ 5:10, 11 ላይ “አምላክ” እና “ኃይል” ተብለው ተገልጸዋል። የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ በኢየሩሳሌም ስለተፈጸመ ሁኔታ የሚገልጸው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ታሪክ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ ያቋቋመው አምላክ እንደሆነ በግልጽ ያመለክታል። (ሥራ 2:1-47) ጉባኤው የአምላክ ሕንፃ እንዲሁም ቤተሰብ እንደሆነ ተገልጿል። (1 ቆሮ. 3:9፤ ኤፌ. 2:19) በዛሬው ጊዜ ያለው የክርስቲያን ጉባኤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን አደረጃጀትና አሠራር ይከተላል።
በዛሬው ጊዜ ያለው የክርስቲያን ጉባኤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን አደረጃጀትና አሠራር ይከተላል
5 የጥንቱ ጉባኤ ሲቋቋም 120 ገደማ ደቀ መዛሙርት ነበሩት። ኢዩኤል 2:28, 29 ላይ በሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ የፈሰሰው በእነሱ ላይ ነበር። (ሥራ 2:16-18) ሆኖም በዚያው ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በውኃ በመጠመቅ በመንፈስ የተወለዱ ደቀ መዛሙርትን ያቀፈውን ጉባኤ ተቀላቀሉ። ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ቃል ተቀበሉ፤ “የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ።” ከዚያ በኋላ ይሖዋ “የሚድኑ ሰዎችን በየዕለቱ በእነሱ ላይ ይጨምር ነበር።”—ሥራ 2:41, 42, 47
6 በኢየሩሳሌም የነበረው ጉባኤ በፍጥነት እያደገ በመሄዱ የአይሁድ ሊቀ ካህናት፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሩሳሌምን በትምህርታቸው እንደሞሏት በምሬት ተናግሯል። በኢየሩሳሌም ከነበሩት አዳዲስ ደቀ መዛሙርት መካከል ከጊዜ በኋላ ጉባኤውን የተቀላቀሉ ብዙ የአይሁድ ካህናት ይገኙበታል።—ሥራ 5:27, 28፤ 6:7
7 ኢየሱስ “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ሥራ 1:8) እስጢፋኖስ ከተገደለ በኋላ በኢየሩሳሌም ታላቅ ስደት በመነሳቱ በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት በመላው ይሁዳና ሰማርያ ተበተኑ፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ፍጻሜውን አግኝቷል። በሄዱበት ሁሉ ምሥራቹን ማወጃቸውንና ደቀ መዛሙርት ማፍራታቸውን የቀጠሉ ሲሆን ከአዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት መካከል ሳምራውያንም ይገኙበታል። (ሥራ 8:1-13) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ምሥራቹን አይሁዳውያን ላልሆኑ ያልተገረዙ አሕዛብ ለመስበክ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ሆኖ ነበር። (ሥራ 10:1-48) እንዲህ ያለው የስብከት እንቅስቃሴ ብዙ ደቀ መዛሙርት እንዲገኙ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም ውጭ አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ አስችሏል።—ሥራ 11:19-21፤ 14:21-23
8 አዲስ የተቋቋሙት ጉባኤዎች በሙሉ ቲኦክራሲያዊ በሆነ ወይም አምላክ በሚፈልገው መንገድ እንዲደራጁና እንዲመሩ ለማድረግ ምን ዝግጅቶች ተደርገው ነበር? በአምላክ መንፈስ አማካኝነት መንጋውን የሚጠብቁ የበታች እረኞች የሚሾሙበት ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ጳውሎስና በርናባስ በመጀመሪያው ሚስዮናዊ ጉዟቸው ወቅት ጉባኤዎችን ሲጎበኙ ሽማግሌዎችን ሾመዋል። (ሥራ 14:23) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ፣ ጳውሎስ ከኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ስላደረገው ስብሰባ ተርኳል። ጳውሎስ “ለራሳችሁም ሆነ አምላክ በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ እንድትጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ትኩረት ስጡ” ብሏቸዋል። (ሥራ 20:17, 28) እነዚህ ወንድሞች ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል ብቁ የሆኑት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርቶችን በማሟላታቸው ነው። (1 ጢሞ. 3:1-7) የጳውሎስ የአገልግሎት ባልደረባ የሆነው ቲቶ በቀርጤስ ባሉ ጉባኤዎች ሽማግሌዎችን እንዲሾም ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር።—ቲቶ 1:5
9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተጨማሪ ጉባኤዎች እየተቋቋሙ ሲሄዱ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ በሄደው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ዋነኞቹ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። በወቅቱ ለነበረው ጉባኤ የበላይ አካል ሆነው አገልግለዋል።
10 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው የክርስቲያን ጉባኤ አንድነቱን ጠብቆ መኖር የሚችለው ከአምላክ መንፈስ ጋር ተባብሮ በመሥራት እንዲሁም ለኢየሱስ ክርስቶስ የራስነት ሥልጣን በታማኝነት በመገዛት ነው። ሐዋርያው በዚያ የነበሩት ክርስቲያኖች ትሕትናን እንዲያዳብሩና በጉባኤው ውስጥ ካሉት ሁሉ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት በመፍጠር “የመንፈስን አንድነት [እንዲጠብቁ]” አሳስቧቸዋል። (ኤፌ. 4:1-6) ከዚያም ይሖዋ ያደረገውን ዝግጅት ለመግለጽ መዝሙር 68:18ን ጠቅሶ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ሐዋርያት፣ ነቢያት፣ ወንጌላውያን፣ እረኞችና አስተማሪዎች በመሆን ጉባኤው የሚያስፈልገውን አገልግሎት እንደሚያሟሉ ተናግሯል። እነዚህ ወንዶች የይሖዋ ስጦታዎች እንደመሆናቸው መጠን መላውን ጉባኤ በመገንባት አምላክን ደስ ወደሚያሰኝ የመንፈሳዊ ጉልምስና ደረጃ እንዲደርስ ያስችሉታል።—ኤፌ. 4:7-16
በዛሬው ጊዜ ያሉ ጉባኤዎች ሐዋርያት የተዉትን አሠራር ይከተላሉ
11 በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ተመሳሳይ የሆነ የአደረጃጀት ሥርዓት ይከተላሉ። እነዚህ ጉባኤዎች በቡድን ደረጃ ሲታዩ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ማዕከል ያደረገ አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ናቸው። (ዘካ. 8:23) እንዲህ እንዲሆን ያስቻለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ” ከእነሱ ጋር እንደሚሆን ቃል በገባው መሠረት ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱን በታማኝነት ሲደግፍ ቆይቷል። እድገት እያደረገ ካለው ጉባኤ ጋር የሚቀላቀሉ ሰዎች የአምላክን ምሥራች ይቀበላሉ፣ ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ይወስናሉ እንዲሁም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ይጠመቃሉ። (ማቴ. 28:19, 20፤ ማር. 1:14፤ ሥራ 2:41) “ጥሩ እረኛ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በመላው መንጋ ላይ ይኸውም በመንፈስ በተቀቡትና ‘በሌሎች በጎች’ ላይ ራስ እንደሆነ አምነው ይቀበላሉ። (ዮሐ. 10:14, 16፤ ኤፌ. 1:22, 23) ይህ “አንድ መንጋ” የክርስቶስን የራስነት ሥልጣን በታማኝነት አምኖ በመቀበልና ክርስቶስ ለሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማለትም እሱ ለሚጠቀምበት ድርጅታዊ የመገናኛ መስመር በመገዛት አንድነቱን ይጠብቃል። እኛም በዛሬው ጊዜ ባለው በዚህ የመገናኛ መስመር ላይ ሙሉ እምነት ይኑረን።—ማቴ. 24:45
ሃይማኖታዊ ማኅበራት የሚጫወቱት ሚና
12 ድርጅቱ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ማኅበራትን የሚያቋቁመው መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው ለማቅረብና መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የመንግሥቱ ምሥራች እንዲሰበክ ለማድረግ ነው። እነዚህ ሕጋዊ ማኅበራት፣ በተለያዩ አገሮች ውስጥ ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል፤ እንዲሁም እርስ በርስ ተደጋግፈው ይሠራሉ። ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ለማዳረስ እንደ መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ።
ቅርንጫፍ ቢሮዎች የተደራጁበት መንገድ
13 አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ሲቋቋም በአገሪቱ ውስጥም ሆነ በዚያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ባሉ ሌሎች አገሮች ውስጥ ለሥራው አመራር የሚሰጥ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ሽማግሌዎችን ያቀፈ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ይሾማል። ከኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው አስተባባሪ ሆኖ ያገለግላል።
14 በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ያሉ ጉባኤዎች በወረዳዎች ይደራጃሉ። ወረዳዎች መልክአ ምድራዊ አቀማመጥን፣ ቋንቋንና በቅርንጫፍ ቢሮው ሥር ያሉትን ጉባኤዎች ብዛት ግምት ውስጥ በማስገባት የሚቋቋሙ በመሆናቸው ስፋታቸው ይለያያል። በእያንዳንዱ ወረዳ ውስጥ ያሉትን ጉባኤዎች የሚያገለግል አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ይሾማል። ቅርንጫፍ ቢሮው የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ኃላፊነቱን የሚወጣበትን መንገድ በተመለከተ መመሪያ ይሰጣል።
15 ጉባኤዎች ለሁሉም ጥቅም ሲባል የሚደረጉትን ድርጅታዊ ዝግጅቶች ይቀበላሉ። እንዲሁም በቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ በወረዳዎችና በጉባኤዎች ውስጥ ሥራውን በበላይ ተመልካችነት የሚመሩትን ሽማግሌዎች ሹመት ይቀበላሉ። ታማኝና ልባም ባሪያ በወቅቱ የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ በጉጉት ይጠብቃሉ። በዛሬው ጊዜ ያለው ታማኝ ባሪያም በበኩሉ ለክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይገዛል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይጠብቃል እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን አመራር ይከተላል። ሁላችንም በአንድነት ተባብረን ስንሠራ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ጉባኤዎቹም በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ” በማለት የገለጸው ዓይነት ውጤት እናገኛለን።—ሥራ 16:5